Saturday, July 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ከቅስም ሰባሪ ይሰውረን!

ሰላም! ሰላም! ‹‹ሥልጣን ከላይ ካልተሰጠ በቀር ከሌላ ከማንም አይገኝም፤›› እያሉ ባሻዬ ሰሞኑን ይሰብኩኛል። ሙጋቤን ለመደገፍ ሳይሆን አይቀርም። ወይም ሌላ ሰው አላውቅም ብቻ። የማውቀው አንድ ነገር ነው። ሲያበቃ ሁሉም ያበቃል። ኃያላን በኃይላቸው፣ ጎበዛዝት በጉብዝናቸው አይበረቱም። እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት የባሻዬን ያህል ዕድሜና መንፈሳዊ ዕውቀት ባይኖረኝም፣ ታሪክ የነገረኝ እኔም እየሰማሁት ብዙ አለ። አይደለም እንዴ? ምነው እናንተስ? ‹የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ› እያላችሁ መዝፈን ብቻ ነው እንዴ? ለያዩት እንጂ። ዘንድሮ እኮ አባባል የሚሳያምር ሰው አይደለም የጠፋው። አባባሉን ተረድቶ የሚያስረዳ ነው ያጣነው። እውነቴን እኮ ነው። አንዱ ለምሳሌ በቀደም ለታ ሲበር መጥቶ፣ ‹‹አንበርብር!›› አለኝ። ‹‹ወይ?›› አልኩት። ‹‹ታሪክ ራሱን ደገመ፤›› አለኝ። ‹‹ምን ተፈጠረ?›› ስለው፣ ‹‹ወንድ ልጅ ከነቃጭሉ ዱብ አደረግኩ፤›› አይለኝ መሰላችሁ? ይኼውላችሁ እንዲህ ዓይነቱን ማለቴ ነው።

በተከፈለበትና በተደገመበት መሀል ያለውን ልዩነት የሚረዳው ጥቂት ብቻ ሆኗል። በ93 ዓመቱም በፍፁማዊ አገዛዝ ያላማራጭና ምርጫ ያስተዳደረውን መሪውን የዚምባቡዌ ሕዝብ በምን ሊመስለው ነው? የሚለውን ጥያቄ ለጊዜው እንተወው። ጥያቄ ሲበዛም ጥሩ አይደለማ። አዎ። ጤና መጠያየቅ ተውን እኮ። የችግራችንና የጥያቄያችን ብዛት ጉንጭ አላስመትር እያለ መክሳት መጥቆራችንን ታዝቦ የሚነግረን ሰው ማግኘትም አቅቶናል። እና እኔ ምለው ጤናችሁን ግን ደህና ናችሁ? መፈንቅለ ዕድሜ ሳይመጣ እባካችሁ ለራሳችሁ ስትሉ የጤናችሁን ነገር አደራ እሺ። ኋላ የመጣ ቀን ግን እንደ ሙጋቤ ወታደሮች መፈንቅለ ሥልጣን ማሸጋሸጊያ ነው እንደማይል ዕወቁ። ዕድሜ የማያሳየውና የማይፈነቅለው ነገር የለም መቼም። አይ መሰንበት ደጉ!

መቼስ ወግ አይደል። ወግ ደግሞ በዓይን ይገባል። አሁን እንኳ በቴክስት፣ በቫይበር፣ በፌስቡክና በትዊተርም እየገባ ነው። ማን ዓይን ለዓይን ይተያያል? እውነቴን ነው። ኔትወርክ ቢጠፋ ደግሞ ‹ኩዚ ጉኒ› አሉ። ቀን ቀን በምርቃና ማታ ማታ በምርቃና ተዘጋግተን ውለን ተዘጋግተን ማደር ሆኗል እኮ ነገራችን። ስንተያይ ደግሞ የራሳችንን ምሰሶ ሳንነቅል የሰው ጉድፍ ካላወጣን እያል አገር ይያዝልን ሆኗል ሙያችን። ይኼው ያልነው አልቀረልንም እማማ ኢትዮጵያ፣ ይህች የሆሜር ድርሰት አድማቂ፣ የሦስት ሺሕ ዓመት ተጀምረው ያልተጨረሱ ሥልጣኔዎች ባለቤት እርስ በርስ በመነቋቆርና በመጠዛጠዝ ግርግር ተይዛልን አረፍነው። እሰየው አይባል አገር፣ እንቢየው አይባል ፍቅር ነስቶን በ‘ምን አባህ! የት አባሽ! ምን ታመጣለህ?! ምን ታመጫለሽ?!’ ግልምጫ ማናለብኝነታችን ፋፋ። ‹‹ምነው ግን በልጅነታችን የበላነው ፋፋ ደግ ደጉ ባህላችን ላይ አላፋፋን አለ?›› ብዬ የባሻዬን ልጅ ስጠይቀው፣ ‹‹ከጥያቄህ በፊት የሚቀድመው ‘ስንት ፐርሰንቷ ኢትዮጵያ ናት ይኼን ምግብ እኩል ተመግባ የፋፋችው?’ የሚል ጥያቄ አለ፤›› ብሎኝ አረፈው። እሱ ደግሞ እንዴትም እንዴትም ብሎ ‘ፐርሰንት’ እና ‘ዕድገት’ የሚባሉ ቃላት ንግግሩ መሀል መደንጎር ይወዳል። ኤድያ!

እኔም ቆርጦ አይቆርጥልኝ ዞሬ ዞሬ ለእሱን ነው የሆዴን የማጫውተው። ሆዴ ከሞላና ጨዋታ ‘ኤክስፖርት’ የማድረግ አቅም ካለው ነው ታዲያ። ለነገሩ ተመስገን ነው! እኛ እኛ ምንም አንልም። ለእነሱ ለእነሱም በልማታዊ ብልፅግና ጎርፍ፣ በሥልትና ጥበብ (ጥበብ የሚለው የፀደቀ ስለመሰለኝ አቋራጭ ማለቱን ትቻለሁ) ተሽለው ለሚታዩትም አገሩ አማን ነው። ግን ደግሞ አሉ ወዲያ። ከአደባባዩ ባሻገር፣ ፍሳሹ እያስመለሰ ከተማችንን ከፊል ጎርፋማ ከሚያደርገው ፉካ ሥር የሚያድሩ። መጠለያና ንፁህ ምግብ ማግኘት፣ መንግሥተ ሰማያት ‘ቪአይፒ’ ቦታ ከማግኘት እኩል የሆነባቸው ደግሞ አሉ። ‘እንዴት ይረሳል?’ እንዳለው የትዝታው ንጉሥ!

ታዲያ በቁሜ የማየው የዚች ዓለም ትዕይንት በሐዘን እያፈዘዘኝ በቁሜ ላንኮራፋ ‘ሲንግል ዲጂት’ የሮሮ ዕድገት ሲቀረኝ እባንንና እጄ ላይ ያሉትን ሥራዎች ለመጨራረስ እቃብዛለሁ። እዚያ የሚከራይ ቤት አለኝ። ወዲህ ወደ 12.8 ሚሊዮን ብር የሚገመት የተንጣለለ ቪላ ቤት፣ ተከራይና ገዥ የሚፈልጉ ከባድና ቀላል ተሽከርካሪዎችማ አልቆጥርላችሁም። ግን መምረጥ ይከብደኛል። ‘የቱን ቅድሚያ ልስጥ? ማን ደውሎልኝ ነበር? ምን ፈልጎ?’ ስል የሚታዘበኝ አንድ የሙያ ባልደረባዬ፣ ‹‹አይ አንበርብር አንተም ብለህ ብለህ እንደ ሰፊው ሕዝብ ግራ ተጋባህ?›› ይለኛል። እንደ ምታውቁት ባልተጻፈው የጠቅ ጠቅ ፎርሙላችን እገዛ መናገር የምንፈልገውን ቀጥታ ተናግረን አናውቅም። መናገሩን ትታችሁትን መንገድም ቀጥ ብለን አንራመድም። ለምሳሌ ከቤት ወጥተን ጎረቤት ቤት ገብተን፣ ከጎረቤት አውርተን ደግሞ ዕቃ ረሳን ብለን ቤታችን ተመልሰን ገብተን፣ ከዚያ ተመልሰን የሠፈራችን ሱቅ ወይም ከአንድ ባለ ሱቅ ወዳጅ ጋር ቶክቱከን፣ ከዚያ ነው ሊመሽ አካባቢ ሠፈር የምንለቀው እንጂ፣ ከፈረንጅ እኩል 24 ሰዓት ተሰጥቶን ይኼን ያህል የኑሮና የአስተሳሰብ ልዩነት እንዴት ይመጣል? ደግሞ ይኼን ልናጣራ ነው ብላችሁ ዙሩን አክሩት አሉዋችሁ። ሆሆ!

አንድ ቅጥቅጥ አይሱዙ መግዛት የሚፈልግ ደንበኛዬን አንጋግሬ ሳበቃ ሳይውል ሳያድር ላሳየው ቀጠርኩት። ያው እንደምታውቁት በአገራችን መቅጠር እንጂ መድረስ ከባድ ነው። ማቀድ እንጂ ማሳካት ህልም ነው። ማፈንዳት እንጂ ማዳፈን እንዴት ጭንቅ እንደሆነ ለኖረ አይነገረውም። ‹‹. . . ዳሩ ትናንትን ዛሬ እያሰከረው ብዙ ነገር የገባን መስሎን ሳይገባን እየዘለለን ነው። ከታሪካችን አስታውሰን ልንማርበት የሚገባንን ሁሉ እንደምንዘለው ለጤናችን አስበን ገመድ እንኳ አንዘልም፤›› ይሉኛል ባሻዬ የሰሞኑ አጥንት ሰርሳሪ ብርድ በቁርጥማት ጨምድዶ ቤት እያስቀመጣቸው ልጠይቃቸው ስሄድ። መቼም እሳቸውን ታውቋቸዋላችሁ። ሲያመሩም ሲቀልዱም ወግ ይችሉበታል።

ደግሞ መቼ ዕለት ነው፣ ‹‹አንተ ምነው ወጣት ካልተሆነ በረደኝ ተብሎ ሚስት አይፈለግም እንዴ? እስኪ ሚስት ፈልግልኝ፤›› አሉኝ። ‹‹አይ ባሻዬ በፍለጋ ቢሆን ንፋስ እስከ ዛሬ ስንት ሚስቶች ይኖሩት ነበር?›› ስላቸው ከት ብለው እየሳቁ፣ ‹‹እኔ እኮ ገለባ ስለማንጓለል አልጠየኩህም? ከአጨዳና ከጉልጓሎ የቱ እንደሚቀድም የተምታታበት ትውልድ በ‘ኢንተርኔት’ የትዳር አጋር ሲጎለጉል ይውላል ሲባል ስለሰማሁ ለምን ይቅርብኝ ብዬ እንጂ። በላ ምን ይጎለኛል?” ብለው ሳቃቸውን እስኪጨርሱ አጀብኳቸው። ባሻዬ ለቀልድ ነገሩን አነሱት እንጂ እንኳን ትዳር ወገባችንን ታጥቀን የተያያዝነው ያገር ልማት በጎደለ ተሞልቶም አልሞላ ብሏል። እናላችሁ ከሕዝብ ተቀላቅዬ ወደ ደንበኛዬ ስገሰግስ አንዱ፣ ‹‹በቅርቡ ሳተላይት እናመጥቃለን የሚሉን መጀመሪያ መቼ ምድር ለምድር መጠቅን? የታለ ቴክኖሎጂያችን? ራዕይ ከመደራረብ ምናለበት ከሥር ከሥሩ ጫና ብናቀልና የዋልንበትን አረም ባይበላው?›› እያለ ሰውን ሲያስጨንቀው ሰማሁ። ተጨንቆ አስጨናቂ ብቻ ይሙላው መንገዱን?!

 እንሰነባበት መሰለኝ። ዕድሜም ነው መሰለኝ እንጃልኝ፣ መስከረም ከጠባ አንስቶ ዝምታ ምቾቴ ሆኗል። ለወትሮው ስከራከር፣ ስተች፣ ሳጥላላ፣ ሳደንቅና ስወድ የሚያውቁኝ ሁሉ ‘አንበርብር ፈዘዘ’ እያሉኝ ነው። አድማጭ በሌለበት ማውራት ጩኸት ሆኖብኝ ብቻ እንዳይመስላችሁ። እርግጠኛ መሆን፣ ከእኔ እምነትና አስተሳሰብ ውጪ ሌላዌ ላሳር ብሎ ድምዳሜ ፍርኃት እየለቀቀብኝ ስለቸገረኝ ነው። ዕድሜም መሰለኝ ያልኳችሁ ይኼን ነው። ልኩን የማያውቅ ካልሆነ ዕድሜ በበኩሉ በዘመን በዘመን ልክን ከማስመር ቦዝኖ አያውቅማ። የምሬን ነው። ሲኩል በልክ፣ ሲድር በልክ፣ ሲሰጥ በልክ፣ ሲነሳ በልክ እንደሆ እኔ የዕድሜ አንዱ ምስክር ነኝ። እኔን ያላመነ ደግሞ ጋዳፊ፣ ሳዳም ሁሴን፣ ወይም የሰሞኑ ሙጋቤ አሉለት።

ዕድሜም ሰውም መክሮት ልኩን የሚያልፍ ሲገጥማችሁ፣ ዝምታ የትኛውም ሚዲያ ያላስተዋወቀው ምቹ ፍራሽ ሆኖ ታገኙታላችሁ። ብቻ ቅድም ያልኳችሁን እንዳትረሱት። መፈንቅለ ዕድሜ ሳይመጣ ደግ ደጉን ሠርተን ደግ ደጉን አውርተን ማለፍ ነው። ዘንድሮ ሳያልፍ እያለፈበት ስንቱ በቁም ያንጎላጃል መሰላችሁ? ካላመናችሁኝ እስኪ ጎዳናውን እዩት። ጭር አላላባችሁም? የዶላር እጥረት ብቻ ይመስላችኋል? ወይስ የኑሮ ውድነቱ ብቻ ጭር ያረደገው? ሳያልፍ ያለፈበት በዝቶ እኮ ነው። እና በአጭሩ ሥልጣን ብቻ ሳይሆን ጤናም ያልፋል፣ ያልቃል። ሳንቀደም መቅደም መታደል ነው ለማለት ነው። ሌላውን ደግሞ ለንፋሱ ስል ምን ትዝ አለኝ መሰላችሁ? የንፋስ አመጣሾች ነገር ነዋ፡፡ እነዚህ አገር ምድሩን የሞሉት ንፋስ አመጣሽ ባለሀብቶችን ማለቴ ነው፡፡ የኀዳር ንፋስና ንፋስ አመጣሾችን ስንገጣጥመቸው፣ አንድ ምስል ይፈጥራል፡፡ ንፋሱ ቁርጥማት ሲለቅብን፣ ንፋስ አመጣሾቹ ደግሞ ቅስማችንን ይሰብራሉ፡፡ ከቅስም ሰባሪ ይሰውረን! መልካም ሰንበት!

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት