Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ውኃ አልባው ወደብ እየሰፋ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ የመጀመርያው የደረቅ ወደብ አገልግሎት ወደ ሥራ የገባው በ2001 ዓ.ም. ነው፡፡ ከአዲስ አበባ 70 ኪሎ ሜትር ላይ በምትገኘው ሞጆ ከተማ እንዲገነባ የተደረገው ሞጆ ደረቅ ወደብና ተርሚናል ለአገሪቱ የመጀመርያ የሆነውን አገልግሎት የጀመረው 1.5 ሔክታር መሬት በመረከብ ነበር፡፡

በኢትዮጵያ የደረቅ ወደቦች ኢንተርፕራይዝ ሥር ሆኖ ይተዳደር የነበረው የሞጆ ደረቅ ወደብና ተርሚናል፣ አሁን በኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ሥር እንዲካተት ተደርጓል፡፡ የአገሪቱን የወጪ ገቢ ንግድን ለማቀላጠፍ በተለይም ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ የተለያዩ ምርቶች በጂቡቲ ወደብ የሚቆዩበትን ጊዜ ለማሳጠር ሲባል የደረቅ ወደቦች አስፈላጊነት ታምኖበት ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡  በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ውስጥ አራት የደረቅ ወደቦች ያሉ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ የሞጆ ደረቅ ወደብ በግዙፍነቱ ይታወቃል፡፡ ወደ ሥራ ከገቡት አራቱ ደረቅ ወደቦች በተጨማሪ አዳዲስ ደረቅ ወደቦችን የማቋቋም ዕቅድ እንዳለ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይህ ውጥን በጥቂት ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የደረቅ ወደቦች ቁጥርን ወደ ስምንት ለማደርስ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ 

ሞጆ ደረቅ ወደብ

ሞጆ ደረቅ ወደብ በ2001 ዓ.ም. ሥራ ሲጀምር በቂ መሠረተ ልማት ተሟልቶለት አልነበረም፡፡ የሞጆ ደረቅ ወደብና ተርሚናል ዳይሬክተር አቶ ታዬ ጫላ እንደገለጹትም፣ በቀይ አሸዋ ላይ ለዕቃዎች መፈተሻ የሚሆን አንድ አነስተኛ ድንኳንና አሮጌ የዕቃ መጫኛና ማውረጃ መሣሪያዎችን በመያዝ ወደ ሥራ የገባ ነው፡፡

ደረቅ ወደቡ አገልግሎት ሲጀምር በአንዴ 200 ኮንቴይነሮችን ይረከብ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ታዬ፣ በአሁኑ ወቅት ግን የደረቅ ወደቡን መሠረተ ልማት በማጠናከር የተለያዩ ዘመናዊ መሣሪያዎችን በመጠቀም የአገልግሎት አሰጣጡን እያሳደገ መምጣቱን ይገልጻሉ፡፡ እንደ ሥራ ኃላፊው ማብራሪያ በአሁኑ ወቅት የሞጆ ደረቅ ወደብ በአንዴ 12,726 ኮንቴይነሮችን ማስተናገድ የሚችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ይህም በመሆኑ ደረቅ ወደቡ ከመቋቋሙ በፊት በጂቡቲ ወደብ የነበረውን የአንድ ኮንቴይነር የመቆያ ጊዜ ማሳጠር አስችሏል፡፡

ቀደም ብሎ አንድ ኮንቴይነር በአማካይ 60 ቀናት ይቆይ እንደነበር የገለጹት አቶ ታዬ፣ አሁን ግን በመልቲ ሞዳል ሥርዓት ወደ ደረቅ ወደቦቹ የሚመጡ ኮንቴይነሮችን በማብዛት የጂቡቲ ቆይታውን ወደ 7.5 ቀናት ማሳጠር ተችሏል፡፡ በጂቡቲ ወደብ የነበውን የቆይታ ጊዜ ማጥበብ የተቻለው የሞጆ ደረቅ ወደብ የማስተናገድ አቅም በየጊዜው እያደገ ከመምጣቱ ጋር የተያያዘ ነው ተብሏል፡፡ እንደ ምሳሌ የተጠቀሰውም ደረቅ ወደቡ በመጀመርያው የሥራ ዘመን 945 ባለ ሃያ ጫማ መጠን ያላቸው ኮንቴይነሮችን ብቻ የመያዝ አቅም የነበረው ሲሆን፣ በ2003 ዓ.ም. 1,175 ኮንቴይነሮች ማስተናገድ እንዲችል ተደርጓል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን (በ2007 ዓ.ም.) 12,726 ኮንቴይነሮችን የማስተናገድ አቅም ላይ መድረሱ የዕድገቱ ማሳያ ነው ተብሏል፡፡ አሁን እየሠራ ያለው የማስፋፊያ ሥራ ሲጠናቀቅ ደግሞ ወደቡ ከ15,600 ኮንቴይነሮች በላይ ማስተናገድ ይችላል፡፡

የሞጆ ደረቅ ወደብና አዲስ የማስፋፊያ ጥያቄው

የሞጆ ደረቅ ወደብ አገልግሎትና ጠቀሜታ እያደገ በመምጣቱ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ተከታታይ ማስፋፊያ ሥራዎችን እንዲያደርግ እያስገደደው ነው፡፡

በ1.5 ሔክታር መሬት በመረከብ ወደ ሥራ የገባው ይህ ወደብ በ2003 ዓ.ም. ይዞታውን ወደ 2.5 ሔክታር አሳድጓል፡፡ በተከታታይ ዓመታትም ይዞታውን በማስፋፋት  አጠቃላይ ይዞታው 64 ሔክታር መሬት ይዟል፡፡ ከዚህ ውስጥ 20 ሔክታሩ የኮንቴይነር ማስተናገጃ ብቻ ሆኖ እያገለገለ ነው፡፡ ቀሪው ይዞታው ከደረቅ ወደቡ አገልግሎት ጋር የተያያዙ ሌሎች ግንባታዎች ያረፈባቸውና ተጨማሪ ግንባታዎች የሚካሄዱባቸው እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ አሁንም ቢሆን ካለው ፍላጎት አንፃር ተጨማሪ ግንባታዎች የሚሻው ይህ ወደብ፣ አዲስ የማስፋፊያ ፕሮጀክት በማቅረብ ለዚህ የማስፋፊያ ሥራም 40 ሺሕ ሔክታር ቦታ እንዲሰጠው ጥያቄ አቅርቦ ተፈቅዶለታል፡፡ አቶ ታዬ እንደገለጹት፣ የሞጆ ደረቅ ወደብ ለአዲሱ የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ የተፈቀደለት 40 ሺሕ ሔክታር መሬት አሁን ካለው ይዞታ ጎን የሚገኝ ሲሆን፣ በቅርቡ ቦታውን ይረከባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የወደቡ አገልግሎት እያደገ መምጣቱን የሚገልጹት የሥራ ኃላፊዎች ይህም በተለየ መንገድ ይገለጻል ይላሉ፡፡ በዓለም አቀፍ የወደብ አገልግሎት አሰጣጥ ደረጃ የራሱ መለያ ያለው ሲሆን፣ ከዚህ አንፃር ወደቡ አገልግሎት የሚሰጥባቸው የተለያዩ መሣሪያዎች አቅም አንዱ ነው፡፡ በ2006 ዓ.ም. ወደቡ የነበሩት ዘመናዊ መሣሪያዎች በሰዓት 22 ኮንቴይነሮችን የሚያስተናግዱ ነበር፡፡ በ2007 ዓ.ም. ደግሞ በሰዓት 23 ኮንቴይነሮችን ማስተናገድ የሚችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ አንድ ወደብ የሚያስተናግደው 25 ኮንቴይነሮች አካባቢ በመሆኑ፣ ሞጆ ደረቅ ወደብ የደረሰበት ደረጃ ምን ያህል እንዳደገ ያመለክታል ተብሏል፡፡

