የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ለኮንዶሚኒየም ቤቶች ፕሮጀክቶች የሚቀርቡ ግብዓቶችን ተቋራጮች እንዲያቀርቡለት የሚያስችለውን የመጨረሻ ዝግጅት እያደረገ ነው፡፡
ከአሁን ቀደም ቢሮው በሥሩ ባቋቋመው የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት አማካይነት አብዛኛዎቹ ግብዓቶች ይቀርቡለት ነበር፡፡ በአዲሱ አሠራር መሠረት ግን ግብዓቶቹ በተቋራጮች እንዲቀርቡ ይደረጋል ተብሏል፡፡
ከአሁን ቀደም ይህ አዲስ አሠራር በከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር በኩል ውሳኔ አግኝቶ በፌደራል ደረጃ ውይይት የተደረገበት ሲሆን፣ የአሁኑ በአዲስ አበባ በኩል የሚደረገው ውይይት ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ያተኩራል፡፡
አዲሱ አሠራር የመጣው በኮንዶሚኒየም ቤቶች ላይ ያለውን መዘግየት ለማስቀረት እንደሆነ፣ የፕሮጀክቱ ጽሕፈት ቤቱ ኃላፊዎች ይገልጻሉ፡፡
‹‹አዲሱ አሠራር በፕሮጀክቶቹ ላይ ያለውን መዘግየት በመጠኑም ቢሆን ይቀርፋል ተብሎ ይጠበቃል፤›› ሲሉ የፕሮጀክቱ ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ግርማ መኮንን ገልጸዋል፡፡ የቤቶች ፕሮጀክት ከተጀመረባቸው ከአሥር ዓመታት ወዲህ 175,000 ቤቶች ለተጠቃሚዎች ተላልፈዋል፡፡ ነገር ግን ይህ ቁጥር በአሁኑ ጊዜ ተመዝግበው ከሚቆጥቡት አንድ ሚሊዮን ያህል የአዲስ አበባ ነዋሪዎች አንፃር፣ የፕሮጀክቱ ፍጥነት አሁንም ከሚፈለገው በታች እንደሆነ ይነገራል፡፡
በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ወደ 350,000 ቤቶች ለማስተላለፍ ታቅዶ ነበር፡፡ 160,000 የሚሆኑ ነዋሪዎች ለ40/60 እየቆጠቡ ሲሆን፣ ይህን ፕሮጀክት የሚያስተዳድረው የቁጠባ ቤቶች ኤጀንሲ አንድም ቤት ለተመዝጋቢዎች አላስተላለፈም፡፡
ከአሁን ቀደም ለቤቶች ፕሮጀክት የሚውሉ የአርማታ ብረቶች፣ ሴራሚክስ፣ ሲሚንቶ፣ እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ግብዓቶች በፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ በሚደረግ ጥቅል ግዢ ይቀርቡ ነበር፡፡ በአጠቃላይ 520 የሚሆኑ ዝርዝር ግብዓቶች በፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ይቀርቡ ነበር፡፡
በአዲሱ አሠራር ከብረት፣ ከሲሚንቶና ከኤሌክትሪክ ዕቃዎች ውጪ ያሉት ግብዓቶች በተቋራጮች እንዲቀርቡ ይደረጋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ወደ 2,500 የሚጠጉ የግንባታ ተቋራጮች በኮንዶሚኒየም ፕሮጀክቶች ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡
ከአሁን ቀደም በነበረው ጥቅል ግዢ መንግሥት ከአሥር በመቶ እስከ 15 በመቶ በተናጠል ከሚገዛው የዋጋ ቅናሽ ነበረው፡፡ በአዲሱ አሠራር የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ የዋጋ ጭማሪን ለማስቀረት አጥንቶ በሚያቀርበው ዋጋ የግንባታ ተቋራጮች እንዲያቀርቡ ይደረጋል፡፡
‹‹አሁን የሚቀረን ከተቋራጮቹ ጋር ውይይት ማድረግና ውሳኔያችንን ለሚኒስቴሩ ማቅረብ ነው፤›› ሲሉ አቶ ግርማ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
በተቋራጮች በኩል የሚቀርቡ ግብዓቶች ላይ ጽሕፈት ቤቱ የጥራት ቁጥጥር ያደርጋል፡፡ ከዚህም ጋር በተያያዘ እንደ ጠጠርና አሸዋ ያሉ ግብዓቶች በጥቃቅንና አነስተኛ በተደራጁ ድርጅቶች እየቀረቡ ይቀጥላሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ 13,000 የሚጠጉ በጥቃቅንና አነስተኛ የተደራጁ ኢንተርፕራይዞች ይገኛሉ፡፡
በተያዘው የበጀት ዓመት 15 ቢሊዮን ብር ለቤቶች ፕሮጀክት መንግሥት መድቧል፡፡ ከዚህም ጋር በተያያዘ በተጀመረው አዲስ የአከፋፈል ሥርዓትና በተፈጠረው የክፍያ መዘግየት የሥራ ተቋራጮችና ግብዓት አቅራቢዎች ሲያማርሩ ይሰማሉ፡፡