Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየቴክኖሎጂ ወጋገን

የቴክኖሎጂ ወጋገን

ቀን:

የአሥራ አራት ዓመቱ ይትባረክ አረፋይኒ የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ነው፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮ ለቴክኖሎጂ ቅርብ የሆነው ታዳጊው የተለያዩ ፈጠራዎችን የመሥራት ልምድ አለው፡፡ ከሠራቸው ሥራዎች መካከል ወላጆቹ ቤት ውስጥ የሚገለገሉበት በስልክ የሚሠራ ፕሮጀክተር አንዱ ነው፡፡

የፊዚክስና የሒሳብ ትምህርትን ከሌሎች አስበልጦ የሚወደው ይትባረክ፣ የትራፊክ አደጋን መቀነስ የሚችል ፈጠራ እየሠራ እንደሚገኝ ይናገራል፡፡ ተሽከርካሪዎችን እርስበርስ ከመጋጨት የሚያግድ ቴክኖሎጂ እያዳበረ ሲሆን፣ ሌሎችም እሱና ቤተሰቦቹ የሚገለገሉባቸውን የፈጠራ ሥራዎች አበርክቷል፡፡

የይትባረክ የፈጠራ ችሎታ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከወላጆቹና በቅርብ ከሚያውቁት ጓደኞቹ በስተቀር ብዙም አይታወቅም ነበር፡፡ ከሰሞኑ ግን ከራሱ አልፎ አገሩን በዓለም አቀፍ ደረጃ ማስጠራት የቻለበት አጋጣሚ ተፈጥሯል፡፡ በቅርቡ በካናዳ ተዘጋጅቶ በነበረው የሮቦቲክስ ውድድር ላይ ከአንድ ጓደኛው ጋር በሠሩት ሮቦት አንደኛ በመውጣት የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡

የቴክኖሎጂ ወጋገን

 

የሠሩት ሮቦት  የተዘጋጀለትን መስመር ተከትሎ አንድን ቁስ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ማንቀሳቀስ የሚችል ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ የሠሩት ሮቦት ያለ ሰው መንቀሳቀስና መሥራት የሚችል ኤክስካቫተር ነው፡፡ የሮቦቱን አጠቃላይ ቁመናና ፕሮግራሙን የሠሩት ታዳጊዎቹ እርስ በርስ በመረዳዳት ነው፡፡

‹‹ፕሮግራሙን ለመሥራት ጠለቅ ያለ የሒሳብና የፊዚክስ ዕውቀት ይጠይቃል፡፡ በውድድሩ ትልቁን ነጥብ የሚይዘውም የፕሮግራሚንግ ክህሎት ነበር፤›› አለ እንደ የዕድሜ እኩዮቹ ተሯሩጦ መጫወትን ወደ ጎን ብሎ ወደ ፈጠራ ሥራዎች ያዘነበለው ታዳጊው ይትባረክ፡፡

ተወዳድረው ባሸነፉበት ዓለም አቀፍ ውድድር ላይ አብሮት የተሳተፈው ነብዩ ዳንኤል ነበር፡፡ የ16 ዓመቱ ነብዩ የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ነው፡፡ እንደ ይትባረክ ሁሉ ለሒሳብና ለፊዚክስ ትምህርት ልዩ ፍቅር አለው፡፡ ‹‹ምክንያቱም የቁጥር ትምህርትና ፍልስፍና ደስ ይለኛል፤›› አለ ጉርምስናው ድምፁን እያጎረነነው፡፡

ነብዩ በውድድሩ ተሳትፎ ከማድረግ በዘለለ ጥሩ ነጥብ ይዞ ስለመውጣት ያሰቡት ነገር እንዳልነበር ይናገራል፡፡ 16 አገሮች በተሳተፉበት በዚህ ውድድር ተሳታፊዎች ታችኛው፣ መካከለኛውና ላይኛው በሚል ሶስት ደረጃዎች ተደልድለው ነበር፡፡ ድልድሉ በትምህርት ደረጃ የወጣ ሲሆን፣ ይትባረክና ነብዩ የተወዳደሩት በመካከለኛው ደረጃ ነበር፡፡ አንደኛ መውጣታቸውን ሲያውቁ እንደተደሰቱ አገራቸውን ማስጠራታቸው ደግሞ ይበልጥ እንዳኮራቸው ይገልጻሉ፡፡ ታዳጊዎቹ ቅዳሜ ኅዳር 2 ቀን 2010 ዓ.ም. በሞዛይክ ሆቴል ተዘጋጅቶ በነበረው የእንኳን ደህና መጣችሁ ፕሮግራም ላይ ኮከቦች ነበሩ፡፡

ታዳጊዎቹ ያሉትን የተለያዩ መሰናክሎች አልፈውና ቴክኖሎጂው ተሟልቶላቸው ከሚሠሩ የሌላው አገር ተወላጆች ጋር ተወዳድረው አንደኛ መውጣታቸው ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡

እነዚህ ታዳጊዎች ያላቸው የፈጠራ ክህሎት ይበልጥ እንዲጎለብት በማድረግ የተሻለ ዕድል እንዲያገኙ የሚደግፋቸው አይከን ኢትዮጵያ ነው፡፡ ድርጅቱ የፈጠራ ችሎታ ያላቸው ታዳጊዎች መጠነኛ ገንዘብ ከፍለው በወርክሾፑ በሚገኙ ቁሳቁሶችና መምህራን በመታገዝ ክህሎታቸው አንድ ዕርምጃ ከፍ እንዲል የማድረግ ሥራ ይሠራል፡፡ የተለየ ችሎታ የሚታይባቸውን ደግሞ በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ እንዲሳተፉ በማድረግ አቅማቸውን እንዲፈትሹና የበለጠ ለመሥራት እንዲነሳሱ ያደርጋል፡፡

በአገሪቱ ጥሩ አቅም ያላቸውና ተስፋ የሚጣልባቸው ታዳጊዎች ቢኖሩም፣ እንዲህ ላሉ ፈጠራዎች የሚሰጠው ትኩረት እምብዛም በመሆኑ የአብዛኞቹ አቅም የጋን ውስጥ መብራት ሆኖ ይቀራል፡፡ አልያም ከራሳቸው ባለፈ ለአገሪቱ የጎላ ፋይዳ ያለው ነገር ሳያበረክቱ ያልፋሉ፡፡ ሲያልፍ ደግሞ በችሎታቸው መስራት ወደሚችሉባቸው አገሮች ይሰደዳሉ፡፡ እነዚህን ሁሉ መሰናክሎች አልፎ እንደነ ነብዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን አሸንፈው የአገራቸውን ስም የሚያስጠሩትም ጥቂት ናቸው፡፡

የአይከን ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሠናይ መኮንን ከመማር ማስተማሩ ሒደት ጋር ተያይዘው በሚሠሩ ፈጠራዎች ላይ የሚንፀባረቁ እክሎችን የሚቀርፉና እንዲህ ያሉ መሰል የቴክኖሎጂ ዘርፎችን የሚደግፍ አካል ያስፈልጋል ይላሉ፡፡ ድርጅቱም ይህን ዓላማ አድርጎ ከተቋቋመ ከስምንት ዓመታት ወዲህ በዘርፉ ችሎታ ያላቸውን በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ያሳትፋል፡፡ በውድድሮቹ የሚካፈሉ ታዳጊዎችም አዳዲስ ፈጠራዎችን የማፍለቅ ፍላጎታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱንም አስተውለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአይከን 120 የሚሆኑ ተማሪዎች የሚገኙ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ የተሻለ ችሎታ ያላቸው ተመርጠው በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ እንዲሳተፉ ይደረጋል፡፡ በካናዳ ተዘጋጅቶ በነበረው ውድድር ላይ ዘጠኝ ተማሪዎች እንዲሳተፉ የተደረገ ሲሆን፣ 33 አገሮች በሚካፈሉበትና በቻይና በሚደረገው ውድድር ላይ ለመሳተፍ ደግሞ 18 ታዳጊዎችም ኅዳር 7 ቀን 2010 ዓ.ም ወደ ቻይና አቅንተዋል፡፡

እነዚህ ታዳጊዎች ምናልባት በአገሪቱ ከሚገኙ ይህንን ዕድል ማግኘት ካልቻሉ ታዳጊዎች የተሻሉ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን እንዲህ ባሉ ትልልቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ብዙ ነገር ተሟልቶላቸው ከሚሠሩት ጋር እንዴት እኩል መወዳደር ይቻላቸዋል? የሚለውን ለመፍታት ለሳይንስና ቴክኖሎጂ የተሰጠው ትኩረት ይፈታዋል የሚል ተስፋን ያጭራል፡፡

ሆኖም በማህበረሰቡ ዘንድ የሮቦቲክስን ፅንሰ ሐሳብ ከመረዳት ጀምሮ የተለያዩ ችግሮች እንዳሉ የሚናገሩት አቶ ሠናይ፣ ዓለም በቴክኖሎጂ በተራቀቀበት በአሁኑ ዘመን ልጆቹን ኮትኩቶና ያላቸውን ክህሎት አንጥሮ ለማውጣት ብዙ እንደሚቀር ይገልጻሉ፡፡

የተለየ ችሎታ አላቸው ተብለው ከሚመረጡ ተማሪዎች መካከል ከፍለው ለመማር የማይችሉ ታዳጊዎች አሉ፡፡ እነዚህ ታዳጊዎች ያላቸው ልዩ ክህሎት በድህነት ተዳፍኖ እንዳይቀር አይከን የሚሰጣቸው ሁለተኛ ዕድል ፋይዳው የጎለ ነው፡፡ ችግሩ በዓለም አቀፍ ውድድሮች ለመሳተፍ የሌሎችን ድጋፍ ሲያጡ ነው፡፡

የታዳጊዎቹን የአውሮፕላን ቲኬት ስፖንሰር እንዲያደርጉ ከሚጠየቁ መንግሥታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከጥቂቶች በስተቀር አብዛኛዎቹ ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎቱ የለቸውም፡፡ ከቅብጠት የሚቆጥሩም አሉ፡፡ ምንድነው ነገሩ የሚለውን ነገር ለማወቅ እንኳ ጆሮ የማይሰጡ ያጋጥማሉ፡፡ ‹‹ድጋፍ ስንጠይቅ፡፡ በርቱ ጥሩ ነው ከማለት ውጪ ገፍቶ የመሄድ ፍላጎት የላቸውም፤›› በማለት አቶ ሠናይ ድጋፍ ለማሰባሰብ በሚያደርጉት ጥረት በተደጋጋሚ ጊዜ የሚያጋጥማቸውን ገልጸዋል፡፡

በየጊዜው አዳዲስ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች በሚታዩበት በአሁኑ ወቅት እንደ ስማርት ፎን፣ ታብሌቶችና የተለያዩ የቴክኖሎጂ ትሩፋቶች ዓለምን አጥለቅልቀዋል፡፡  ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕድገት መሠረት ከጣሉ እንደ መብራት፣ ኮምፒውተር፣ የማተሚያ ማሽንና ሌሎችም በዘመናቸው ብርቅዬ የነበሩ ፈጠራዎች አሁን ላለው የቴክኖሎጂ ልቀት ትልቁን ሚና ተጫውተዋል፡፡

ዓለም አንድ መንደር እንድትሆን ባደረገው በሉላዊነት ዘመን የትም ሆነው ማንኛውንም መረጃ ማግኘት፣ ማውጣትና ሌሎችም ከዚህ ቀደም እንደ ብርቅ የሚታዩ ነገሮችን ማድረግ ተችሏል፡፡ የቴክኖሎጂ ርቀት በኢንዱስትሪው እድገት ውስጥም ከፍተኛ ድርሻ አለው፡፡ በቴክኖሎጂ በየፋብሪካው የሚሰሩ አብዛኛዎቹን አድካሚና አደገኛ  ሥራዎች በማሽን ማሠራት አስችሏል፡፡ ሰውን ተክተው የሚሠሩ ሮቦቶችም እየበዙ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ስሜትን መግለጽ የሚችሉ ሮቦቶች ሁሉ እየተሠሩ ይገኛሉ፡፡ አብዛኛዎቹ በሰዎች ይሠሩ የነበሩ ሥራዎች በሮቦት እንዲሠሩ እየተደረገ ይገኛል፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት እ.ኤ.አ. በ2021 በአሜሪካ ስድስት በመቶ የሚሆኑት በሰዎች ይሠሩ የነበሩ የሥራ ዓይነቶች በሮቦቶች የሚሰሩ ይሆናሉ፡፡ ይህም የሳይንስና ቴክኖሎጂ የምጥቀት ደረጃን የሚያሳይ በዘመኑ ክስተት ላይ የተመሰረተ ራዕይ ነው፡፡

የቴክኖሎጂ ወጋገን

 

የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕድገት የአንድን አገር ሥልጣኔና ብልፅግና ማሳያም ነው፡፡ የአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ተቀባይ እንጂ ብዙም መፍለቂያ ያልሆነችው ኢትዮጵያ ዕድገቷ ከምዕራባውያን አንፃር ሲገመገም የሰማይና የምድር ያህል የተጋነነ ልዩነት እንዳለው ግልጽ ነው፡፡

የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ ስምንተኛው አገር አቀፍ የሳይንስ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሽልማት ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ለአገሪቱ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ቁልፍ ነው ብለዋል፡፡ ይሁንና አገሪቱ ብዙ እንደሚቀራት በመጀመርያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን በጀት የነበረውን የኢንዱስትሪና የግብርና ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት ድርሻ በማነፃፀር ገልጸዋል፡፡

በ2007 ዓ.ም. ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት የግብርናው ድርሻ 38 በመቶ፣ የኢንዱስትሪው ድርሻ ደግሞ 15.6 በመቶ እንደነበር፣ በ2017 ዓ.ም. የአገሪቱ ኢንዱስትሪ ድርሻ ቢያንስ ወደ 32 በመቶ ማደግ እንደሚጠበቅበትና በአንፃሩ ደግሞ የግብርናው ድርሻ መቀነስ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም ይህንን ታሳቢ በማድረግ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ልማትን በተመለከተ የሚሠራቸውን ሥራዎች ሂደት ‹‹ከእርምጃ ወደ ሩጫ›› በሚል መሪቃል መሠረት ማድረጉን አስታውቋል፡፡ እንደ እነነብዩ ያሉ የተለየ ችሎታ ያላቸው ታዳጊዎች ችሎታቸው በሚጠይቀው መልኩ ከሌሎች ተለይተው ለብቻቸው የሚማሩበትን ትምህርት ቤት ከማዘጋጀት ጀምሮ የተለያዩ ነገሮች እየተደረጉ እንደሚገኙ ይናገራሉ፡፡

የዘርፉን ባለሙያዎች ውጭ ልኮ ማስተማርም የዚሁ አካል ነው፡፡ የፈጠራ ዝንባሌ ያላቸው ወጣቶች የሚያስፈልጓቸውን ግብዓቶ ማግኘት የሚችሉባቸው የሳይንስ ካፍቴሪያዎችም ተገንብተዋል፡፡

ካዛንቺስ በሚገኘው የወጣቶች ማዕከል ስድስት ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎ የተዘጋጀው የሳይንስ ካፍቴሪያም ባለፈው ሰኞ ኅዳር 4 ቀን 2010 ዓ.ም. ተመርቋል፡፡ በከተማው የሚገኙ የሳይንስ ካፍቴሪያዎች ቁጥርም አምስት ደርሷል፡፡ በከተማዋ ተጨማሪ ሁለት የሳይንስ ካፍቴሪያዎችና በክልል ከተሞችም እንደዚሁ ሌሎች የሳይንስ ካፊቴሪያዎችን የመገንባት ዕቅድ መኖሩን ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

በከተማው ብሔራዊ የቴክኖሎጂ ሀብ ለመገንባት 4.6 ሔክታር መሬት ከሊዝ ነፃ መረከባቸውንና የተሠሩና በመሠራት ላይ የሚገኙ አዳዲስ የአገሪቱ የቴክኖሎጂ ውጤቶች መኖራቸውን፣ አንዳንዶቹም በሥራ ላይ መዋላቸውን ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

‹‹ለመቶ እርምጃ መነሻው አንድ ነው›› እንዲሉ፣ ይህ አበረታች ጅምር ሊባል ይችላል፡፡ የተሰጠው ትኩረትም ሳይቋረጥ መቀጠል ያለበት ነው፡፡ መጪው ትውልድ በተሻለ የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት እንዲጠቀምና እንዲፈጥር ዕድል የሚሰጥ ነው፡፡

የቴክኖሎጂ ሽግግር ፖሊሲ በአገሪቱ የፖሊሲ ማዕቀፍ ውስጥ ትልቅ ቦታ ይይዛል ያሉት የዕለቱ የክብር እንግዳ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን ናቸው፡፡ ያደጉት አገሮች ከደረሱበት የቴክኖሎጂ ምጥቀት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በአቋራጭ ለማደግ እንደሚረዳና ብልጥ ሆኖ መጠቀም እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ የሳይንስና ቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት፣ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን አጀንዳውን እንዲደግፍ ተደርጎ መዋቀሩንም ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...