Sunday, February 25, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የመድን ድርጅቶች ለሞተር ካሳ የሚያውሉት ክፍያ እየተባባሰ መምጣቱን አስታወቁ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • 7.5 ቢሊዮን ብር በላይ ዓረቦን አሰባስዋል

የአገሪቱ 17 የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በ2009 ዓ.ም. ከነበራቸው እንቅስቃሴ አኳያ ከ7.5 ቢሊዮን ብር በላይ ዓረቦን አሰባስበዋል፡፡ ሰሞኑን ሪፖርታቸውን ይፋ ሲያደርጉ የሰነበቱት የመድን ድርጅቶች፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን ዋቢ በማድረግ እንደገለጹት ኩባንያዎቹ በጠቅላላው ካሰባሰቡት ዓረቦን ውስጥ 7.1 ቢሊዮን ብሩ ሕይወት ነክ ካልሆነው የኢንሹራንስ ዘርፍ የተገኘ ነው፡፡

16ቱ የግልና መንግሥታዊው የኢትዮጵያ መድን ድርጅት፣ ሕይወት ነክ ካልሆነው የኢንሹራንስ ዘርፍ ያሰባሰቡት የዓረቦን መጠን 500 ሚሊዮን ብር ብቻ እንደሆነ ያመለክታል፡፡

የኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ ካሰባሰቡት ጠቅላላ የዓረቦን መጠን ውስጥ ሕይወት ነክ ያልሆነው የኢንሹራንስ ዘርፍ ከ95 በመቶ በላይ ከፍተኛውን ድርሻ ይዞ ይገኛል፡፡ ይህም ሕይወት ነክ በሆነው የኢንሹራንስ ዘርፍ የተሰበሰበው የዓረቦን ገቢ የአምስት በመቶ ድርሻ በመያዝ ባለበት እየተጓዘ እንደሚገኝ መረጃው ያመላክታል፡፡  

የ2009 ዓ.ም. አጠቃላይ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪውን እንቅስቃሴ በተመለከተ የፀሐይ ኢንሹራንስ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ማንደፍሮ እርቁ አቅርበውት በነበረው ሪፖርት እንደገለጹት፣ በ2009 ዓ.ም. የተመዘገበው አጠቃላይ ሕይወት ነክና ሕይወት ነክ ያልሆነው የዓረቦን መጠን 7.5 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህ መጠን ከ2008 ዓ.ም. አፈጻጸም ጋር ሲነፃፀር የ16 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ ከጠቅላላው የዓረቦን ውስጥም 7.15 ቢሊዮን ብሩ ከሕይወት ነክ ካልሆኑ የመድን ሥራዎች እንደተገኘ አስታውሰዋል፡፡ ከጠቅላላው ዓረቦን ገቢ ውስጥ 64 በመቶው የግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች የሰበሰቡት ሲሆን፣ ቀሪውን 36 በመቶ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ድርሻ እንደሆነም የፀሐይ ኢንሹራንስ ሪፖርት ያሳያል፡፡  

ዓምና የተሰበሰበው የዓረቦን ገቢ ከካቻምናው የ16 በመቶ ብልጫ አስመዝግቧል ቢባልም፣ የአገሪቱ የመድን ኢንዱስትሪ ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች አኳያ ሲታይ ግን አነስተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ለመረዳት ተችሏል፡፡

የናይል ኢንሹራንስ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ መቅደስ አክሊሉ በሪፖርታቸው ‹‹ምንም እንኳ የአገሪቱ ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት ፈጣን ቢሆንም፣ ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ጋር ሲነፃፀር የኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ካለው የገበያ ሽፋንና ወደ አዲስ ገበያ ዘልቆ ለመግባት ያለው አቅም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፤›› በማለት ስለ አገሪቱ መድን ድርጅቶች አቅም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ የነፍስ ወከፍ የዓረቦን ገቢ ድርሻ ከአገር ውስጥ ጠቅላላ ምርት አንፃር ሲሰላ ከአንድ በመቶ በታች ወይም የሦስት ዶላር ያህል አነስተኛ ስለመሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ ይህም ከአፍሪካ የሦስት በመቶ (በነፍስ ወከፍ የዓረቦን ገቢ 60 ዶላር) እና ከዓለም አማካይ የስድስት በመቶ ድርሻ ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ በመሆኑ፣ ኢንዱስትሪውን ለመለወጥ በዘርፉ የሚመለከታቸው ተዋናዮች ሰፊ ሥራ እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል፡፡

ኩባንያዎቹ ከሰበሰቡት ዓረቦን አንፃር ምን ያህሉን ለካሳ እንደዋሉ በሚያሳየው መረጃ መሠረትም፣ በ2009 ዓ.ም. ሁሉም ኩባንያዎች የ3.35 ቢሊዮን ብር ካሳ ክፍያ ፈጽመዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ ሕይወት ነክ ላልሆነው የመድን ሽፋን የተከፈለው ካሳ 3.19 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ከ3.19 ቢሊዮን ብር ውስጥ የሞተር ካሳ ድርሻ 88 በመቶውን ይይዛል፡፡ ይህም የአገሪቱ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ በሞተር መድን ሽፋን ላይ የተንጠለጠለና ከዚህ በፊት ሲያሳይ ከነበረው አካሄድ እንዳልተለወጠ ተመልክቷል፡፡

