ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የተፅዕኖ ግምገማ፣ የውኃ ሙሌትና አለቃቀቅ ጥናት ላይ ድርድር እያደረጉ ቢሆንም፣ ግብፅ የቅኝ ግዛት ዘመኑን እ.ኤ.አ. የ1959 ስምምነት ግድቡ ሊያመጣ ለሚችለው ጉዳት መነሻ እንዲሆን ያቀረበችው ጥያቄ በኢትዮጵያና በሱዳን ውድቅ ተደረገ፡፡
የህዳሴ ግድቡ በታችኞቹ የተፋሰስ አገሮች ላይ ስለሚኖረው ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና አካባቢያዊ ተፅዕኖ እንዲሁም የውኃውን ሙሌትና አለቃቀቅ ለማስጠናት በድርድር ላይ የሚገኙት ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ ባለፈው ሳምንት በካይሮ ለ17ኛ ጊዜ ተገናኝተው ቢመክሩም፣ ስምምነት ላይ አለመድረሳቸው ታውቋል፡፡
ሪፖርተር ሰሞኑን ከውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በህዳሴ ግድቡ ተፅዕኖ ግምገማ፣ የውኃ ሙሌትና አለቃቀቅ ላይ በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል ስምምነት ባለመደረሱ ግብፅ ከድርድሩ ራሷን ልታገል እንደምትችል ታውቋል፡፡ በካይሮ ለ17ኛ ጊዜ በሦስቱ አገሮች የውኃ ሚኒስትሮች መካከል የተካሄደው ድርድርም ያለ ስምምነት መጠናቀቁን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ሦስቱ አገሮች በጋራ የቀጠሩት ‹‹ቢአርኤል›› የተሰኘው የፈረንሣይ ድርጅት የሚሠራበትን መመርያ ለማዘጋጀት በተደጋጋሚ ጊዜ የሦስቱ አገሮች የአጥኚዎች ቡድንና የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች እየተገናኙ ቢመክሩም፣ በመመርያው ላይ የጋራ መግባባት እንዳልተፈጠረ ታውቋል፡፡ ሦስቱ አገሮች በአዲስ አበባ በቅርቡ አድርገውት በነበረው 16ኛው የሚኒስትሮች ስብሰባም ግብፅ መመርያው በመዘግየቱ ቅሬታ ማቅረቧን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
የዚህ አካል የሆነው 17ኛው የካይሮ የሚኒስትሮች ስብሰባ ላይም ግብፅ እ.ኤ.አ. በ1959 የነበራት የውኃ መብት እንዲጠበቅላትና የአጥኚ ቡድኑ የጥናት መመርያ ይህን ከግምት ያስገባ እንዲሆን ሐሳብ ማቅረቧ ታውቋል፡፡
የሦስቱ አገሮች የውኃ ሚኒስትሮች በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ተገናኝተው ቢነጋገሩም፣ ስምምነት ላይ ባለመድረሳቸው ድርድሩ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝና በግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ መካከል እንዲካሄድ መወሰኑ ታውቋል፡፡ የሦስቱ አገሮች መሪዎች በታኅሳስ ወር በካይሮ ተገናኝተው መመርያው ስለሚዘጋጅበትና ግድቡ በተፋሰስ አገሮች ላይ ስለሚያደርሰው ጉዳት እንደሚወያዩ፣ የሚኒስቴሩ የሥራ ኃላፊዎች ለሪፖርተር ጠቁመዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት የግብፅ ፕሬዚዳንት አልሲሲ ለግብፅ ሚዲያዎች በሰጡት መግለጫ፣ ‹‹የናይል ወንዝ ለግብፅ ሕዝብ የህልውና ጉዳይ ነው፤›› ብለዋል፡፡ የህዳሴ ግድቡ በታችኞቹ የተፋሰስ አገሮች ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት በተመለከተም፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመነጋገር ላይ መሆናቸውን ጠቁመው ነበር፡፡
የግብፅ የውኃ ጉዳይ ሚኒስትር መሐመድ አብደል አቲ (ዶ/ር)፣ የሱዳኑ የውኃ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ሙታዝ አብደላ ሳሊምና የኢትዮጵያ ውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) ጥቅምት 7 ቀን 2010 ዓ.ም. የህዳሴ ግድቡን መጎብኘታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ከጉብኝቱ በኋላ የግብፅ መንግሥት የግድቡ ግንባታ እየተጠናቀቀ በመሆኑ ከዚህ በኋላ ስለግድቡ ተፅዕኖ፣ አሞላልና አለቃቀቅ ድርድር ማድረግ ትርጉም የለውም የሚል አቋም እንደያዘ ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ምንጮች የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
በታኅሳስ ወር በመሪዎች ደረጃ በግብፅ ካይሮ የሚካሄደው ድርድርም በሁለቱ አገሮች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት በዘላቂነት ይፈታል የሚል እምነት እንዳላቸው የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ባለሙያዎች ገልጸዋል፡፡