Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲ ለምን የለም?

ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲ ለምን የለም?

ቀን:

በገነት ዓለሙ

በየጊዜው አዲስ የሚመስለውና ያረጀ ያፈጀ፣ ነባር መድኃኒት የሚታዘዝለት፣ አዳዲስ ሐኪም የሚሰየምለት የአገራችን ሕመም ‹‹ዴሞክራሲ››ያችን መልክ ብቻ በመሆኑ የመጣ ነው፡፡ ዴሞክራሲንና ዴሞክራሲያዊነትን ከስም ጌጡ ይልቅ እስትንፋሱ ያደረገ ሥርዓት መገንባት ባለመቻላችን ነው፡፡ ዴሞክራሲው መልክና የስም ጌጥ ብቻ ሊሆን የቻለውም ከሁሉም በላይና በዋነኛነት ከቡድንና ከፓርቲ ፖለቲካ ገለልተኛ አውታራዊ ሥሮች ስለሌሉት፣ በተለይም ደግሞ ኢሕአዴጋዊ ወገንተኛ ተፈጥሮ ባላቸው ወታደራዊና ሲቪል አውታራት ላይ የተለጠፈ እዚያ ላይ የተንጠለጠለ በመሆኑ ነው፡፡

በመላ አገሪቱ ያለ ፌዴራላዊም ሆነ ክልላዊ አስተዳደር በሙስናና በማናለብኝነት የጠነዛው፣ ሹሞች በሕዝብ ላይ መዘባነንና መደንፋት የቻሉት የሕዝብን የድምፅ መተማመኛ እናጣለን፣ ተጋልጠን እንጠየቃለን የሚል ፍርኃት ሳያሠጋ ሰላማዊ ተቃውሞን በኃይል መደፍጠጥ ወግ የሆነው፣ ሥር ያለው ዴሞክራሲ ስለሌለ ነው፡፡ እስቲ ከእነዚህ መካከል የሕዝብን የድምፅ መተማመኛ የማጣት ጉዳይ ነጠል አድርገን እግረ መንገዳችንን በምሳሌነት እናንሳ፡፡ ዘንድሮ ኅዳር ሃያ ሦስት ዓመት የሚሞላው ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 54(7) ማናቸውም የምክር ቤት አባል የመረጠው ሕዝብ አመኔታ ባጣ ጊዜ በሕግ መሠረት ከምክር ቤት አባልነቱ ይወገዳል ብሎ ይደነግል፡፡ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በመራጮቻቸው አመኔታ በሚያጠቡት ጊዜ ስለሚወሰድ ዕርምጃ የወጣውም አዋጅ (1989 ዓ.ም.) ሃያ አንድ ዓመት ሆኖታል፡፡ ሕገ መንግሥቱም የሕገ መንግሥቱ ማስፈጸሚያ አዋጅም ከወጣና ‹‹ተፈጻሚ›› መሆን ከጀመረ በኋላ የተወለዱ ልጆች ዛሬ ከመምረጥ መብት (18 ዓመት) ብቻ ሳይሆን፣ የመመረጥ መብት (21 ዓመት) ላይ ቢደርሱም ሕጉ በዚህን ያህል የሕይወት ዘመኑ የሠራው አንድ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ በሕወሓት ውስጥ በ1993 ዓ.ም. በተፈጠረው ክፍፍል ምክንያት የ1992 ዓ.ም. ጠቅላላ ምርጫ የትግራይ እንደራሴዎችን ‹‹መልሶ ለመጥራት›› ማለትም ለማውረድ ብቻ ነው፡፡

ይህ ሕገ መንግሥታዊ መብትና የማስፈጸሚያ ሕግም የወጣለት ለእንደራሴ የሰጡትን ውክልና የማንሳት መብትና ነፃነት እነ አቶ ስዬ አብርሃ መከራ ካዩበት ከዚያች ቀውጢ ጊዜ ውጪ ሥራ ላይ ሲውል ያላየነው፣ ዛሬም የማይሠራው፣ ሥልጣን ከያዘው ቡድን ፈቃድ ውጪ ዴሞክራሲ፣ መብቶችና ነፃነቶች ስለሌሉ ነው፡፡

