Monday, April 15, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

‹‹ውሸት ቢደጋገም እውነትን ማሸነፍ አይችልም››

የጋምቤላ የእርሻ ኢንቨስተሮች ሁለገብ ሕብረት ሥራ ማኅበር

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ተክለ ወልድ አጥናፉ ጥቅምት 29 ቀን 2010 .ም. ታትሞ ለወጣው ሪፖርተር ጋዜጣ የሰጡትን መግለጫ በመቃወም ከጋምቤላ የእርሻ ኢንቨስተሮች ሁለገብ ሕብረት ሥራ ማኅበር የሚከተለውን ጽሑፍ አቅርቧል፡፡  

የጋምቤላ የእርሻ ኢንቨስትመንት ልማት በአገሪቱ ከፍተኛ መነጋገሪያ አጀንዳ ከመሆኑ የተነሳ በውዥንብሩ መንግሥትም ራሱ ሰለባ በመሆኑም ጭምር የጋምቤላ የእርሻ ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ምርመራና ጥናት እንዲካሄድበት 2008 .ም. አጋማሽ ላይ ውሳኔ መንግሥት አስተላልፏል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር ሕፈት ቤት የተመራ የተለያዩ ሚኒስቴሮች አባል የሆኑበት ግዙፍ ኮሚቴ ተቋቁሞ በሁለት ዙር ጥናቱን አካሂዶ ውጤቱን ለመንግሥት አቅርቧል፡፡ ኅዳር 15 ቀን 2009 .ም. በግዮን ሆቴል በተካሄደው የእርሻ ኢንቨስትመንት አገር አቀፍ የምክክር መድረክ ላይም የጥናቱ ውጤት ይፋ ሆነ፡፡

ከዚያ በፊት ይነዙ የነበሩ አሉባልታዎችን በሙሉ ነፍስና ሥጋ አልብሶ ያልነበረውን ክብደት ሰጥቶ እውነቱን በሐሰት ለውጦ የቀረበ ሪፖርት ነበር፡፡ ለእርሻ ልማት ተብሎ ከባንኮች የተሰጠው ብድር ለታለመለት ዓላማ አለመዋሉን መሬቱም 18 በመቶ ብቻ እንደለማና የተረፈው ገንዘብ የት እንደዋለ የማይታወቅ መሆኑን አብራርቶ የቀረበው ሪፖርት ለጋምቤላ ኢንቨስተሮች ከሞት መርዶ የማይተናነስ አስደንጋጭ ሲሆንለአሉባልተኞቹና ለፀረ ልማት ኃይሎች ግን ሠርግና ምላሽ ነው የሆነላቸው፡፡ የጥናት ቡድኑ አወቃቀር ትክክል እንዳልሆነ ገና ከጅምሩ ሲቃወሙ የነበሩት የጋምቤላ ኢንቨስተሮች የጥናቱን ግኝት ሙሉ በሙሉ ውድቅ በማድረግ ይህን የተሳሳተ ሪፖርት መነሻ በማድረግ መንግሥት ዕርምጃዎችን መውሰድ እንደሌለበት በማሳሰብ የጥናቱን ውጤት በሰፊው በማጋለጥ ትግላቸውን ቀጠሉ፡፡ በዚህም መሠረት፡

  1. ከባንኮች በብድር የተወሰደ ገንዘብ በተመለከተ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለሁለት መቶ ተበዳሪዎች 4.9 ቢሊዮን ብር በብድር መሰጠቱን4.9 ቢሊዮን ብር ውስጥ 3.1. ቢሊዮን ብር ለስድስት የውጭ አገር ባለሀብቶች  የተሰጠ መሆኑን፤ የቀረው ብር ደግሞ194 የአገር ውስጥ ተበዳሪዎች የተሰጠ መሆኑንና ከዚህ ገንዘብ  ውስጥ ደግሞ ስምንት መቶ ሚሊዮን ብር ሥራ ላይ የዋለ ሲሆን፣ ሁለት መቶ ሚሊዮን ብር ግን አሁንም በባንኮች እጅ የሚገኝ መሆኑን በማስረዳት ሀቁን ለማስረዳት ተችሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የወሰዱትን የብድር ገንዘብ በትክክል ለታለመለት ዓላማ ያላዋሉ ተበዳሪዎችም በስም ተጠቅሰው እንዲጋለጡ ተደርገዋል፡፡
  2.  የመሬት ልማትን በተመለከተ 3.1. ቢሊዮን ብር የወሰዱት ስድስቱ የውጪ አገር ተበዳሪዎች ማልማት ከነበረባቸው መሬት ስድስት በመቶ ብቻ ማልማታቸው፤ አንድ ቢሊዮን 600 ሚሊዮን ብር የተበደሩት 194 የአገር ውስጥ ተበዳሪዎች ማልማት ከነበረባቸው 55,000 ሔክታር መሬት ውስጥ 53,000 ሔክታር መሬት ያለሙ መሆናቸውን ተጨባጭ ማስረጃ በማቅረብ ተሟግቷል፡፡ እንዲሁም የካምፕ ግንባታ ውጤት 83 በመቶ መሆኑ፣ ከቀረጥ ነፃ የገቡ ተሸከርካሪዎች ማሽነሪዎችና አክሰሰሪዎችም 95 በመቶ በላይ አፈጻጸም እንዳላቸው ተብራርቷል፡፡

በአጠቃላይ ለመንግሥት የቀረበው ሪፖርት መሬት ላይ ካለው እውነት ጋር ፈጽሞ የማይጣጣምና በሐሰት የተሞላ የአገር ውስጥና የውጭ ተበዳሪዎችን የሥራ አፈጻጸም ለይቶ የማያሳይ ኃላፊነት የጎደለው መሆኑ፣ ይመለከታቸዋል ለተባሉ የመንግሥት ኃላፊዎች በተለያዩ መድረኮች በአካልና በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን አማካይነት የማስረዳት ተግባር በሰፊው ተካሂዷል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ እውነቱን እንዲገነዘበው ለማድረግ አሰልቺና ውጣ ውረድ ሁኔታዎችን በማለፍ ጥረት ተካሂዷል፡፡ በዚህም ምክንያት የተደበቀው እውነት እየተገለጠ ሕዝብም እንደገና ሁኔታውን መነጋገሪያ እያደረገው ሀቁን ለመገንዘብ ችሏል፡፡

ይሁን እንጂ ይኼ ሁሉ ተደርጎ እውነቱ እየተገለጠ ቢመጣም መንግሥት የተሳሳተ ሆኖ ለቀረበለት ሪፖርት በመወገኑ ምክንያት የተሳሳቱ ዕርምጃዎችን መውሰድ ጀመረ፡፡ በዚህም ለበርካታ አልሚዎች ማስጠንቀቂያ ሰጠ፡፡ 269 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃዳቸው ተሰርዞ መሬታቸው ተቀማ፡፡ ይህን የተመለከቱ በጋምቤላ የተሰማሩ ባለሀብቶችም የሕግ የበላይነት ይከበር ዘንድና መንግሥት የተሳሳተ ዕርምጃ መውሰዱን እንዲያቆም ይህ ካልሆነ ግን በአጠቃላይ ክልሉን ለቀው የሚወጡ መሆኑን በመግለጽ ፔቲሽን ተፈራርመው ለመንግሥት አሳወቁ፡፡ በዚህ ምክንያት መንግሥት እንደገና ከጋምቤላ ኢንቨስተሮች ጋር ተቀምጦ ሚያዝያ 9 ቀን 2009 .ም. ውይይት ተካሄደ፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ከተካሄደው ስምንት ሰዓት ከፈጀ ግምገማ በኋላ ሁኔታው እንደገና ተመልሶ በኮሚቴው ውስጥ ሳይካተቱ የቀሩት የጋምቤላ ክልል መንግሥት የጋምላ፤ ክልል ኢንቨስትመንት ቢሮ የተካተቱበት አዲስ ኮሚቴ ተዋቅሮ  ሥራውን ጀመረ፡፡ ቅሬታውን አይቶ መስጠት ያለበትን ውሳኔ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የማቅረብ ኃላፊነትም ተሰጥቶታል፡፡

ይህ ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ እያንዳንዷን ጉዳይ በጥልቀት ፈትሿል፡፡ ማስረጃዎችን መርምሯል፡፡ የመስክ ምልከታ በማካሄድ እያንዳንዷን እርሻ በአካል ተገኝቶ በማረጋገጥ ውጤቱንና የውሳኔ ሐሳቡን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በማቅረብ አስፀድቋል፡፡ በዚህም መሠረት መሬታቸው እንዲቀማ ተወስኖባቸው ከነበሩት 269 ባለሀብቶች መካከል 186 ባለሀብቶች በትክክል ልማት ላይ ያሉ በመሆናቸው መሬታቸው ተመልሶላቸዋል፡፡ አራት ባለሀብቶች መሬታቸው ወደ መንግሥት ተመላሽ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ 79 ባለሀብቶች ደግሞ በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ መቀጠል እንደማይፈልጉ በመግለጽ በፈቃዳቸው ለቀው ወጥተዋል፡፡ ሌሎች ጉዳዮችም ተፈትሸው የተደበቀው እውነት ለመውጣት ችሏል፡፡

በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉ ኪራይ ሰብሳቢዎችና ፀረ ልማት ኃይሎች በመቀናጀት በፈጠሩት አሉባልታና ባካሄዱት የስም ማጥፋት ዘመቻ ምክንያት መንግሥት የግብርናውን ኢንቨስትመንት በብድር አቅርቦት መደገፋን ካቆመ እነሆ ዓመታት እንደዋዛ እየነጎዱ ነው፡፡ በዚህ ሰበብም የአገሪቱ የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ እጅጉን መዳከሙና መጎዳቱ በግልጽ እየታየ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ የግብርና ኢንቨስትመንት ተከታታይነትና ስፋት ባለው መልኩ በመንግሥት የማይታገዝ ከሆነ የትም ሊደርስ እንደማይችል ከሁሉም የሚሰወር ጉዳይ አይደለም፡፡

ከዚህ በመነሳትም የግብርናው ኢንቨስትመንት ማነቆዎች የተባሉ ችግሮች  ተለይተው ዘላቂ መፍትሔ እንዲቀመጥላቸው ዘርፉ በአፋጣኝ እንዲነቃቃ እንዲደረግ መንግሥት አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ከሁሉም ክልሎች ተሰብስበው በመመካከር ችግሮችን በመለየት መፍትሔያቸውን ከነ አፈጻጸም ዘዴያቸው በመጠቆም የተዘጋጀ ሰነድ ለመንግሥት እንዲቀርብ ተደርጓል፡፡ መንግሥትም ሰነዱን በማፅደቅ ስትራቴጂ በማዘጋጀት በአስቸኳይ ወደ ተግባር የመግባቱን ሒደት ያፋጥነዋል ተብሎ ይታመናል፡፡ ይህ ሁኔታ በእርሻ ሥራ ተሰማርተው በተለያየ ችግር ተቀስፈው በማጣጣር ላይ የሚገኙ ኢንቨስተሮች የተዳከመ ሞራላቸው እንዲነቃቃና ተስፋ እንዲኖራቸው የሚያደርግ በመሆኑ ሁሉም ከወዲሁ የተደሰተበት ሆኗል፡፡

እንግዲህ ይህ ሁሉ ታልፎ እውነትና ሐሰቱ ተለይቶ መንግሥት ማስተካከያ ዕርምጃ ወስዶ ዘርፉን ማነቃቃት ሊጀምር በተቃረበበት ሰዓት ነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ  ገዥ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ ሒደቱን ሁሉ  ወደ ኋላ የሚቀለብስ ከእውነታው ጋር የሚጋጭ መግለጫ ይዘው ብቅ ያሉት፡፡

የፓርላማው የበጀትና የፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የብሔራዊ ባንክን 2010 .. የሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸምና የዓመቱን ዕቅድ ጥቅምት 27 ቀን 2010 .ም. በሚገመግምበት ወቅት፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የተበላሸ ብድርን በተመለከተ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ ያቀረቡትን ማብራሪያ በጥቅምት 29 ቀን 2010 .ም. የታተመው የሪፖርተር ጋዜጣ በቢዝነስ ዓምዱ ላይ አስፍሮት ተመልክተነዋል፡፡ በዚህ መሠረትም፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የተበላሸ ወይም መመለሱ አጣራጣሪ የሆነ ብድር 25 በመቶ  ወይም ዘጠኝ ቢሊዮን ብር መድረሱንና ለዚህ ምክንያት የሆነው ለጋምቤላ ሰፋፊ እርሻዎች ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ በተሰጠው 4.9 ቢሊዮን ብር ምክንያት መሆኑን፣ ለጋምቤላ ሰፋፊ እርሻዎች የተሰጠው ብድር የተበላ በመሆኑ ወይም ሥራ ላይ ውሎ መመለስ ያልቻለ በመሆኑ የመመለስ ዕድል የሌለው መሆኑ፤ ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተሰጠው ብድር ያልተበላና ሥራ ላይ የዋለ ሲሆንየመክፈያ ጊዜው ተሸሽሎለት ክትትል ከተደረገበት ለመመለስ የሚችል መሆኑን፤ ለጋምቤላ ሰፋፊ እርሻዎች የተሰጠው ብድር ለታለመለት ዓላማ ሳይውል የባከነና የተበላ መሆኑ የተረጋገጠው ባለፈው ዓመት መንግሥት በጋምቤላ እርሻዎች ላይ ባካሄደው ጥናት መሆኑን አብራርተው አስረድተዋል፡፡

ይህ በአቶ ተክለወልድ አጥናፉ የቀረበውን ሪፖርት የተመለከትን በጋምቤላ  በእርሻ ሥራ ተሰማርተን ከመንግሥት ብድር ወስደን በመሥራት ላይ ያለን ዜጎች እጅግ በጣም አዝነናል፡፡ ምክንያቱም፣

  1. የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለጋምቤላ ተበዳሪዎች ያላበደረውን ገንዘብ 4.9 ቢሊየን ብር እንዳበደረ ተደርጎ በመቅረቡ፤
  2. ስድስት የውጪ ዜጎች የወሰዱት 3.1 ቢሊዮን ብር እኛ የአገር ውስጥ ተበዳሪዎች እንደወሰድነው ተደርጎ በመገለጹ፤
  3. ለጋምቤላ ኢንቨስተሮች ከተሰጠው ጠቅላላ ብድር ውስጥ ሁለት መቶ ሚሊዮን ብር ገና በባንኮች እጅ ያለ ሆኖ ሳለ የተወሰደ አስመስሎ በመቅረቡ፤
  4. በጋምቤላ ለምንገኝ ተበዳሪዎች የተሰጠው ገንዘብ 96 በመቶ በትክክል ሥራ ላይ የዋለ መሆኑ የተረጋገጠ ሆኖ ሳለ የተበላና የባከነ አስመስሎ በማቅረቡ፤
  5. የእርሻ (ግብርና) ዘርፍ ችግሮች ተለይተው በትክክል ከታገዘና ክትትል ከተደረገለት ብድር ከመመለስም በላይ ውጤታማ መሆኑ እየታወቀ ይህንን የሚቃረን ሙያዊነት የጎደለው አስተያየት በመሰጠቱ፤
  6. ባለፈው ዓመት በመንግሥት ውሳኔ በጋምቤላ እርሻዎች ላይ ተካሄደ ተብሎ የቀረበው የጥናት ውጤት መንግሥትን ለከፍተኛ ስህተት የዳረገ መሆኑ ተረጋግጦ ውድቅ ተደርጎ እያለ፣ እንደገና ይህንን ዋቢ በማድረግ የቀረበ በመሆኑና ከተጨባጩ እውነት ጋር የማይገናኝ ከዚህ በፊት በተከታታይ ይካሄድብን ከነበረውና ከዓላማ የተነሳ ይነዛብን ከነበረው ፈርጀ ብዙ ስም የማጥፋት ዘመቻ ቀጣይ ክፍል ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የሕዝብና የመንግሥት ገንዘብ በብድር ስም እየተመሳጠሩ በማውጣት ለብክነት የዳረጉ አካላት ተጠያቂ ከማድረግ ይልቅ፤ የመንግሥትና የአገሪቱን የልማት ፖሊሲና ስትራቴጂ በመተግበር ራሳቸውንና አገራቸውን ለመጥቀም የሚታትሩ ዜጎችን ቅስም የሚሰብርና ለተሳሳተ ውሳኔ ሰለባ ለማድረግ የተቀነባበረ ሆኖም አግኝተነዋል፡፡

ከዚህ በመነሳት አቶ ተክለወልድ አጥናፉ የሰጡትን ማብራሪያ ከላይ በሰፊው ባቀረብነው ማብራሪያ ምክንያት አጥብቀን የምንቃወመው መሆኑን እየገለጽንማስተካከያ እንዲደረግለት እንጠይቃለን፡፡ በተጨማሪም በፓርማው የበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከዚህ የተሳሳተ ሪፖርት በመነሳት የተሳሳተ ዕርምጃ ከመውሰዱ በፊት ጉዳዩን በሚገባ እንዲመረምርልን በአክብሮት እንጠይቃለን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

 

 

 

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles