Thursday, July 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ዋሾ ዋጋዎች

የግብይት ሥርዓቱ ውጥንቅጥ መሆን ብቻ ሳይሆን፣ ምቹ የገበያ ሥፍራ በማሰናዳት ለደንበኞች እርካታ ታስቦባቸው አገልግሎት የሚሰጡ አምራቾችም ሆኑ አገልግሎት ሰጪዎች እንደልብ አለመኖቸው አገራዊ ችግር ነው፡፡ ጤናማ የንግድ ውድድር የለም፡፡ ለኅብረተሰቡ አስደሳች አገልግሎት በመስጠት በቀስ በቀስ አትራፊ ለመሆን የሚጣጣሩትን ማየቱም እምብዛም ነው፡፡

 ከአገራችን የተወናበዱ የንግድና የአገልግሎት አሰጣጥ ልማዶች ውስጥ ሁሌም ከሚገርሙኝ አንዱ የኅትመት ኢንዱስትሪውና የመጻሕፍት ገበያ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የሕትመት ዋጋ የሚቀመስ አይደለም፡፡ መጽሐፍ፣ ጋዜጣና መጽሔት ለማሳተም የሚጠየቀው ዋጋ ጉድ የሚያሰኘኝ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የግብይት ሥርዓቱም በችግሮች የተሞላ ነው፡፡

ዜጎች የንባብ ባህል እንዲያዳብሩ፣ ከንባብ የሚገኝ ዕውቀትን የሚያጎናጽፉ የሕትመት ውጤቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ የማግኘት ዕድል እየሳሳ መጥቷል፡፡ በርካታ ጸሐፍት በሕትመት ዋጋ መናር ሳቢያ በየቤታቸውን ያስቀመጧቸው የአዕምሮ ውጤቶቻቸውን ቤት ይቁጠራቸው፡፡

ነገሩን ወደ ኋላ መለስ ብለን ስንመለከተው፣ በጥቂት ዓመታት ውስጥ የታየው የሕትመት ዋጋ ጭማሪ ለማመን የሚከብድ ነው፡፡ በሳንቲሞች ይታተሙ የነበሩ ጋዜጦች ዛሬ ከአሥር ብር በላይ ይጠየቅባቸዋል፡፡ ከዛሬ 15 እና 20 ዓመታት በፊት፣ ባለስምንት ቅጠል ጋዜጣ ለማሳተም ያውም ውድ በተባለ ዋጋ የሚጠይቀው የሕትመት ወጪ ከ30 ሳንቲም አይበልጥም ነበር፡፡ የሚታተመው ጋዜጣ ብዛት ካለውም አንዱን ጋዜጣ በ20 ሳንቲምና ከዚህም ባነሰ ዋጋ ማሳተም የሚቻልበት ጊዜ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ ጣጣውን ችሎ ለገበያ ሲቀርብም ለባለስምንት ቅጠል ጋዜጣ አንባቢው የሚጠየቀው 75 ሳንቲም ነበር፡፡ በፍጥነት እየጨመረ የመጣው የሕትመት ዋጋ ግን የጋዜጦችን የመሸጫ ዋጋ ከአንድ ብር ጀምሮ ሽቅብ እያለ ወደ አምስት ብር መጥቶ ዛሬ የደረሰበት የሕትመት ዋጋ ሲታይ ትክክለኛ ዋጋው ነው ብሎ ለመቀበል ከባድ ሆኖ ይገኛል፡፡

ከ32 እስከ 40 ገጽ ያላቸው መጽሔቶችም ቢሆኑ አንባቢዎችን የሚያስከፍሉት ቢበዛ እስከ ሦስት ብር ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት እስከ 30 ብርና ከዚያም በላይ የሚጠየቅባቸው ሆነው መገኘታቸው እንቆቅልሽ ነው፡፡

 እንደ ጋዜጣና መጽሔቶቹ ሁሉ የመጻሕፍቱም የሕትመት ዋጋ እየተንደረደረ ደራሲያን እንደልብ ማሳተም እንዳይችሉ ያደረገበትን ጊዜ እናስታውሳለን፡፡ ደፍሮ ለማሳተም ትልቅ የገንዘብ አቅም የሚጠይቅ በመሆኑ ብዙዎችን እየተፈታተናቸው ይገኛል፡፡