በቅርቡም ሌላ ዘመናዊ መሣሪያ በማስመጣት ሥራውን የበለጠ  የተቀላጠፈ ያደርገዋል ያሉት አቶ ታዬ፣ ኮንቴይነሮችን የሚያስተናግዱ ሰባት አዳዲስ ዘመናዊ የኮንቴይነር የማስተናገጃዎች በግዥ ሒደቶች ላይ ናቸው ብለዋል፡፡ አዲሶቹ መሣሪያዎች የተለየ የሚያደርጋቸው ስድስት ኮንቴይነሮችን ለመደርደር የሚችሉና አሁን ያሉት መሣሪያዎች ቦታ የማይዙ መሆናቸው ነው፡፡ አሁን በሥራ ላይ ያሉት ግን አራት ኮንቴይነሮችን የመደርደር አቅም ያላቸው ናቸው፡፡ ለደረቅ ወደቡ አገልግሎት መስፋፋት የተለያዩ መገለጫዎች ያሉት ቢሆንም፣ አስመጪና ላኪዎች የመልቲ ሞዳል ሥርዓቱን እየመረጡ በመምጣታቸው ነው ያሉት አቶ ታዬ፣ ይህም በየጊዜው በመልቲ ሞዳል ትራንስፖርት ሥርዓት መጥተው በወደቡ እየተስተናገዱ ያሉ ኮንቴይነሮችን ቁጥር እያሳደገው ነው፡፡  ለምሳሌ ወደቡ በ2006 ዓ.ም. 54 ሺሕ ኮንቴይነሮችን ማስተናገድ የቻለ ሲሆን፣ በ2007 ግማሽ ዓመት ብቻ ያስተናገደው ደግሞ 43 ሺሕ መድረሱ ዕድገቱ ምን ያህል እንደሆነ ያሳያል ተብሏል፡፡

የሞጆ ደረቅ ወደብ እስካሁን ድረስ ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ በሚሆን ወጪ የተለያየ መሠረተ ልማቶች ግንባታ ተካሂደውበታል፡፡ አሁንም ከዚህ የበለጠ ወጪ የሚጠይቁ ሥራዎች ይጠብቁታል፡፡ አሁንም የተለያዩ የማስፋፊያ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ሲሆን፣ ወደ ስድስት የሚሆኑ ተጨማሪ መጋዘኖች የመገንባት ውጥን ይዟል፡፡ ደረቅ ወደቡ በድንኳን ውስጥ የጀመረውን አገልግሎት ቀስ በቀስ እያስፋፋ ሲሄድ ከፍተኛ የሆነ መዋለ ነዋይ ከጠየቁት ግንባታዎች ውስጥ ዋነኛው የዕቃ ማራገፊያና መፈተሻ መጋዘኖች ናቸው፡፡ ከድንኳን የተላቀቀበትንና 15 ሺሕ ካሬ ሜትር ስፋት ያለውን መጋዘን ከገነባ በኋላ፣ በዓለም አቀፍ ወደቦች አገልግሎት ደረጃን የሚያሟላውን የመጀመሪያ መጋዘኑን ከሁለት ዓመት በፊት ገንብቶ ለሥራ አብቅቷል፡፡ ይህ ወደ ወደቡ የሚገቡና የሚወጡትን ዕቃዎች ለመፈተሽ የሚያስችለው ዘመናዊ መጋዘን በወቅቱ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ጠይቋል፡፡ በተመሳሳይ ደረጃ እየተገነባ ያለውም ሁለተኛው መጋዘን ግንባታው እየተጠናቀቀ ነው፡፡ እነዚህ መጋዘኖች ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁት ለግንባታው የሚውሉት ጥሬ ዕቃዎች ሙሉ ለሙሉ ከውጭ የሚገቡ በመሆናቸው ነው፡፡ የግንባታው ወጪ እጅግ ከፍተኛ ቀሪዎቹን ስድስት መጋዘኖችም ተመሳሳይ ወጪ ይጠይቃሉ ተብሎ የተገመተ ሲሆን፣ ግንባታቸውንም ለማካሄድ በጨረታ ሒደት ላይ መሆኑን የአቶ ታዬ ገለጻ ያስረዳል፡፡

የመጀመሪያው መጋዘን ግንባታ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት መብቃቱ እጅግ ብዙ ሥራ አቃሏል ተብሏል፡፡ ዕቃዎች የሚፈተሹበት በቂ ቦታ አለመኖር ከደንበኞች ይመጣ የነበረውን ሮሮ ማስቀረት ችሏል፡፡ ለቀናት ይዘገይ የነበረው አገልግሎትም በአንድ ቀን ተጠናቅቆ የጉምሩክ ፎርማሊቲዎችን አሟልቶ የዕቃው አስመጪ ዕቃዎችን እንዲረከብ አስችሏል፡፡ ከዚህ ቀደም በነበረው አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከደንበኞች ይነሳ የነበረው ተደጋጋሚ ሮሮ ይኸው ከመጋዘን እጥረት ጋር የተያያዘ ችግር ነበር፡፡ አቶ ታዬም እንዳሉት በወቅቱ ያለን የወደብ መሠረተ ልማት አቅርቦት ባለመጣጣሙ  በደንበኞች  ሰፊ ቅሬታ ነበር፡፡ ቅሬታው ከኪራይ ሰብሳቢነትም መንስዔ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ አሁን ግን ይህ ችግር ተፈትቷል ያሉት አቶ ታዬ፣ አንድ ደንበኛ ዕቃውን አስፈትሾ ለማስወጣት ጥያቄ ሲያቀርብ በዕለቱ ይስተናገዳል፡፡ ቀም ብሎ ግን 15 እና 20 ቀናት ወረፋ በመያዝ ብቻ ይቆይ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡

የደረቅ ወደቡና አነጋጋሪ ደንበኞቹ

ከሞጆ ደረቅ ወደብ የሥራ ኃላፊዎች መገንዘብ እንደተቻለው ለአገልግሎት አሰጣጣቸው ላይ ከፍተኛ ተግዳሮት የሆነው ደንበኞች በወቅቱ ዕቃዎቻቸውን ያለማንሳት ችግር ነው፡፡ ይህንን ችግር አቶ ታዬ ‹‹ትልቁና ይቺንም አገር ከሌሎች ዓለም አቀፍ የወደብ አገልግሎት ደረጃ አንፃር ወደኋላ የሚያስቀራት የኮንቴይነሮች የወደብ ቆይታ ከፍተኛ ነው፤›› ብለውታል፡፡

በአሁኑ ወቅት በሞጆ ደረቅ ወደብ አንድ ኮንቴይነር የወደብ ቆይታው 55 ቀናት ነው፡፡ ዓለም አቀፍ ደረጃ ግን ሦስትና አራት ቀናት ነው፡፡ ዕቃዎቻቸውን ለወራት ያለማንሳት ፈቃደኛ ያልሆኑ አስመጪዎች በአገልግሎት አሰጣጣቸው ላይ እንቅፋት እየሆኑ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት እንኳን ደንበኞች ያልተረከቡዋቸው ኮንቴይነሮች ቁጥር ከስምንት ሺሕ በላይ ናቸው፡፡ በደረቅ ወደቡ አሠራር መሠረት አንድ አስመጪ ዕቃው ደረቅ ወደብ ከደረሰ በኋላ ለተከታታይ ስምንት ቀናት ምንም ዓይነት ክፍያ የማይጠየቅ ሲሆን፣ ከስምንት ቀናት በኋላ ግን ለእያንዳንዱ የመጋዘን ኪራይ እንዲከፍል ይገደዳል፡፡ ይህም ሆኖ ግን ጥቂት የማይባሉ አስመጪዎች ዕቃውን አውቀው ሳያወጡ ይቀራሉ፡፡

ዕቃዎቻቸውን ለምን እንደማያወጡ የዳሰሳ ጥናት የተደረገ ስለመሆኑ የገለጹት የሥራ ኃላፊዎች፣ አንዳንዶቹ ደረቅ ወደቡ የሚያስከፍለውን ክፍያ እየከፈሉ መቆቱን ስለሚመርጡ ነው፡፡ እንዲህ ያሉት አስመጪዎች ዕቃቸውን በደረቅ ወደብ አቆይተው የሚከፍሉት የመጋዘን ክፍያ መርካቶ ወይም በሌላ መጋዘን ቢያስቀምጡት ከሚከፍሉት ክፍያ አንፃር አነስተኛ በመሆኑ፣ በደረቅ ወደቡ ዕቃቸውን አቆይተው ማውጣት የመምረጥ ልምድ ማደጉ ለደረቅ ወደቡ አሠራር እንቅፋት እየሆነ ነው፡፡

ይህ አካሄድ ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው ቢሆንም ዕቃ ላለማንሳት እንደ ምክንያት ከሆኑ ነጥቦች መካከል አንዱ ሆኗል፡፡ ከባንክ ጋር በተያያዘ ችግርም ዕቃውን ለማውጣት የማይፈልጉም መኖራቸው ታውቋል፡፡ ምንም ይሁን ምን ዕቃው ደረቅ ወደብ ከደረሰ በኋላ ዕቃውን የማውጣት ኃላፊነት አለባቸው ተብሏል፡፡ ደረቅ ወደቡም ዕቃቸውን እንዲያነሱ ተደጋጋሚ ውትወታዎችንና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ቢሠራም ችግሩ ሊቀርፍ አልቻለም፡፡

የቦታ ጥበት ያለበት የሞጆ ደረቅ ወደብ ለወራት አንዳንዴም ከዓመት በላይ የቆዩ ዕቃዎችን ባሉበት እንዲቆዩ ከማድረግ ውጭ፣ የሚወስደው ዕርምጃ አለመኖር ችግሩ ዘላቂ መፍትሔ እንዳያገኝ አድርጎታል፡፡ ከሁሉም በላይ ከስምንት ቀናት በኋላ በየአንዳንዱ ቀን ተሰልቶ ዕቃዎቹ ለቆዩበት ጊዜ ተባዝቶ እንዲከፈል የሚደነግገው መመርያም የመጋዘን አገልግሎት ክፍያው 45 ቀናት ብቻ መሆኑ ነው፡፡ ከ45 ቀናት በኋላ የመጋዘን አገልግሎት የማይጠየቅበት በመሆኑ ዕቃው እንዲቀመጥ ይደረጋል፡፡

መንግሥት እንዲህ ዓይነቱን አሠራር የዘረጋው የሎጅስቲክ ወጪ ከፍ እንዳይል ካለው አቋም ነው፡፡ ሆኖም ይህ አካሄድ ተቀይሮ ዕቃዎች በወቅቱ እንዲነሱ ለማድረግ አስገዳጅ ወደሆኑ አሠራሮች መግባት ግድ እየሆነ ነው፡፡ በሌሎች አገሮች እንደሚደረገው በወደቡ የደረሰን ዕቃ የማይረከብ አንድ አስመጪ በወቅቱ ዕቃውን ካላነሳ ይወርሱበታል፡፡ በብዙዎቹም አገሮች ከሁለት ወራት በላይ በወደብ የቆየን ዕቃ መንግሥት እንዲወርሰው ይደረጋል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ግን ይህንን ለማድረግ የሚያስችል ሕግ ባለመኖሩ የዕቃዎች የወደብ ቆይታ እንዲረዝም በማድረጉ ይህንን ለመከላከል የሚያስችል ሕግ እየተቀረፀ ነው፡፡ ይህንንም ጉምሩክ የሚያስፈጽም ሲሆን ለዚህ የሚሆን ደንብ በመረቀቅ ላይ እንደሆነም ከደረቅ ወደቡ የሥራ ኃላፊዎች ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ይህ በእንዲግ እንዳለ ወደቡ በአሁኑ ወቅት አገልግሎቱን ለማመዘን የአይቲ ሲስተም የሌለው መሆኑም የተቋሙ ሌላ ተግዳሮት ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች