ከአፍሪካ አገሮች ለኮንፈረንስ፣ እንዲሁም ከአውሮፓና ከአሜሪካ ለጉብኝት ኢትዮጵያ ለሚመጡ ቪዛ በቦሌ ኤርፖርት የሚያገኙበት አሠራር መመቻቸቱን፣ የኢምግሬሽንና ዜግነት ጉዳዮች ዋና መምርያ አስታወቀ፡፡
የዋና መምርያው የዓለም አቀፍና ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ መኰንን አንጀሎ ዓርብ ኅዳር 8 ቀን 2010 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፣ የአፍሪካ አገሮች በኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ቪዛ ለማግኘት የሚወስድባቸውን ጊዜ ለመቀነስና እንዳይንገላቱ አዲሱ አሠራር ተመቻችቷል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ከአውሮፓና ከአሜሪካ ወደ አገሪቱ የሚመጡ ቱሪስቶችም በኦንላይን ቪዛ የሚያገኙበት ሥራ መጀመሩን የገለጹት ኃላፊው፣ ቱሪስቶች በድርጅቱ ድረ ገጽ ገብተው አጠቃላይ ዳታ በማግኘትና ፎርሙን ሞልተው ቪዛው ሲፈቀድ፣ ቦሌ ኤርፖርት ሲደርሱ መቀበል እንደሚችሉ አስርድተዋል፡፡
ለውጭ አገር ዜጎች ይሰጥ የነበረው የቪዛ ዕድሳት ከሁለት ቀናት ወደ 45 ደቂቃ ማውረድ መቻሉን፣ በውጭ ያሉ ቆንስላ ጽሕፈት ቤቶችም አገልግሎታቸውን ፈጣን እንዲሆን የሚያስችል አካሄድ መያዙንም አውስተዋል፡፡
በሌላ በኩል በሪፎርም ደረጃ እየተሠሩ ካሉት መካከል የፓስፖርት ዕደላ በፖስታ ቤት እንደተደረገው ሁሉ፣ ክፍያውን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎች ለማከናወን የሚያስችል እንቅስቃሴም በመካሄድ ላይ ነው፡፡
ከግንቦት 2009 ዓ.ም. ወዲህ የፓስፖርት ዕደላን በኮሚሽን እየሠራ ያለው የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሯ ወ/ሮ ዝይን ገድሉ፣ ድርጅቱ በገባው ውል መሠረት የዕደላውን ሥራ ለደንበኞች በፍጥነት ለማድረስ በሰው ኃይልና በቴክኖሎጂ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ የፓስፖርት ዕደላው በአዲስ አበባ በዋናው ፖስታ ቤት እየተከናወነ መሆኑን፣ በቀጣይ በአራት ኪሎ፣ በልደታ፣ በአራዳና በለገሐር ቅርንጫፎች አማካይነት ዕደላው ይካሄዳል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ፖስታ ቤት በስድስት ወራት ውስጥ ከ200 ሺሕ በላይ ፓስፖርት ማደሉን ገልጿል፡፡ በስድስት የክልል ከተሞች ጅማ፣ መቐለ፣ ድሬዳዋ፣ ደሴ፣ ሐዋሳና ባህር ዳርም አገልግሎቱን ለማስፋፋት እየተሠራ መሆኑን ዳይሬክተሯ ገልጸዋል፡፡
ሰሞኑን ፓስፖርት በፖስታ ቤት ሲጠባበቁ የነበሩ ደንበኞች በተፈጠረው መጨናነቅ ምክንያት መቸገራቸውን መናገራቸው ይታወሳል፡፡ ፖስታ ድርጅት ግን ችግሩ የተፈጠረው የኢምግሬሽንና የዜግነት ጉዳዮች ዋና መምርያ ለአንድ ሳምንት ፓስፖርት አዘጋጅቶ መላክ በማቆሙ ምክንያት እንደሆነ መግለጹ አይዘነጋም፡፡