Friday, May 24, 2024

ሕገ መንግሥታዊነትን የማረጋገጥ ጫናና ዝግጁነት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የ1987 ዓ.ም. የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት ሥራ ላይ ከዋለ 22 ዓመታት አለፉ፡፡ ሕገ መንግሥቱ ከመሠረታዊ መብቶች ጋር ስምሙ የሆነ የሕግና የፖለቲካ ሰነድ እንደሆነ ብዙዎች ቢስማሙም፣ በተግባር ላይ ስለመዋሉ ወይም ሕገ መንግሥታዊነቱ ስለመረጋገጡ፣ ወይም ለሰብዓዊ መብት መረጋገጥ ዋስትና የመሆኑ ጉዳይ ግን አወዛጋቢ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ሕገ መንግሥት የአንድ መንግሥታዊ ሥርዓት መሠረታዊ ሕግ በመሆኑ፣ በአንድ አገር መንግሥትና ሕዝብ መካከል ያለውን የመብትና የግዴታ ግንኙነት የሚወስን፣ የሕግን ልዕልና የሚያረጋግጥ፣ ለማንኛውም ሥልጣን ገደብ የሚያበጅ፣ በዓበይት የመንግሥት አካላት መካከል የሥልጣን ክፍፍልን የሚያደርግ፣ በአሠራራቸውም ላይ ቁጥጥርን የሚያሰፍን፣ የዜጎችን መብቶችና ነፃነቶች የሚያረጋግጥና ግዴታዎችንም የሚጠቁም መሠረታዊ ሰነድ ነው:: የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ከቀደሙት ሕገ መንግሥቶች በበርካታ መሥፈርቶች ፈጽሞ የተሻለ ቢሆንም፣ ከተገለጸው ተቀባይነት ካለው የሕገ መንግሥት ትርጉም አንፃር ከታየ ግን በርካታ ጉድለቶች እንዳሉበት የብዙዎች እምነት ነው፡፡  

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአገሪቱ ከተከሰተው የፖለቲካ ቀውስ ጋር በተያያዘ ሕገ መንግሥቱና ተፈጻሚነቱ በተደጋጋሚ ሲነሱ ተስተውሏል፡፡ በአንድ በኩል አመፅና ተቃውሞው የተቀሰቀሰው ከመሬት ጋር የተያያዙትን ጨምሮ ሕገ መንግሥታዊ መብቶች ተጥሰዋል በሚል ነው፡፡ በሌላ በኩል በሕገ መንግሥቱ የተደነገጉ መሠረታዊ መብቶችን መፈጸም የፖለቲካ ምኅዳሩንና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሒደቱን እንደሚያሻሽለው ክርክር ይቀርባል፡፡

በተመሳሳይ አንዳንዶች ከሕገ መንግሥቱ ዲዛይንና ይዘት አኳያ ማሻሻያ ሲጠይቁ በተደጋጋሚ ተሰምተዋል፡፡ ከዚሁ አንፃር ገዥው ፓርቲና አገር አቀፍ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የፖለቲካ ምኅዳሩን በተለያየ መንገድ ለማሻሻል እያደረጉ ባለው ድርድር፣ ሕገ መንግሥታዊ መሠረት ያለው የአብላጫ ድምፅ የምርጫ ሥርዓት በድብልቅ የምርጫ ሥርዓት እንዲቀየር መስማማታቸው ይታወሳል፡፡

በተጨማሪም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝም ጥናት ማዕከል ኃላፊና በንፅፅራዊ ፌዴራሊዝም ጥናት ከተቀዳሚ ኤክስፐርቶች መካከል አንዱ የሆኑት አሰፋ ፍስሐ (ዶ/ር)፣ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየጎለበቱ ከመጡ አዳዲስ ጉዳዮች መካከል በፌዴራል ግዛት፣ በአናሳዎች መፈናቀልና በፌዴራል ፖሊስና በመከላከያ ሠራዊት አባላት የክልል ሥምሪት ላይ የክልሎች ፈቃድ መቼ መጠየቅ እንደሚኖርበት ዳግም የተነሱት ሕገ መንግሥታዊ ክርክሮች ተጠቃሽ እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ላይ የተመሠረተ የውሳኔ አሰጣጥ መርህን ጠብቆ የማቆየት ጉዳይ፣ የማይገረሰስ የገዥው ፓርቲ ምሰሶ እንደሆነ የፓርቲው ሊቀመንበርና የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡ የፓርላማው አፈ ጉባዔ አቶ አባዱላ ገመዳ ከሥልጣን ለመልቀቅ መፈለጋቸውን በይፋ ከገለጹ በኋላ፣ የሕዝባቸውንና የድርጅታቸውን ክብር ለማስመለስ እንደሚታገሉ መግለጻቸውም ይታወቃል፡፡ ‹‹አቶ አባዱላ አሁንም ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነትን ጥሰዋል ማለት አይደለም፡፡ መልቀቂያቸውን አስመልክቶ ድርድር ላይ ነን፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ድርጅቱ በወሰነው መሠረት የመሄድ ግዴታ አለባቸው፤›› ብለዋል፡፡ ይሁንና ተቺዎች ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት በሕገ መንግሥቱ ከተካተቱ መሠረታዊ የዴሞክራሲያዊ ውሳኔ አሰጣጥ እሴቶችና መርሆዎች ጋር አብሮ እንደማይሄድ ይከራከራሉ፡፡

ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ጋዜጣዊ መግለጫ ቀደም ብሎ የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ባደረገው ጉባዔ መጠናቀቂያ ላይ ከወጣው የአቋም መግለጫ ነጥቦች መካከል አንዱ፣ ኦሕዴድ ሕገ መንግሥቱ ሳይሸራረፍ እንዲተገበር ለመታገል ቁርጠኛ እንደሆነ ያትታል፡፡ ከእነዚህ ሁነቶች በኋላ በድንገት የመጣው ነገር፣ ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት የሰላማዊ የተቃውሞ ስብሰባ መከልከልን ጨምሮ በአገሪቱ የተለያዩ የፀጥታ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ማሳለፉ ነው፡፡ የዚህ ውሳኔ ሕገ መንግሥታዊነት ላይ ጥያቄዎች መነሳታቸውን ቀጥለዋል፡፡ ከቀናት በፊት የኦሮሚያ ፍትሕ ቢሮ ተመሳሳይ ጥያቄ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡

መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት ሕገ መንግሥቱን ተግባራዊ እንዳያደርጉ የሚገድቡ በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም፣ በርካታ የሕገ መንግሥት አጥኝዎች የፌዴሬሽን ምክር ቤትና የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ አደረጃጀት፣ እንዲሁም ሥልጣንና ተግባር ዋነኛው የችግሩ ምንጭ እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡

ይኼው ሐሳብ በመቐለ ከተማ ዘማርያስ ሆቴል ከጥቅምት 27 እስከ ኅዳር 2 ቀን 2010 ዓ.ም. በግራዝ ዩኒቨርሲቲ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰብዓዊ መብት ማዕከል፣ በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲና በመቐለ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት በጋራ በተዘጋጀውና በሕገ መንግሥታዊነትና በሰብዓዊ መብት ላይ ባተኮረው የፖሊሲ የውይይት መድረክ ላይ ተንፀባርቋል፡፡

በሕገ መንግሥቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሚልኳቸው አባላት የሚወከሉበት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሕገ መንግሥቱን የመተርጎም ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ ከአባላቱ ስብጥርና አመራረጥ ሥነ ሥርዓት አኳያ ምክር ቤቱ የፖለቲካ ተፅዕኖ ያረፈበትና ነፃ ያልሆነ ተቋም ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ክልሎችንና የፌዴራል መንግሥቱን የሚያስተዳድረው ፓርቲ አባላት በምክር ቤቱ አባል መሆናቸው ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ የክልል ፕሬዚዳንቶች የምክር ቤቱ አባል መሆን ጀምረዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ሕገ መንግሥቱን የመተርጎም ሥልጣን ለምክር ቤቱ ሊሰጥ አይገባም ነበር ብለው የሚከራከሩ በርካቶች ናቸው፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ይታገዛል፡፡ እርግጥ ጉባዔው የውሳኔ ሐሳብ ለምክር ቤቱ ከመስጠት የዘለለ የወሳኝነት ሚና የለውም:: አጣሪ ጉባዔው ደግሞ በአባልነት የያዛቸው አሥራ አንድ አባላት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅራቢነት በሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት የሚሾሙ፣ በሙያ ብቃታቸውና በሥነ ምግባራቸው የተመሰከረላቸው ስድስት የሕግ ባለሙያዎችና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከአባላቱ መካከል የሚወክላቸው ሦስት ሰዎች የፖለቲካ ተጋላጭነታቸው ግልጽ ቢሆንም፣ አብዛኛዎቹ ቢያንስ (ሙሉ በሙሉም ሊሆን ይችላል) የሕግ ባለሙያዎች በመሆናቸው የሙያ ድጋፍ ለምክር ቤቱ ለማቅረብ ብቃቱ እንዳላቸው ይታመናል፡፡

ነገር ግን የአጣሪ ጉባዔው አባላት የትርፍ ጊዜ ሠራተኞችና በዓመት ሁለት ጊዜ ብቻ የሚሰበሰቡ መሆናቸው፣ በተቋሙ ውጤታማነት ላይ ጉልህ ተፅዕኖ መፍጠሩ በተደጋጋሚ የተገለጸ ጉዳይ ነው፡፡

ከእነዚህ ሁለት ተቋማት ጋር በተያያዘ በሕገ መንግሥቱ ዲዛይንና ይዘት ላይ የሚነሳው ጥያቄ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ተቋማቱ ንቁ እንቅስቃሴ ያደርጉ ነበር ማለት ያዳግታል፡፡ ከሰብዓዊ መብት ጋር በተያያዘ የሚቀርቡ የግለሰብ ቅሬታዎች በጣም ጥቂት ነበሩ፡፡ በዚህም የተነሳ ሰብዓዊ መብትን ከማስፈጸም አንፃር የተቋማቱ ሚና እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም፡፡

ይሁንና ባለፉት ሦስት ዓመታት ለተቋማቱ የሚቀርቡ ጉዳዮች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው፡፡ አብዛኛዎቹ ቅሬታዎችም ከሰብዓዊ መብት ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ በመቐለ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት መምህራን ወ/ት ተጓዳ አለባቸውና አቶ ገብረ መስቀል ኃይሉ በአጠቃላይ 2,610 ጉዳዮች መቅረባቸውንና አጣሪ ጉባዔው ከ1,800 በላይ ጉዳዮች ላይ እንደወሰነ፣ 44 ጉዳዮች ላይ የሕገ መንግሥት ትርጉም እንደሰጠ፣ 1,760 ጉዳዮችን ውድቅ እንዳደረገ፣ እንዲሁም 806 ጉዳዮች ደግሞ በእንጥልጥል ላይ እንዳሉ ጠቅሰዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል 807 ጉዳዮች የቀረቡት ባለፉት ሦስት ዓመታት እንደነበርና በ2008 እና በ2009 ዓ.ም. ብቻ በ25 ጉዳዮች ላይ ውሳኔ እንደተሰጠም አመልክተዋል፡፡

በሕገ መንግሥቱ ላይ በርካታ የምርምር ሥራዎችን ያሳተሙት ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር)፣ በፌዴሬሽን ምክር ቤትና በሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ሥልጣንና ተግባርን በወሰኑ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎች ላይ ጥልቅ የሆነ አካዴሚያዊ ክርክር እንደሚደረግ ይጠቁማሉ፡፡

በዶ/ር ጌዲዮን ሐሳብ የሚስማሙት ዶ/ር አሰፋ ከፍተኛ የፖለቲካ ጠቀሜታ ያላቸውንና ራስን በራስ የማስተዳደር መብትን ያረጋገጡትን ውሳኔዎች በስልጤና በቅማንት ጉዳዮች ላይ ውሳኔ በመስጠት ወሳኝ ሚና ቢጫወትም፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አብዛኛዎቹ ውሳኔዎች ለማዕከላዊ መንግሥት የሚያዳሉ እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡

ወ/ት ተጓዳና አቶ ገብረ መስቀል ሁለቱ ተቋማት ካለባቸው የአደረጃጀት ችግር አንፃር፣ አገሪቱ በሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት እንድትተካቸው አሳስበዋል፡፡

ዶ/ር ጌዲዮን ከ2007 እስከ 2009 ዓ.ም. ድረስ በፌዴሬሽን ምክር ቤት የተወሰኑ 23 ጉዳዮችን በመተንተን አዝማሚያዎችን ያሳዩ ሲሆን፣ በዚህም በመሬት ሽያጭና ልዋጭ ላይ ምክር ቤቱ ጠንካራ አቋም መውሰዱን ጠቅሰዋል፡፡ በተለይ የገበሬዎችን ከመሬታቸው የመፈናቀል ጉዳይ የሚገባውን ትኩረት ሰጥቶ መወሰኑን አመልክተዋል፡፡

ይሁንና ሁለቱም ተቋማት ሕገ መንግሥታዊ ክርክሮችን ወይም ትርጉሞችን የሚያስነሱ ጉዳዮችን ከማያስነሱት ለመለየት፣ ግልጽ የሆኑ የመለያ መሥፈርቶች ፈጥረዋል ለማለት አዳጋች እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ለደረሱበት ውሳኔ ወይም ድምዳሜ በቂ ማብራሪያና ትንታኔ እንደማይሰጡ ተችተዋል፡፡ በውሳኔዎቹ የሚጠቀሱት መብቶች የተፈጻሚነት ወሰን፣ አላባውያን፣ የመብቱ ተጠቃሚዎችና የግዴታዎቹ ተሸካሚዎች ማንነት፣ እንዲሁም ተቀባይነት ያላቸው ገደቦች በአግባቡ እንደማይካተቱም ጠቁመዋል፡ የመብት ጥሰት ከሌለ ሕገ መንግሥቱ ትርጉም አያስፈልገውም የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ መያዛቸውንና ለመልስ ሰጪ ተከራካሪዎች ሐሳባቸውን የማቅረብ ዕድል እንደማይሰጡም አመልክተዋል፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሚቀርቡ ሕገ መንግሥታዊ ቅሬታዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ቢጨምርም፣ ከሕገ መንግሥቱ ጋር እንደማይጣጣሙ የሚነገርላቸው አዋጆችና በተደጋጋሚ ጊዜ ይፈጸማሉ የሚባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ፣ ወደ እነዚህ ተቋማት ቅሬታ እንደማይቀርብ ዶ/ር ጌዲዮን  ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰብዓዊ መብት ማዕከል ዳይሬክተር ወንድማገኝ ታደሰ (ዶ/ር) በተመሳሳይ ይህንኑ ችግር ያስተዋሉ ሲሆን፣ አዝማሚያው የተፈጠረው ከዚህ ቀደም የቀረቡ ተመሳሳይ ጉዳዮች ውድቅ በመሆናቸው እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡ ‹‹ብዙ ጊዜ በፓርላማው አዋጆችና በአስፈጻሚው አስተዳደራዊ ውሳኔዎች ላይ ቅሬታ አይቀርብም፡፡ ሲቀርብ ደግሞ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ችግር የለባቸውም ብሎ ይወስናል፡፡ ይህ አዝማሚያ መሰል አቤቱታዎች ማቅረብን የሚያቅብ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ሁለቱ ተቋማት ካለባቸው የዲዛይንና የአፈጻጸም ውስንነቶች በተጨማሪ ከፍርድ ቤቶች ጋር ያላቸው የሥልጣን መደራረብና አሻሚነት ሌላ ተግዳሮት ፈጥሯል፡፡ ዶ/ር አሰፋ ይህን ችግር ለመቅረፍ ፍርድ ቤቶች ተነሳሽነት ሊወስዱ እንደሚገባ ይከራከራሉ፡፡ ‹‹ሕገ መንግሥቱን የመተርጎም የመጨረሻ ሥልጣን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ወይም የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ነው፡፡ ይሁንና ከዚያ በመለስ ፍርድ ቤቶች ሕገ መንግሥቱን ማስፈጸም ይችላሉ፡፡ ምንም ዓይነት ትርጉም ቢሰጡ የመጨረሻ ሊሆን አይችልም፡፡ በፍርድ ቤቶች ውሳኔ ደስተኛ ያልሆነ ማንኛውም አካል ጉዳዩን ወደ እነዚህ ተቋማት መውሰድ ይችላል፤›› ብለዋል፡፡

ዶ/ር ወንድማገኝ ግን የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች በቀጥታ እንደማይፈጸሙ አመልክተዋል፡፡ ጥሰት ሲፈጸም ራሱ የሚያስከትለው ቅጣት በአብዛኛው እንዳልተቀመጠ ጠቁመዋል፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎችን ማስፈጸሚያ ተብለው የሚወጡ ዝርዝር ሕጎችም በተግባር ይበልጥ አሳሪ መሆናቸው ችግሩን እንዳባባሰው አስገንዝበዋል፡፡ ‹‹ምንም መብት መርህ የሌለው ይመስል በልዩ ሁኔታዎች የተሞሉ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡

ሌላው ዶ/ር ወንድማገኝ እንደ መሠረታዊ ችግር ያዩት ጉዳይ ሕጎችን እየመረጡ ተግባራዊ ማድረግ ነው፡፡ ሕጎች የተወሰኑ ሰዎችን ለመጥቀም፣ ሌሎችን ደግሞ ለመጉዳት ጥቅም ላይ ሊውሉ እንደሚችሉ የገለጹ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ በርካታ ሕጎች የተወሰኑ ሰዎችን ለመጉዳት ወጥተዋል እንደሚባሉ አመልክተዋል፡፡ ለአብነትም የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁን ጠቅሰዋል፡፡ በአገሪቱ ለሕግ የበላይነት ትንሽ ቦታ ቢኖርም፣ መንግሥት ግን የሕገ መንግሥታዊ መብቶችን ትርክት በመጠቀም የሚፈልገውን ጉዳይ ለማሳካት ሲጠቀምበት በየዕለቱ እንደሚስተዋል ተከራክረዋል፡፡

ዶ/ር ወንድማገኝ በአጠቃላይ ለሕገ መንግሥቱ፣ ለሕግ የበላይነት፣ በሕግ ፊት እኩል ሆኖ መቆጠርና ፍርድ ቤቶችን ጨምሮ ለተቋማት ነፃና ገለልተኝነት ያለው ዝቅተኛ ቁርጠኝነት  የአገሪቱ ሥርዓት መለያዎች መሆናቸውንም አስገንዝበዋል፡፡                 

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የሥልጣን ምንጭ ሕዝብ መሆኑን የሚገልጹ፣ ሉዓላዊነት የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መሆኑን የሚገልጹ፣ የሕገ መንግሥቱን የበላይነት የሚጠቅሱ፣ የሰብዓዊ መብት መከበር የተገለጸበት፣ የመንግሥትና የሃይማኖት መለያየት በግልጽ የተገለጸበት፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት ተጠያቂነትን የሚያሳይ፣ ለመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ሽፋን የሚሰጥ፣ ለባህላዊና ለሃይማኖታዊ ሕጎች ዕውቅና የሚሰጥ፣ ሰብዓዊ መብቶች በዓለም አቀፍ ስምምነቶች መሠረት እንዲተረጎሙ የሚገልጹ ድንጋጌዎችን ያካተተ ነው::

እነዚህ ከላይ የተገለጹት መብቶችና ነፃነቶች ሁሉ በተግባር ተፈጽመዋል ማለት ግን አይቻልም ያሉት ዶ/ር ወንድማገኝ፣ መንግሥት የሕገ መንግሥቱን መንፈስና ቃላት በተመቸው ሁኔታ እየቀለበሰ እንደመጣ ይተቻሉ፡፡ ይሁንና ለግለሰቦችና ለቡድኖች መብቶች መከበር እየቀረቡ ያሉ ጥያቄዎች ከዕለት ዕለት እየጎለበቱ መምጣታቸውን ያለፉት ሦስት ዓመታት የአገሪቱ ልምድ በግልጽ እያሳየ፣ ይህን ጤናማ ያልሆነ አዝማሚያ መቀጠል አደገኛ እንደሆነ የሚያስጠነቅቁት በርካቶች ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -