- በተደረገው የምንዛሪ ለውጥ እምብዛም የዋጋ ጭማሪ አላየሁም ብሏል
የዓለም ባንክ ከኢትዮጵያ መንግሥት የልማት ግቦች ጋር የተሳሰሩ ሥራዎቹን የሚመራበትን የኢትዮጵያ የአጋርነት ማዕቀፍ የተሰኘ የፕሮጋራም ሰነድን ባስተዋወቀበት ወቅት ይፋ ባደረገው መሠረት፣ 4.7 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ለመስጠት መወሰኑን አስታውቋል፡፡
እ.ኤ.አ. ከ2018 እስከ 2022 ተግባራዊ የሚሆነው የአጋርነት ማዕቀፍ (Country Partnership Framework) መሠረት፣ ባንኩ በኢትዮጵያ ለሚከናወኑ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፕሮጀክቶች በጠቅላላው 4.7 ቢሊዮን ዶላር ብድርና ዕርዳታ ለመስጠት ወስኗል፡፡ በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ የሱዳንና የደቡብ ሱዳን ዳይሬክተር ካሮሊን ተርክ እንደገለጹት፣ ለኢትዮጵያ መንግሥት የሚቀርበው ገንዘብ 50 በመቶው በብድር፣ ቀሪው በዕርዳታ እንደሚሰጥ አስታውቀዋል፡፡
ባንኩ ለኢትዮጵያ የሚሰጠው ገንዘብ በአገሪቱ በታየው ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ለውጥ ላይ መሠረት ያደረገ እንደሆነ ያብራሩት ዳይሬክተሯ፣ የመንግሥት ውጤታማ በጀት አጠቃቀም በባንኩ ትልቅ ቦታ እንደሚሰጠውም አክለዋል፡፡ በመሆኑም የዓለም ባንክ ይፋ ያደረገው የአጋርነት ማዕቀፍ ሰነድ በሦስት ዋና ዋና የተግባር ምሰሶዎች ላይ እንደሚያጠነጥን ያብራራል፡፡
አንደኛው መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ለውጥ ሲሆን፣ ሁለተኛው ለድርቅና መሰል ችግሮች ያለውን ተጋላጭነት የሚቋቋም አቅም መገንባት ላይ ያተኩራል፡፡ ሦስተኛው የባንኩ ዋና ተግባር በተቋማት ተጠያቂነትና በሙስና ላይ ያጠነጠነ ነው፡፡ በተጠያቂነትና በሙስና ላይ ማተኮር የተፈለገበትን ምክንያት እንዲያብራሩ ሪፖርተር ጥያቄ ያቀረበላቸው ካሮሊን ተርክ፣ የመንግሥት አካላት ለሚያስተዳድሩት የሕዝብ ሀብትና ንብረት ያለባቸውን ተጠያቂነት ሕዝብ እንዲገነዘብ ለማድረግ በማሰብ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ መንግሥት በቅርቡ በሙስና ወንጀል ተጠርጣሪዎች ላይ የወሰደውን ዕርምጃ ያስታወሱት ዳሬክተሯ፣ እንዲህ ዓይነት ተግባራትን ለመግታት በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ባንኩ ድጋፉን ለመስጠት እንሚሠራም ጠቁመዋል፡፡
መንግሥታዊ ተቋማት ስለበጀት አጠቃቀማቸው፣ ወጪና ገቢያቸው፣ ትርፍና ኪሳራቸው፣ ወዘተ. የሚያትቱ መረጃዎችን እስከ ታችኛው የወረዳና የቀበሌ መዋቅር ባለው ዕርከን ለሕዝብ ይፋ የማድረግ ኃላፊነት እንደተጣለባቸው የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትሩ አብርሃም ተከስተ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
ላለፉት ዓመታት በአገሪቱ ከመንግሥት የኢኮኖሚና የልማት ዕቅዶች ጋር በተገናኘ ተግባራዊ ሲደረግ የቆየው የኢትዮጵያ አጋርነት ስትራቴጂ የተሰኘውን ፕሮግራም የተካው አዲሱ ማዕቀፍ፣ ምላሽ ይሰጥባቸው ተብለው የተቀመጡ ግቦችም ይፋ ተደርገዋል፡፡ ባንኩ ባካሄደው ጥናት መሠረት በጤናና በትህምርት መስክ ዝቅተኛ የሰው ሀብት ልማት መታየቱ፣ የንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦትና የሳኒቴሽን ችግር ከፍተኛ መሆኑ፣ በከተማ ደረጃ የሚሰጥ የሴፍቲኔት ድጋፍ አለመኖሩ ባንኩ ከጠቀሳቸው መካከል ይመደባሉ፡፡
በመሆኑም በመጪዎቹ ሦስት ዓመታት ውስጥ በአገሪቱ ከሚኖው ሕዝብ ቢያንስ 50 በመቶው የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ተጠቃሚ እንደሆን ማድረግ የአጋርነት ማዕቀፉ አንዱ ተልዕኮ ሲሆን፣ የንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦትን በ20 በመቶ ማሳደግ፣ የሳኒቴሽን አቅርቦትን ወደ 43 በመቶ ማድረስ ባንኩ ካስቀመጣቸው ግቦች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ ሌሎችም እንደ መንገድ ያሉት መሠረተ ልማቶች እንዲስፋፉ በሚያስችሉ ሥራዎች ላይ የባንኩ ድጋፍ እንደሚኖር ተጠቅሷል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ መንግሥት በቅርቡ በወሰደው የምንዛሪ ለውጥ ሳቢያ ይህ ነው የሚባል የዋጋ ጭማሪ አለመታየቱን ባንኩ እንዳረጋገጠ ዳይሬክተሯ አስታውቀዋል፡፡ በተለይ በአገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶች በምንዛሪ ለውጡ ሳቢያ የዋጋ ጭማሪ እንደማይታይባቸው ተናግረው፣ ከውጭ የሚገቡት ምርቶች ግን ለውጥ ሊያሳዩ እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትሩ በበኩላቸው የምንዛሪ ለውጡ ከውጭ የሚገቡ ሸቀጦች ዋጋ እንዲወደድ፣ በአንፃሩ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች በምንዛሪ ለውጡ ሳቢያ ከቀድሞው የተሻለ ዕድል እንዲያገኙ ለማስቻል የተወሰደ ዕርምጃ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ይሁንና የግሉ ዘርፍ በዚህ ዕርምጃ በመጠቀም ማምረትና ለገበያ ማቅረብ እንደሚጠበቅበትም አስታውቀዋል፡፡