የ2007 ዓ.ም. አምስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ያቋቋመው አምስተኛ ፓርላማ ገና ሥራውን እንደ ጀመረ ኅዳር 2008 ዓ.ም. አንስቶ መላውን አገሪቱን ያዳረሰው ተቃውሞም ዋነኛ መነሻ ኢሕአዴግ ዛሬም ድረስ እንደሚለው የወጣቱን የሥራ ፍላጎት በአግባቡ የሚያሟላ የሥራ ዕድል አለመፍጠርና የመንግሥት አስተዳደር የአፈጻጸም ጥፋቶች ብቻ አይደለም፡፡ ዋነኛውና ለሌሎችም ምንጭና አለቃ የሆነው ችግር ከላይ እንደተገለጸው ሥርዓታዊ ነው፡፡ የመንግሥት የሥልጣን ዓምዶች በቡድናዊ ወገናዊነት ላይ የታነፁ፣ ማለትም ለአምባገነንነት የተዘጋጁ ስለሆኑና የአገሪቱ ሕዝቦች በአምስት ዓመት አንድ ጊዜ ካርድ ሳጥን ውስጥ የመክተት ግርግራዊ ሆያ ሆዬና ትርዒት ከማድመቅ በቀር፣ ድምፅ የለሽ አጨብጭቦ አዳሪ መደረጋቸው ነው፡፡ ዛሬ ደጅ የወጣውንም ሆነ ተዳፍኖ የሚንተከተከውን የሕዝብ ብሶት፣ ሥራ በመፍጠር ብቻ የማይታጠብ የሕግ ማስከበር ሥራን በማጠናከር ብቻ የማይፈታ፣ ከዚያ አልፎ የዴሞክራሲያዊ አገዛዝን መቋቋም የሚጠይቅ ነው፡፡ በተለይም በአሁኑ የሕዝብ ሰፊ የተቃውሞና የኢሕአዴግ ‹‹በጥልቀት የመታደስ›› ዙር የኢሕአዴግ የራሱ የውስጥ ኅብረት እንደ ወትሮው ጥብቅ አይደለም፡፡ ይልቁንም ያለወትሮው ንፋስ ገብቶበታል በሚባልበት ወቅት መፍትሔው መፈለግ ያለበት ፀጥታና ደኅንነት ዕርምጃዎች ሳይሆን፣ ከፖለቲካዊና ከዴሞክራሲያዊ ነገረ ሥራችን ውስጥ ነው፡፡ በፖለቲካ ሰላም ላይ ያልተመሠረተ፣ በስነጋ የተገኘ ጊዜያዊ ረጭታና ፀጥታ ሰላምና መረጋጋትም፣ መፍትሔም አይደለም፡፡

በዚህ ረገድ ኢሕአዴግም ‹‹ዴሞክራሲን ማጥለቅ›› የሚለው ነገር አለው፡፡ የዚህ ትርጉም የኢሕአዴግ የራሱን ሰዎች ተሃድሶ የማጥለቅ፣ ሕዝብ የማገልገል፣ ቃል ኪዳንን የማደስ ጉዳይ ከሆነ በሕዝብ ተመራጭና ተከባሪ ለመሆን አሁን የተነሳውን ቁጣ ለማብረድ ብለው የሚያደርጉት ፓርቲያዊ ጉዳይ ከሆነ ጥያቄው መልስ አያገኝም፡፡ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ የኢሕአዴግ ተሃድሶ ማለት አይደለምና የዴሞራክሲ ግንባታ ጥያቄ እንዳፈጠጠ ይቆያል፡፡ ኢሕአዴግ በራሱ ተሃድሶ ራሱን በመደበቅ ውስጥ ተወስኖ እንዲቀር አንፈልግም፡፡ የሕዝብና የተቃዋሚ ፓርቲዎችን፣ ዛሬ ደግሞ የገዛ ራሱን ፓርቲ አባል ድርጅቶችን እኩል ተሳትፎና አመኔታ ያተረፈ ዴሞክራሲ የሚፈልጋቸውን የአውታራት ገለልተኝነት የማነፅ ሒደት ውስጥ መግባት ይኖርበታል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ የመጨራረስንም ሆነ የመጠፋፋትን ዕድል አምክኖ ዴሞክራሲን የመቀዳጀት ተስፋ ውስጥ የምንገባውና መንገዱንም የምንይዘው፣ ከተለመደውና ከድሮው አላዋጣ ያለ መንገድ ስንወጣ ነው፡፡ የሃይማኖት መሪዎች ስብከትና የኢሕአዴግ ኮንፈረንስ ጋጋታ መንገድ አያሳዩም፡፡ ኢሕአዴግን በጭፍኑ መሸከምም ሆነ እሱኑ በአመፅ እገላገላለሁ ማለት ፈጽሞ አያወጣም፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም ፖለቲካዊ ሰላም እንደማያመጣ ዓይተነዋል፡፡

በሕገ መንግሥቱ ከተደነገገው ውጪ በማናቸውም አኳኃን የመንግሥት ሥልጣን መያዝ የተከለከለ ነው፡፡ ይህን የሚለው ራሱ ሕገ መንግሥቱ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ይህን የሚለው ደግሞ በሕገ መንግሥቱ የበላይነት ድንጋጌ ውስጥ ነው፡፡ በዚህ ድንጋጌና ቃል መሠረት የተከለከለው የመንግሥትን ሥልጣን በሕገ መንግሥቱ ከተደነገገው ውጪ መያዝ ብቻ አይደለም፡፡ ይዞ መቆየትም ጭምር ነው፡፡ የመከላከያ ኃይልን ወይም የፀጥታ ኃይልን ለመንግሥት ግልበጣ መገልገል መፈቀድ እንደሌለበት ሁሉ፣ ሕገ መንግሥታዊው ሥርዓት አደጋ ላይ ነው በማለት የጨነቀው ገዥ ሥልጣን ላይ ለመቆየት የሚያካሂደውን ሕገወጥነትም መከላከል ነቅቶ የሚጠብቅና የሚገታ ሥርዓት ያስፈልጋል፡፡

የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ችግር ትግሉ ከሰላማዊና ከሕጋዊ ትግል ውጪ መውጣቱ ነው፡፡ በዚህ የሚከሰሱት በትጥቅ ትግል ውስጥ የገቡት ብቻ አይደሉም፡፡ የእነሱ ችግር ክስና ውንጀላ የታወቀና የለየለት ነው፡፡ የትጥቅ ትግል ዋናው ከሚባለው ከሕገወጥነቱ በላይ መንግሥትን ብቻ ሳይሆን፣ ከመንግሥት ጋር አገርን አብሮ የሚያደቅና የሚያወድም ነው፡፡ ለረዥም ዓመታት ሲታኮሱ፣ ፈንጂ ሲዘሩና መሠረተ ልማት ሲያወድሙ ኖረው ደግሞ እንደገና ሥልጣን ከጨበጡ በኋላ መልሶ ግንባታ የሚል በዛሬ ዘመን እብደት የሆነ የትግል ሥልት ነው፡፡ ገዥው ቡድንም በሕገወጥ ትግል አካሂያጅነቱ ብርቱ ተከሳሽ ነው፡፡ ከሕገወጡ ይበልጥ ሕጋዊውን መንገድ ተመራጭና ቀላል የሚያደርግ የፖለቲካ ባህልና አሠራር ማልማት አለመቻሉና አለመፈለጉ ችግሩ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ሕግ አስከባሪነቱና ሕግ አስፈጻሚነቱ ለሕጋዊነት ወግ እንኳን ጨርሶ የማይጨነቅ ነው፡፡ በሕጋዊነት መቀጠል ወይም ወደ ሕገወጥነት መዞር እያለ ነጋ ጠባ የሚታገላቸውን፣ የሚኮረኩማቸውን፣ አስፈላጊም ሲሆን እንዳሻው የሚያደርጋቸውን ተቃዋሚዎች የጫካን መንገድ በሚያመላክት ፕሮፓጋንዳ ይቀሰቅሳቸዋል፣ ይገፋቸዋል፡፡

ኢሕአዴግ ተቃዋሚዎች ተማርረው፣ አያዋጣንም ብለውም ወደ ስደትና ወደ ጫካ ቢሄዱ እንደተገላገላቸው መቁጠሩ ለራሱም ለአገርም መርዝና ጠንቅ ሆኗል፡፡ የውስጥ ተቃውሞን ማዳከም ለኢሕአዴግ ጥንካሬ አልሰጠም፡፡ አስደንግጦ ወደ ውጭ ማባረርም መገላገል አልሆነም፡፡ ይልቁንም በሰላምና በዴሞክራሲ መንገድ ሊፈታ ያልቻለ የውስጥ ተቃውሞ ከጎረቤት ባለጋራነት ጋር እንዲሸራረብ ተደርጓል፡፡ ከሁሉም ይበልጥ ደግሞ ከፕሮፓጋንዳውና ከ‹‹ፀጥታው›› ሥጋጃ ሥር ሲንተከተክ የኖረው ሕጋዊና ዴሞክራሲያዊ ማስተንፈሻ ያጣው ተቃውሞ በተለያዩ አካባቢዎች አገሪቷን ለአደጋ አጋልጧል፡፡

ከዚህ ሁሉ አደጋ መገላገል የሚቻለው እሳት በማጥፋት ሥራ ላይ ተጠምዶ በመባከን ሳይሆን፣ አደገኛ ተቃውሞን የሚፀንሱ፣ የጠብ እሳት የሚጭሩ፣ የሥር ምክንያቶችን ለማጥፋት ዴሞክራሲያችንን ከሥር ከመሠረቱ አሳምሮ መገንባት ነው፡፡ ለዚህ አስተማማኙ ጎዳናና የጥበብ መጀመርያው ገለልተኛ አውታር የመፍጠር ጉዳይ ነው፡፡

ዴሞክራሲ የሚጠልቀውና የሚስፋፋው፣ ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር ወረትን የተሻገረ ዕድሜ ሊኖራቸው የሚችለው ደግሞ፣ ምንጊዜም ህልውናቸው ከሥራ አስፈጻሚውና ከቡድን በጎ ፈቃድ ውጪ ሲሆኑ ብቻ ነው፡፡ የሥልጣነ መንግሥቱ ወታደራዊና ሲቪል ዓምዶች ከቡድናዊ ሙሽትና መረባዊ ውጦሽ ሲፀዱና ሲጠበቁ፣ እንዲሁም የሕግ ተርጓሚው፣ የሕግ አውጪውና የአስፈጻሚው የሥልጣን ዘርፎች ያላግባብ የመገልገል ዝንባሌዎችን ለመቆጣጠር በሚያስችል ተገናዛቢነት ሲደራጁ ነው፡፡

ዛሬ የኢትዮጵያን መንግሥታዊ አውታራት ከኢሕአዴግ መለየት እስኪሳነን ድረስ የአንድ ፓርቲ አገዛዝ ተንሠራፍቷል፡፡ ችግሩ የአንድ ፓርቲ አገዛዝ መንሠራፋቱ ብቻ አይደለም፣ ወይም የፌዴራልም ሆነ የክልል የመንግሥታት ሥልጣን በ‹‹ምርጫ›› የተሞላው በአንድ ፓርቲ ብቻ በመሆኑ አይደለም፡፡ የመንግሥት አዕማድ ከአንድ ፓርቲ ጋር የተሳከረና የተወራረሰ በመሆኑና ነፃ ህልውና ባለማግኘቱ ነው፡፡ እንዲህ ያለ ሁኔታ ውስጥ ዘቅጠን በመጥፋታችን የብዙ ፓርቲ አገር መሆን አልቻልንም፡፡ ሥልጣን የሚያዘውና በሥልጣን የሚቆየው በሕገ መንግሥቱ መሠረት መሆኑ ገና በጭራሽ አልተሞከረም፡፡ ለማንኛውም ፓርቲ በሥልጣን የመቆየትም ሆነ ወደ ሥልጣን የመምጣቱ ዕድል በፖለቲካ አቋሙ ውጤታማነትና ማራኪነት ላይ የተንጠለጠለ መሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ የማይሠራው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ውስጥ ስላልገባን ነው፡፡

ይህንን ጉዳይ ሰፋ አድርጎ ለማብራራት የተለያዩ ጥያቄዎችን እያነሳን ጉዳዩን እንመርምር፡፡ አማራጭ ፓርቲዎች በምርጫ ተወዳድረው ሕገ መንግሥቱ በሚደነግገው መሠረት ሥልጣን የሚያዝበት ሥርዓት ገንብተናል ወይ? መናጋት ሳይፈጠር የአገርና የሕዝብ የተረጋጋ ሕይወት ሳይረበሽ ኢሕአዴግን ወይም ሌላ ሥልጣን የያዘ ፓርቲን በምርጫና በአማራጭ ፓርቲ መቀየር ይችላል ወይ?

የመጀመርያው ችግር (ለምርጫ የሚያስፈልገው መንዕስ (መነሻ) የዴሞክራሲያዊ ሁኔታዎች አለመኖር ራሱ አንዱ ችግር ሆኖ) ኢሕአዴግን በአማራጭና በምርጫ የሚፈታተን ብርቱ ፓርቲ አለመኖሩ አንዱ የአገር ሕመም ነው፡፡ የተለያየ ምክንያት ቢሰጠውም ይህ በሁሉም ዘንድ የታወቀ ችግር ነው፡፡ ተቃዋሚዎች ጠንክረው ባለመውጣታቸው ኢሕአዴግን ይከሳሉ፡፡ ኢሕአዴግም ጠንካራ ተፎካካሪ ፓርቲ ባለመኖሩ ‹‹አለመታደሉን›› ይገልጽ የነበረው ከጥንት ከጠዋቱ ጀምሮ ነው፡፡ እንዲያውም በ1997 ዓ.ም. የምርጫ ቅስቀሳ የመጨረሻ ቃለ ምልልስ ላይ አቶ መለስ ዜናዊ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ምርጫ እያጣ ኢሕአዴግን የሚመርጥ ከሆነ ሥጋት ነው፤›› ማለት ድረስ በተቃዋሚዎች ‹‹ደካማነት›› ላይ ተሳልቀው ነበር፡፡ በየትኛውም ምክንያት ቢሆን፣ (በገዥው ፓርቲ ክፋትም ሆነ በተቃዋሚዎች ጥፋት) ጠንካራ ተፎካካሪና አማራጭ ሆኖ የቀረበ ፓርቲ አለመኖሩ አንዱ የሥርዓት ግንባታ ችግራችን ነው፡፡

ከወገናዊነት ነፃ የሆነ የምርጫና የውድድር ሜዳ አለመኖሩ ሌላው ችግር ነው፡፡ አገራችን ፍላጎት፣ ውዴታና ድምፅ መስጠት ገና ያልተገባበት አገር ናት፡፡ ለምርጫ መመዝገብና መምረጥ እንደ ድጋፍ ሠልፍ የኑሮ ግዴታ ነው፡፡ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ይካሄዳል ብሎ መከራከርና አፍን ሞልቶ መናገር ይቅርና ነፃና ፍትሐዊ የሚሉትን ቃላት ለመጠቀም የሚያበቃ ቀናነት የሌለን መሆኑ በብዙ ተያያዥ ነውሮች፣ ቅሌቶችና ገመናዎች ታጅቦ መሸጋገሪያ መላ እንኳን ሳይኖረው በቀጠሮ ያደረው የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን አመራር ምርጫ በቂ ምስክር ነው፡፡

ሌላም ተከታይ ችግር አለ፡፡ በምርጫ ማሸነፍ አንድ ጊዜ ቢቀና ትርምስ ሳይኖር፣ አፍርሶ መገንባት ሳይመጣ ጉዞ ስለመቀጠሉ እርግጠኛ የሚያደርግ ሥርዓትም ሌላው ጎዶሏችን ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ አሸናፊው እኔ ነኝ ብሎ በጉልበቱ ሥልጣን ላይ እቆያለሁ የማይልበትን፣ አሸናፊ ነው በተባለው ወገንና ሥልጣን አልለቅም ባለ ወገን መካከል ሰው ተከፋፍሎ ቀውስ ውስጥ የማይገባበትን፣ ይህ ሁሉ የልማት ሥራ ለውድመት የማይጋለጥበትን አሠራርና ሥርዓት ያደላደለ ብርቱ ችግር አለብን፡፡

ነባሩ ገዥ ፓርቲ ወርዶ ተቃዋሚው ፓርቲ ሥልጣን ያዘ እንበል፡፡ ይህን ጊዜ ደግሞ ሌላው ችግር ይመጣል፡፡ አዲሱ ፓርቲ የቀድሞውን ፓርቲ ቡድናዊ አሻራና ቁጥጥር ለማፅዳት ሲል የነባሩን ወገናዊ አውታራት ያበራያል፡፡ የራሱን ይፈጥራል፡፡ የዚህ ሁሉ መነሻ ከቡድናዊ ወገናዊነት ነፃ የሆኑ የመንግሥት አውታራትን የመገንባት ተግባር አለማከናወናችን ነው፡፡

በዚህ ረገድ የአፍሪካ የእርስ በርስ መገማገሚያ ሥልት የ2003 ዓ.ም. የኢትዮጵያን የግምገማ ውጤት መጥቀስና ማስታወስ የምናውቀውንና ቀን በቀን የምንኖርበትን ከሌላ አካል መልሶ ማድመጥ ያህል ጠቃሚ ነው፡፡ የሪፖርቱ ሐተታ እንዲህ ይላል፡፡

‹‹እንደ ኢትዮጵያ ባለ በቀላሉ ሊቀጭ በሚችል ታዳጊ የዴሞክራሲ ባህል ውስጥ ለተቃዋሚ ክብር (አክብሮት) መስጠት ሲበዛ ወሳኝ ነው፡፡ ለተቃውሞ አክብሮት የማይሰጥ ገዥ ፓርቲ የመከፋፈልና ያለመተማመንን ዘር ይዘራል፡፡ እሱ ራሱ ተቃዋሚ ፓርቲ እንዳይሆን ይከላከላል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲ የሚሆንበት ያን ቀን ከወዲሁ እንዲጠላ፣ እንዲፈራ፣ በፍርኃቱም እንዲጨነቅ ያደርገዋል፡፡ ያችም ቀን ምንም ቢሆን በጭራሽ እንዳትመጣ የሚያረጋግጥ ያሻውንና የፈቀደውን ዕርምጃ እንዲወስድ ያደርገዋል፡፡ ስለዚህም የዴሞክራሲ ቃል ኪዳን የሆነውንና ተቃዋሚውንም ታማኝ የሚያደርገውን ሥልጣን ላይ መፈራረቅን በእጅጉ ይጎዳል፡፡››

ዴሞክራሲን አልገነባንም፣ ዴሞክራሲ መገንባት አለበት የምንለው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ የአንድ ገዥ ፓርቲ ከሥልጣን መውረድ የማንም ሥጋት እንዳይሆን ነው፡፡ የነባሩ ገዥ ፓርቲ ከሥልጣን መወገድን ከአሮጌ ሥርዓት መምጣት ጋር አንድ ያደረገ ማደናገሪያን፣ ሕዝብ ይተላለቃል ወደ መገነጣጠል መሄድ ይመጣል ማስፈራሪያን ለማክሸፍ ነው፡፡

እዚህ የዴሞክራሲ ግንባታ ግብ ላይ ለመድረስ አስተማማኙ መንገድ የማንም ፓርቲ ተቀፅላ ያልሆኑ ገለልተኛ ተቋሞችን ዕውን ማድረግ ነው፡፡ በተለይ በተለይ የአገሪቱ የመከላከያ ኃይል ከመናጋትና ከመፍረስ አደጋ ጋር ሳይገናኝ፣ የአገሪቱ የመረጃና የደኅንነት አውታርም የአገሪቱን የልማት ሀብቶች፣ የሕዝቦችን ደኅንነትና ሰላም ነቅቶ ከመጠበቅ ለአንድ አፍታም ሳያቋርጥ ከገዥ የፖለቲካ ቡድን ታማኝነትና ደባል አገልጋይነት እንዲላቀቅ፣ በአጠቃላይም የተክለ መንግሥቱ (ማለትም የስቴቱ) አውታራት ገለልተኛ ባህርይን እንዲጎናፀፍ ማድረግ ነው፡፡

ለጥቆ የሚመጣው ጥያቄ ደግሞ ይህንን ተግባር እንዴት መፈጸም ይቻላል? የሚለው ነው፡፡ ይህን ለማድረግ የሚቻለው ኢሕአዴግና የተቃውሞ ወገኖች በጠረጴዛ ዙሪያ በእኩልነት ተገናኝተው አብሮ ለመሥራትና የተክለ መንግሥቱን መንሻፈፍ ለማቃናት ዴሞክራሲን ለማደላደል መደራደር፣ መነጋገርና መስማማት አለባቸው፡፡ በዚህ ምክንያት ተወደደም ተጠላም የዚህ ትግል ዒላማ ገዥው ፓርቲ አይደለም፡፡ የትግሉ ዒላማ ገዥው ቡድን ሳይሆን፣ ሥልጣንና እውነተኛነት የእኔ የብቻዬ ነው ብሎ  በመንግሥታዊ ሥርዓቱ በአስተሳሰብና በአሠራር ባህል ላይ ያደረሰው ብልሽት በመሆኑ፣ መንግሥታዊ አውታሩ (የመከላከያ፣ የደኅንነት፣ የፍትሕ፣ የምርጫ፣ የመረጃና የፕሮፓጋንዳ ተቋሙ ሁሉ) ከየትኛውም ቡድን ይዞታነት እንዲላቀቅና የዴሞክራሲያዊ መብቶች ችሮታነት እንዲያከትም መታገል ነው፡፡

ይህን የማያነሳና የማያካትት እንኳንስ በምርጫ ቦርድ ስያሜ ላይ፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 54(4) ውስጥ በተደነገገው የምርጫ ሥርዓት ላይ ጭምር የሚደረገው ድርድር ዋናውን ሕመምና ችግር የሳተ ሥራ ፈትነትና ከንቱ ልፋት ነው፡፡ የትኛው የምርጫ ሥርዓት ይሻላል ብሎ ውይይት ውስጥ የሚገባው መጀመርያ እንዲያ የሚያቀናጣ ምርጫንና አማራጭ ፓርቲን አቅፎና ደግፎ የሚያስተናግድ የተክለ መንግሥት አውታራት ሲኖሩ ነው፡፡ ይህ ጨርሶ በሌለበት ሁኔታ በምርጫ ሥርዓቱ አማራጭ ላይ መንገታገት የኢትዮጵያን ችግርና መፍትሔ መሳት ነው፡፡

ኢሕአዴግን የዚህ ድርድር አካል የሚያደርጉ በርካታ ምክንያቶች የመኖራቸውን ያህል፣ ከዚያ እኩል በኢሕአዴግ ላይ ይህንን የመንግሥት አውታራት ገለልተኛ ባህርይ እንዲጎናፀፍ የማድረግ ግዴታ የሚያቋቁምበት ምክንያትም አለ፡፡ ኢሕአዴግ ይህን ለመሰለ ትርጉም ላለው ድርድርና አብሮ ለመሥራት ጀርባ ከሰጠ ‹‹ሕገ መንግሥቱን በአመፅና በኃይል ሊያፈርሱ ነው፤›› እያለ በሌሎች ላይ የሚያቀርበውን ክስ በገዛ ራሱ ላይ መመሥረቱ ነው፡፡ የመንግሥት አውታራትን ገለልተኛ ባህርይ እንዲጎናፀፍ አለማድረግ፣ ከገዥ የፖለቲካ ቡድን ታማኝነትና ደባል አገልጋይነት አለማላቀቅና አለማፅዳት፣ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱንና ሕገ መንግሥቱን በኃይል እንዲፈርስና እንዲናድ፣ ሕዝቦች እንዲበጣበጡና እንዲተላለቁ መጋበዝና ራሱን ኢሕአዴግንም ጨምሮ አገሪቱንም ሊበላ የሚችል መከፋፈልና ግብታዊ ነውጥ መጥራት ነው፡፡

በዚህ ጉዳይ ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ የመምጣትና ተባብሮ የመሥራት ጉዳይ ከመበጣበጥና ከመተላለቅ የመትረፍና ያለመትረፍ ጉዳይ በመሆኑ፣ ለኢትዮጵያ ሕዝቦችና ለዴሞክራሲ የተጨነቀ አሳቢነት ዛሬ በድርድሩ አዳራሽ ውስጥ ከሚነሳውና ከሚሰማው ‹‹ጭቅጭቅ›› ማለፍ አለበት፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡        

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኩባንያ አስተዳደር ለኢትዮጵያ ባንኮች ውጤታማነት

የጠቅላላ ጉባኤ፣ የጥቆማና ምርጫ ኮሚቴ፣ የተቆጣጣሪ ቦርድ፣ የዳይሬክተሮች ቦርድና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...