Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገር“የንፁኃን ሙሰኞችን” ጩኸት ማን ይስማ? 

“የንፁኃን ሙሰኞችን” ጩኸት ማን ይስማ? 

ቀን:

በአሲዮ ዳን

በዳኝነት ሙያ በማገልገል ላይ ከሚገኝ አንድ ወዳጄ ጋር አንድ ካፌ ውስጥ ቁጭ ብለን እያወጋን ነው። ወደ ካፌው እየገቡ የነበሩ በጉልምስና ዕድሜ የሚገኙ ሰውዬ ወዳጄን እንዳዩት ፈራ ተባ እያሉ ወደ ተቀመጥንበት መጡ። ኮፍያቸውን አውልቀው ለወዳጄ ሰላምታና የምሥጋና ቃላት አዥጎደጎዱለትና ለጠጣነው ማኪያቶ ሒሳብ ካልከፈልኩኝ የሚል እሰጥ አገባ ውስጥ ገቡ። ወዳጄ ሰውዬውን የት ነው የማውቃቸው በሚል ጥርጣሬ እየተመለከታቸው “ተከፍሏል እናመሰግናለን” አላቸው። ሰውዬው የወዳጄ ግራ መጋባት ገባቸው መሰለኝ ግራ ቀኙን እየተገላመጡ ድምፃቸውን ዝግ በማድረግ “የላኩልዎት ዕቃ ደረሰዎት ጌታዬ?” አሉ። “የምን ዕቃ?” አለ ወዳጄ እሱም ዙሪያውን በመሳቀቅ እየተገላመጠ። “ያው ጌታ…ዬ … እንት…ኑን ነዋ… በጠበቃዬ በኩል የላኩልዎት ዕቃ…” አሉ ሰውዬው እየተቅለሰለሱና ወደ እኔ እየተመለከቱ። ሰውዬው ስለምን እንደሚያወሩ የገመተው ወዳጄ በእኔ ፊት ቢነግሩት ችግር እንደሌለው ለማሳወቅ ትከሻዬን አቀፍ አደረገኝ። “ገንዘቡን ነዋ!’’ አሉ አሁንም ድምፃቸውን ዝግ አድርገው። “ምን?! ለመሆኑ ስንት ነው የሰጡት?!” አለ ወዳጄ በምፀት። “ያው ለእርስዎ 60 ሺሕ ለረዳትዎ 15 ሺሕ ነው ጌታዬ … ካነሰ ግን ጌታዬ ዛሬውኑ ጨምሬ እልካለሁ፤” አሉት ‘ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ’ በሚል የመተማመን ስሜት።

የወዳጄ ፊት እንደ አዲሱ የትራፊክ መብራት ቦግ ብሎ ቀላ። “ይሰማሉ?! እኔ ከእርስዎ የተቀበልኩት አንዳች ነገር የለም። ሥራዬንም ያከናወንኩት በንፁኅ ህሊናዬ ነው!!!” እያለ ጉዳዩን ለማጣራት ሲከራከሩበት የነበረውን የመዝገብ ቁጥርና ስልክ ቁጥራቸውን ተቀብሎ እንዲሄዱ ነገራቸው። “እሺ … እሺ ጌታዬ” ብለው በፍጥነት ስልካቸውን አውጥተው እየደወሉ ወደ ካፌው በረንዳ ወጡ። ወዳጄ በብስጭት አቀርቅሮ ቀረ፡፡ ሰውዬው ጥቂት ቆይተው እጃቸውን እያወናጨፉ ስልኩን ዘግተው ወደ እኛ ቀረቡ። ወዳጄን እየተመለከቱ “ይቅርታ ጌታዬ … በጣም ይቅርታ … የማምነው ጠበቃዬ ነው ጉድ የሠራኝ … በጣም ይቅርታ … ሰኞ እኔ ራሴ ይዤ እመጣለሁ። በጣም ይቅርታ ጌታዬ…” ብለውት አረፉት። 

ወዳጄ የእሱንና መሰል የሥራ ባልደረቦቹን የዘወትር ምሬት በተሰበረ ስሜት ዘርዝሮ አጫወተኝ። እኔም በዚህ አጋጣሚ መነሻነት የጉዳዩን ዙሪያ ገባ ለመዳሰስ የተለያዩ ባለሙያዎችን በማነጋገር ገጠመኞቻቸውንና ምልከታቸውን አጠናቅሬ ይህቺን ጽሑፍ እንደሚከተለው አዘጋጀኋት። በቅድሚያ ግን ወዳጄ ምሬቱን ያሳረገበትን ንግግር ፍሬ ሐሳብ  ላቅርብላችሁ። “ይኼ ሰውዬ የትኛውን ክርክር ይዞ እኔ ወደ ተሰየምኩበት ችሎት እንደመጣና ምን እንደ ወሰንኩኝ የማስታውሰው አንዳችም ነገር የለም። በእርግጠኝነት የምነግርህ ነገር ግን የሰጠሁት ውሳኔ ምንም ይሁን ምን ዕውቀትና ክህሎቴ በፈቀደልኝ መጠን ሕግን መሠረት ያደረገ እንደሆነ ነው። እውነቱ ይኼ ሆኖ ሳለ እንደምታየው ለዳኛው ጉቦ ልስጥልህ ብሎ በስሜ 60 ሺሕ ብር የተቀበለ ሰው አለ። አሁን ደግሞ ጠበቃው ሰውዬውን ምን ሊያደርግ እንደሚችል ታውቃለህ? ‘እንዴት ዳኛውን የላኩልህ ጉቦ ደረሰህ ወይ ብለህ በአደባባይ ትጠይቀዋለህ?’ ይቺን ብር እንደ ገንዘብ ቆጥሯት በሰው ፊት አዋረደኝ ብሎ ንድድ ነው የሚለው። ስለዚህ አሁን ትንሽ ገንዘብ አምጣና ሄጄ ይቅርታ ልበለው’ ይለውና ሌላ ብር አሁንም በስሜ ሊቀበለው፣ ሰውዬውም ሊሰጠው ይችላል። የእኔን ንፅኅና እኔና አምላኬ እናውቀዋለን። ለሌላው ሰው ግን እንደምትመለከተው ስሜ በየጥጋጥጉ የሚብጠለጠል “ሙሰኛ ዳኛ” ነኝ ከምኑም የሌለሁበት “ንፁኅ ሙሰኛ”።

ለመሆኑ “ንፁኃን ሙሰኞች” እነማን ናቸው?  

 “የንፁኃን ሙሰኞች” ምፀት በየቦታው ይስተዋላል። በባንክ ብድርና በውጭ ምንዛሪ፣ በጨረታ፣ በገቢዎችና ጉምሩክ፣ በመሬት አስተዳደር፣ በመድኅን (ኢንሹራንስ)፣ በንግድ ፈቃድ … ሥራዎች የተሰማሩ ብዙኃን ሠራተኞች የዚህ አሳዛኝ ድርጊት ሰለባ ናቸው። ከሥራው ባህሪ አንፃርም ዋነኞቹ የዚህ ድርጊት ተጎጂዎች የፍትሕ አካላቱ እንደሆኑ ብዙዎች ይስማሙበታል። የምትፈልገውን ውሳኔ አሰጥልሃለሁ፣ በዋስ አስለቅቅሃለሁ፣ ከተከሰስክበት የወንጀል ክስ ነፃ አስወጣሃለሁ፣ ቅጣት አስቀንስልሃለሁ፣ የንብረት እግድ አስወጣልሃለሁ፣ የቀጠሮ ቀን አሳጥርልሃለው ወይም አስረዝምልሃለሁ፣ መዝገቡን አስጠፋልሃለሁ ወይም አዘጋልሃለሁ በሚሉና ሌሎች ምክንያቶች በስማቸው ጉቦ ከሚሰበሰብባቸው ሰዎች መካከል ዋነኞቹ ዳኞች፣ የፍርድ ቤት ሹማምንት፣ ረዳት ዳኞች፣ የመዝገብ ቤት ሠራተኞች፣ ዓቃቢያነ ሕጎች፣ በተለያየ ደረጃ የሚገኙ የዓቃቢያነ ሕግ ኃላፊዎች፣ የፖሊስ አመራሮችና መርማሪ ፖሊሶች ናቸው። ለዛሬ በፌዴራል ፍርድ ቤቶችና የዓቃቤ ሕግ መሥሪያ ቤቶች ስለሚገኙት “ንፁኃን ሙሰኞች” ላስቃኛችሁ፡፡  

ፍርድ ቤቶች

በዳኞችና በሌሎች ንፁኃን ሰዎች ስም ጉቦ ይቀበላሉ ተብለው በዋነኝነት የሚታሙት በሥራቸው አጋጣሚ ወይም ባህሪ የተነሳ በክርክር መዝገቦች ላይ የሚከናወነውን ተግባር ለማየት ወይም ለመስማት፣ የዳኞች ውሳኔ ይፋ ከመደረጉ አስቀድሞ ወይም ከውሳኔው በኋላ ከተከራካሪ ወገኖች ቀድመው ለማወቅ ዕድሉ ያላቸው፣ ወደ ዳኞች ጽሕፈት ቤት በሥራ አጋጣሚ የሚመላለሱ ሠራተኞችና በተለያየ አጋጣሚዎች ለዳኞች ቅርብ የሆኑ ወይም ቅርብ የሆኑ መስለው ለመታየት ከሚጥሩ የፍርድ ቤት ሠራተኞች መካከል የተሰገሰጉ፣ ስለ ዳኞቹም ሆነ ስለ ተቋሙ ስምና ክብር አንዳችም የማይጨነቁ “በልቶ አዳሪዎች” ናቸው። ይሠሩባቸው ከነበሩ የተለያዩ የፍትሕ አካላት መሥሪያ ቤቶች በተለያዩ ምክንያቶች ከለቀቁ ወይም ከተባረሩ ሠራተኞች መካከልም በዚህ ሥራ የተሰማሩ እንዳሉ ጉዳዩን የታዘቡ ሁሉ ይስማሙበታል። የዚህ ሥራ አጋፋሪ እንደሆኑ ከሚታመኑት ሰዎች መካከል አብዛኛዎቹ የፈለቁት “ጉዳይ አስፈጻሚ” ወይም “ጉዳይ ገዳዮች ”በመባል ከሚታወቁት ሰዎች መካከል ነው። የድጋፍ ሰጪ ሠራተኞችን ከሊቅ እስከ ደቂቅ የሚያውቁት እነዚህ ሰዎች በፍርድ ቤቶቹ ውስጥ ከደመወዝተኛው የፍርድ ቤቱት ሠራተኛ እምብዛም የማይተናነስ የፈጻሚነት ሚና እንዳላቸው ለባለጉዳዮች የሚያሳዩት፣ በፍርድ ቤቶች ውስጥ ያለማንም ከልካይ ከሥራ ሰዓት ቀድመው በመግባትና ሲብስም በተለያዩ የድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ቢሮ ውስጥ የመረጡትን ወንበር ስበው በመቀመጥ ጭምር ነው፡፡  

ማሳያ አንድ

ከሁለት ዓመት በፊት በልደታ ምድብ ከሚገኙ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች በአንዱ ውስጥ የአንድ ዳኛ ረዳት ሆኖ ሲሠራ የነበረ ሠራተኛ በራሱና በዳኛው ስም ጉቦ ሲቀበል በፀጥታ ሠራተኞች እጅ ከፍንጅ ተይዞ፣ በዚህ መነሻነት ዳኛውን ጨምሮ ሌሎች ተጠርጣሪዎች ታስረው ምርመራ ተጀምሮ ነበር። ጉዳዩንም “ጉቦ ሲቀበሉ እጅ ከፍንጅ የተያዙት ዳኛና ረዳታቸው በቁጥጥር ሥር ዋሉ፤” ብለው የተለያዩ የኅትመትና የኤሌክትሮኒክ የመገናኛ ብዙኃን በፊት ገጻቸውና በአርዕስተ ዜናነት በስፋት ዘገቡት። ምርመራው ከቀጠለ በኋላ ግን ዳኛው በጉዳዩ ውስጥ እጃቸው እንደሌለ በመረጋገጡ በነፃ ተለቀው በረዳት ዳኛው ላይ የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የወንጀል ክስ አቅርቦበት ጉዳዩ በፍርድ ቤት በመታየት ላይ ነበር። የዳኛው በሙስና ተጠርጥረው መታሰርን ጮክ ብለው ከዘገቡ መገናኛ ብዙኃን ውስጥ ከጥቂቶቹ በቀር የዳኛውን በነፃ የመለቀቅ ዜና ለመዘገብ ብዙም አልተጨነቁም። አልያም መለቀቃቸውን አልሰሙም።

ማሳያ ሁለት

ከጥቂት ወራት በፊት አንድ በፍርድ ቤት ክርክር ያላቸው ሰው ጉዳዩን ወክሎ የሚከራከርላቸው ጠበቃ ያቆሙና ሙግት ይጀምራሉ። ጠበቃቸውም ጉዳዩን የያዘውን ዳኛ በሰው ስላገኘሁት ጉቦ እንስጠው ይላቸዋል። ጉቦ ለዳኛው ብሰጥ የምፈልገውን ውሳኔ አገኛለሁ የሚል ዕምነት ያደረባቸው ተከራካሪም ለዳኛው ተብለው የተጠየቁትን እጅግ በጣም ብዙ ሺሕ ብር ለጠበቃቸው ይሰጣሉ። ዳኛው የሰጡት ውሳኔ ግን ጉቦ የላኩትን ተከራካሪ ሳይሆን፣ ሌላኛውን ተከራካሪ የሙግቱ አሸናፊ አደረገ። ይኼኔ ለዳኛው ብሎ የተቀበለውን ብር ለራሱ ባደረገው ጠበቃና በደንበኛው መካከል ከፍተኛ ፀብ ተፈጠረ። ዕውነታውን ያወቁት የጠበቃው ደንበኛም ጉዳዩን ለፍትሕ ሚኒስቴር የጠበቆች ዲሲፕሊን ኮሚቴ በማቅረባቸው ጉዳዩ እንዲጣራና የጠበቃው የጥብቅና ፈቃድ እንዲታገድ ተደርጎ ነበር።

ዓቃቢያነ ሕግ

ፍትሕ ሚኒስቴር መሠረታዊ የሥራ ሒደት ለውጥ (BPR) አከናውኖ ወደ ሙሉ ትግበራ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ የወንጀል ምርመራን ከፖሊስ ጋር በጋራ ማከናወን፣ በምርመራ መዝገቦች ላይ ቀልጣፋና ጥራቱን የጠበቀ ውሳኔ ለመስጠት ይረዳል በሚል እምነት የፌዴራል ዓቃቢያነ ሕጎችን በየፖሊስ ጣቢያው መድቦ ማሠራት ጀምሯል። ዓቃቤ ሕግ በምርመራ መዝገብ ላይ የሰጠውን ወይም የሚሰጠውን ውሳኔ ከከሳሽ ወይም ከወንጀል ተጎጂውና ከተከሳሽ በፊት በሥራቸው አጋጣሚ ማየት የሚችሉ ወይም የሚገምቱ በፖሊስም ሆነ በዓቃቤ ሕግ ተቋም ውስጥ የመሸጉ “አንዳንድ” ሠራተኞች በዚህ ድርጊት በዋነኝነት የሚሳተፉ መሆኑን የሚያስረዱ ተጨባጭ ምሳሌዎችን የሚጠቅሱ ዓቃቢያነ ሕጎች ጥቂት አይደሉም። በዓቃቤ ሕግ ስም ጉቦ ከሚቀበሉ መካከል የሁሉም ከሳሽ ወይም ተከሳሽ ወንድም፣ አባት፣ ባል፣ አብሮ አደግ፣ የአክስት ልጅ … ነን የሚሉ በየፖሊስ ጣቢያው የሚያውቁት ሰው የማይጠፋው “ጉዳይ ገዳዮች” ይገኙበታል። የእነዚህ ‘ጉዳይ ገዳዮች’ ድርጊት በስፋት ስለሚታወቅ እነዚህ ሰዎች በዓቃቢያነ ሕጉም ሆነ በብዙዎቹ ፖሊሶች በኩል በጥርጣሬ የሚታዩና ፊት የሚነሱ ናቸው።

“ከሁሉ በላይ የሚያሳፍረው ግን” ይላል አንድ ዓቃቤ ሕግ “የወንጀል ምርመራ ሥራ ባህሪ የግድ ስለሚል በምርመራው ሒደትና በሚመጣው ውጤት ላይ በምርመራ መዝገቡ ላይ ውሳኔ ከመስጠትህ በፊት አብረውህ ከሚሠሩ መርማሪ ፖሊሶች፣ የምርመራ ክፍል ኃላፊዎችና ሌሎች ዓቃቢያነ ሕግና ኃላፊዎች ጋር ትመካከራለህ፣ ትከራከራለህ። ከውስጣችን የተሰገሰጉ እንክርዳዶች ግን ይህንን ውይይት ለንግድ ይጠቀሙበታል። በመጨረሻ ውሳኔ የምትሰጠው አንተ ነህና በስምህ ከከሳሽም ሆነ ከተከሳሽ ጉቦ ይቀበሉበታል፡፡ በጥቅሉ ያለምግባራችን ስማች በየቦታው ይብጠለጠላል፤” በማለት ችግሩ ምን ያህል መልካም ስማቸውን እንደሚያጎድፍ ይገልጻል። በዚህ ዓይነት ሁኔታ ከሚሠሩ ዓቃቢያነ ሕጎች መካከል ሁለቱ ያጫወቱኝን ገጠመኞቻቸውን እንደሚከተለው አሰናዳኋቸው።

