አገርን ወደ ብጥብጥ ለመግፋት የሚደረጉ አሳዛኝ ጥረቶች በስፋት ይታያሉ፡፡ ከአገር ውስጥ እስከ ውጭ ድረስ የተሠለፉ ኃይሎች መነሻቸውም መድረሻቸውም የሕዝብ አጀንዳ ባለመሆኑ፣ አገሪቱን የማያባራ ቀውስ ውስጥ ለመክተት ይሯሯጣሉ፡፡ ለመንግሥት ሥልጣን ከሚደረገው ሽኩቻ ጀምሮ ብሔርተኝነትን በማራገብ፣ የሕዝብን ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ለመናድ የሚደረጉ ጥረቶች በአሳዛኝ ሁኔታ ቀጥለዋል፡፡ በገዥው ፓርቲ ውስጥ በድብቅ የሚካሄደው መጠላለፍና ንቁሪያ ራሱን የቻለ የቀውስ መንገድ ሲሆን፣ በሌላው ጎራ ደግሞ አገርን ለትርምስ የሚዳርግ ውሉ የጠፋ ሴራ ይጎነጎናል፡፡ በዚህ መሀል የሕዝብ ፍላጎት ወደ ጎን እየተገፋ ወደ ብጥብጥ የሚያመራ አጉል እንካ ሰላንቲያ አየሩን ይሞላዋል፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚደረገው ሰላማዊ ትግል ከፖለቲካ ምኅዳሩ ውስጥ ተገፍቶ ወጥቶ፣ የጥፋት አታሞ የሚደልቁ ኃላፊነት የጎደላቸው ኃይሎች ዘራፍ እያሉ ነው፡፡ ይህ አጥንት ድረስ ዘልቆ የሚሰማ ሥጋት በፍጥነት እንዲገታ ካልተደረገ፣ ማንም አሸናፊ የማይሆንበት ቀውስ ነው የሚፈጠረው፡፡
ማንም ዜጋ የመሰለውን በነፃነት የመጻፍና የመናገር መብቱ መከበር አለበት፡፡ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቹም ሳይሸራረፉ መከበር አለባቸው፡፡ የሕግ ጥበቃና ከለላም ሊያገኝ ይገባል፡፡ በገዛ አገሩ ባይተዋርነት ሳይሰማው በእኩልነት የመኖር መብቱ በተግባር መረጋገጥ አለበት፡፡ በዚህ መንገድ አገሪቱን ለችግር የዳረጉ ብሶቶች ረግበው መነጋገር ሲቻል፣ የሕዝብ ፍላጎቶች ገዥ ይሆናሉ፡፡ ከዚህ ቀደም የነበሩ አላስፈላጊ ጭቅጭቆች፣ የመብት ረገጣዎች፣ በቂምና በበቀል የተጀቦኑ ጥላቻዎችና ጨለምተኛ አስተሳሰቦች ወደ ቀናው ጎዳና ይመለሳሉ፡፡ በዚህ መሠረት ሁሉም ወገን አደብ ገዝቶ መነጋገር ወይም መደራደር ካልተቻለ ግን አገር ወደ ብጥብጥ ታመራለች፡፡ ሁሉም ጎራ ለይቶ የብጥብጡ ተዋናይ ሲሆን ደግሞ የሶሪያ ዓይነት ዕልቂትና ውድመት ይከተላል፡፡ አሸናፊም ተሸናፊም የሌለበት ውድመት፡፡ ይህንን መገንዘብ ያቃታቸው ወይም የፈለገው ይምጣ የሚሉ ኃይሎች ከእልህና ከግትርነት ካልተላቀቁ ጎዳናው የሚያሳየው ጥፋት ብቻ ነው፡፡
በተደጋጋሚ ለማለት እንደሞከርነው ሕዝብን አለማክበርና አለማዳመጥ መዘዙ የከፋ ነው፡፡ ይህ ኩሩና አስተዋይ ሕዝብ የሚፈልገው ሰላምና ዴሞክራሲ ነው፡፡ ይህ በማስተዋል የሚታወቅ ጀግና ሕዝብ በታሪኩ የሚያውቀው ጦርነትም ሆነ ግጭት ለድህነትና ለኋላቀርነት እንደዳረገው ከማንም በላይ ጠንቅቆ ይረዳል፡፡ ታሪኩ በግጭቶችና በጦርነቶች የተሞላ መሆኑን ስለሚገነዘብ፣ ለሰላምና መረጋጋት ትልቅ ግምት አለው፡፡ በእርስ በርስ ግንኙነቱም ችግሮችን የሚፈታባቸው በርካታ አኩሪ ሥርዓቶች አሉት፡፡ ይህንን የመሰለ ሰላማዊና አስተዋይ ሕዝብ በሚኖርባት አገር ውስጥ፣ ከራሳቸውና ከቡድናቸው ጥቅም በላይ የማይታያቸው ራስ ወዳዶች ግን በጭፍንነት ብሔርተኝነትን እያቀነቀኑ የጥፋት መልዕክቶች ያሠራጫሉ፡፡ ‹‹የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው›› በሚባለው የደካሞች አስተሳሰብ በመመራት፣ ከሥልጣንና ከሚያስገኘው ጥቅም በላይ ምንም አይታያቸውም፡፡ እርስ በርሱ ተከባብሮና ተፋቅሮ የሚኖር ጨዋ ሕዝብ ባቆያት አገር ውስጥ የብሔር ግጭት በመቀስቀስ አገሪቱን ቀውስ ውስጥ ለመክተት የሚዳክሩ እኩዮች ተፈልፍለዋል፡፡ እነዚህን በሕግ ማለት ይገባል፡፡ ከሕዝብና ከአገር በላይ ማንም የለም፡፡
ሥልጣን ላይ ያለው ገዥው ፓርቲም ሆነ ተቃዋሚዎች፣ እንዲሁም ሌላ አጀንዳ የተሸከሙም ጭምር ማመን የሚገባቸው የአገሩ ባለቤት ሕዝብ መሆኑን ነው፡፡ የአገሪቱ የሥልጣን የመጨረሻው ሉዓላዊ ባለቤት ሕዝብ እንደሆነ ሳያንገራግሩ መቀበል አለባቸው፡፡ ሥልጣን ላይ ያለው ከመንበሩ ላለመገፋት ሲል ብቻ በለመደው መንገድ መቀጠል እንደማይችል ማመን አለበት፡፡ ሥልጣኑ በሕግ ተገርቶ ለሰላማዊና ለዴሞክራሲያዊ ሒደት መገዛት እንዳለበት ማመን አለበት፡፡ የኃይል ተግባር ፋይዳ የለውም፡፡ ብልሽትሽቱ የወጣው የፖለቲካ ምኅዳር በቶሎ ተስተካክሎ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚገባበትን መደላድል በቶሎ ማዘጋጀት አለበት፡፡ ያኔ ምርጫ ፍትሐዊ፣ ነፃና ዴሞክራሲያዊ የሚሆንበት አዲስ ጎዳና ይዘረጋል፡፡ የሥልጣኑ ባለቤት የሆነው ሕዝብ በነፃነት ያሻውን የሚመርጥበት ዓውድ ይመቻቻል፡፡ እኔ ከሌለሁ ወይም ካልተቆጣጠርኩ ማለት ተረት ይሆናል፡፡ በተቀውሞ ጎራም ያለው ያንን የመነቸከና ጊዜ ያለበፈት የትግል ሥልት አስወግዶ ለሕጋዊ፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ጉዞ ራሱን ብቁና ንቁ ለማድረግ ይዘጋጅ፡፡ ከዘመኑ አስተሳሰብ ጋር እኩል በመራመድ የሕዝብን ቀልብ የሚያማልል አጀንዳ ለመቅረፅ ብቃቱን ያረጋግጥ፡፡ በኢትዮጵያ ምድር የመንግሥት ሥልጣን የሚያዘው በሕጋዊ መንገድ ብቻ እንዲሆን ራሱን አሳምኖ ለተግባራዊነቱ ይበርታ፡፡ በስመ ተቃዋሚነት በተለመደው የስህተት አረንቋ ውስጥ መዘፈቅ ይብቃ፡፡ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እልህ አስጨራሽ እንደ መሆኑ መጠን፣ ለብልኃትና ለትዕግሥት ትኩረት ይስጥ፡፡ ከሕገወጥ ተግባራት ራሱን ያርቅ፡፡ ይህ ተግባራዊ ሲደረግ ጉዞው ወደ ብጥብጥ ሳይሆን ወደ ዴሞክራሲ ይሆናል፡፡
የተለየ አጀንዳ አለን የሚሉ ወገኖች ካሉ ደግሞ መጀመርያ የሕዝብን ፍላጎት፣ ቀጥሎ ደግሞ ዘመኑ የደረሰበትን የዕድገትና የሥልጣኔ ደረጃ ቢያጤኑ መልካም ነው፡፡ ኢትዮጵያውያንን በመከፋፈል ሥልጣን ላይ ለመውጣት የሚደረገው ሙከራ ትርፍ አይገኝበትም፡፡ ሃይማኖትን፣ ብሔርንና የመሳሰሉ ልዩነቶችን በማራገብ ኅብረ ብሔራዊውን አንድነት ለመናድ መሞከር ከጠላት ተላላኪነት ተለይቶ አይታይም፡፡ ኢትዮጵያ የአማራው፣ የትግሬው፣ የኦሮሞው፣ የደቡብ ሕዝቦች፣ የአፋሩ፣ የሶማሌው፣ የጋምቤላው፣ የቤኒሻንጉሉ፣ የሐረሪው፣ ወዘተ. አንጡራ ሀብት ናት፡፡ የመላው ኢትዮጵያውያን እናት ናት፡፡ አስተዋዩና ኩሩው ሕዝብ ደግሞ በክፉም በደጉም ጊዜ ተደጋግፎና ተጎዳኝቶ የኖረው በዚህ ተምሳሌታዊ እሳቤ ነው፡፡ ይህንን ጥልቅና ወሰን የሌለው መስተጋብር በመሸርሸር አገርን መቀመቅ ለመክተት መሞከር ሰይጣናዊ ድርጊት ነው፡፡ የብሔር ስም እየጠሩ በመሳደብና በማንቋሸሽ ግጭት ለመፍጠር የሚደረገው ደግሞ የጠላት ሴራ ውጤት ነው፡፡ ይህንን ዓይነቱን ከንቱ ፕሮፓጋንዳ ለወጣቱ በመጋት በየቦታው ግጭት ለመቀስቀሻ መጠቀም መወገዝ አለበት፡፡ በግለሰቦች መካከል የተነሳ ጠብን ወደ ብሔር እየገፉ አገርን ለማተራመስ የሚደረገው ጥረት መክሸፍ አለበት፡፡ አሸናፊም ተሸናፊም አይኖርበትም፡፡ አገር ከማጥፋት በስተቀር፡፡
እያወቁም ሆነ ሳያውቁ አገርን ለማውደም የተነሱ ወገኖችን ማስቆም በፍፁም የማያልፉት የኢትዮጵያውያን የጋራ ኃላፊነት ነው፡፡ ‹‹ብልህ ከሌሎች ጥፋት ሲማር ሞኝ ግን ከራሱም ጥፋት አይማርም›› እንዲሉ፣ ከሶማሊያ ጀምሮ እስከ መካከለኛው ምሥራቅ ድረስ የታዩ ውድመቶችን እዚህ መድገም በታሪክም በትውልድም ያስጠይቃል፡፡ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ብልፅግና የሚመጡት ኢትዮጵያውያን የጋራ መግባባት ሲኖራቸው ነው፡፡ በአንድ ወገን የበላይነት ብቻ አገር መተዳደር የለበትም፡፡ ኢትዮጵያውያን በነፃና በሰላማዊ ምርጫ በፈለጉት ፓርቲ እንዲተዳደሩ ለሕግ መገዛት ተገቢ ነው፡፡ ሰላማዊውና ዴሞክራሲያዊው ጎዳና በስፋት እንዲከፈት ደግሞ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በሙሉ በቅንነት መሥራት አለባቸው፡፡ በጉልበት የሚሆን እንደሌለ ሁሉ፣ በአሻጥርም የትም መድረስ አይቻልም፡፡ ይህችን የተከበረች ጥንታዊና ታሪካዊ አገር በከንቱ ድርጊቶች ለማጥፋት የሚፈልጉ ወገኖች ወደ ቀልባቸው ይመለሱ፡፡ የግልና የቡድን ጥቅም አገርን አይወክልም፡፡ ሥልጣን ላይ ብቻ ሙጭጭ ማለት ለአገር አይጠቅምም፡፡ ሥልጣን በአቋራጭ ለማግኘት ሲባል አገርን ማበጣበጥም ፋይዳ የለውም፡፡ የሚበጀው ቀናውን ጎዳና መያዝ ብቻ ነው፡፡ እሱም ለሰላም፣ ለዴሞክራሲ፣ ለማኅበራዊ ፍትሕና ለብልፅግና የሚያበቃ ነው፡፡ በሕግ የበላይነት ሥር የሚተዳደር ሥርዓት ለመገንባት ፍቱን መፍኃኒት ነው፡፡ ከዚያ ውጪ አገርን ወደ ብጥብጥ መውሰድ አሸናፊም ተሸናፊም የማይኖርበት ውድመት ነው!