የማሳተሚያ ዋጋ እየተወደደ መሄድ የሕትመት ኢንዱስሪውን ስለማቀጨጩ  አቤት ሲባልበት የቆየ ነው፡፡ የማሳተሚያ ዋጋ እየናረ መምጣቱ በተደጋጋሚ ሲገለጽና መንግሥትም በወረቀት ውጤቶች ላይ የጣለውን ታክስ ያንሳ አሊያም ይቀንስ የሚሉ ጥያቄዎች ተደጋግመው ቢቀርቡም አወንታዊ ምላሽ አልተሰጠበትም፡፡ ተደጋግሞ ለቀረበው ጥያቄ ከመንግሥት የተሰጠው ምላሽ ‹‹ለወረቀት ድጎማ አይሰጥም›› የሚል ነበር፡፡ በመሆኑም የሕትመት ዋጋ መጋለቡን እንደቀጠለ ይገኛል፡፡

ይህም ሆኖ ግን በሚፈለገው መጠንና ጥራትም ባይሆን፣ ከጊዜ ወዲህ በርካታ መጻሕፍት ለሕትመት ሲበቁ እያየን ነው፡፡ ዋጋቸው አብዛኛውን የኅብረተብ ክፍል ያላማከለ፣ አንድ ገዝቶ ሌላ ለመድገም ቢፈልግ እንኳ የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡

እርግጥ ነው የሕትመት ዋጋው ባይቀንስም፣ በየመንገዱ የሚሸጡልን መጻሕፍት ጀርባ ላይ የሚለጠፈው ዋጋ ግን የመጻሕፍቱን ይዘት፣ የሕትመት ጥራት ደረጃ፣ የሕትመት ዋጋ፣ የደራሲውን ላብና የመሳሰሉትን በቅጡ በመተመን የሚወጣ አይመስልም፡፡ የሕትመት ዋጋ የቱንም ያህል ቢወደድ እንኳ መጻሕፍቱ የሚለጠፍባውን ያህል ዋጋ እንደማያወጡ እየታየ ነው፡፡ የሚወጣላቸው የዋጋ ትመና ግራ ያጋባል፡፡

ከአዙዋሪዎች እጅ የምንገዛው መጽሐፍ፣ በመጽሐፉ የጀርባ ሽፋን በተገለጸው ዋጋ መሠረት ሳይሆን በድርድር እስከ ግማሽ በሚቀንስ ዋጋ እየሆነ ነው፡፡ በቀደመው ጊዜ ዋጋው ይደለዝና ይፋቅ ነበር፡፡

አሁን ግን 150 ብር እንዲሸጥ በጀርባው የተጻፈበት መጽሐፍ እንደ ገዥው ድርድር 100 አሊያም 120 ብር ሊሸጥለት ይችላል፡፡ እንደ ሸማች ዋጋው መቀነሱ ጥሩ ነው ሊባል ይችላል፡፡ ነገር ግን ይህ የዋጋ አተማመንና ሽያጩ የመጻሕፍቱን ዋጋ ውሸታም አድርጎታል፡፡

የመጻሕፍት የመሸጫ ዋጋ በመጻሕፍቱ ሽፋን ላይ ከሰፈረው በታች ሆኖ መሸጡ፣ ከግብር አከፋፈል ጋርም ሊያያዝ ይችላል፡፡ 150 ብር እንደሚሸጥ ተጠቅሶ በ100 ብር ከተሸጠ፣ መንግሥት ባለመብቶቹን ግብር ቢጠይቅ እንዴት ሊስተናዱ ነው፡፡ እንዲህ ያለውን ገበያ ሥርዓት ማስያዝ ግራ ያጋባል፡፡

የሆነ ሆኖ የሕትመት ዋጋ ካልቀነሰ፣ ገበያውም ካልተስተካከለ አስቸጋሪ ነው፡፡ በኢንተርኔትም ቢሆን እኮ መጽሐፍትን ለማንበብ መጀመርያ መጽሐፍ መኖር ስላለበት የሕsትመት ኢንዱስትሪውን ለማጠናከር ግብይቱንም ሥርዓት እንዲይዝ ሁሉም የበኩልን ያድርግ፡፡ ጥያቄውም ተደራጅቶ ይቅረብ፡፡ ሰሚ ከተገኘ ማለት ነው፡፡ አለበለዚያ በዋሾ ዋጋዎች ስንዳረቅ መክረማችን ነው፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት