Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየማታ ትምህርት ወደ ውድቀት?

የማታ ትምህርት ወደ ውድቀት?

ቀን:

ከትውልድ ቀዬዋ ወደ አዲስ አበባ የመጣችው ስምንተኛ ክፍልን አጠናቃ ነበር፡፡ የቀን ተማሪም ነበረች፡፡ አዲስ አበባ ከመጣች ወዲህ ግን የቀን ተማሪ የመሆን ዕድል አላጋጠማትም፡፡ በሰው ቤት ሠራተኝነት ተቀጥራ ትምህርቷን የማታ ቀጠለች፡፡

ከዘጠኝ እስከ አሥር ለመድረስ የትምህርት መመሪያው በሚፈቅደው መሠረት ሦስት ዓመት ወስዶባታል፡፡ በክፍሏ ጎበዝ ተማሪ የነበረች ሲሆን፣ ውጤቷን የተመለከቱት መምህሮቿና አሠሪዎቿም እንድታጠናና አጋዥ መጽሐፍ እንድትጠቀም ያበረታቷት እንደነበር ትናገራለች፡፡

የአሥረኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተናን በ2009 ዓ.ም. የተፈተነችው ታዳጊ ወጣት፣ በአሠሪዎቿም ሆነ በመምህራን ጥሩ ውጤት ታመጣለች የሚል ግምትን አሳድራ ነበር፡፡ እሷ እንደምትለውም፣ አስተማሪዎቿ የክፍል ተሳትፎዋንና ውጤቷን እያዩ ያበረታቷትና ውጤት እንደምታመጣም ተስፋ ይሰጧት ነበር፡፡ አሠሪዎቿም ቢሆኑ እንዲሁ፡፡ ‹‹አሠሪዬ ቢያንስ ከ2.4 በላይ ታመጫለሽ ትለኝ ነበር›› የምትለው ታዳጊ፣ ተስፋ ከተጣለባት በተለየ ያመጣቸው ውጤት 1.85 መሆኑን ትናገራለች፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ሁለት ትምህርት ‹‹ኤፍ›› ማምጣቷን በመግለጽም፣ በሞዴል ፈተና ወቅት ሁለቱንም ትምህርቶች ከ80 በላይ ያመጣቻቸው እንደነበሩ፣ መምህሮቿም ቁጣና ሐዘኔታ በተቀላቀለበት አነጋገር ‹‹አንቺን ጠብቀን ነበር፡፡ ከማታ ተማሪ ግን ያንቺ የተሻለ ነው›› እንዳሏት ትገልጻለች፡፡

ይህች ታዳጊ እንደምትለው፣ ያገኘችው ውጤት ቴክኒክና ሙያ ሊያስገባት እንደሚችል አሠሪዎቿ ቢነግሯትም ትምህርቱን እንዴት የቀን መከታተል እንደምትችል ሐሳብ ገብቷት ነበር፡፡ ሆኖም አሠሪዎቿ ፈቅደውላትና ተያዥ ሆነውላት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቴክኒክና ሙያ በኮልፌ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ በሆቴልና ሆስፒታሊቲ የትምህርት ዘርፍ መማር እንደጀመረች ትናገራለች፡፡

ምን ያህሉ የማታ ተማሪዎች የአሠሪዎቻቸውን ድጋፍ ያገኛሉ? በየወረዳው ያልተማሩ ልጆች እንዲማሩ በየቤቱ እየተንኳኳ የሚነገረውን ምን ያህሉ አሠሪዎች ይቀበሉታል? ቢቀበሉትስ ለሠራተኞቻቸው የማጥኛ ጊዜ ይሰጣሉ ወይ? ይከታተላሉስ? ተማሪዎቹስ ምን ያህል ፍላጎቱ አላቸው? ተስማምተውስ ከአንድ ቦታ ረግተው ይኖራሉ ወይ? የማታ ትምህርት ከመሆኑ አንፃር ትምህርት ቤትስ በአቅራቢያቸው ያገኛሉ ወይ? የሚሉትና ሌሎች ብዙ ተያያዥ ጉዳዮች በሰው ቤትም ሆነ በቀን ሥራ ተቀጥረው ከአንደኛ እስከ 12ኛ ክፍል የሚሰጠውን የማታ ትምህርት የሚማሩ ተማሪዎችን የሚፈትኑ ጉዳዮች ናቸው፡፡

ይህም የማታ ተማሪዎች የቱንም ያህል በክፍል ውስጥ ተሳታፊና ጎበዝ ቢመስሉም፣ በስምንተኛውና በአሥረኛው ክፍል ብሔራዊ ፈተና ያላቸው ውጤት አነስተኛ እንዲሆን ምክንያት መሆኑን ለስድስት ዓመታት ያህል በብርሃነ ዛሬ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የቋንቋ መምህር የነበሩት አቶ ዮሐንስ ሞላ ይናገራሉ፡፡

እሳቸው የማታ ተማሪዎችን፤ ፍላጎት፣ አቅምና ጉጉት ያላቸው፣ ከቤት መውጫ ያደረጉና ፍላጎቱና አቅሙ ሳይኖራቸው በግፊትና ሥራ በመሸሽ የሚመጡ ሲሉ ይከፍሏቸዋል፡፡ ፍላጎቱ ሳይኖራቸው የማታ ትምህርትን ከቤት መውጫ ያደረጉት ክፍል መግባት የማይፈልጉና አሉታዊ ሥነ ምግባር ያላቸውም ናቸው፡፡

ቀን በሥራ ደክመው የሚመጡ በመሆናቸው፣ ቤተ መጻሕፍት ለመጠቀም ዕድሉ ካለመኖሩና መጽሐፍ እንደቀን ተማሪ ካለማግኘታቸው ጋር ተደምሮ ብቁና በቂ መምህራን በማታው ክፍለ ጊዜ አለመኖራቸውም ለማታ ለተማሪዎች ውጤት እንዳያመጡ ምክንያት ያነሳሉ፡፡

መምህራን ቀን ደክመው መዋላቸው፣ ብዙዎቹ ራሳቸውን ለመለወጥ የማታ መማራቸው፣ ክፍያ በመቶኛ ተሠልቶ ጥቂት መሆኑም ሌላው ፈተና ነው፡፡

አቶ ዮሐንስ፣ የስምንተኛ ክፍል የሚኒስትሪ ውጤት ሲመጣ መምህራን በአብዛኛው ያፍሩ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ አንድ ጊዜ ከ250 ተማሪ 26 ተማሪዎች አልፈው ታሪክ እንደተባለ፣ ብዙውን ጊዜም በየዓመቱ አምስት ወይም ስድስት ተማሪዎች ብቻ ያልፉ እንደነበር ያክላሉ፡፡

 አንዳንዶቹ የማታ ለመማር በአቅራቢያ ትምህርት ቤት ሲያገኙ አጥተው ከመማር የሚደናቀፉም ቀላል አይደሉም፡፡ በተለይ ዘንድሮ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች የማታ ተማሪዎችን ለማስተናገድ ፈተና ገጥሟቸዋል፡፡ ብዙዎቹም ተዘግተዋል፡፡

የቤት ውስጥ ሠራተኛዋ አስናቀች አበበ ለትምህርት ያላት ፍላጎት ከፍተኛ  በመሆኑ በትውልድ ሥፍራዋ እስከ አራተኛ ክፍል፣ ወደ አዲስ አበባ ካቀናችበት ጊዜ ጀምሮ ደግሞ በማታው መርሐ ግብር እስከ ሰባተኛ ክፍል ተምራለች፡፡ ዘንድሮ ስምንተኛ ክፍል መሆኛዋ ነበር፡፡ ሆኖም ወደ ትምህርት ቤቷ ለመመዝገብ ስትሄድ በማስታወቂያ ሰሌዳው ያየችው ያልጠበቀችውን ነበር፡፡

የማስታወቂያ ሰሌዳው ‹‹በ2010 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን የማታው መርሐ ግብር መቋረጡን እናስታውቃለን፤›› ይል ነበር፡፡ ይህንንም ከርዕሰ መምህሩ አጣርታ እውነት መሆኑን አመነች፡፡ ተስፋ ሳትቆርጥ በአካባቢዋ የሚገኙ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን በር ብታንኳኳም፣ እናስተምራለን የሚል እንዳጣችና በዚህም ግራ እንደተጋባች ነግራናለች፡፡

እኛም ይህንኑ መነሻ በማድረግ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች የሚገኙና የማታውን መርሐ ግብር ካቋረጡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መካከል የጥቂቶቹን ርዕሳነ መምህራን ተዘዋውረን አነጋግረናል፡፡ ከየትምህርት ቤቱ ርዕሳነ መምህራን የተረዳነውም ለማታው መርሐ ግብር መቋረጥ የመምህራን የማታ ትምህርት አገልግሎት ክፍያ ማነስ፣ መምህራን የኮንዶሚኒየም ቤት ዕጣ ባለ ዕድል እየሆኑ ራቅ ወዳሉ ሥፍራዎች መሄዳቸውና ከምሽቱ ሁለት ሰዓት በኋላ ወጥተው ቤት ለመድረስ የትራንስፖርቱ ሁኔታ አለመመቸቱ ዋና ዋናዎቹ ምክንያቶች ናቸው፡፡ የተማሪዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣትም ለችግሩ መባባስ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ተማሪዎችም ለማታው ክፍለ ጊዜ የሚከፍሉት ክፍያ ‹‹ተወደደ›› ይሉታል፡፡

መምህራን በማታው መርሐ ግብር ላይ የሚሳተፉት ከመደበኛ ሥራቸው ውጭ በትርፍ ሰዓታቸው መሆኑና የሚያገኙት ክፍያ ከመደበኛ ደመወዛቸው ጋር ተደምሮና 35 በመቶ ታክስ ተጥሎበት የሚያገኙት አነስተኛ መሆኑም መምህራኑን አያበረታታም፡፡  ይህም ትርፉ ድካም ብቻ ከመሆኑም በላይ ለኪሳራ ስለዳረጋቸው የትርፍ ሰዓት ሥራቸውን ማቋረጥ ግድ ሆኖባቸዋል፡፡

የማታ ተማሪዎች ወርኃዊ ክፍያ የሚፈጽሙት በሥርዓተ ትምህርቱ ላይ በወጣው መመሪያ መሠረት እንደሆነ፣ በዚህም መመሪያ በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ለአንደኛ ክፍል 29 ብር ከ75 ሳንቲም፣ ለስምንተኛ ክፍል ደግሞ 63 ብር እንደሚከፈል፣ ይህ ዓይነቱ ክፍያ አነስተኛ የሚባል ዓይነት ቢሆንም ከጥቅምትና ከኀዳር ወራት በኋላ ተማሪዎች የማቋረጥ፣ አካባቢን የመቀየር ሁኔታ እንደሚስተዋልባቸውና በዚህም የተነሳ የመምህራን ክፍያ በእጅጉ እያሽቆለቆለ እንደሚሄድ ርዕሳነ መምህራኑ አስረድተዋል፡፡

በየትምህርት ቤቶቹ አካባቢ ቤት ተከራይተው ይኖሩ የነበሩ መምህራን በዕጣ ወደ ደረሳቸው ኮንዶሚኒየም ቤት መሄድም በማታው መርሐ ግብር ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ በዕጣ ከደረሳቸውም ኮንዶሚኒየም ቤቶች መካከል የካ አባዶ፣ ቱሉ ዲምቱ፣ ገላን፣ ቃሊቲ፣ ቦሌ አራብሳ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ የማስተማር ሥራቸውን ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ከሩብ ላይ ከጨረሱ በኋላ ወደተጠቀሱት መኖሪያ መንደራቸው ለመሄድ ያለው የትራንስፖርት ፈተና በእጅጉ አሰቃቂ ነው፡፡ ለመንግሥት ሠራተኞች የተመደበው ሲቪል ሰርቪስ ባስ ለቀን እንጂ ለማታ አገልግሎት ባለመስጠቱም የተነሳ ያላቸው ብቸኛ አማራጭ የትርፍ ሰዓት ሥራቸውን መተው ብቻ ሆኗል፡፡

ከአስተያየት ሰጪዎች ርዕሳነ መምህራን መካከል በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የሚገኘው የዕድገት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የአደረጃጀትና የትምህርት ፕሮግራም ምክትል ርዕሰ መምህር አቶ ፍፁም መልኬ እንደገለጹት፣ የመምህራን ክፍያን አስመልክቶ በርዕሳነ መምህራን ደረጃ ከአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡ በዚህም ውይይት በተጣለው ታክስ ላይ ማሻሻያ እንዲደረግበት ጥያቄ ቢቀርብም፣ ውይይቱም ሆነ ጥያቄው እስካሁን ውጤት እንዳላስገኘ አመልክተዋል፡፡

ዘንድሮ የማታ ትምህርት ፈላጊዎች ቁጥር ብዙ እንደነበሩ፣ ለዚህም በትርፍ ሰዓታቸው ማስተማር ለሚፈልጉ በማስታወቂያ ጥሪ እንደተላለፈላቸው፣ ጥሪውን ተቀብለው የተመዘገቡት ግን ስድስት መምህራን ብቻ እንደሆኑና በዚህ ቁጥር ለማስተማር አስቸጋሪ በመሆኑ ትምህርቱን ማቋረጥ ግድ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በማታው መርሐ ግብር ላይ መምህራን በትርፍ ሰዓት ሥራቸውን መተው የጀመሩት ዓምና እንደነበር፣ በዚህም የተነሳ የቀሩት መምህራን የትርፍ ሰዓት ሥራቸው ላይ የቀሩትንም ደርበው እንዲሠሩና ርዕሳነ መምህራን በማስተማሩ ሥራ ላይ እንዲሳተፉ በማድረግ የተከሰተውን ክፍተት በመሸፈን የወቅቱ ትምህርት እንዲያልቅ መደረጉንም፣ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ ርዕሰ መምህር ነግረውናል፡፡

 ዜጎች ቀን እየሠሩ ማታ መማራቸው ለአገር ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸው፣ ትምህርቱ ቀጣይነት እንዲኖረውና ውጤታማም እንዲሆን መምህራንን የሚስቡ ሁኔታዎች መመቻቸት እንዳለባቸው ከሚመቻቹትም ሀኔታዎች መካከል የትምህርት ቤት ወርኃዊ ክፍያን ከፍ፣ አለበለዚያ ደግሞ የተጣለው ታክስ ዝቅ እንዲል ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የፈተና ዝግጅት አስተዳደር  ዳይሬክተር አቶ መረሳ አብርሃ ስለዚህ ጉዳይ ተጠይቀው ችግሩ የገንዘብ ነው? ወይስ የመምህራኑ ቁርጠኝነት ማነስ ነው? የሚለውን ለይቶ ለማወቅ የሚያስችል ጥናት ማካሄድ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

ቀን ሥራ ላይ የዋሉ ማታ መማር ያለባቸው መሆኑን በማውሳት መምህራን ማስተማርን ከጥቅም አኳያ ብቻ ሳይሆን ዜጎችን ከማስተማርና አገርን ከመገንባት ጭምር እንዲያዩት ጠይቀዋል፡፡

 የታክስ መጠኑ ከ35 በመቶ ወደ ሁለት በመቶ ዝቅ እንዲልላቸው ቢሮው ጉዳዩ ከሚመለከተው መንግሥታዊ አካል ጋር በመደራደር ላይ እንደሆነ የሚገለጹት አቶ መረሳ፣ አጠቃላይ በማታ ትምህርት ክፍተት፣ በመምህራኑ ችግር በትምህርት ጥራት ዙሪያ በቅርቡ ውይይት እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ መረሳ፣ ባለፈው ዓመት በተካሄደው የስምንተኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ላይ ከተቀመጡት የአዲስ አበባ የማታ ተማሪዎች መካከል 84 በመቶ ያህሉ ሲወድቁ፣ ያለፉት 16 በመቶው ብቻ ናቸው፡፡ የአሥረኛ ክፍሉም ቢሆን ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡

ለዚህም ውጤት ማሽቆልቆል እንደምክንያት የሚቀርበው መምህራኑ በክፍያ ማነስ ሳቢያ የትርፍ ሰዓት ሥራቸውን መተዋቸው፣ በመምህራን በኩል ክፍተት መኖሩ እንዲሁም የተማሪዎቹ ዝግጁነት ማነስና ሁልጊዜም በትምህርት ገበታቸው ላይ አለመገኘት ነው፡፡

 ከዚህ ባለፈም እንደ ቀን ተማሪዎች በቤተሰባቸው ክትትል የማይደረግላቸው መሆኑና በግላቸው ወይም በቤት ሠራተኝነት የሚተዳደሩ በመሆናቸውም ሥነ ምግባራቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ በቅርቡ ይደረጋል የተባለው ስብሰባም  እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ያለመ እንደሚሆን አቶ መረሳ ተናገረዋል፡፡

በምሕረት ሞገስና ታደሰ ገብረማርያም

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...