Thursday, June 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየመድኃኒት ዋጋና ፈዋሽነት

የመድኃኒት ዋጋና ፈዋሽነት

ቀን:

ፒያሳ አካባቢ የሚገኝ አንድ መድኃኒት ቤት (ፋርማሲ) በራፍ ላይ ሰዎች ተሰልፈው መድኃኒት ለመግዛት ይጠባበቃሉ፡፡ አንዳንዶቹ የሐኪም ትዕዛዝ ያለበትን ወረቀት ይዘዋል፡፡ ከፊሎቹ ደግሞ ስስ ፌስታል በእጃቸው አንጠልጥለዋል፡፡ እኔም ለተመሳሳይ ጉዳይ የመጣሁ ስለሆነ ሰልፉን ተቀላቀልኩ፡፡ ወዲያውም ተራዬ ደርሶ ወደ ውስጥ ገባሁ፡፡ ሠራተኞች ወይም ፋርማሲስቶቹ በሥራ ተወጥረዋል፡፡ ከመደርደሪያው መድኃኒት እያወጡ ለተጠቃሚው ይሰጣሉ፡፡ በዛው ልክም ስለአጠቃቀሙ ያብራራሉ፡፡ የያዙትን ሳይጨርሱ ሌላው ይተካል፡፡ ፋታ አጥተዋል፡፡

ግርግሩና ውጥረቱ ትንሽ እረገብ እስከሚል ድረስ ባንኮኒውን ደገፍ ብዬ በመቆም በዓይኔ ግድግዳውን ማማተር ጀመርኩ፡፡ ወዲያውኑ በስተቀኜ በኩል ባለ ግድግዳ ላይ የተለጠፈው የመድኃኒት ዋጋ ዝርዝር ቀልቤን ሳበው፡፡ ለደም ግፊት የሚውሉ ኒፌዲፒን 20 ሚሊ ግራም አሥር ፍሬ የጀርመን 38 ብር፣ የሳይፕረስ 15 ብር፣ የሕንድ 4 ብር፣ እንዲሁም አሚዬዲፒን 10 ሚሊ ግራም አሥሩ ፍሬ የጀርመን 63 ብር፣ የሕንድ 14 ብር ይላል፡፡

ለዚህ በሽታ የሚውል ሌላው አቴኖሎን 50 ሚሊ ግራም የጀርመን 29 ብር፣ የሕንድ 4 ብር፣ አታካንድ 16 ሚሊግራም 28 ፍሬ የሲዊድን 468 ብር፣ ካንዲስታን 16 ግራም 30 ፍሬ የስሎቬኒያ 267 ብር እያለ ለሌሎች በሽታዎች የሚውሉ መድኃኒቶችን የተለያየ ዋጋ በዝርዝሩ ውስጥ አካትቷል፡፡

ተመሳሳይ በሽታን የመፈወስ አቅም አላቸው ተብለው ወደ አገር ውስጥ የገቡት እነዚሁ ‹‹አንድ ዓይነት›› መድኃኒቶች በዋጋ ይህን ያህል መለያየታቸው ግራ ገባኝ፡፡ ዋጋቸው ከፍ ያሉ መድኃኒቶች ምናልባት ቶሎ የመፈወስ ባሕሪ ሊኖራቸው ይችል ይሆናል የሚል ግምትም አደረብኝ፡፡ በመካከሉ የገበያው ግርግር ጋብ ብሎ ነበርና አንደኛውን ፋርማሲስት ስለዚህ ጉዳይ እንዲያብራሩልኝ ጠየኳቸው፡፡

ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉት ፋርማሲስት፣ ‹‹ለተለያዩ በሽታዎች የሚታዘዙ ሁሉም መድኃኒቶች ምንም እንኳን የዋጋ ልዩነት ቢኖራቸውም በዓለም አቀፍ ደረጃ የወጣውን መስፈርት አሟልተው የተመረቱ፣ ጥራታቸው፣ ፈዋሽነታቸውና ደህንነታቸው ተረጋግጠው የገቡ ናቸው፡፡ ይህም ሆኖ ግን የፈዋሽነታቸው ባህሪ ይለያያል›› አሉኝ፡፡

እንደ ፋርማሲስቱ ማብራሪያ፣ አንዳንዶቹ እንደተወሰዱ ወዲያውኑ የመፈወስ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ የመዘግየት ባህሪ አላቸው፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ከየፋብሪካዎቹ እየተመረቱ የሚወጡት መድኃኒቶች አክቲቭ ኢንግሪደንት (ንጥረ ነገር) መጠናቸው ስለሚለያይ ነው፡፡  ወይም ዲሲንትግሪት እና ባይንደሪት የተባሉ ተጨማሪ ግብዓቶች ስላሉባቸው ነው፡፡ ከእነዚህም መካከል ዲሲንትግሬት የተባለው ግብዓት ወደ ሆድ የገባው እንክብል ቶሎ ተሰባብሮ እንዲሁም ባይንደሪት የተባለው ሌላው ግብዓት ደግሞ በዱቄት መልክ ዘልቆ የገባው መድኃኒት በፍጥነት ተገጣጥሞ ፈውስን እንዲያፋጥኑ በማድረግ የጎላ ሚና ይጫወታሉ፡፡ ይህም ሁኔታ የዋጋ ልዩነት እንዲኖር ያደርጋል፡፡

ከዋጋ አንጻር በአውሮፓ አገሮች የተመረቱ መድኃኒቶች ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠይቁ ናቸው፡፡ ከሕንድ የሚገቡት ግን ዋጋቸው ዝቅተኛና የአብዛኛውን ተጠቃሚ አቅም ያማከለ ነው፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው የአውሮፓ አገሮች የመድኃኒት ፋብሪካዎች ለምርምር ሥራና ለባለሙያዎቻቸው ክፍያ የሚያወጡት የገንዘብ መጠን ከፍተኛ በመሆኑ ነው፡፡ ከማሸጊያ ጀምሮ የሚጠቀሙት ዕቃ ይዘትና ጥራት ደረጃም ለመድኃኒቱ ዋጋ ከፍ ማለት አስተዋጽኦ እንዳለው ፋርማሲስቱ ገልጸዋል፡፡

ወ/ት ሄራን ገርባ የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ እንደገለጹት የኢትዮጵያ የመድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ ከውጭ አገር መድኃኒት የሚያስገባው ወይም የሚገዛው በባለሥልጣኑ መሥሪያ ቤት ዕውቅና ከተቸራቸው ፋብሪካዎች ብቻ ነው፡፡

አንድ መድኃኒት ከጥሬ ዕቃ ጀምሮ እንደ መድኃኒት ሆኖ እስከሚወጣ ድረስ የሚያልፍባቸው የተለያዩ ሂደቶች አሉ፡፡ የእነዚህም ሂደቶች ሰነድ በሙሉ ለባለሥልጣኑ መሥሪያ ቤት ተልኮ እንደሚገመገም፣ ከግምገማው በፊት ግን ፋብሪካው ከዓለም ጤና ድርጅትና ከአይኤስኦ የማምረት ሥርዓት ሰርተፊኬት ማግኘቱንና ይህንንም ሥርዓት እየተከተለ ማምረቱን ለማረጋገጥ የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ኢንስፔክተሮች ፋብሪካው ያለበት አገር ሄደው እንደሚያጣሩ ወ/ት ሄራን ይናገራሉ፡፡

‹‹ከየፋብሪካዎቹም የተላከው የመድኃኒቱ ናሙና በባለሥልጣኑ መሥሪያ ቤት የመድኃኒት ጥራት ማረጋገጫ ላባራቶሪ ተፈትሾ ጥራቱ የተጠበቀና እንከን አልባ ሆኖ ከተገኘ ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ ይደረጋል›› ብለዋል፡፡

ወ/ት ሄራን የመድኃኒቶች የፈዋሽነት ባህሪ የተለያየ ነው፡፡ የዛኑም ያህል ዋጋው ይለያያል የሚለውን አስተያየት ፈጽሞ አይቀበሉም፡፡ ‹‹አንድ መድኃኒት ከተዋጠ በኋላ በምን ያህል ደቂቃ ውስጥ ተሰባብሮ ወደ ደም ስር መግባት እንዳለበትም አናጣራለን፡፡ ይህም የሚጣራው ለዚሁ ሲባል በተዘጋጀውና ኢትዮጵያም በተቀበለችው ዓለም አቀፍ መስፈርት ነው፡፡ በዚህ መልኩ በሚደረገውም የማጣራት ሂደት እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት ልዩነት አልተከሰተም፤›› ብለዋል፡፡

የአውሮፓ አገሮች መድኃኒቶች ላይ የዋጋ መናር ሊታይ የሚችለው ለመጀመርያ ጊዜ በፋብሪካዎቹ ባለሙያዎች የተፈለሰፉና ለዚህም የፈጠራ መብታቸው ጥበቃ ያላለቀባቸው ከሆኑ ነው፡፡ ነገር ግን የፈጠራ መብታቸው ካለቀ በኋላ ሌሎች አምራቾች እንዲያመርቷቸው ይፈቀድላቸዋል፡፡ አምራቾቹም ዋጋ ቀንሰው ለገበያ ያቀርባሉ፡፡

ተገልጋዮች መድኃኒት ላይ የጥራት ችግር ካዩ በየትኛውም መስክ ወደ ባለሥልጣኑ ሪፖርት ማድረግ እንደሚቻል ለዚህም ሪፖርት የሚደረግበት ሥርዓት እንደተዘረጋ ያስረዳሉ፡፡ ስለሆነም በጤና ተቋማት የሚገኙ የሕክምና ባለሙያዎች በመድኃኒት ፈዋሽነት ላይ ችግር ሲያጋጥማቸው ሪፖርት የሚያደርጉበት ፎርማት ለየተቋማቱ ተሰራጭቷል፡፡ ኅብረተሰቡም በ8482 ነፃ የስልክ መስመር መመጠቀም ይችላል፡፡     

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ከቀጣዩ ዓመት በጀት ውስጥ 281 ቢሊዮን ብሩ የበጀት ጉደለት ነው ተባለ

ለቀጣዩ በጀት ዓመት ከቀረበው 801.65 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ በጀት...

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው አሠራር ወጣ ያለውን ‹‹የወደፊት ግብይት›› ሥርዓት በይፋ አስጀመረ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው የማገበያየት ተግባሩ ወጣ ያለና በኢትዮጵያ...

የባንክ ማቋቋሚያ መሥፈርት እንደሚጠነክር ሚኒስትሩ ተናገሩ

 ባንኮች ስለውህደት እንዲያስቡም መክረዋል በኢትዮጵያ ውስጥ ባንክ ለማቋቋም የሚያስፈልገው መሥፈርት...