ሁሉም ኩባንያዎች ከፍተኛውን የካሳ ክፍያ የፈጸሙት ከተሽከርካሪዎች አደጋዎች ጋር ለተያያዙ ጉዳቶች በመሆኑ፣ ኩንያዎቹ በሞተር መድን ሽፋን ዘርፍ ብርቱ ፉክክር ውስጥ ለመግባት መገደዳቸውንና ሌሎች የመድን ሽፋኖችን በወጉ እንዳያቀርቡ እያስገደዳቸው እንደሚገኝ ተጠቅሷል፡፡ አንዳንዶቹ የሞተር መድን እያከሰራቸው እንደሚገኝ ከተለያዩ ኩባንያዎች ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል፡፡

የፀሐይ ኢንሹራንስ ቦርድ ሰብሳቢ እንደሚሉት፣ ምንም እንኳ የሞተር መድን ሽፋን ከፍተኛ የኪሳራ ምጣኔ ቢኖረውም ከሞተር መድን የሚሰበሰበው የዓረቦን ክፍያ በረዥም ጊዜ ተቀማጭ ሒሳብ አማካይነት በሚያስገኘው የወለድ ገቢ የኩባንያዎቹን የገቢ መጠን እንደሚደግፍ ጠቅሰዋል፡፡ የሞተር ኢንሹራንስ እያከሰረም ቢሆን ሽፋኑ የሚሰጠው ከሚሰበሰበው ገንዘብ በሚገኘው የወለድ ገቢ መሆኑን የሌሎች ኩባንያዎች ኃላፊዎችም ይስማሙበታል፡፡

በዓረቦን አሰባሰብ ረገድ በ2009 ዓ.ም. ከግል የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ቀዳሚ ሆነ የተገኘው አዋሽ ኢንሹራንስ ነው፡፡ አዋሽ ኢንሹራንስ ካቻምና ያሰባሰበው ገቢ 595.9 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ ኒያላ ኢንሹራንስ በበኩሉ 435.8 ሚሊዮን ብር ገቢ አሰባስቧል፡፡

የአገሪቱ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች የትርፍ ምጣኔ ሲታይም፣ ለመጀመርያ ጊዜ 17ቱ ኩባንያዎች አጠቃላይ የተጣራ ትርፋቸው ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ መሻገር ችሏል፡፡ በ2002 ዓ.ም. የሁሉም ኩባንያዎች የተጣራ ትርፍ 235.18 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ ይህ የትርፍ መጠን እያደገ በመምጣት በ2006 ዓ.ም. ወደ 823.5 ሚሊዮን ብር አሻቅቧል፡፡ ካቻምናም የ10 ሚሊዮን ብር ጭማሪ በማሳየት የ835.3 ሚሊዮን ብር ትርፍ ለማስመዝገብ አስችሏል፡፡ ሆኖም ይህ መጠን ባንኮች ከሚያገኙት ትርፍ አንፃር ሲታይ ግን የኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ የትርፍ ምጣኔ ዝቅተኛ ነው ተብሏል፡፡

17ቱ ኩባንያዎች በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ያስመዘገቡት 835.3 ሚሊዮን ብር፣ በአሁኑ ወቅት አንድ የግል ባንክ ከሚያገኘው ትርፍም ያነሰ ነው፡፡ በ2009 ዓ.ም. አዋሽና ዳሸን ባንክ ለየብቻ ያስመዘገቡት ዓመታዊ ትርፍ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ነው፡፡ የኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ በጠቅላላው ተደምረውም አንድ ባንክ ከሚያገኘው ትርፍ በታች ማስመዝገባቸው የሚገኙበትን ዝቅተኛ ደረጃ ይጠቁማል፡፡

ከትርፍ አንፃር ከግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች በ2009 የሒሳብ ዓመት ከፍተኛ ሊባል የሚችለውን ትርፍ በማስመዝገብ ቀዳሚ የሆነው ኒያላ ኢንሹራንስ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ኒያላ ኢንሹራንስ ከታክስ በፊት 137 ሚሊዮን ብር ከታክስ በኋላ ደግሞ 122.2 ሚሊዮን ብር ማግኘቱን አስታውቋል፡፡ ይህም ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ በግል የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የተመዘገበ ከፍተኛው ትርፍ ሆኗል፡፡ የተጣራ ትርፉም ቢሆን በግል ኩባንያዎች እስካሁን ያልተመዘገበ ከፍተኛው መጠን እንደሆነ ታውቋል፡፡ ሰሞኑን አዋሽ ኢንሹራንስ ለሪፖርተር በላከው መግለጫ፣ ከታክስ በፊት 101.7 ሚሊዮን ብር፣ ከታክስ በኋላም 88 ሚሊዮን ብር ማትረፉን ገልጾ ነበር፡፡

