Saturday, April 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉአገራችን ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በሰላም እንድትሸጋገር ለማድረግ የቀረበ የመነሻ ሐሳብ

አገራችን ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በሰላም እንድትሸጋገር ለማድረግ የቀረበ የመነሻ ሐሳብ

ቀን:

በግርማ ሠይፉ ማሩ

ኢትዮጵያ አገራችን አሁን የምትገኘው የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በሕገ መንግሥቱ በተቀመጠው መሠረት የማይከበሩበት፣ ይህን ለማድረግ የሚያስችል የፖለቲካ ሥርዓት መፍጠር የሚጠበቅባቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች በፍፁም መንቀሳቀስ ያልቻሉበትና የአንድ ፓርቲ ፍፁም አምባገነን ኢዴሞክራሲያዊ አገዛዝ በሠፈነበት ሁኔታ ነው፡፡ አሁን በአገራችን የሚታዩት ዘርፈ ብዙ ችግሮች በምንም መመዘኛ ኢሕአዴግ እንደሚለው በኢሕአዴግ መስመር ብቻ የሚፈቱ አይደሉም፡፡ ስለእውነት ለመናገርም በኢሕአዴግ አገዛዝ ብቻ የተፈጠሩም አይደሉም፡፡ ስለዚህ ሁሉንም ባለድርሻ፣ ተሳታፊና ባለቤት ሊያደርግ የሚችል ሁሉን አቀፍ መፍትሔ መፈለግ ወቅቱ የሚጠይቀው ወሳኝ ጉዳይ ሆኖ ከፊታችን ቀርቧል፡፡

ችግር መኖሩን ተገንዝበው እጅግ ብዙ ባለሙያዎችና ያገባናል የሚሉ ዜጎች በተደጋጋሚ አስተያየት ሲሰጡ የነበረ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት ያለንበትን ሁኔታ በግልጽ የተገነዘቡ የተለያዩ አካላት፣ ቀደም ሲል የሕወሓት ታጋዮች የነበሩና ሥርዓቱን ሲያገለግሉ የነበሩ ሰዎችን ጨምሮ ችግሩ መኖሩንና ለውጥ እንደሚያስፈልግ ምክር እየለገሱ ሲሆን፣ ችግር መኖሩን መንግሥትም ቢሆን የካደው ጉዳይ አይደለም፡፡ መንግሥት ችግሩን አምኖም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ መገደዱ ይታወሳል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከተነሳም በኋላም ሁኔታዎች መሻሻል አለማሳየታቸው ብቻ ሳይሆን፣ መንግሥት ችግሮቹን በኢሕአዴግ መስመር እፈታቸዋለሁ ከሚለው አቋሙ ፈቀቅ ማለቱን የሚያሳይ ፍንጭ ያለመታየቱ፣ ጉዳዩን በማባባስ ሌሎች ኃይሎችም ማንኛውንም አማራጭ ተጠቅመው ለውጥ ለማምጣት መወሰናቸውና ሕዝቡ በይፋ ‹‹በቃ›› ብሎ አደባባይ መውጣቱን መቀጠሉ ነው፣ የምንወዳት አገራችን በጥፋት ጎዳና ላይ እንደሆነች እንዲሰማን እያደረገ ያለ ያፈጠጠ ሀቅ ነው፡፡

የዚህ ምክረ ሐሳብ ዓላማም መንግሥት ለዚህ ውስብስብ ችግር በተናጠል መፍትሔ ለማምጣት የማይችል መሆኑን በመገንዘብ፣ አቋሙን እንዲያለሳልስ በመጠየቅ በመፍትሔ ፍለጋው ላይ ሌሎች ኃይሎችም እንዲሳተፉበት ለማድረግ ፖለቲካዊ ዕርምጃ እንዲወስድ ሲሆን፣ ሌሎች ተሳታፊ ኃይሎችም በተመሳሳይ አቋማቸውን እንዲያለዝቡና ወደ አማካይ መስመር እንዲመጡ ለማድረግ መንገዱ ተቀራርቦ መወያየት መሆኑን ለማሳየት ነው፡፡ ሕዝቡም አሁን የጀመረውን የመብት ጥያቄ መስመር ወደ ከፋ ብጥብጥና ቀውስ ሳያድግ፣ የሚፈልገውን ለውጥ በዴሞክራሲያዊ መስመር ማሳካት የሚችልበትን ምቹ ሁኔታ የሚፈጠርበት ሁኔታ መኖሩን በማመን ወደ መደበኛ ተግባሩ እንዲያተኩር ለማስቻል ነው፡፡ 

በአገራችን ኢትዮጵያ በዋነኝነት በፖለቲካ መድረክ ተሳትፎ አለን የምንል በግራም ሆነ በቀኝ መታዘብ የሚቻለው ሀቅ፣ ቀደም ሲል በተከናወኑ ለታሪክ መተው ባለባቸው ኩነቶች ላይ ስንነታረክና በአንድ ወይም በሌላ አጋጣሚ አባል የሆንበትን ቡድን በመከላከልና ሌላውን ጥፋተኛ በማድረግ (Self Defensing and Blaming Others) ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ይህ አካሄድ ከአርባ ዓመታት በላይ አብሮን በመኖሩ ተፈጥሮዓዊ እስኪመስለን ድረስ ተዋህዶን ለልጆቻችን እያስተላለፍን እንገኛለን፡፡ ከዚህ አዙሪት ለመውጣት የሚያስችል የመፍትሔ ሐሳቦች በተለያዩ አካላትና ግለሰቦች ቀርበዋል፡፡ ነገር ግን ሰሚ አግኝቶ ወደ ተግባር መግባት አልተቻለም፡፡ አሁንም ለዚህ የመፍትሔ ሐሳብ ትኩረት ሰጥቶ ወደ ተግባር መሸጋገር ከፊታችን የተደቀነ ወሳኝ የወቅቱ ፈተና ነው፡፡ ኳሱ በገዥው ፓርቲ ሜዳ ቢሆንም፣ ሌሎችም ትኩረት ሰጥተው መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል፡፡

አሁን በአገራችን ያለው ነባራዊ ሁኔታ በአጠቃላይ ሲታይ ገዥው ፓርቲና መንግሥት ዜጎች የሚፈልጉትን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ጥያቄዎች በአግባቡና በተገቢው መንገድ ለመመለስ ያለመቻላቸውን በግልጽ የሚያመላክት ነው፡፡ የዜጎች ሁለገብ ጥያቄዎች በተበራከቱበትና መንግሥት ጥያቄዎቹን መመለስ ባልቻለበት ሁኔታ በተደረገ ‹‹ምርጫ››፣ ገዥው ፓርቲ መቶ በመቶ ምርጫ አሸንፌያለሁ ብሎ ሥልጣን ላይ ለመቆየት በወሰነበት የመጀመርያ ዓመት ጀምሮ በመላው አገሪቱ ከፍተኛ ሕዝባዊ ንቅናቄዎች ተፈጥረው ለብዙ ዜጎች በአሳዛኝ ሁኔታ ሕይወት መጥፋት ምክንያት የሆኑ ሲሆን፣ እጅግ በርካታ ንብረቶችም ወድመዋል፡፡ ይህ ሁኔታ በዚሁ እንዲቀጥል ከተተወ አገሪቱ ልትወጣው ወደማትችለው የቀውስ አዙሪት ውስጥ ልትገባ እንደምትችል የብዙዎች እምነት ነው፡፡

አሁን በአገራችን ያለውን ችግር ለመፍታት ዋነኛውና ወሳኝ ጉዳይ ሁሉም ያገባኛል ባይ፣ ‹‹የእኔ መንገድ ብቻ ነው ልክ›› ከሚል ግትር አስተሳሰብ ወጥቶ ለውይይት ራሱን በማዘጋጀት፣ ‹‹በሰጥቶ መቀበል›› ሥልጡን ፖለቲካ አካሄድ መፍትሔ እንደሚገኝ በማመን በሒደቱ ውስጥ ለመሳተፍ ሲወስን ነው፡፡ ሁሉም አሸናፊ ሆኖ የሚወጣበት መንገድ ለመፈለግ ተነሳሽነት መውሰድ የግድ የሚልበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ መንግሥት ከፓርቲዎች ጋር እየተወያየሁ ነው በሚል የተለመደውን በድርድር ስም በሕዝብና በአገር ላይ የሚደረግ ቀልድ መቆም እንዳለበት፣ በዚሁ አጋጣሚ አበክሮ መጠቆም አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡ በአገራችን ያለው ችግር የምርጫ ሥርዓት ሳይሆን የፖለቲካ ምኅዳሩ ሆን ተብሎ ለአንድ ገዥ ቡድን መተው ነው፡፡

ይህ ጽሑፍ ሁሉም አሸናፊ ይሁን ከሚል መንፈስና ማንም ተንበርካኪ ሆኖ በተሸናፊነት ስሜት የሚቀርብበት መሆን ስለሌለበት፣ የአገሬ ጉዳይ ያገባኛል በሚል መነሻ የተዘጋጀ ነው፡፡ ይህ ሐሳብ መድረሻው ቢዘገይ በቀጣይ 2012 ዓ.ም. በሚደረግ ምርጫ ኢሕአዴግን ጨምሮ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በነፃ በሚያደርጉት ውድድር፣ ተጠያቂነት ያለበት መንግሥት እንዲመሠረት የሚያስችል ጥርጊያ መንገድ መክፈት ነው፡፡ ይህን ለማድረግ መንግሥት የሚጠበቅበት አሁን ከያዘው ብቻዬን መልስ እሰጣለሁ ማለቱን ማቆም ሲሆን፣ ሌሎች ተፎካካሪዎችም እኛ ከምንለው ውጪ ከሚል ግትር አቋም ራሳቸውን መግራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህን የመፍትሔ ሐሳብ ተግባራዊ ለማድረግ መነሻ የስምምነት ነጥቦች (Point of References or Pillars) የሚከተሉት ቢሆኑ፣ ከተለመደው የቀድሞውን አጥፍቶ ከዜሮ ከመጀመር የዜሮ ድምር አስተሳሰብ የሚታደግ ይሆናል፡፡ ሰጥቶ የመቀበል አስተሳሰብም በተግባር እነዚህን ነጥቦች ከመቀበል ይጀምራል፡፡

 1. አሁን ተግባራዊ እንዲሆን የሚታሰበው የፖለቲካ ምኅዳር ማስፋት እንቅስቃሴ (Political Reform) ሕገ መንግሥቱን መሠረት አድርጎ ሲሆን፣ ሕገ መንግሥቱ እንደ አስፈላጊነቱ በሕዝብ ይሁንታ ሊሻሻሉ የሚችሉ ጉዳዮች እንዳሉት ከግንዛቤ በማስገባት ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ እንዲሻሻል ፍላጎት ያላቸው ኃይሎች አማራጫቸውን በሚፈጠረው ነፃ የፖለቲካ ምዕዳር ማቅረብ ይችላሉ፡፡
 2. ነፃ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ (በሁሉም ተወዳዳሪዎች በቂ ዝግጅት ለማድረግ የሚሰጠው ጊዜ እንደተጠበቀ ሆኖ ቀኑ በሒደት የሚወሰን ይሆናል፡፡ ነገር ግን ከግንቦት 2012 ዓ.ም. ሊያልፍ አይችልም) ተደርጎ መንግሥት እስኪመሠረት ድረስ፣ ኢሕአዴግና አጋር ፓርቲዎች የመንግሥትን የዕለት ከዕለት ተግባራትን በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜትና ተጠያቂነት እንዲወጡ መፍቀድ፡፡ ወሳኝ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ምንም ዓይነት ውሳኔ ከመስጠት እንዲታቀቡ ማድረግ፡፡
 3. የፓርቲና የመንግሥት ሥራ በግልጽ ተለይተው ይከናወናሉ፡፡ ኢሕአዴግ እንደ ማንኛውም ፓርቲ በሒደቱ ውስጥ ተሳትፎ ያደርጋል፡፡ የመንግሥት ኃላፊዎች ያለባቸውን የመንግሥትና የፓርቲ ኃላፊነት በሚመጥን ደረጃ እንዲንቀሳቀሱ ክትትልና ቁጥጥር ይደረጋል፡፡ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የተደራጁ የፓርቲ መዋቅሮች በሙሉ ይፈርሳሉ፡፡ ወደ ፓርቲያቸው መዋቅር ፓርቲው በሚያዘጋጀው መስመር ይጠቃለላሉ፡፡
 4. የመከላከያ፣ የፖሊስ ሠራዊትና የደኅንነት መሥሪያ ቤቶች ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌላቸው መሆኑ ተረጋግጦ፣ ማንኛውም አሸናፊ ፓርቲ ለሚመሠርተው መንግሥት በሚሰጠው መመርያ መሠረት ሕዝብን ማገልገል በሚችል መልኩ ተከታታይ ሥልጠናና የመዋቅር ማሻሻያ ይደረጋል፡፡ በሁሉም ጊዜ የአገርን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ በሚያስችለው ቁመና ላይ እንዲሆን ይደረጋል፡፡ የፖለቲካ ተሳትፎ ፍላጎት ያላቸው የሠራዊት አባላት በፈቃዳቸው ከሥራቸው መልቀቅና በፖለቲካ ቀጥታ መሳተፍ ይችላሉ፡፡
 5. ልዩ ሁኔታ ካልተፈጠረ በስተቀር በአገር ውስጥ የሚከናወኑ የፀጥታ ሥራዎች በሙሉ በፌዴራልና ክልል ፖሊሶች ብቻ ይከናወናሉ፡፡ በአገሪቱ ልዩ ኃይል የሚባል አደረጃጀት በሙሉ ወደ ፖሊስና መከላከያ ይጠቃለላል፡፡
 6. የፍትሕ ሥርዓቱ ከማንኛውም የሥራ አስፈጻሚ ተፅዕኖ ነፃ ሆኖ እንዲሠራ ይጠበቅበታል፡፡ ይህን ለማድረግ የሚያስችል የአቅም ግንባታና ድጋፍ በተከታታይ ይሰጣል፡፡

ከዚህ በላይ የተቀመጡት ሐሳቦች በዋነኝነት የመንግሥት ሥልጣን የሚያዘው በሕዝብ ይሁንታ መሆኑን ለማረጋገጥ፣ እየቀረበ ያለው ጥያቄ ሥልጣን በአቋራጭ የማግኘት ያለመሆኑን፣ መንግሥትን ከፖለቲካ ፓርቲ በመለየት የሥርዓት ቀጣይነትን ለማረጋገጥ፣ ገዥው ፓርቲ በተሸናፊነት ስሜት ሳይሆን በኃላፊነት ስሜት እንዲንቀሳቀስ የሚጠበቅበት መሆኑን ለማሳየት፣ ሌሎች ኃይሎችም በጭፍን ምክር ቤት ይፍረስ፣ የሽግግር መንግሥት ይቋቋም የሚሉትን የሁለት ወገን አሸናፊነት የማያሳይ መሆኑን ለማስጨበጥ፣ ወዘተ የሚረዱ ስለሆነ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ ኃይሎች በቅንነት ተመልክተው ሊቀበሉት ይገባል፡፡

ከላይ በቀረቡት የመነሻ የስምምነት ሐሳቦች መግባባት ከተደረሰ፣ ይህን መሠረት ያደረገ ለውጥ እንዲደረግ የሚከተሉት ወሳኝ ተግባራት መከናወን ይኖርባቸዋል፡፡

 1. አገር አቀፍ ጉባዔ ሊጠራ የሚችል በመንግሥት፣ በአገር ውስጥና በውጭ ከሚገኙ ኃይሎች ይሁንታ ያገኙ የጉባዔ ጠሪ ኮሚቴ ማወቀር፣
 2. በሕዝብ ዘንድ አመኔታ ያላቸው ዜጎች የሚወከሉበት አገር አቀፍ ኮንፈረንስ በአጭር ጊዜ እንዲጠራ ተደርጎ የሽግግር ሥራዎችን የሚሠራ ኮሚሽን እንዲቋቋም ማድረግ፣
 3. የኮሚሽኑ አባላት በመንግሥትና በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ በሚገኙ አካላት ተቀባይነት ያላቸው መሆናቸውን ማረጋገጥ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

እነዚህን ተግባራት በአጭር ጊዜ በማከናወን ገዥው ፓርቲ አሁን ከገባበት ምናልባትም አገርን ሊበትን ከሚችል አዙሪት ለመውጣት መወሰኑን ያረጋግጣል፡፡

ይህ ኮሚሽን በዋነኝነት በአገሪቱ ወሳኝ የሆነውን ምቹ የፖለቲካ ምኅዳር ለመፍጠር ነው፡፡ ይህ ኮሚሽን የሚከተሉትን ዋና ዋና ተግባራት ማከናወን እንዲችል በሕግ ሥልጣን ይሰጠዋል፡፡ (የሚቀነስ የሚጨመር መኖሩ የሚታይ ነው፡፡)

 • በቀጣይ በአዲስ አበባና በሌሎች አካባቢዎች ሊደረግ የታሰበው ምርጫ እንዲራዘምና ከቀጣይ አገር አቀፍ ምርጫዎች ጋር በጋራ እንዲከናወን ያደርጋል፡፡
 • ለአገራዊ መግባባት አስፈላጊ ናቸው ተብለው የሚታመንባቸው እስረኞች እንዲፈቱ፣ በውጭ የሚገኙ ማንኛቸውም የፖለቲካ ኃይሎች በነፃነት በአገር ውስጥ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ሁኔታዎችን ያመቻቻል፣ መንግሥት አጠቃላይ የምሕረት አዋጅ እንዲያውጅ ሐሳብ ያቀርባል፡፡
 • የመንግሥት ሚዲያዎች ለሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በሕገ መንግሥት ድንጋጌ መሠረት ክፍት ይሆናሉ፡፡ የመንግሥት ሚዲያ ቦርድ አባላት ይህን በሚያረጋግጥ ሁኔታ እንደገና ይደራጃሉ፡፡
 • የግል ሚዲያ ተቋማት በሕግ መሠረት እንዲንቀሳቀሱ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ (በዘርና በሃይማኖት መሠረት ወይም ደግሞ ከኢትዮጵያዊነት ባህል ውጪ የሆኑት ላይ ተገቢውን ቁጥጥር ማድረግ እንደተጠበቀ ሆኖ)፣ በተቻለ መጠን ጋዜጠኞች መረጃ ከመስጠት በተጨማሪ ተጠያቂነት እንዲሰፍን የመረጃ ማግኘት ነፃነታቸው ይከበራል፡፡
 • ለነፃ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ እንቅፋት የሆኑ ሕጎች ተለይተው እንዲሻሻሉ ወይም ተግባራዊ እንዳይሆኑ ያደርጋል፡፡
 • በፖለቲካ አስተምህሮ ላይ መሥራት የሚፈልጉ ነፃ ሲቪል ማኅበራት በተጠያቂነት ስሜት እንዲንቀሳቀሱና ሕዝቡ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቱን ለመጠቀም እንዲችል ድጋፍ እንዲያደርጉ ይደረጋል፡፡
 • በሕገ መንግሥት የተፈቀደውን የዜጎች የመደራጀት መብት ሳይጋፋ የፖለቲካ ሥልጣን ለመያዝ የሚወዳደሩ ፓርቲዎች ይህን ለማድረግ የሚያስችል አቅም ያላቸው መሆኑ ለማረጋገጥ ሕግ ይወጣል፡፡ በዚሁ መሠረት ተረጋግጦ ምዝገባ ይደረጋል (ዝርዝሩ በሕግ የሚወሰን ይሆናል)፡፡ ይህንን መሠረት አድርጎ የፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ እንዲሻሻል ይደረጋል፡፡ አሁን ተመዝግበው ያሉ ፓርቲዎች የሚቀመጠውን ዝቅተኛ መሥፈርት ማሟላታቸው ሲረጋገጥ ድጋሚ ምዝገባ ያደርጋሉ፡፡
 • የምርጫ ቦርድን ጨምሮ ሌሎች ተጠሪነታቸው ለምክር ቤት የሆኑ አካላት (አሁን ምክር ቤቱ በአንድ ፓርቲ የተያዘ መሆኑ ከግንዛቤ በማስገባት) አወቃቀራቸው ተቀባይነት እንዲኖረው ከማድረግ በተጨማሪ፣ ሪፖርታቸውን ለሕዝብና ለሚዲያ በይፋ ያቀርባሉ፣ ያቀረቡት ሪፖርት በማንኛውም አካል ይፋ ሆኖ ተዓማኒነቱ ይረጋገጣል፡፡

ከላይ የቀረበው ሐሳብ በዋነኝነት መንግሥት የዚህችን አገር ችግር ለብቻዬ ልፍታ ከሚል የተለመደ መንገድ እንዲወጣ፣ ተቃዋሚ ወገኖችም በሚፈጠረው ምቹ የፖለቲካ ምኅዳር ለአገራቸው የሚያስቡትን በጎ ነገር ሁሉ ለሕዝብ በይፋ እንዲያቀርቡ፣ ወሳኙ ሕዝብ መሆኑን ሁሉም አካል ተቀብሎ አገራችን ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግር በሰላም እንድታድግ ለማድረግ ነው፡፡ በዚህ መነሻ ሐሳብ መሠረት መንግሥት ሌሎች ሁኔታውን ሊያሻሽሉ የሚችሉ ተጨማሪ ጉዳዮችን በመጨመር ለተግባራዊነቱ በይፋ መነሳት ይኖርበታል፡፡ ይህ ሲሆን አሁን በሥልጣን ላይ ያሉ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች አገር የግላቸው እንደሆነ አድርገው ብቻቸውን ከመጨነቅ የሚወጡበት መንገድ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡

ይህች አገር በአፋጣኝ ወደ ወሳኝ የፖለቲካ ምኅዳር ለውጥ ማሸጋገር ሳይቻል ቀርቶ፣ አሁን በተያዘው ሁኔታ በሚደረጉ ጥገናዊ ለውጦችና ሠራዊት በመጠቀም በሚደረግ አፈና ከቀጠለ ወደማንወጣው ቀውስ ከመውሰድ የዘለለ ምንም ለውጥ ሊሆን የሚችል ነገር መጠበቅ አይቻልም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የቀድሞ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ አመራርና የፓርላማ አባል የነበሩ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected]. ማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተወግዘው የነበሩ ሦስቱ ሊቀጳጳሳትና 20 ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት ውግዘት ተነሳ

_ቀሪዎቹ ሦስት ህገወጥ ተሿሚዎች የመጨረሻ እድል ተሰጥቷቸዋል ​ ጥር 14...

በሕወሓት አመራሮች ላይ ተመስርቶና በሂደት ላይ የነበረው የወንጀል ክስ ተቋረጠ

በቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤ,(ዶ/ር)ና ባለፈው ሳምንት በተሾሙት...

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...