Thursday, June 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ጥረት የባህር ዳርና ኮምቦልቻ ጨርቃ ጨርቅን ለመጠቅለል የሦስት ወራት ማራዘሚያ ተፈቀደለት

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአማራ ክልላዊ መንግሥትን ከሚያስተዳድረው ከብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ትስስር ያለው ጥረት ኮርፖሬት፣ የባህር ዳርና የኮምቦልቻ ጨርቃ ጨርቅ አክሲዮን ማኅበራትን ጠቅልሎ ለመያዝ የሚያስቸለውን ሙሉ ክፍያ ለመክፈል የሦስት ወራት ጊዜ እንዲሰጠው ያቀረበው ጥያቄ ተፈቀደ፡፡

ከአሁን ቀደም ድርጅቱ ለሁለቱ አክሲዮን ማኅበራት 765 ሚሊዮን ብር የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ባወጣው ጨረታ እንዳቀረበ ይታወሳል፡፡ በዚህም መሠረት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በሰጠው ውሳኔ ፋብሪካዎቹ ለጥረት እንዲተላለፉ ተወስኖ ነበር፡፡

ሚኒስቴሩ ጨረታውን ካወጣ በኋላ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ጣልቃ ገብነት ጠይቆ ነበር፡፡ ይህም የሆነው በወቅቱ ጥረት ለሁለቱም ፋብሪካዎች አቅርቦት የነበረው ዋጋ ሚኒስቴሩ አቅርቦ ከነበረው ዋጋ በታች ሆኖ ስለተገኘ ነበር፡፡

በጊዜው ጥረት ለኮምቦልቻ ጨርቃ ጨርቅ 450 ሚሊዮን ብር፣ ለባህር ዳር ጨርቃ ጨርቅ ደግሞ 315 ሚሊዮን ብር አቅርቦ ነበር፡፡

ከአራት ዓመት በፊት የኮምቦልቻ ጨርቃ ጨርቅ አጠቃላይ ቋሚ ሀብት 401 ሚሊዮን ብር የነበረ ሲሆን፣ በተመሳሳይ ጊዜ ግማሽ ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ የፋብሪካውን አቅም ለማሳደግ በመንግሥት ወጪ ተደርጓል፡፡ በ1970ዎቹ የተመሠረተው ኮምቦልቻ ጨርቃ ጨርቅ ባለፈው ዓመት ከወጪ ንግድ 1.95 ሚሊዮን ዶላር አግኝቷል፡፡

በተመሳሳይ ጊዜ የባህር ዳር ጨርቃ ጨርቅ ሀብት 505 ሚሊዮን ብር ገደማ ነበር፡፡ በ1953 ዓ.ም. የተመሠረተው የባህር ዳር ጨርቃ ጨርቅ ከአሥር ዓመት በፊት በቻይና ባለሀብቶች በኪራይ ለ18 ወራት ተይዞ ነበር፡፡ በ2004 ዓ.ም. መንግሥት 500 ሚሊዮን ብር ገደማ ወጪ በማውጣት ፋብሪካውን አሻሽሎታል፡፡

በዚህም መሠረት ጥረት ባቀረበው ዋጋ ፋብሪካዎቹን እንዲረከብ ተፈቅዶለታል፡፡ ይህንንም ተከትሎ ሚኒስቴሩ እንዲረከብ የጠየቀ ቢሆንም፣ ጥረት ግን የሦስት ወራት ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡

የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት ጥረት ኮርፖሬት ገንዘቡን እስኪያሰባስብ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡ ጥረት ኮርፖሬት በ1987 ዓ.ም. ከብአዴንና ከ25 መሥራች አባላት በተገኘ 26.1 ሚሊዮን ብር ነው የተመሠረተው፡፡ በአሁን ጊዜ በሥሩ ዳሸን ቢራን ጨምሮ 18 ኩባንያዎች ይገኛሉ፡፡

ጥረት ኮርፖሬት በአቶ ታደሰ ካሳ ዋና ሥራ አስኪያጅነት ይመራል፡፡ ሪፖርተር አቶ ታደሰን አግኝቶ ለማነጋገር ያደረገው ሙከራ አልተሳካም፡፡

‹‹እስከ ሦስት ወራት ድረስ እንጠብቃቸዋለን፤›› ሲሉ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሚኒስትር የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ወንድአፍራሽ አሰፋ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በቅርቡ አቶ ታደሰ ለአማራ ክልል የብዙኃን መገናኛ ኤጀንሲ ጥረት ባሳለፈው የአውሮፓውያን ዓመት ሰባት ቢሊዮን ብር የሚጠጋ የምርት ሽያጭ ማከናወኑን ገልጸው ነበር፡፡ በተያያዘም ጥረት የተጣራ 442.8 ሚሊዮን ትርፍ ማግኘቱ ተገልጿል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2017 700 ሚሊዮን በሚጠጋ ብር ከመንግሥት የገዛቸውን የባህር ዳርና የኮምቦልቻ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ጨምሮ፣ ሌሎች የታቀዱ ፋብሪካዎችን ወደ ሥራ ለማስገባት እየተዘጋጀ መሆኑን ተናግረው ነበር፡፡

ከአሁን ቀደም ሚኒስቴሩ ሁለቱን ፋብሪካዎች ወደ ግል ይዞታ ለማስተላለፍ ባወጣው ጨረታ የግል ባለሀብቶች ጥረት ካቀረበው ያነሰ ዋጋ ሰጥተው እንደነበር ይታወሳል፡፡ በዚህም አቶ ድንቁ ደያሳ የተባሉ ባለሀብት ሁለቱን ፋብሪካዎች ለመግዛት 606 ሚሊዮን ብር አቅርበው የነበረ ቢሆንም ሚኒስቴሩ ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡ ጥረት ሁለቱን ኩባንያዎች በሥሩ ለማድረግ ፋብሪካዎቹ ያለባቸውን ዕዳ አብሮ ይረከባል፡፡

 

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች