በታዛቢው ላ.
ይህ ርዕሰ ጉዳይ በጥናት ተደግፎ በርካታ ቅፅ የሚወጣው ጽሑፍ ሊዘጋጅበት ይችላል፡፡ የአሁኑ ትዝብት ግን በርካታ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን እግር ተወርች ጠፍሮ ከያዛቸው ማነቆዎች መካከል ለማሳያ የሚሆን አንድ ሰበዝ በመምዘዝ፣ የብዙዎችን ጩኸት ለማስተጋባትና ከሚመለከተው ግለሰብ እስከ ተቋም ራሱን ፈትሾ የአሠራር ማስተካከያ እንዲደረግ ለማሳሰብ ነው፡፡ ትዝብቱ በቅንነት የሚያገለግሉ፣ አሠራሮችን ለማሻሻል የሚተጉ፣ ዕውቀታቸውንና ክህሎታቸውን በማዳበር የአገልጋይነትን ስሜትና ኃላፊነት ገንዘባቸው በማድረግ አቅም የፈቀደውን ሁሉ የሚያደርጉትን ሠራተኞችና ተቋማት አይመለከትም፡፡
የመንግሥት ተቋማት በተለይም የአስተዳደር መሥሪያ ቤቶች ከእነዚህም አገልግሎት በመስጠት የተሰማሩትን በግል ጉዳያችንም ሆነ የሌሎችን ጉዳይ በሕጋዊ ውክልና ለማስፈጸም ስንጎበኝ እንደ ጉዳዩ ዓይነት፣ እንደምንስተናገድበት መሥሪያ ቤትና እንደሚያስተናግደን ባለሙያ ወይም ኃላፊ የሚገጥሙን ችግሮችና ተግዳሮቶች አሉ፡፡
በቅርቡ በንግድ ሥራ የሚሰማሩ ደንበኞቻችንን የንግድ ምዝገባና ፈቃድ ለማስፈጸም ከአንዴም ሁለቴ ወደሚመለከተው ክፍለ ከተማ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ከሥራ ባልደረባዬ ጋር ሄጄ የገጠመኝ ጉዳይ የአገልግሎት አሰጣጡ በሚያስደነግጥ ሁኔታ ወዴት እየሄደ ነው እንድል አስገድዶኛል፡፡ በሌላ ክፍለ ከተማ የገቢዎች ጽሕፈት ቤት ደግሞ አንድ ሠራተኛ ከቀኑ 5፡30 ሰዓት ላይ ከሚያስተናግድበት ቦታ በመነሳት ከዚህ በኋላ አልሠራም ‹‹መብቴ ነው›› በማለት በተገልጋዮች ላይ ሲደነፋ የዓይን ምስክር ሆኜአለሁ፡፡ አለቃውም ስትለማመጠው አስተውዬአለሁ፡፡ አንድ ልጨምር፡፡ ነገር በሦስት ምስክር ይፀናል እንዲሉ አበው፡፡ በሌላ ክፍለ ከተማ የገቢዎች ጽሕፈት ቤት መዝግቡኝና ግብር ልክፈል ብሎ መረጃ የሚጠይቅ ባለጉዳይን አንድ ሠራተኛ የሥራ ባልደረባዋን በጩኸትና በኃይለ ቃል አንድ ሰው ወደኔ እንዳትልክ ‹‹ሥራዬን ልሥራበት›› ስትል ታዝቤአለሁ፡፡ ይህ የአሠራር ችግር ከተራ ‹‹ኤክስፐርት›› እስከ ኃላፊነት የተቀመጠውን ሠራተኛ ይመለከታል፡፡ የክፍላተ ከተሞችና የወረዳዎች ችግር ብቻ ሳይሆን ከሞላ ጎደል በበርካታ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ይስተዋላል፡፡
ለዚህ ጽሑፍ መነሻ ወደሆነኝ ጉዳይ ስመለስ፡፡ በንግድ ማኅበር/ኩባንያ ምሥረታ ውስጥ ከሚከናወኑ በሕግ ከተቀመጡ ግዴታዎች አንዱ የንግድ ምዝገባ መፈጸም ነው፡፡ በዚህም ሒደት የሚቋቋመውን ኩባንያ የመመሥረቻ ጽሑፍና የመተዳደሪያ ደንብ ሥልጣን ለተሰጠው አካል በማቅረብ በመጀመሪያው የሚከናወነው ተግባር፣ ለንግድ ማኅበሩ በአማራጭ የቀረቡ ስሞችን ሕጉን መሠረት በማድረግና መዝጋቢው ተቋም ከያዘው የመረጃ ቋት በማጣራት ስሙ ተቀባይነት ካገኘ ተገቢውን የአገልግሎት ክፍያ በማስከፈል የማረጋገጫ ደብዳቤ መስጠት ነው፡፡ ስሙ ተቀባይነት ካላገኘ ደግሞ ሕጋዊና አመክንዮን መሠረት ያደረገ ምክንያት በጽሑፍ ከመስጠት በተጨማሪ፣ ተቀባይነት ሊኖረው የሚችል ስያሜ እንዲያቀርብ ለአመልካቹ ምክር መለገስ ከባለሙያው ይጠበቃል፡፡ የንግድ ማኅበር ስም ተራ ነገር ነው ብለን የምናልፈው ጉዳይ አይደለም፡፡ በንግድ ድርጅቱ በሚመረተው ምርት ወይም በሚሰጠው አገልግሎት ዕርካታን ባገኙ ደንበኞች አማካይነት በሒደት የሚፈጠር መልካም ስም/ዝና መለያ (ብራንድ) ሆኖ ያገለግላል፡፡ ይህ መልካም ስም/ዝና በንግድ ውስጥ ከፍተኛ ዋጋ ያለው አላባ ነው፡፡
በክፍለ ከተማው የንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ከተራው ‹‹ኤክስፐርት›› እስከ ኃላፊው የተያዘው አቋም ጠቅለል አድርገን ስናስቀምጠው፣ ለንግድ ማኅበር የሚሰጥ ስም የንግድ ማኅበሩ አባላትን መጠሪያ ስም ወይም የስማቸውን የመጀመሪያ ፊደል በመውሰድ መጠቀም ከሚቻል በስተቀር፣ ሌሎች ስሞች ተቀባይነት የላቸውም የሚል ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ በዚህም አቋም አሳማኝ ሕጋዊና ተጠየቂያዊ ምክንያት ሳይሰጥ እኛን ጨምሮ ብዙዎች አመልካቾችን ሲመልሱ ታዝበናል፡፡ ሁለቱንም ጊዜ ቢሮው/ጽሕፈት ቤቱ ያልተቀበለውን ስያሜ የንግድ ሚኒስቴር ተቀብሎ አስተናግዶናል፡፡ ስያሜው ተቀባይነትን አግኝቶ የማረጋገጫ ደብዳቤ ሲዘጋጅ እንኳን ዋናው ቅጅ ለአመልካቹ አይሰጥም፡፡ ዋናውን በበቂ ቅጅ አዘጋጅቶ ካስፈለገም የአገልግሎት ክፍያውን አስተካክሎ አመልካቹ እንዲደርሰው ማድረጉ ችግር አለው ወይ?
የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ቁጥር 686/2002 (እንደተሻሻለ) አገር አቀፍ ተፈጻሚነት ያለው ሕግ ነው፡፡ እዚህ ላይ አጽንኦት መስጠት የምንፈልገው የሚኒስቴሩ ማስተናገድ አንድ ጉዳይ ሆኖ፣ (በሚኒስቴሩም ደረጃ አንዳንድ አገልግሎቶች ያለ ሕግ አግባብ የሚከለከሉበት ሁኔታ አለ፡፡ እንዳስፈላጊነቱ ለወደፊቱ ለማንሳት እንሞክራለን፡፡) ሚኒስቴሩ በአዋጁ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት አስፈላጊ ማስፈጸሚያ ደንቦችና መመርያዎች እንዲወጡና ለሚመለከታቸው አስፈጻሚ አካላት እንዲደርሱ በማድረግ፣ እንዲሁም አስፈላጊውን ሥልጠና በመስጠት ኃላፊነቱን በአግባቡ ተውጥቷል ወይ ስንል አዎንታዊ መልስ ለማግኘት እንቸገራለን፡፡ በሌላ በኩል የሚያስፈጽሙትን ሕግ ጠንቅቆ ማወቅ፣ ከሚመለከተው አካል በቃልም ሆነ በጽሑፍ ጠይቆ መረዳት፣ ችግሩ የሕግም ከሆነ ሕጉ እንዲሻሻል ሐሳብ ከማቅረብ ጋር ሕጉ እስኪሻሻል ከሚመለከተው ጋር በመነጋገር ጊዜያዊ አስተዳደራዊ መፍትሔ መሻት የክፍለ ከተማው ባለሙያዎችና ኃላፊዎች ድርሻ ይመስለናል፡፡ ሕግ ችግር ለመፍታት፣ ሥርዓት ለማስያዝና አሠራርን ለማቅለል ካልሆነ ፋይዳው ምንድነው? ሚኒስቴሩ ከየካቲት 17 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ሥራ ላይ የዋለ የንግድ ስም ምዝገባና የአመዘጋገብ ሥርዓቱን ለማቀላጠፍ መመርያ ቁጥር 003/2007ን አውጥቷል፡፡ ዕርምጃው የሚደገፍ ቢሆንም ለሚመለከታቸው የክፍላተ ከተሞች የንግድና ኢንዱስትሪ ጽሕፈት ቤቶች በቶሎ የማስተዋወቁ ወይም የማሠልጠኑ ተግባር ካልተከናወነ የተገልጋዩ መጉላላት ይቀጥላል፡፡ ምክንያቱም መመርያው ከወጣም በኋላ የመከልከሉ አባዜ በአንዳንድ ክፍላተ ከተሞች ቀጥሏልና፡፡
በፈቃድ ሰጪ አካላትም ይሁን የተለያዩ አገልግሎት በሚሰጥባቸው መሥሪያ ቤቶች የሚታይ ውሳኔን ያለመስጠት፣ ሕግን ሥራ ላይ በሚውልበት መንገድ ሳይሆን በዘፈቀደ የመተርጎም ጉዳይ፣ ለተገልጋይ መብት ሳይጨነቁ ‹አይቻልም› ብሎ መሸኘት፣ ለክልከላም ሆነ ለፈቃድ ምክንያታዊ አለመሆን፣ የሚያስፈጽሙትን ሕግ ዓላማ የማያራምዱ ቅፆች ይዘት፣ ከሕግ በላይ የሆኑና የአሠራር ግልጽነትና ወጥነት የማይታይባቸው ለክልከላ የተቀመጡ ልማዳዊ አሠራሮች መስፈን፣ ወዘተ ምክንያቶች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡
- የብቃት ችግር (በተሰማሩበት ሥራ በቂ ዕውቀትም ሆነ ልምድ አለመኖር)፣ በዚህም ምክንያት በራስ መተማመንን ማጣት፣
- መከልከል እንደ ‹ንቅዘት› ታይቶ ተጠያቂነትን ስለማያስከትል ኃላፊነትን መሸሻና የሰነፎች መደበቂያ ዋሻ መሆን፣
- የሕጉን መንፈስ ያራምዳል፣ አመክንዮአዊና ተገቢ ነው ብለው በሚያምኑበት መንገድ ለማስተናገድ የሚፈልጉ ሠራተኞች ደግሞ ‹‹ግምገማን›› እና ‹‹ጉቦ ተቀብሎ ነው ያስተናገደው›› የሚል ክስን (ብሎም አላስፈላጊ የሆነ የሥራ ዝውውርን ሲከፋም ስንብትን) በመፍራት ‹‹የማያስጠይቀው›› የ‹‹ከልካዮች›› ጎራ ውስጥ መቀላቀል፣
- ቅንነት መጥፋት (ለመስተናገድ ቢሮዎችን የሚጎበኙ ባለጉዳዮች ራሳቸውን ዝቅ አድርገው እንዲሽቆጠቆጡና እንዲያጎበድዱ የሚደረግበትና ከጥበቃ እስከ ኃላፊ ያለው ሠራተኛ አገልጋይነቱን ዘንግቶ በንቀትና በማናለብኝነት የሚኮፈስበት ልማድ መንሰራፋት)፣
- በተለያዩ ስብሰባዎች አማካይነት ባለጉዳይን ማጉላላት (የኃይል መቋረጡ፣ የኔትወርኩ ችግር እንዳለ ሆኖ፣ አሁን የተያዘውና እጅግ የሚያሳፍረው ፈሊጥ ደግሞ ተገልጋይን አሠልፎና ጎልቶ እዚያው ስብሰባ መቀመጥ)፣
- አንድ ሠራተኛ በተለያዩ ምክንያቶች በሥራ ገበታው መገኘት ሳይችል ሲቀር እስኪመለስ ተተኪ አለመመደብ፣ በምዝገባና ፈቃድ አሰጣጥ ላይ የተሰማሩ ሠራተኞችን እያዘዋወሩ በማሰራት የተሟላ ልምድ እንዲኖራቸው የሚያደርግ አሠራር አለመኖር፣
- በተግባር ሥራ ላይ የዋሉ ጠቃሚ አሠራሮችን በመመርያ መቅረፅ ወይም አገልጋዩና ተገልጋዩ የሚያውቅበት ግልጽ የአሠራር ሥርዓት አለመኖር ለአብነት ይጠቀሳሉ፡፡
ከላይ ለማሳያነት የተጠቀሱት የአሠራር እንከኖች እንደ ኮሶ የተጣባንን የልማድ ዘባተሎና ቡትቶ፣ በመሠረታዊነት የተቃኘንበትን የአመለካከትና የአስተሳሰብ ስንኩልነት አጉልቶ የሚያሳይ ይመስለናል፡፡ ፈጣሪ፣ አሰላሳይ፣ መፍትሔ ፈላጊ ጭንቅላት ባይኖረን እንኳ ቅንነት/በጎነት ለምን ብርቅ ሆነ? የሚወሩልን ‹‹መልካም እሴቶች›› ተሸርሽረው አልቀው በቅርስነት ቤተ መዘክር ይሆን የሚገኙት? ብዙ የሚባልለት ‹‹ሃይማኖተኝነታችን›› ያፈራው ጭፍን ‹‹ተከታዮችን›› ነው ወይስ መንፈሳዊ ልዕልና ያላቸውና ስለሌሎች ደኅንነትና መብት የሚጨነቁ ዜጎችን?
ዛሬ አገልግሎት በሚሰጥባቸው በርካታ የመንግሥት ተቋማት ብዙዎችን የሚያመሳስላቸው ወይም አንድ የሚያደርጋቸው ቋንቋ ‹‹አይቻልም››፣ ‹‹አይፈቀድም››፣ ወዘተ የሚሉ ክልከላዎች ናቸው፡፡ ኧረ ጎበዝ ለዚህ ለተጠናወተን የክልከላ አባዜ መድኃኒቱ ምን ይሆን?
እንዴት ሰው ከቤቱ ማልዶ ወጥቶ ሊስተናገዱ የመጡ ተገልጋዮችን በክልከላ መልሶ ‹‹ሥራ ሠራሁ፣ አገለገልኩ›› የሚል በጎ ኅሊና ይኖረዋል? እንዴትስ ሰላማዊ እንቅልፍ ይተኛል? ወገኖቼ በዚህ ‹‹የመከልከል በሽታ›› የተለከፈውም አባዜው ባስከተለው ጠንቅ እኩል የምሬቱ ተካፋይ መሆኑ አይገርምም? ጆሮ ያለው መስማትን ይስማ፣ ልቡናም ያለው ያስተውል፡፡
ከአዘጋጁ፡– ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