Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ይድረስ ለሪፖርተርነፃ አውጪዎቻችን ነፃ አውጪ ያስፈልጋቸዋል

ነፃ አውጪዎቻችን ነፃ አውጪ ያስፈልጋቸዋል

ቀን:

አሁን ኢትዮጵያ አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ናት፡፡ ብዙ ነፃ አውጪዎች  እያመሷት ነው፡፡ እስራኤላውያንን ከግብፅ መከራ ለማውጣት አንዱ ሙሴ በቂ ነበር፡፡ ሙሴ ደፋ ቀና ያለው የአገሩን ሰዎች ከሰቆቃ ለማውጣት ነው፡፡

የዘመኔ ሙሴዎች ደፋ ቀና የሚሉት ግን ኢትዮጵያን ሳይሆን፣ ቋንቋቸውን ወይም ብሔራቸውን ነፃ ለማውጣት ነው፡፡ የዘመኔ ሙሴዎች ከሕዝቡ ጋር የማይኖሩ፣ በሕዝብ ውስጥ የሌሉና መስዋትነት የማይከፍሉ ናቸው፡፡ የዘመኔ ሙሴዎች አንዱን በወረቀት (በፓስፖርት) አንዱን በፈጣሪ ስጦታ ያገኙት ሁለት አገር ያላቸው ናቸው፡፡ በወረቀት ባገኙት አገር እየኖሩ በፈጣሪ የተቸረችዋን እመት አገር ኢትዮጵያን  እንደሰንበት መክፈልት ለመቆራረስ የተዘጋጁ ናቸው፡፡ የዘመኔ ሙሴዎች (ነፃ አውጪዎች) የብሔራቸውን እንጂ የኢትዮጵያን ስም በአግባቡ መጥራት የማይችሉ ናቸው፡፡ የዘመኔ ሙሴዎች የብሔርና የቋንቋቸው ነፃነት ዕውን የሚሆነው በፈራረሰች ኢትዮጵያ ላይ እንደሆነ የሚያምኑ ናቸው፡፡

  በቅርቡ አንድ የማደንቀው አርቲስት ወደ አሜሪካ  ኮበለለና  ‹‹አገሬ ውስጥ ያለው ሰቆቃ ስለሚያሳስበኝ ሰቆቃው እስኪቆም ወደ አገሬ አልመለስም፤›› አለ፡፡  ከአክቲቪስቶች ጋር ፎቶ ሲነሳ ታየ፡፡ ከጥቂት ወራት በኋላ በዚያው አገር ምን የመሰለ ቁርጥ ቤት ከፈተ ተባለ፡፡ የዘመኔ ሙሴዎች እንዲህ ያሉት ናቸው፡፡ አጋጣሚውን ተጠቅመው ወደ ዛሬዋ ከነዓን (አሜሪካ) ለመፈርጠጥ እንጂ ከፈጣሪ ጋር ስለሚማልዱ፣ የእናት ኢትዮጵያን ትንሳዔ ስለሚሹ አይደለም፡፡

- Advertisement -

    ኢሕአዴግ ከአምባገነናዊ መንግሥት ደርግ ሥልጣን ለመቀማት ጫካ ገብቶ ገድሏል ሞቷል፡፡ ይሁን እንጂ አምባገነናዊ መንግሥት ከመሆን እንዳልወጣ ግን የሚታዩበት ምልክቶች ያረጋግጣሉ፡፡ አክቲቪስቶቹም ከኢሕአዴግ ሥልጣን ለመቀማት አሜሪካ ገብተው ብዙ ሊያጋድሉ ይችላሉ፡፡ እየሞቱ ግን አይደለም፡፡ እነኚህ ናቸው የዘመኔ ሙሴዎች፡፡ እነኚህ ናቸው የዘመኔ ነፃ አውጪዎች፡፡ እመት ኢትዮጵያን የሚያሳምሙ እንጂ ሕመሟን የማይጋሩ ሙሴዎች፡፡

  የኤርትራ መገንጠል ከብዙ ጊዜ ጀምሮ ሲንከባለል የመጣ ቢሆንም፣ በተግባር ዕውን ሁኖ የተቋጨው ግን በነፃ አውጪ ተብዬዎች ነው፡፡ ዛሬም ቁጥራቸውና ሴራቸው የበዛ ነፃ አውጪዎች ለኢትዮጵያ በእጅጉ ያሰጓታል፡፡ ከብዙ ገልቱ ኃላፊዎች መካከል አንዱ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ኮሚቴ በጣም ስለበዛ ይኼን ኮሚቴ የሚያስወግድ አንድ ኮሚቴ እናቋቁም›› እንዳለው እንደ አሸን የፈሉትን ነፃ አውጪዎች ለመቀነስ ሌላ ነፃ  አውጪ ማቋቋም ስህተትን ማብዛት እንጂ ሌላ አይሆንም፡፡

 ፌስቡክ መንግሥታትን ለመገልበጥ እንዳበቃ ከአንዳንድ አገሮች ታሪክ ሰምተናል፡፡ ይህ ግን ስንት ገንዘብ የሚታለብበትን የቴሌኮም ኢንዱስትሪ ለሌላ አሳልፎ መስጠት እንደ እብደት ኢሕአዴት በሚያስብበት፣ ኢንተርኔት ጭምር ተጠርንቆ በተያዘበት አገር ውስጥ ግን እንዲህ ያለው የመንግሥት ለውጥ በፌስቡክ እገዛ ዕውን ይሆናል ማለት ከእውነትነቱ ይልቅ ተረትነቱ ያደላል፡፡ ጫጫታው ሲበረታ እንዳሻው የሚዘጋ ኢንተርኔት ተይዞ፣ በአንድ ኮምፒውተርና በወረቀት በተገኘ ሁለተኛ አገር ውስጥ ቁጭ ብሎ አክቲቪስት ነኝ እያሉ ለመዋጋት መፍጨርጨር በኢሕአዴግ መልካም ፈቃድና በኢንተርኔት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ያለአግባብ ለሚፈሰው የሰው ደም ኢሕአዴግን እና አክቲቪስት ተብዬዎችን ጊዜ ይጠይቃቸዋል፡፡

እኔም እላለሁ፡- ‹‹ፈጣሪ ሆይ! ነፃ ካልወጡ ነፃ አውጪዎች በትር ኢትዮጵያን ጠብቃት አደራ!!›› ቸር እንሰንብት!!

            (ብርሃኑ በቀለ፤ ከአዲስ አበባ)

                       *******

ለእግር ኳሳችን ትንሳዔ ምን እናድርግ?

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን በመመሥረት ቀደምት ከሆኑት አገሮች ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗ ይታወቃል፡፡

የአፍሪካ አገሮች ነፃነታቸው ከማግኘታቸው በፊት፣ ኢትዮጵያ ወደ አውሮፓ በመጓዝ የወዳጅነት ውድድሮችን ስለማካሄዷ የታሪክ ድርሳናት ይተርካሉ፡፡ እንደውም በ1950ዎች አጋማሽ የአፍሪካ ብራዚል እስከመባል የደረሰችበት ወቅት ነበር፡፡

ትናንት በወርቃማው ዘመን የነበረንን የእግር ኳስ ታሪካችን ዛሬ ላይ ሆነን ስንመለከተው፣ ውድቀታችን ምን ያህል የከፋ እንደሆነ መገንዘብ አይከብድም፡፡

የቀድሞዎቹ እግር ኳስ ተጫዋቾች የረባ ክፍያ ሳይሰጣቸው ክለባቸውንና አገራቸውን በመወከል ያሳዩንን ድንቅ ጨዋታ ባጣጣምነበት ስሜትና ዓይን የዛሬዎቹ ተጫዋቾች በአካል ብቃት፣ በሥነ ልቦና፣ በፍላጎትና በሥነ ምግባር ደካማ ሆነው ሲታዩ ምን እንደነካን ለመቀበል ይከብዳል፡፡ ከፍተኛ ደመወዝ ያውም በአብዛኛው ከመንግሥት ካዝና ሲከፈላቸው ማየት፣ ለመናገርም ለመቀበልም የሚከብድ ነው፡፡

በዓለም ዙሪያ ለእግር ኳስ ተጫዋቾች የሚከፈለው ደመወዝ ከተለያዩ የገቢ ምንጮች ማለትም ከሜዳ ገቢ፣ ከቴሌቪዥን ሥርጭት መብት፣ ከስፖንሰርሺፕ፣ ከአባላት መዋጮና ከመሳሰሉት በማሰባሰብ ከሚያገኝ ገንዘብ ነው፡፡ ክለቦቹ ወጪያቸውን ከገቢያቸው ጋር በማጣጣም ጤናማ የፋይናንስ ሥርዓት ዘርግተው ክለቦቻቸውን ያስተዳድራሉ፡፡

ወደ እኛ አገር ስንመጣ ግን ብዙ አስተዋጽኦ ለሚያደርገው የጤና ሐኪም ከ10,000 ብር በታች እየተከፈለው ሕሙማንን ሲያክም ሲረዳ ይውላል፡፡ በተቃራኒው አንገት ለሚያስደፋ እግር ኳሳችን ያውም ለፊርማ የሚከፈለውን ገንዘብ ሳያካትት ከመቶ ሺሕ ብር በላይ ወርሃዊ ደመወዝ ለተጫዋቾች መከፈሉ፣ አንድም የክለቦቻችን መሪዎች የአገሪቱን ኢኮኖሚ አለያም የእግር ኳሱን ደረጃ የማይገነዘቡ ናቸው ቢባል ግነት አይደለም፡፡

ይህ ሁኔታ በዚህ አካሄድ መቀጠል እንደሌለበት በማመን፣ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ክለቦች ቆም ብለው እንዲያስቡና አማራጮችን እንዲፈልጉ ይመክራል፡፡

ምን መደረግ ከተባለም የሚከተሉትን ነጥቦች በመትሔነት መመልከት ይቻላል፡-

  1. እያንዳንዱ ክልል የራሱ የእግር ኳስ አካዴሚ እንዲኖረው ማድረግ (ትልልቅ የአዲስ አበባም ሆኑ የክልል ክለቦች የራሳቸውን አካዴሚ ሊገነቡ ይችላሉ)፡፡
  2. ክልሎች በየዞናቸው ዕድሜያቸው ከ10 እስከ 12 እንዲሁም ከ13 እስከ 15 ዓመት ዕድሜ የሆናቸውን ታዳጊዎች በመመልመል ዓመታዊ ውድድር ማካሔድ ይችላሉ፡፡
  3. በዓመቱ መጨረሻ እንደየዕድሜያቸው ደረጃ በክህሎታቸውና ችሎታቸው መርጦ በየአካባቢው በተገነቡት አካዴሚዎች ቢያንስ ለአንድ ዓመት አለያም ለሁለት ዓመት ሥልጠና እንዲከታተሉ ማድረግ፡፡
  4. ከዚህ ሥልጠናና ውድድር በኋላም በአገር አቀፍ ደረጃ የክልሎች ውድድር በማካሔድ ጥሩ ችሎታ ያላቸውን ወጣቶች መርጦ (ከ30  እስከ 40 የሚደርሱ) ወደ አዲስ አበባ ወጣቶች አካዴሚ በመላክ በልዩ ትኩረት በብቁ አሠልጣኞች የታገዘ አሠለጣጠን በመስጠት ለብሔራዊ ቡድን የሚመጥኑ ተጫዋቾችን ማፍራት ይገባል፡፡
  5. በሥልጠናው ወቅት በችሎታቸውና በክህሎታቸው ልዩ የሚባሉ ተጫዋቾች ሲገኙም፣ የስፖርቱ ኃላፊዎች ከወዳጅ አገሮች ጋር ግንኙነት በመፍጠር ከፍተኛ ሥልጠና በውጭ የሚያገኙበትን መንገድ ማመቻቸት ይገባል፡፡ ሲያስፈልግም ሥልጠና በሚወስዱበት አገር በሚገኙ ክለቦች መጫወት እንዲችሉ ቢደረግ፣ ለወደፊቱ በአገር አቀፍ ደረጃ ለምንሳተፍባቸው ውድድሮች አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች በጠቅላላው ከ1.5 ቢሊዮን ብር በላይ በየዓመቱ ወጪ እንደሚያደርጉ ይገመታል፡፡ ይህን ያህል ገንዘብ ወጥቶም ያስገኘው ፋይዳ ስለሌለ የተጫዋቾችን ደመወዝ ዝቅ ማድረግና ክልሎች ትልቁን ወጪያቸውን ለአካዴሚው ግንባታና ለወጣት ሠልጣኞች ቢያውሉት ፍሬያማ ይሆናሉ፡፡ ምናልባት ተጫዋቾቹ የሚቀነስባቸውን ደመወዝ ላይቀበሉት ይችላሉ፡፡ ሆኖም የአገሪቱን ውድድር በብሔራዊ ሊግ ተጫዋቾች ማስኬድና በአካዴሚ የሚሠለጥኑትን ተጫዋቾች ፍሬ መጠበቁ የተሻለ ነው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ግን አሁን ከፍተኛ ደመወዝ የሚከፈላቸው ተጫዋቾች ባስገኙት ውጤት ልክ እንዲከፈላቸው ማደረጉም ሌላ አማራጭ ነው፡፡ በስምምነት ከፍተኛ ውጤት ሲያመጡ ጠቀም ያለ ክፍያ እንዲያገኙ ማድረጉ ይበጃል፡፡

በመጨረሻም መንግሥት ከስፖርቱ ባለድርሻዎች ጋር በመተባበር እግር ኳስ ያቆሙ ተጫዋቾችን መርጦ በማካተትና ተጨማሪ የእግር ኳስ ሥልጠና በውጭም በአገር ውስጥም በመስጠት ወደ ክልሎች እንዲመደቡ ቢደረግ ጥሩ ውጤት ሊገኝ ይችላል በማለት እንደሆነ አስተያየቴን አቀርባለሁ፡፡

(ጌታቸው ላቀው፣ ከአዳማ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...