ኒያላ ኢንሹራንስ የተጠቀሰውን ትርፍ ከማስመዝገቡ ባሻገር፣ በትርፍ ድርሻ ክፍፍልም አብላጫውን ድርሻ ይዟል፡፡ የኩባንያው የትርፍ ድርሻ 539 በመቶ አስመዝግቧል፡፡ በዓረቦን ገበያ ውስጥ ከግል መድን ድርጅቶች ትልቁን ድርሻ የያዘው አዋሽ ኢንሹራንስ፣ በትርፍ ድርሻ ክፍፍሉ ያስመዘገበው 178 በመቶ ነው፡፡ ይህም ከቀዳሚው ዓመት ቅናሽ የታየበት ነው፡፡ እንዲህ ያሉት ጉዳዮች ኢንዱስትሪው ችግሮች እንዳሉበት ያመላከቱ ናቸው፡፡  

እንደ አቶ መቅደስ ከሆነ ምንም እንኳ በ2009 ዓ.ም. ኢንዱስትሪው ከፍተኛ  ዕድገት ቢያስመዘግብም፣ በአብዛኛው ኅብረተሰብ ዘንድ ስለኢንሹራንስ አገልግሎት ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ መሆን አንዱ የችግሩ ምንጭ ነው፡፡ አዳዲስና በቴክኖሎጂ የታገዙ የአገልግሎት ዓይነቶች ወደ ገበያ ማምጣት አለመቻላቸው፣ ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት አለመዘርጋቱ፣ እንደልብ ለመሥራት የሚያስችሉ ሕጎችና አስተዳደራዊ ጉዳዮች በቂ አለመሆናቸው፣ የኢንሹራንስ ባለሙያዎችና ኃላፊዎች እጥረት መኖሩ፣ ኢንዱስትሪው በሚፈለገው መጠን እንዳያድግ አስተዋጽኦ ካደረጉ ተግዳሮቶች መካከል ይመደባሉ፡፡

የመድን ኢንዱስትሪው ከሚታይበት የሰው ኃይል እጥረት አኳያ በአሁኑ ወቅት የሚታየው የሠራተኞች ፍልሰት አብዛኞቹን ኩባንያዎች እያሳሰበ መጥቷል፡፡ የሠራተኞች መነጣጠቅ የኢንዱስትሪው ከፍተኛ ችግር ስለመሆኑም እየተገለጸ ነው፡፡ የሠራተኛ ንጥቂያው በሥራ አስፈጻሚዎች ደረጃ ጭምር የሚታይ መሆኑም አሳሳቢነቱ እንዲያይል ማድረጉ እየተገለጸ ነው፡፡

በአንፃሩ የዜጎች ገቢ እያደገ በመምጣቱና መካከለኛ ገቢ ያለው የኅብረተሰብ ክፍል ቁጥር በመጨመሩ፣ የኢንሹራንስ ተጠቃሚዎች ፍላጎትም እየጨመረ መምጣቱ መልካም ዕድል ነው ተብሏል፡፡ ኢንዱስትሪው አስጊ የገበያ ሁኔታ ባይኖርበትም፣ የዘርፉን ዝቅተኛ የገበያ ሽፋን ለማሳደግና ወደ አዳዲስ ገበያዎች ለመስገባት የሚያስችል እምቅ አቅም በአገሪቱ በመኖሩ፣ ኢንዱስትሪውን ለማሻሻል ሁሉም ኩባንያዎች ጥረት እንዲያደርጉ በማለት አቶ መቅደስ ይመክራሉ፡፡  

ኢንዱስትሪውን በመለወጥ በአገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚኖረውን ሚና ለማሻሻል ቁርጠኝነትና በተግባር የተደገፈ እንቅስቃሴ ማድረግ፣ በኢንዱስትሪው ውስጥ ለሚታዩት ተግዳሮቶችም ወቅታዊ መፍትሔ መስጠት አስፈላጊ የሆነበት ደረጃ ላይ እንደተደረሰም ተናግረዋል፡፡

በኢንዱስትሪው ዋጋን ብቻ መሠረት ያደረገ ፉክክር መኖሩ፣ ዝቅተኛ የዓረቦን ምጣኔ መታየቱ፣ በዘርፉ የሠለጠነ የሰው እጥረት መበራከቱና የመሳሰሉትን ችግሮች  የገለጹት አቶ ማንደፍሮ፣ ከተሽከርካሪ አደጋ መበራከት አኳያ የመድን ኩንያዎች የኪሳራ ምጣኔ ከፍተኛ መሆኑም ከፍተኛ ችግር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ያላሰለሰ ጥረት  ማድረግ እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡

በ2008 ዓ.ም. መጨረሻ የነበረው የ17ቱ ኩባንያዎች ሀብት 11.5 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ ይህ መጠን በ2000 ዓ.ም. ከነበረው ጋር ሲነፃፀር፣ ከሁለት እጥፍ በላይ እንዳደገ ተጠቅሷል፡፡ በ2002 ዓ.ም. የተመዘገበው የሀብት መጠን 3.2 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች