Monday, June 24, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ራሱን ይፈትሽ ወይም ይፈተሽ!

በመንሹ ስ.

መንግሥት ዜጎች ቆጥበው በተመጣጣኝ ዋጋ የተሻለ መጠለያ እንዲያገኙ በዘረጋው መርሐ ግብር መሠረት፣ ባለፉት አሥርት ዓመታት ብዙዎች የቤት ባለቤት ሆነዋል፣ እየሆኑም ነው፡፡ ለዓመታት በተከማቸ የቤት እጦት ምክንያት፣ በተጨማሪም አዳዲስ ቤት ፈላጊዎች በመፈጠራቸው መንግሥት የኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታን በአዳዲስ ሳይቶች በየዓመቱ ቁጥራቸውንም በመጨመር በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡ ጎን ለጎንም በእያንዳንዱ የልማት መንደር አስፈላጊውን ተያያዥ የመሠረተ ልማት ማለትም መንገዶች (ዋናና የውስጥ ለውስጥ)፣ የፍሳሽ ድሬኔጅ መስመሮች፣ የኤሌክትሪክና የውኃ አገልግሎቶች ለማቅረብ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ዜጎችም ከዕለት ጉርሳቸው ቀንሰው በ10/90፣ በ20/80 አንዲሁም በ40/60 መርሐ ግብሮች ተመዝግበው በመቆጠብ ከዛሬ ነገ ይደርሰናል፣ የቤት ችግራችን ይቀረፋል በሚል በጉጉት በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ፡፡

ፕሮጀክቶችን ለማስፈጸም የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ያለው ብቃት ሲፈተሽ

በቅርቡ በሚሊንየም አዳራሽ ለሦስት ቀናት በተደረገው አዲሱ የኮንስትራክሽን ፖሊሲ የባለድርሻ አካላት ውይይትና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስብሰባ ላይ፣ ቁጥራቸው ከ3,500 እስከ 4,000 የሚደርሱ የዘርፉ ተዋንያን በተወካዮቻቸው አማካይነት ተገኝተው ነበር፡፡ በዚህ ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ያነሱትን ነጥብ መጥቀስ ይገባል፡፡ ‹‹የአንድ ተቋም የማስፈጸም አቅም ግንባታ ሲባል የግብዓት አቅርቦት አንዱ ቢሆንም፣ የተቋሙ ሙያተኞችና የሥራ መሪዎች ችሎታና ክህሎት፣ የሥራ ተነሳሽነት፣ የሙያ ሥነ ምግባርና የማስፈጸም አቅም ዋና ዋና ምሰሶዎች (Pilars) ናቸው፤›› በማለት አስቀምጠው ነበር፡፡ ይህ እሳቸው ያነሱት ነጥብ እውነተኛና እንዳሉትም አንድ ውጤታማ ሥራ ለመሥራት ጠቃሚ ነው፡፡ ሥራዎች ሳይጀመሩም ሆነ ከተጀመሩ በኋላ በሒደት ደረጃ በደረጃ እየተፈተሹ መስተካከል ያለባቸው እንዲሰተካከሉ እየተደረጉ፣ በሥራው ሒደት የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችም ለሌሎች መተላለፍ ሲችሉ ብቻ ነው የተሳካ ሥራ ማከናወን የሚቻለው፡፡

የቤቶች ልማት አሁን ባለው ቁመና ባለፉት አሥር ዓመታት ባከናወናቸው ተግባራት ግን የጥራት፣ የተነሳሽነት፣ የሙያ ሥነ ምግባር፣ የፈጻሚዎችና የመሥሪያ ቤቱ ሙያተኞች ችሎታና ክህሎት እጅግ አጠያያቂ ከመሆኑም በላይ፣ ከድጡ ወደ ማጡ እየሆነ ነው፡፡ ዜጎች ለዓመታት ጠብቀው በደረሳቸው ቤት ላይ በሚያጋጥማቸው የጥራት ማነስ የተነሳ ለተጨማሪ ወጪ በመዳረጋቸው፣ እንዴት አድርገው ቢሠሩት ነው ተብሎ ከመነጋገሪያነት በዘለለ ለትልቅ ምሬት መዳረጋቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡

የጥራት ችግሩ ከግንባታው ስትራክቸር ይጀምራል፡፡ የደረጃ መወጣጫዎች በወጥነት እንዳያደናቅፉ አለመገንባት፣ የመፀዳጃ ቤት መስመሮች አዘረጋግ ችግር፣ የኤሌክትሪክ መስመሮችና መቆጣጠሪያዎች ዝርጋታ በተገቢው ማቴሪያልና የሙያ ግብዓት አለመከናወን፣ የግድግዳ ብሎኬቶች ጥራት ችግር፣ የሚገነቡበት የሲሚንቶና የአሸዋ ውህድ (Mix proportion) ትክክል አለመሆን፣ ውኃ ያለማጠጣት፣ የሶሌታና የግድግዳ ወጣ ገባነት፣ የሴራሚክ ሥራዎች በአግባቡ አለመሠራት፣ የበርና የመስኮት ሥራዎች ጥራት እጅግ ዝቅተኛ መሆን፣ የጣሪያ ማፍሰስ፣ የፍሳሽ መስመር ዝርጋታ (Drainage Network) ችግር፣ የጎርፍ መከላከያ ፉካዎችና ግንቦች (Ditch and Retaining Walls) አለመኖር ወይም በአግባቡ አለመሠራት እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡

ለመሆኑ በአነስተኛ አቅም (Low Cost) የሚገነቡ ቤቶች ማለት የጥራት ደረጃቸው የወረደ ማለት ነው እንዴ? በአነስተኛ ካፒታል የሚገነቡ ቤቶች ፕሮጀክቶች (Low Cost Housing Projects) ወጪ ቆጣቢ እንዲሆኑ የሚያስችላቸው ጽንሰ ሐሳብና የአሠራር ብልኃት ምንድነው?

አንዳንድ ነጥቦችን እናንሳ

 1. በዝቅተኛ ወጪና በብዛት የሚሠሩ ቤቶች ወጪ ቆጣቢ የሚያደርጋቸው አንደኛው ዘዴ በ(Modular system) በተደጋጋሚ የሚሠሩ የግድግዳ፣ የወለልና የመሳሰሉትን ሥራዎች ወጥነት ባለው መንገድ ቀለል ባለ የአሠራር ዘዴ (Methodology) ማከናወን ነው፡፡ ለዚህም በፓይለት ፕሮጅክቶች ሙያተኞችን ባሳተፈ ሁኔታ ሠርቶ በማሳየት፣ በሥራው ላይ ለሚሳተፉ ሌሎች ሙያተኞች ትክክለኛ የሥራ ላይ ሥልጠና መስጠት ተገቢ ነው፡፡  
 2. ሌላው ለምሳሌ ዘጠኝ ሜትር ካሬ የሆነን ክፍል ለመሥራት ብንፈልግ 3×3 ሜትር ካሬ ወይም 4.5×2 ሜትር ካሬ ወይም 1×9 ሜትር ካሬ በማለት የተለያየ ‹‹ፓተርን›› ልንከተል አንችላለን፡፡ ይህንን ዘጠኝ ሜትር ካሬ አስፈላጊ ቦታ ለመገንባት የምንጠቀምቸው የጣራ፣ የግድግዳና የወለል ማቴሪያሎች በርዝመት፣ በወርድና በከፍታ የሚባዙ (Lateral space) የሚባሉ ሲሆኑ፣ የምንፈልገውን ዘጠኝ ሜትር ካሬ ለመገንባት የትኛው ‹‹ፓተርን›› ወጪ ቆጣቢ ነው ብሎ በጥልቀት ማሰብን ይጠይቃል፡፡
 3. ሌላው በጋራ ቤቶች ላይ የምንጠቀምባቸው ኮሪደሮችና ደረጃዎች (Circulation and common spaces) ወጪ ቆጣቢና ተገቢውን አገልግሎት በሚሰጡ የዲዛይን አማራጮችን በማሰብ መገንባት፣ ሌላው የአነስተኛ ወጪ አገነባብ ዘዴ ነው፡፡  
 4. ከዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ ከዕቃ አቅራቢዎችና ከአምራቾች ጋር በመነጋገር ዘመናዊና ወጪ ቆጣቢ የግንባታ ግብዓቶችን ማሰብ፣ መሞከርና ሙከራውን በተግባር ለማዋል የምርምርና የፓይለት ፕሮጀክቱን ማዘጋጀት ተገቢ ነው፡፡
 5. ፕሮጀክቶችን በታቀደላቸው ጊዜ መፈጸም ወሳኝ ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ባለአራት ፎቅ ሕንፃ ለመገንባት የሚቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ አንድ ዓመት ተኩል ሆኖ እያለ በዕቃ አቅርቦት፣ በክፍያ መዘግየት፣ በውሳኔ አሰጣጥ ዝርክርክነት፣ ኃላፊነት በመውሰድ ፍርኃት፣ በችሎታ ማነስ፣ አድልኦ በመፈጸምና በመሳሰሉት ምክንያቶች መዘግየቶች ተፈጥረው አንዳንድ ፕሮጀክቶች እስከ አራት ዓመት የሚፈጁበት ጊዜ አለ፡፡ ከውጭ በሚገቡ ግብዓቶች ላይ የውጭ ምንዛሪ ለውጥ፣ ለአማካሪዎች በሚከፈል ተጨማሪ ክፍያና በሌሎች ወጪዎች የተነሳ ከዓመት ዓመት የዕጣ ዕድለኞች በሚከፍሉት የቤት ዋጋ ላይ ከአሥር እስከ 20 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን፣ በየዓመቱ የሚወጡ የቤት ግዢ ተመኖችን ማየት ይቻላል፡፡ በመሆኑም ባለፉት አሥርት ዓመታት የታዩ ድክመቶችን በማረም እንዴት ቢደረግ? ምን ብናደርግ? በታቀደለት የጊዜ ሰሌዳ ፕሮጀክቶቻችንን መጨረስ እንችላለን ብሎ ማሰብ ይጠይቃል፡፡
 6. በበጀት ዝግጅት፣ በመሬት ዝግጅት፣ በጨረታ ማውጫ የጊዜ ሰሌዳ፣ ሥራዎችን ለአሸናፊዎች ግምገማ አድርጎ በመስጠት፣ በትክክልና በተመጠነ ሁኔታ በተዘጋጁ የግብዓት አቅርቦት ሰሌዳዎች (Material disbursement Schedule) መሠረት ቀድሞ በመዘጋጀት ማቅረብ፣ ችግሮች ሲከሰቱ በፍጥነት ምላሽ መስጠት፣ በክፍያ ሠርተፊኬት ማፅደቅን አለማዘግየት የመሳሰሉት ፕሮጀክቱን በጊዜው ለማጠናቀቅ ይረዳሉ፡፡ ገንዘቡን እየቆጠበ ቤት ደረሰኝ አልደረሰኝ እያለ ለሚጠባበቀው ዜጋ በተገቢው ጊዜ ለማስረከብና አሁን እየታየ የሚገኘውን የሽያጭ ዋጋ ንረትን ማስቀረት ባይቻል እንኳን ለመቀነስ ይቻላል፡፡

አሁን በምናየው ሁኔታ ግን ወጪ ቆጣቢ ተብለው የሚገነቡት የኮንዶሚኒየም ቤቶች ደረጃቸውን ባልጠበቁ ዕቃዎች (Sub-standardized Materials) ይገነባሉ፡፡ የአሠራር ብልኃቱም (Workmanship) በግድየለሽነት እየተሠራ ያለና በእርግጥ ወጪ ቆጣቢ ነው ወይ? የሚል ጥያቄ የሚያስከትል ነው፡፡ ዜጎች ቆጥበው መንግሥትም ባለው ውስን አቅም በሚበጅተው አገራዊ ሀብት ላይ እየተቀለደ ይመስላል፡፡ በዚህም ከዓመት ዓመት ከመሻሻል ይልቅ ቁልቁል እየተሄደ ነው ያለው፡፡

ለመሆኑ ይህንን  የሚያደርጉት እነማን ናቸው?

አንድ በሙያው መሐንዲስነት የሆነ ባልንጀራዬ በአማካሪ መሐንዲስነት ሲሠራ ከሁለት ዓመት በፊት በካራቆሬ ሳይት ላይ ያጋጠመውንና የነገረኝን ጉዳይ ላካፍላችሁ፡፡ በካራቆሬ ሳይት ላይ ሥራ ላይ እንዲውል በበርካታ የጭነት ተሽከርካሪዎች ተጭኖ የተላከው የጣራ ክዳን ኤጋ ቆርቆሮ በሥራ ዝርዝሩ (Specification) ላይ 0.40 ሚሊ ሜትር መሆን እንዳለበት ተገልጿል፡፡ ወደ ሳይቱ የተላከው ኤጋ ቆርቆሮ ግን በካሊፐር በሚለካበት ጊዜ 0.30 ሚሊ ሜትር ሆኖ ይገኛል፡፡ በመሆኑም የአማካሪ ድርጅቱ መሐንዲሶች ደረጃውን ያልጠበቀ በመሆኑ አንረከብም ብለው መኪኖቹ ይውላሉ፣ ያድራሉ፡፡

በዚህን ጊዜ የቤቶች ልማት ኃላፊ መሐንዲሶች ከዋና መሥሪያ ቤት በመደወል ትረከባላችሁ ተረከቡ፣ አለበለዚያ መኪኖቹ የቆሙበትን ወጪ አማካሪ ድርጅቱ ይከፍላል ከሥራም ይሰናበታል ተብሎ ማስፈራሪያ ይደርሳቸዋል፡፡ በመሆኑም ሥራቸውን ከማጣትና ከቅጣት ለመዳን ተረክበው ሥራው ተሠራ፡፡ ይህንን ለአብነት አነሳሁት እንጂ በየኮንዶሚኒየም ሳይቱ የሚገቡ የግንባታና የማጠናቀቂያ ዕቃዎች ጥራት ጉድለት ላይ ያለው ኪራይ ሰብሳቢነት በጥራት ላይ እያስከተለ ያለው ጉዳት፣ በእርግጥም አሳዛኝና የሚያስቆጭ ነው፡፡ በዚሁ የሙስና መረብ ውስጥ ያሉት ደግሞ የግብዓት አቅራቢዎችና የቤቶች ልማት አድራጊ ፈጣሪ የሥራ ኃላፊዎችና መሐንዲሶች ናቸው፡፡

ሌላው ከዚህ በፊት ደካማ አፈጻጸም ያላቸውን የኮንዶሚኒየም ሥራ ተቋራጮችን ጥቁር መዝገብ ላይ አስፍሮ በሌሎች ግንባታዎች ላይ እንዳይሳተፉ መደረግ ሲገባው፣ በእከክልኝ ልከክልህ እሳቤ እነዚህ የቤቶች ልማት የሥራ ኃላፊዎችና መሐንዲሶች አምና ያበላሸውን ኮንትራክተር ዘንድሮም እንዲያበላሽ አዲስ ሥራ ጀባ ይሉታል፡፡ በምትኩም በሥርዓት የሚሠሩ ሥራ ተቋራጮችን እያንገዋለሉ ከሥራ ያሰናብቷቸዋል፡፡

ኧረ ለመሆኑ ሌላ አገር አለን ወይ? ይህች ከድህነት ለመውጣት በምትውተረተር አገር ላይ መቀለድስ ምን ይባላል?  ከዚህስ የሚገኝ  ብልፅግና ምን ያስደስታል? ስንትስ ዓመት በደስታ ያኖራል? መልሱን ለፈጻሚዎቹ ልተው፡፡

በተጨማሪም የሥራውን ጥራት የሚቆጣጠሩ አማካሪ መሐንዲሶች መረጣና ኮንትራት ላይ የሚፈጸመው ወንጀል አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ በእነርሱ አሠራር ቤተኞች የሚሏቸውን አማካሪ መሐንዲሶች በላይ በላዩ የ40/60፣ የ20/80 እና የ10/90 ፕሮጀክቶችን እየሠጡ ሊቆጣጠሩት ከሚችሉት በላይ ሥራ እያሸከሟቸው ለጥራት ጉድለቱ አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒሰትር ኃይለ ማርያም በሚሊንየም አዳራሽ ስብሰባ ማጠናቀቂያ ላይ፣ ‹‹ከሚያላምጡት በላይ የጎረሱትን ከጀርባቸው መታ በማድረግና በማስተፋት በልካቸው መጉረስ ይገባቸዋል፤›› ያሉትን መጥቀስ አግባብ ይሆናል፡፡ ይሁንና ቢሮ ተከራይተው፣ ሙያተኛ ቀጥረው፣ አስፈላጊውን የመንግሥት ግብር የሚከፍሉና ሥራ የተጠሙ አማካሪዎች እነሱ ያዘጋጁትን የሙስና ግድግዳ (Firewall) በአሳዛኝ ሁኔታ ሳያልፉ እንዲወድቁ እየተደረጉ፣ የጥቀመኝ ልጠቀም የግፍ ፅዋ ሞልቶ እየፈሰሰ ይገኛል፡፡

የመሥሪያ ቤቱ ኃላፊዎች እነዚህን ቤተኛ አማካሪዎች ሥራ ለመስጠት ሲሉ ከዚህ በፊት በእጁ ያለውን ሥራ (80 በመቶ) ያልፈጸመ አማካሪ ድርጅት በአዲስ ጨረታ ላይ አይሳተፍም ብለው ያወጡትን መመርያ በመሻር፣ ይህንኑ መመዘኛ ወደ 70 በመቶ አፈጻጸም ዝቅ እንዲል አድርገዋል፡፡ ከዚህ ባለፈ እነዚህኑ አማካሪዎች አፈጻጸማቸው ወደተባለው (70 በመቶ) ላይ እስኪደርስ ድረስ፣ በአንድ ዓመት  ውስጥ ያወጡዋቸውን ሁለት የአማካሪ መሐንዲሶች ጨረታዎችን ካለ አሳማኝ ምክንያት እስከ መሰረዝ በቅተዋል፡፡

በተጨማሪም በማኅበራት ከተደራጁ የግብዓት አቅራቢዎች ጋር በመመሳጠር ከተመረተበት ቦታ እስከሚሠራበት ቦታ ተጭኖ እስኪራገፍ ድረስ በመንገድ ላይ ከ30 እስከ 40 በመቶ የሚደርሰው ብሎኬት ይሰባበራል፡፡ በተጨማሪም የብረት፣ የበርና የመስኮት እንዲሁም የከንች የማቴሪያል ጥራት አሠራር እጅግ የወረደ እንዲሆን ይደረጋል፡፡ የቤቶች ልማት ቅርንጫፍ (ኃላፊዎችና መሐንዲሶች) ከእነዚሁ የማኅበራት አባላት ጋር የተጠላለፉበትን የሙስና መረብ ለመበጠስና ጥራት እንዲጠበቅ የሚተጉ የአማካሪ ድርጅቶችን ከማስጠንቀቅ አስከ ማባረር የተደረሰበት ሁኔታ ላይ ደርሰናል፡፡ የቤቶች ልማት ጉድለትን በየስብሳባው ላይ የሚያጋልጡ ሥራ ተቋራጮችን ደግሞ አናት አናታቸውን ብለው ከሥራው  ያስወግዷቸዋል፡፡

ሌላው መነሳት ያለበት ደግሞ የሌብነት ጉዳይ ነው፡፡ የቤቶች ልማት አወዳድሮ የቀጠራቸው የጥበቃ አባላትና ሌሎች ‹‹የመንግሥት ሌቦች›› በቅንጅት የኮንትራክተሮችን አርማታ ብረት፣ ሚክሰር፣ ቫይብሬተር፣ ጥቅል የኤሌክትሪክ ሽቦ፣ ሲሚንቶና የመሳሰሉትን ግብዓቶች በውድቅት ሌሊት ከግቢ በማውጣት መቸብቸብ ተያይዘውታል፡፡ በተጨማሪም የቤቶች ልማት ሎጂስቲክስ ክፍል 16 ሜትር ኩብ በሚጭን መኪና ከ10 እስከ 13 ሜትር ኩብ የሚሆን የአርማታ ጠጠር በማራገፍ ሥራ ተቋራጩን በመረከቢያ ቅጽ ላይ እንዲፈርም ያስገድዱታል፡፡ ካልተረከበም አቅርቦት ላይ ማዕቀብ ይጣልበታል፡፡ የውኃ አቅርቦትም ልክ እንደ ጠጠሩ ሁሉ በልኬት ጉድለት የታጀበ በመሆኑ፣ ሥራ ተቋራጩን ለኪሳራ ሥራውን ደግሞ ለጥራት ጉድለት ይዳርጉታል፡፡

ይህን ችግር በጥልቀት ለመዳሰስ የሞከርኩት መንግሥት እየወሰደው ባለው ቁርጠኛ ልማታዊ አመራር ላይ ከሥሩ የመሸጉ ‹‹የመንግሥት ሌቦች›› ከሌሎች ኃላፊነት ከማይሰማቸው ዜጎች ጋር በማበር በአገር ላይ እያደረሱት ያሉትን ብክነት፣ በጥራት ጉድለት የተነሳም በቀጣይ የሚደርሰውና እየደረሰ ያለው ጉዳት እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መሆኑን በመጠቆም አንድ እንዲባል ነው፡፡

ምን ይደረግ ታድያ?

 1. በቤቶች ልማት ሥራ ላይ ያሉ የመንግሥት ዋና አስፈጻሚ የፖለቲካ ሹማምንት ከተቻለ የዘርፉ ዕውቀትና ክህሎት ያላቸው ቢሆኑ ይመረጣል፡፡ አለበለዚያም ያሉትን ችግሮች በመረዳት ክፍተቶችን በፍጥነት ለማረም የሥራ ላይ ሥልጠና ቢስጣቸው ተገቢ ነው፡፡ (ሐኪሞች በተሰበሰቡበት አዳራሽ ውስጥ ያለ መሐንዲስ ሐኪሞች ለሚወያዩበት አጀንዳ ያለው መረዳት 40 በመቶ ብቻ ማለትም ከግማሽ በታች መሆኑን ልብ ይሏል) በተጨማሪም በበላይ ኃላፊዎች ዘንድ ጉዳዮችን ለመረዳትና ለማስረዳት በሚኬድበት ጊዜ ራሳቸው የወሰኑዋቸውን ውሳኔዎች ዓይኔን ግንባር ያድርገው ብለው የሚክዱ በመሆናቸው፣ የግልጽነትና የታማኝነት ችግር አለባችው፡፡ የኪራይ ሰብሳቢነት አባዜ የተጠናወታቸው ደግሞ ከቦታቸው መነሳት ይኖርባቸዋል፡፡
 2. የቤቶች ልማት ውስጥ የሚሠሩ ትጉኃን ሠራተኞች የመኖራቸውን ያህል፣ ጥቂቶች የብዙኃኑን ሠራተኛ ስምና ልፋት የሚያጎድፍ ተግባር እየፈጸሙ ናቸው፡፡ ይህ ችግር ግምት ውስጥ ገብቶ በአገር ሀብትና በዜጎች ጥሪት፣ እንዲሁም በመንግሥት ቀና ልማታዊ አቅጣጫ ላይ የሚቀልዱት የቤቶች ልማት የምሕንድስና ኃላፊዎች፣ የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት መሐንዲሶችና የሥራ መሪዎች ላይ ጠበቅ ያለና አፋጣኝ ግምገማ ተደርጎ ጥግ እንዲይዙ መደረግ ይኖርበታል ብዬ አምናለሁ፡፡
 3. ከሚገባቸው በላይ ሥራ ወስደው በኪራይ ሰብሳቢነትና የሙያ ሥነ ምግባርን ባልተከተለ ሁኔታ ጥራቱን የሚያዛቡ አማካሪ ድርጅቶች ከሚያላምጡት በላይ የጎረሱትን በማስተፋት፣ በልካቸው አንዲጎርሱ ቢደረግና ሌሎች ሥራ የጠማቸው አማካሪዎች የበኩላቸውን የዜግነት አስተዋፅኦ በልማቱ ላይ እንዲጨምሩ ቢደረግ፡፡
 4. ካለሙያቸውና በኪራይ ሰብሳቢነት እሳቤ ወደ ሥራ ተቋራጭነት የገቡትን ኮንትራክተሮች እስካሁን በሕዝቡ ላይ የቀለዳችሁበት ይበቃል፣ ሌሎች ችሎታውና ብቃቱ ያላቸው ደግሞ ገብተው በታማኝነት፣ በሙያዊ ሥነ ምግባርና በኃላፊነት ስሜት ሥራቸውን ይሥሩ ሊባሉ ይገባል፡፡
 5. በማኅበራት የተደራጁ ወጣቶች ሥራ ፈጣሪነትን በማነሳሳት ራሳቸውንና ወገናቸውን እንዲጠቅሙ መንግሥት ያስቀመጠው አቅጣጫ ተገቢ መሆኑ እንዳለ ሆኖ፣ እነዚህ ዜጎች ያለባቸውን የክህሎት ጉድለት ለማጥበብ እንዲቻል የሙያ ሥልጠና ቢሰጣቸው፣ በተጨማሪም በጥሩ ሥነ ምግባርና በኃላፊነት ስሜት ሥራቸውን እንዲሠሩ ቢደረግ፣ አጥፊዎቹን ደግሞ ገለል ማድረጉ ተገቢ ነው እላለሁ፡፡
 6. ለቤቶች ልማት ሌሎች የማጠናቀቂያና የግንባታ ቁሳቁስ የሚያቀርቡ አቅራቢዎችንን ደግሞ እስከዛሬ የፈጸሙዋቸውን ግዢዎችና አቅርቦቶች በተገቢው ሁኔታ መንግሥት ገምግሞ፣ በትክክል የሚሠሩትን በማበረታታት አጥፊዎችን ደግሞ አደብ እንዲገዙ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ በተጨማሪም በሥፍርና በልኬት ላይ የሚታየው ጉድለት በአቅራቢዎችና በቤቶች ልማት ሎጂስቲክስ ሠራተኞች በቅንጅት የሚከናወን የኪራይ ሰብሳቢነት ልክፍት፣ በጥራት ላይ የሚያስከትለው ጉዳት እጅግ አሳሳቢ መሆኑን በመገምገም በአፋጣኝ አጥፊዎቹ እንዲቀጡ መደረግ ይኖርበታል፡፡
 7. ዜጎች እንደ ዜግነታችን የሚፈጸሙ ጉድለቶችን በማጋለጥ ለመንግሥት አቤት በማለት፣ የኪራይ ሰብሳቢነት አባዜ የተጠናወጣቸውን ሁሉ በቃችሁ ማለት ይገባናል፡፡
 8. መንግሥት በዘርፉ ላይ ያሉትን ችግሮች ትኩረት ሰጥቶ በአፋጣኝ ካልገታው፣ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ በየዓመቱ የሚፈስበት የቤቶች ግንባታ ዘርፍ ከዚህ በላይ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ የማይቀር መሆኑን እጠቁማለሁ፡፡ በመንገድ ዘርፍ ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት በብቃት መንገዶችን የገነባው የመንገዶች ባለሥልጣን የጨረታ አወጣጥ፣ አተናተን (Evaluation) እና አሰጣጥ፣ እንዲሁም የሥራ ቁጥጥር ተሞክሮን አሥር ዓመት ላለፈው የቤቶች ልማት ዘርፍ በምርጥ ተሞክሮነት እንዲጠቀመው ይደረግ፡፡ አጥፊዎች በአስቸኳይ እንዲታረሙ፣ እንዲቀጡና ጥሩዎች እንዲበረታቱ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ አለበለዚያ ‹‹ገንዘብ ሲናገር ዳኛ ዝም ይላል›› የሚባለው እንዳይሆን እሠጋለሁ፡፡

እናንተስ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ትላላችሁ?

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

       

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles