ከሦስት ሺሕ በላይ አባላት ያሉዋቸው 65 የታክሲ ማኅበራት፣ ያለቀረጥ አዳዲስ ታክሲዎችን ለማስገባት ያቀረቡት ጥያቄ በመዘግየቱ ቅሬታ አቀረቡ፡፡
ቅሬታውን ያቀረቡት የታክሲ ማኅበራት ኃላፊዎች ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የአዲስ አበባን ገጽታ የሚቀይሩና ዘመናዊ መሣሪያ የተገጠመላቸው ከሦስት ሺሕ በላይ ታክሲዎችን ለማስገባት ከአንድ ዓመት በፊት ለመንግሥት ጥያቄ ቢያቀርቡም፣ እስካሁን ድረስ ወደ ተግባር አልተገባም፡፡
የአንድነት ሜትር ታክሲ ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ወንድወሰን ለገሰ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ‹‹ከዛሬ አንድ ዓመት በፊት ተደራጅተን ከመንግሥት የቀረጥ ነፃና ብድር ተመቻችቶልን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግራችንን ለመፍታት እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ የተለያዩ የቢሮ ኃላፊዎች ድረስ በመሄድ ጉዳያችንን ስናስፈጽም ቆይተናል፡፡ አንዳንድ መንግሥታዊ ድርጅቶች ግን ለጉዳዩ ትኩረት ባለመስጠት ነገሮች በፈለግነው መንገድ እንዳይሄዱ እያደረጉ ነው፤›› ብለዋል፡፡
እስካሁን ድረስም ድጋፍ የሰጧቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እንዳሉ ጠቁመው፣ የሚቀሩ ሥራዎች በመኖራቸውና ጊዜው በተራዘመ ቁጥር ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮች እየተፈጠረባቸው በመሆኑ መንግሥት አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ ‹‹ጉዳዩ ከአገሪቱ ፖሊሲ ጋር የሚጣጣምና ዘመናዊ ታክሲዎች ወደ አገሪቱ ሲገቡ የከተማዋን ገጽታ የሚቀይር በመሆኑ ዛሬ ነገ ሳይባል መፍትሔ ቢሰጠን ጥሩ ነው፤›› ሲሉ አቶ ወንደወሰን ገልጸዋል፡፡
የካዛንችስ ታክሲ ማኅበራት ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘለዓለም አዱኛ በበኩላቸው፣ ‹‹65 የታክሲ ማኅበራት ተደራጅተን ብዙ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን አንኳኩተን በጎ ምላሽ አግኝተን ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ለአንድ ዓመት ያህል መንግሥት ውሳኔ ባለመስጠቱ ቅሬታ ገብቶናል፤›› ብለዋል፡፡
ስልሳ አምስት የታክሲ ባለንብረቶች ማኅበራት የከተማውን የታክሲ አገልግሎት የጉዞ ርቀትን በሜትር በሚያነቡ፣ የሬዲዮ መገናኛና ጂፒኤስ በተገጠመላቸው አዲስ ሞዴል ተሽከርካሪዎች ለመተካት ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ፈቃድ መስጠቱን ከዚህ በፊት መዘገባችን ይታወሳል፡፡
የማኅበራቱን ጥያቄ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት በተጨማሪ የከተማዋ የትራንስፖርት ባለሥልጣን፣ የመንገድና ትራንስፖርት ቢሮ፣ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ይሁንታን ማግኘት እንደቻለም ሪፖርተር አረጋግጧል፡፡
የታክሲ ማኅበራቱ ተወካዮች፣ በአብዛኛው የሚመለከታቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ይሁንታና ፈቃድ ያገኙ ቢሆንም፣ የሚቀሩ ትንንሽ ሥራዎች ስላሉ መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡
የታክሲ ማኅበራቱ በአንድ ማኅበር በመጠቃለል ታክሲዎቹ ወደ አገር ውስጥ ከገቡ በኋላ ዘመናዊ የታክሲና የአምቡላንስ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ፣ ማኅበሩ የራሱ የነዳጅ ማደያ እንዲኖረውና አስተማማኝ ነዳጅ ማቅረብ፣ አሽከርካሪዎች በሥነ ምግባር የተሻሉ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራዎችን እያከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