ማሳያ ሦስት

በአንድ ወቅት የሚሸጣቸው ንብረቶች የተዘረፉበት ነጋዴ በአንድ ፖሊስ ጣቢያ ክስ ያቀርብና የወንጀል ምርመራ ተጠናቅሮ መዝገቡ በክፍሉ ለተመደበው ዓቃቤ ሕግ ይቀርብለትና መዝገቡን መርምሮ በተጠርጣሪው ላይ የወንጀል ክስ በማቅረብ ተከሳሹን በፈጣን የወንጀል ችሎት (RTD ይሉታል) እንዲቀርብ ያደርጋል። ጉዳዩን ያየው ፍርድ ቤትም ተከሳሹን ጥፋተኛ ነው በማለት ቅጣት ይጥልበትና ወደ ማረሚያ ቤት እንዲወርድ ይወስንበታል። ይህንን ተከትሎ ፖሊስ ቀድሞ በኤግዚቢትነት ይዟቸው የነበሩ ብዛት ያላቸው አዳዲስ ጫማና ልብሶች ለነጋዴው እንዲመለሱለት በሕጉ አግባብ በመወሰን ዓቃቤ ሕጉ በዚህ ምርመራ መዝገብ ላይ የነበረውን ሥራ ያጠናቅቃል። ይኼ ሁላ ሲሆን፣ የቀረበለትን መዝገብ እንደማንኛውም ጉዳይ ከመርማሪው ተቀብሎ ከመሥራት ውጪ ከከሳሽ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት አልነበረውም።

ጉድና ጅራት ወደ ኋላ ነው እንዲሉ ጉዳዩ እልባት ካገኘ ከረጅም ጊዜ በኋላ ዓቃቤ ሕጉ ያንን ነጋዴ ሚኒባስ ታክሲ ውስጥ ያገኘዋል። ነጋዴው ማንነቱን አስታውሶት በኤግዚቢትነት ተይዘውበት የነበሩት አልባሳትና ጫማዎች በአፋጣኝ እንዲመለሱለት ዓቃቤ ሕጉ ስለወሰነለት ከፍተኛ ምሥጋና ካቀረበለት በኋላ፣ “የላኩልህ ጫማዎች እንዴት ናቸው ተስማሙህ?” በማለት ወደ እግሩ ይመለከተዋል። የሰማው ነገር ሊገምተው የማይችል እጅግ በጣም አዋራጅ ድርጊት የሆነበት ዓቃቤ ሕግ ነጋዴውን ምን ማለቱ እንደሆነ እንዲያብራራለት የተለያዩ ጥያቄዎችን ያከታትልበታል። ነጋዴው የሰጠው መልስ ይበልጡኑ አድርቆ አስቀረው። ለካስ አሁን ማንነቱንና የሥራ ድርሻውን ሊገልጸው የማይችለው ሥነ ምግባርና ሞራል ያልጎበኘው ሰው፣ ጉዳዩን አፋጥኜ አስወስንልሃለሁ በማለት በመዝገቡ ላይ ከተደራረደረ በኋላ ለራሱ ጥቂት አልባሳትን ከተቀበለ በኋላ የዓቃቤ ሕጉ ምርጫ ናቸው ያላቸውን ጫማዎች በዓቃቤ ሕጉ ስም ከነጋዴው ተቀብሎ ወስዷል። የሆነውን ነገር የሰሙም ሆነ ተመሳሳይ ድርጊቶችን ማስቆም ያልቻሉ ዓቃቢያነ ሕጎች አፍረውበት የነበረው የጫማው ጉዳይ ዛሬ ዛሬ መቀለጃ ሆኗል ይላሉ አስተያየታቸውን የሰጡኝ ዓቃቢያነ ሕጎች። አዲስ ጫማ፣ ልብስ ወይም ተንቀሳቀሽ ስልክ ቀይሮ የመጣ ዓቃቤ ሕግ ከባልደረቦቹ የትኛው ባለጉዳይ ነው የላከልህ? የሚል ጥያቄ ይቀርብበታል።  

ማሳያ አራት

ሌላ ዓቃቤ ሕግ ካጫወተኝ ገጠመኞቹ አንዱን ከሞላ ጎደል እንደወረደ ይህንን ይመስላል። “ከሜክሲኮ ወደ ብሔራዊ ቴአትር እጓዛለሁ። ወደ ሜክሲኮ አቅጣጫ የሚነጉድ አንድ ዲኤክስ ተሽከርካሪ ሰንጋ ተራ ትራፊክ መብራት ጋ ሲደርስ መኪናውን አቁሞ በኋላ ማርሽ ይከተለኛል። መስኮቱን ከፍቶ እጁን እያወዛወዘ ሲከተለኝ መንገድ ወይም ቦታ እንድጠቁመው የፈለገ አልያም የሚያውቀኝ ሰው መስሎኝ ወደ መኪናው ጠጋ አልኩ። እሱም መኪናውን አቁሞ ሞቅ ያለ ሰላምታ ሲሰጠኝ ፊቴ ላይ የሚነበበው ግርታ ነገረው መሰለኝ “አላወቅከኝም?” አለኝ። “አላወቅኩህም ማን ልበል?” ሲለው፣“በአንተ ውለታ እኮ ነው ዛሬ እዚህ ያለሁት። ሰው ገጭቼ ታስሬ እኮ አንተ ነህ ያስፈታኸኝ!!! ውለታህን አልረሳውም። እባክህ ግባና ሻይ ቡና እንበል፤” “አመሰግናለሁ አልገባም … ግን የትና መቼ ነው ያስፈታሁህ?” ይለዋል፡፡ “በዚህ በዚህ ጊዜ እገሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ታስሬ በነበረ ጊዜ፤” አለኝ። “በገጨኸው ሰው ላይ የደረሰው ጉዳት ምንድን ነበር?” ጠየቅኩት። “ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ያመጣሁት የሕክምና ማስረጃ ጉልበቱና እግሩ በትንሹ እንደተላጠ ነው የሚያሳየው፤” አለኝ። “ነው … በል እሺ ደህና ሁን፤” ብዬ ጉዳዩ የትኛው ሊሆን እንደሚችል እያሰላሰልኩ ትቼው መንገዴን ጀመርኩኝ። “ኧረ እባክህ ግባና ወደ ፈለግከው ቦታ እንሂድና ሻይ ቡና እንበል። አለበለዚያ እኔ አልፌ ልጠብቅህ (ሰው እንዳያይህ ፈርተህ ስለሆነ የሚመችህን ቦታ ንገረኝ መሆኑ ነው)” አለኝ። የእኔ በአቋሜ መፅናት ለእሱ መግደርደር ስለመሰለው በንዴት ትቼው ስሄድ ፀጉሩን እየፈተለ፣ “እሺ ካልተመቸሽ ሌላ ጊዜ እንገናኛለን። እንዲያው አሁንም አንዲት ሌላ ክስ ነበረችኝ፡፡ ይህቺንም እንደባለፈዋ የሆነ ነገር ልግጭሽና ብትሠሪልኝ?” አለኝ (አሁንም ያልደረሰኝን ጉቦ ልስጥህ ማለቱ ነው)። ታዲያ ሰውዬው ከነገረኝ ፍሬ ነገሮች ተነስቼ ለብቻዬ ነገሩን ለማስታወስ ሞከርኩ።

በቸልተኝነት በማሽከርከር በመኪና ተገጭቶ አደጋ የደረሰበት ሰው ጉዳት ቀላል ከሆነ (ልክ ጉልበቱና ጭንቅላቱ ተላጠ እንዳለኝ ሰው ዓይነት ከሆነ) የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ ገጪውና ተገጪው ከታረቁ ዓቃቤ ሕግ ክስ ለማቅረብ ሥልጣን እንደሌለው ይደነግጋል። ይህንን የማያውቁ እንደዚህ ዓይነት ሾፌሮች ግን ዓቃቤ ሕጉ መዝገቡን እንዲዘጋልህ ጉቦ ልስጥልህ እየተባሉ እጁ ሙስና ውስጥ በሌለው ዓቃቤ ሕግ ስም ጉቦ ለራሳቸው የሚቀበሉ ሰዎች ሲሳይ ይሆናሉ። ዓቃቤ ሕጉም ጉቦ ተቀብሎ መዝገብ ዘጋ ይባላል፤” በማለት ጨዋታችንን ፈገግ ባሰኘኝ ምኞቱ ቋጨው።

“ጉቦ ተቀብዬ ባላውቅም በስሜ የሚበላው ጉቦ ግን ጉቦ ከሚቀበሉ ሰዎች በላይ አንገቴን እንዳጎበጠው ይሰማኛል። በዚህ ምክንያት አብዛኛው ባለጉዳይ ንፅኅናህ አይገባውም፣ አያምንህምም። ይኼ ደግሞ ያማል!!! አንዳንዴ ምን እንደምመኝ ታውቃለህ? ጉቦ መስጠት ወንጀል መሆኑ አያጠራጥርም። ይህንን መተላለፍ የመረጠ ግን ለእኛ መልካም ስም ሲል የሚልከውን ጉቦ ምናለ ለተቀባዩ ሰው በሐዋላ ቢልከው?! ያኔ በልበ ሙሉነት ለእገሌ ጉቦ ሰጠሁ ይበል። እንዲህ ቢሆን ኖሮ ምናልባት እኔና አንተም ዛሬ በዚህ ጉዳይ ላይ ላናወራ እንችል ነበር።”

ማጠቃለያ

ስማቸው ያላግባብ እየጎደፈ ያሉ “ንፁኃን ሙሰኞች” በስማቸው ጉቦ የሚቀበሉ ሰዎችን ሕግ ፊት አቅርበው በማስቀጣት ድርጊቱን እንዳይከላከሉ ትልቅ ፈተና የጋረጠባቸው አንደኛው ምክንያት፣ ጉቦን “በጉዳይ ገዳይ” ወይም “አገናኝ“ በኩል መቀበል የ“ሀቀኞቹ ሙሰኞች” ቀዳሚ ምርጫ ወይም “ልማዳዊ አሠራር” በመሆኑ ጉቦ ለመስጠት የሚመርጥ ሰው ይህንኑ መንገድ የሚከተል መሆኑ ነው። ሁለተኛው ምክንያት የሚባለው ምንም እንኳን ጉቦ መስጠት ሕገወጥ ቢሆንም ይህንን የሚመርጡ ግን የሚልኩት ጉቦ ለተባለው ሰው የሚሰጥ ሳይሆን፣ ተቀባዮቹ ጋ የሚቀር መሆኑን ባለማወቃቸው ጉዳዩ ይፋ ሳይወጣ የሚቀር መሆኑ ነው። ሦስተኛው ምክንያት ብለው የሚያስቀምጡት ደግሞ በተለያዩ አጋጣሚዎች ዕውነታው ሲታወቅ ጉቦውን የሰጡት ሰዎች በራሴ ላይ ተጠያቂነት ወይም ጥቃት ይመጣብኛል በሚል አመለካከት በሌላ ሰው ስም ጉቦ በተቀበሉት ሰዎች ላይ ለመመስከር ፈቃደኛ አለመሆናቸው ነው። ለመመስከር ፈቃደኛ ቢሆኑም ደግሞ ጉቦውን የሚቀበሏቸው ሰዎች ድርጊቱን ሕገወጥ እንደሆነ ስለሚያውቁ ጉቦውን የሚቀበሉት በረቀቀ መንገድ በመሆኑ ማስረጃ ለማግኘት አስቸጋሪ መሆኑ ሌላኛው የማያሸንፉት ተግዳሮት እንደሆነ ብዙኃኑን “ንፁኃን ሙሰኞች” ያስማማል። ዘላቂ መፍትሔ እስኪያገኝም ተቋማቱም ሆነ “ንፁኃን ሙሰኞቹ” የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ችግሩን ለመቅረፍ የሚያደርጉትን ጥረት ቀጥለዋል። የእኔም የማጠቃለያ መልዕክት አንድ ነው ጉቦ አትስጡ!!! ጉቦ መስጠትን ከመረጡ ግን የሰጡት ሰው የላኩለትን ጉቦ መቀበሉን እስካላረጋገጡ ለእከሌ ጉቦ ሰጠሁ አይበሉ!!!” ብሩህ ቀናትን ተመኘሁ። ሰላም።

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

     

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...