Monday, July 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለአዲስ አበባ ከሚያስፈልጉ ባቡሮች አገር ውስጥ የገቡት 33 ደረሱ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ዘጠኝ ማቋረጫዎችን ለመገንባት ታቅዷል

የአዲስ አበባ ከተማ የቀላል ባቡር አገልግሎት ሲጀመር መንገደኞችን ለማጓጓዝ ከሚያስፈልጉ 41 ባቡሮች ውስጥ ወደ አገር ውስጥ የገቡት 33  መድረሳቸው ተገለጸ፡፡  በቻይና የተሠሩት እነዚህ ባቡሮች እያንዳንዳቸው 46 መቀመጫዎች ያሉዋቸው ሲሆን፣ በጠቅላላው ከ317 በላይ መንገደኞችን በአንዴ ማጓጓዝ የሚችሉ ናቸው ተብሏል፡፡

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ወ/ት አበበች ድሪባ እንደገለጹት፣ እስካለፈው ሳምንት መጀመርያ ድረስ ኮርፖሬሽኑ የተረከባቸው ባቡሮች ቁጥር 25 ነበሩ፡፡ በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ደግሞ ስምንት ባቡሮች የገቡ በመሆኑ በጠቅላው የተከረባቸው ባቡሮች ቁጥር 33 ሊደርስ ችሏል፡፡ ቀሪዎቹ ባቡሮች ደግሞ እስከ ሚያዝያ 2007 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ የሚገቡ እንደሆነም ታውቋል፡፡ 41ዱ ባቡሮች ሰማያዊያና አረንጓዴ ቀለም ያላቸው ሲሆን፣ ሰማያዊ ቀለም ያላቸው 21 ባቡሮች ከደቡብ ወደ ሰሜን፣ አረንጓዴ ቀለም ያላቸው 20ዎቹ ባቡሮች ደግሞ ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ ባለው መስመር ላይ አገልግሎት ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ከአንድ ወር ተኩል  በፊት በይፋ የሙከራ ሥራ የጀመረው የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት አሁንም በተከታታይ የሙከራ ሥራዎች ላይ ነው፡፡ የኮንስትራክሽን ግንባታ የማጠናቀቂያ ሥራዎቹም ወደ መጨረሻው ምዕራፍ ላይ ነው ተብሏል፡፡ እንደ ሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዋ ገለጻ፣ የባቡር ትራንስፖርቱ ከሦስት ወራት በኋላ አገልግሎት ይጀምራል ተብሎም እየተጠበቀ ነው፡፡

የቀላል ባቡሩ አገልግሎት በይፋ ሥራ ከመጀመሩ በፊትም የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን የጠቆሙት የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዋ፣ ከነዚህ መካከል አዋጭና ፍትሐዊ የሆነ የቀላል ባቡር ትራንስፖርት ታሪፍ ለማውጣት የሚያስችለው ጥናት ነው፡፡ ታሪፉን ለመቅረፅ የሌሎች አገሮችን ልምድ በመውሰድ ጭምር እየተሠራ በመሆኑ፣ በጥናቱ መሠረት የቀላል ባቡር ትራንስፖርት ዋጋ ይፋ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ከዚህም ሌላው ከቀላል ባቡሩ ጋር የተያያዙ አዳዲስ ሕጎች መቀረፅ ስላለባቸው  የባቡር ትራንስፖርቱ አገልግሎት ከመጀመሩ በፊት ሕጎቹን ለማውጣት ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡ ይወጣሉ ተብለው ከሚጠበቁ ሕጎች መካከል አንዱ ከትራፊክ ደኅንነትና ከቀላል ባቡሩ አገልግሎት ጋር ትስስር ያላቸው መሠረተ ልማቶችን ለመንከባከብና ከአደጋ ለመጠበቅ የሚያስችለው ሕግ ይጠቀሳል፡፡ በሐዲዱ ላይ ቆሻሻ መጣል፣ አጥር መዝለልና በባቡር መስመሩና ተያያዥ መሠረተ ልማቶች ላይ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ አካላት ላይ በሕግ ዕርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ሕግ ነው፡፡ ይህ ሕግ ከትራንስፖርት ሚኒስቴር ጋር በመሆን የሚዘጋጅ ስለመሆኑም ከተደረገው ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

 ሕጉ በቶሎ እንዲወጣ የተፈለገበት ዋና ምክንያት የባቡር ትራንስፖርቱ ገና በሙከራ ሥራ ላይ በሚገኝበት ወቅት በመሠረተ ልማቱ ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት አሳሳቢ በመሆኑ ነው፡፡ እስካሁን ባለው መረጃ የቀላል ባቡሩ የሚያልፍባቸው በተለያዩ ቦታዎች ላይ ከሰባት በላይ በሚሆኑ ቦታዎች በተሽከርካሪዎች መገጨታቸው ለአብነት ተጠቅሷል፡፡

 ከቀላል ባቡሩ አገልግሎት መጀመር ጋር ተያይዞ የትራንስፖርት ሚኒስቴር የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት የዕለት ዕለት ሥራውን የሚከታተል የባቡር ተቆጣጣሪ አካል ያዋቅራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በሁለቱም የቀላል ባቡር መስመር አቅጣጫዎች ለእግረኛና ለተሽከርካሪዎች መሸጋገሪያ ይሆናሉ የተባሉ ተሻጋሪ መንገዶችን ለመገንባት የሚያስችል ዕቅድ መነደፉ ተገልጿል፡፡ በሁለቱም አቅጣጫዎች የእግረኛ መሸጋገሪያ ያስፈልጋቸዋል የተባሉ ዘጠኝ ቦታዎች የተመረጡ ሲሆን፣ እነዚህን መሸጋገሪያዎች ለመገንባትም የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ጋር በመነጋገር ላይ እንደሆነ ታውቋል፡፡ እነዚህ መሸጋገሪያ መንገዶች እግረኞች ረዥም መንገድ ሳይጓዙ በቀላሉ እንዲሻገሩ የሚያስችሉ ናቸው ተብሏል፡፡ እንደ ወ/ት አበበች ገለጻ፣ በአሁኑ ወቅት በሁለቱም አቅጣጫዎች በተዘረጋው የቀላል ባቡር መስመር 37 መሸጋገሪያዎች አሉ፡፡ በአንዳንድ የከተማው ነዋሪዎች ዘንድ ግን ለማቋረጫ በተሠሩት መንገዶች መካከል ያለው ልዩነት ረዥም በመሆኑ መንገደኞችም ሆኑ እግረኞች በቀላሉ እንዳይሸጋገሩ ምክንያት እየሆነ ነው ይላሉ፡፡

የመሸጋገሪያ እጥረቱ ለምን ተከሰተ? ቀድሞ ዲዛይኑ ላይ አልነበረም ወይ? ለሚለው ጥያቄም ወ/ት አበበች፣ ‹‹መሸጋገሪያዎቹ ቀደም ብሎ በዲዛይን ላይ የነበሩ ናቸው፡፡ ነገር ግን በተወሰኑ ቦታዎች ላይ በተለይ ከሰሜን ወደ ደቡብ ባለው መስመር በተወሰነ ደረጃ የመኪና መሻገሪያ እጥረት አለ፤›› ብለዋል፡፡ ይህም በአንድ ቦታ ብቻ 1.2 ኪሎ ሜትር የሚርቅ መሸጋገሪያ ከመኖሩ ውጭ በሌላው ቦታ ግን በጣም የተስተካከለ ማቋረጫዎች እንዳሉ ይገልጻሉ፡፡ አሁን ባለው ደረጃ አንድ መሸጋገሪያ ከሌላው መሸጋገሪያ የሚርቀው በአማካይ 745 ሜትር ነው፡፡ ይህ ርቀት ረዥም እንዳልሆነ ያብራሩት ወ/ት አበበች፣ ‹‹እንደውም በቀላል ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሠራበት ሕግ በአጭር ርቀት ማቋረጫዎች መሠራት የሌለባቸው መሆኑን ነው፤›› ይላሉ፡፡ ለዚህም እንደ ምክንያት የሚቀርበው ባቡር ፈጣን አገልግሎት መንገደኞችን ማጓጓዝ ስላለበት በአጫጭር ርቀት ማቋረጫዎች እንዲኖሩ ስለማይፈለግ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ግን በአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ከተሠሩለት ማቋረጫዎች ሌላ በ27ቱም ፌርማታዎች ላይ እግረኞች ከግራ ወደ ቀኝ እንዲሁም ከቀኝ ወደ ግራ ሊሸጋገሩ የሚችሉበት ዕድል አለው፡፡

የወ/ት አበበች  ገለጻ ግን አሁን ለማቋረጫነት የተሠሩት ቦታዎች አንዱ ከአንዱ ብዙም ርቀት የሌለው መሆኑን የሚጠቁም ነው፡፡ ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ጋር በመነጋገር ይሠራል የተባለው መሸጋገሪያ መንገድ ደግሞ አለ የሚባለውን ችግር ያቃልላል የሚል እምነት አላቸው፡፡

 የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት በጥቅሉ 475 ሚሊዮን ዶላር የሚፈጅ ነው፡፡ 32.2 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለውን ይህን ፕሮጀክት የሚገነባው የቻይና ምድር ባቡር ኩባንያ ሲሆን፣ አማካሪው ደግሞ የስዊዲኑ ሲሮድ የተባለ ኩባንያ ነው፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች