Tuesday, May 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየስድስት ዓመት ሕፃን በምትማርበት ትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ ተደፈረች

የስድስት ዓመት ሕፃን በምትማርበት ትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ ተደፈረች

ቀን:

  • ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተጠቁሟል

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 ገላን ቁጥር ሁለት ትምህርት ቤት ውስጥ የምትማር የስድስት ዓመት ሕፃን፣ ጥቅምት 29 ቀን 2010 ዓ.ም. በሁለት ወጣቶች መደፈሯ ተሰማ፡፡

የሕፃኗ ወላጅ እናት ወ/ሮ ዘሪቱ ሰይድ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በልጃቸው ላይ ጥቃቱ የተፈጸመው ጥቅምት 29 ቀን 2010 ዓ.ም. ነው፡፡

በዕለቱ ሕፃኗ ቤቷ እንደ ደረሰች ‹‹ብረት ወግቶኝ ሆዴን አሞኛል›› ብላ ወደ መፀዳጃ ቤት እየሮጠች ከገባች በኋላ እንደ ጮኸች ወ/ሮ ዘሪቱ ገልጸዋል፡፡ ምን እንደሆነች ሲጠይቋት አጥጋቢ ምላሽ ባለመስጠቷ ተጠራጥረው ያደረገችውን ታይትና የውስጥ ሱሪ አስወልቀው ሲያዩዋት ግን መድማቷን ተናግረዋል፡፡ በኋላ ላይ ለታላቅ ወንድሟ እንደተናገረችም ገልጸዋል፡፡

- Advertisement -

በመማር ላይ እያለች መፀዳጃ ቤት መሄድ ፈልጋ በማስፈቀድ ደርሳ ስትመለስ እጇን በመታጠብ ላይ እያለች፣ ሁለት ወንዶች ታቅፈው ከትምህርት ቤቱ በስተኋላ በመውሰድ ተፈራርቀው እንደ ደፈሯት ለወንድሟ እንደነገረችው ገልጸዋል፡፡ ‹‹ብረት ወግቶኝ ነው›› እንድትልና ሌላ ነገር ብትናገር እንደሚገድሏት እንዳስፈራሯትም መግለጿን አክለዋል፡፡

የተደፈረችው ሕፃን የሆነችውን ሁሉ ለወንድሟ ከገለጸች በኋላ፣ ወ/ሮ ዘሪቱ ልጃቸውን በአካባቢው በሚገኝ የሕዝብ ጤና ጣቢያ መውሰዳቸውን አስረድተዋል፡፡ ከጤና ጣቢያ በቀጥታ የገላን አካባቢ ቆርኬ ፖሊስ ጣቢያ የሴቶችና ሕፃናት ክብካቤ ይዘዋት ሲሄዱም፣ የሚቀበሉት የጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታልን የምርመራ ውጤት ብቻ እንደሆነ ስለተገለጸላቸው ሕፃኗን ይዘው ወደ ጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል መሄዳቸውንም አስረድተዋል፡፡

የጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል ሕፃኗ መደፈሯንና በመጎዳቷም ደም እየፈሰሳት መሆኑን በማረጋገጥ፣ ውጤቱን አሽጎ ለፖሊስ ጣቢያው እንደላከና እንዳደረሱ ገልጸዋል፡፡

ሆስፒታሉ የደፈሯት ወንዶች የጤና ሁኔታ ስለማይታወቅ የቅድመ ኤችአይቪ ኤድስ መከላከያ ለ28 ቀናት እንድትወስድ እንዳዘዘ፣ ሐኪሞችም የተለያዩ የአባላዘር በሽታዎች መከላከያ መርፌዎች እንደ ወጓትና ለጊዜው ይፈሳት የነበረው ደም አልቆም ብሏቸው የተለያዩ ሕክምናዎችን እንዳደረጉላት ተናግረዋል፡፡

ውጤቱን የተቀበለው የቆርኬ ፖሊስ ጣቢያ የዕለቱ ተረኛና መርማሪ ፖሊስ፣ ‹‹ይህንን ጉዳይ ለትምህርት ቤቱ እንዳታሳውቂ›› ስላላቸው፣ እስከ ኅዳር 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ ዝምታን የመረጡ ቢሆንም፣ የእሳቸውን ቃል ከመቀበል ውጪ ምንም ሊያደርጉ እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡

የአካባቢው ፖሊስ ጣቢያና የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምርያ ለጉዳዩ በቂ ትኩረት አልሰጡም ብለው ያመኑት ወ/ሮ ዘሪቱ፣ ጉዳዩን ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዋና መሥሪያ ቤት ሊወስዱ መገደዳቸውን አስረድተዋል፡፡ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጉዳዩን እንደሰማ ክፍለ ከተማውን በመጠየቁና አፋጣኝ ዕርምጃ እንዲወስድ ትዕዛዝ በመስጠቱ የክፍለ ከተማው መምርያ ኃላፊ ጠርተው እንዳነጋገሯቸው የገለጹት ወ/ሮ ዘሪቱ፣ ሌላ የወንጀል ምርመራ ኃላፊ እንዳገናኟቸውና እሳቸው ደግሞ ወደ ሌላኛው የወንጀል መርማሪ ፖሊስ እንዳስተላለፏቸው አስረድተዋል፡፡

አንድ የወንጀል መርማሪ ፖሊስ ኅዳር 4 ቀን 2010 ዓ.ም. ይዘዋቸው ወደ ትምህርት ቤቱ ከሄዱ በኋላ ስለልጃቸው መደፈር ሲነግሯቸው፣ የትምህርት ቤቱ ኃላፊዎች ምንም የሚያውቁት እንደሌለ ነገር ግን ክትትል አድርገው እንደሚያሳውቋቸው እንደነገሯቸውም አክለዋል፡፡

ወ/ሮ ዘሪቱ ልጃቸው ደፋሪዎቿን እንደምታውቃቸው ገልጸው፣ ‹‹ተማሪዎቹ ይሠለፉና ትጠቁም›› ቢሉም ትምህርት ቤቱ አለመስማማቱን፣ ወይም ተማሪዎች ሲመዘገቡ በሚሰጡት ፎቶ እንድትጠቁም ቢጠይቁም ምላሽ ማጣታቸውን አስረድተዋል፡፡

ድርጊቱ ተፈጸመበት የተባለውን ገላን ቁጥር ሁለት ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ኦሊያድ ወጋሪን ሪፖርተር አነጋግሯቸው፣ ‹‹የሰማሁት ኅዳር 4 ቀን 2010 ዓ.ም. ነው፡፡ በወቅቱ ሥልጠና ላይ ነበርኩ፡፡ አሁን ከፖሊስ ጋር ሆነን ጉዳዩን እየተከታተልን ነው፤›› ብለዋል፡፡

የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምርያ የወንጀል ምርመራ ኃላፊ ኮማንደር ተስፋዬን ሪፖርተር አነጋግሯቸው ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሴቶችና ሕፃናት ክብካቤ ማስተባበሪያ ኮማንደር አፀደን አነጋግረናቸው፣ ‹‹ጉዳዩ በምርመራ ላይ ነው፡፡ እየተከታተልነው ነው፤›› ከማለት ውጪ ተጨማሪ ማብራሪያ ለመስጠት አልፈለጉም፡፡

ሪፖርተር ዘግይቶ እንዳረጋገጠው በሕፃኗ ላይ ድርጊቱን ፈጽመዋል የተባሉት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...