Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየግንቡ ዙሪያ ቅርሶች

የግንቡ ዙሪያ ቅርሶች

ቀን:

በጠባብና ጠመዝማዛው የሐረር የውስጥ ለውስጥ መንገድ ተጓጉዘን ከአቶ አብዱላሒ አሊ ሸሪፍ ሙዝየም ቅጥር ግቢ የደረስነው ረፋድ ላይ ነበር፡፡ ነጭ ካናቴራና ጀለቢያ ለብሰው በሙዝየሙ መግቢያ በር ላይ ቁመዋል፡፡ ፈጠን ፈጠን በሚል ንግግራቸው፣ በፈገግታ ተሞልተው በግላቸው ስላደራጁት ሙዝየም ማብራራት ጀመሩ፡፡

አቶ አብዱላሒ ተወልደው ካደጉበት ሐረር ከተማ ውስጥ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ከተለያየ አካባቢ ሔደው ትምህርት ቤቱን የተቀላቀሉ ተማሪዎች ስለ ባህላቸው እንዲያስረዷቸው ይጠይቋቸው ነበር፡፡ ብዙም ዕውቀት ያልነበራቸው አቶ አብዱላሒ፣ በወቅቱ የማንነት ጥያቄ በውስጣቸው እንደተፈጠረ ያወሳሉ፡፡ ባህላቸውን የሚያንፀባርቅ ቅርስ ለማሰባሰብ ቆርጠው የተነሱትም ከጥያቄው እፎይታ ለማግኘት ነው፡፡

ለመነሻነት ያሰባሰቡት የሐረሪ ዘፈኖችን ነበር፡፡ ቀጥለው በልዩ ልዩ የኢትዮጵያ፣ አፍሪካና አውሮፓ ክፍሎች የተዜሙ ዘፈኖችን ቅጂዎች አሰባሰቡ፡፡ የአካባቢያቸውን አዛውንቶች ደጃፍ እያንኳኩ ቅርሶችን ማሰባሰብ ቀላል እንዳልነበር ይገልጻሉ፡፡ በመጀመርያዎቹ ጊዜያት ግለሰቦች ቅርሶችን ሲሰበስቡ የት እንደሚያደርሱት ስለማይታወቅ ሰዎች ያላቸውን ቅርስ ለመስጠት ፍቃደኛ ባይሆኑም ከጊዜ በኋላ ተአማኒነት አግኝተዋል፡፡ የሕዝቡን እምነት መገለጫና ጥንታዊ የብራና መጽሐፍ በሙዝየማቸው ለመገኘት የበቃውም ሕዝብ እምነቱን ስለጣለበቸው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

በሙዝየማቸው ከ800 ዓመት በላይ የሆናቸው የብራና መጽሐፍት ይገኛሉ፡፡ 3,700 የሐረሪ መገበያያ የነበሩ የገንዘብ ኖቶችና ሳንቲሞች አሏቸው፡፡ የአካባቢውን ባህል የሚያሳዩ አልባሳትና ጌጣጌጦች፣ የጦር መሣሪያዎች እንዲሁም የቤት ውስጥ መገልገያ ቁሳቁሶች በሙዝየሙ አሉ፡፡ አካባቢውን ያስተዳድሩ የነበሩ መሪዎችን እንዲሁም አጠቃላይ አኗኗሩን የሚያንፀባርቁ ሥዕሎችም ይገኛሉ፡፡ አብዛኞቹ ከኅብረተሰቡ የተሰጣቸው ቢሆንም፣ በግላቸው የሰበሰቧቸው ቅርሶችም ጥቂት አይደሉም፡፡

መኖሪያ ቤታቸውን ሙዝየም አድርገው ለ17 ዓመታት ቅርሶችን ያስጎበኙት አቶ አብዱላሂ፣ በአሁኑ ሰዓት ለሙዝየም የሚሆን ቤት ስላገኙ ቅርሶቻቸውን አዘዋውረዋል፡፡

ዕድሜ ጠገብ መጽሐፍትና ቁሳቁሶችን ጠጋግኖ ለማደራጀት ያደረጉት እንቅስቃሴ ከእሳቸው አልፎ ባለቤታቸውና ልጆቻቸውን የአስም ታማሚ ቢያደርጋቸውም፣ ዛሬ የማንነት ጥያቄአቸውን ከመመለስ አልፎ የብዙዎች መዳረሻ የሆነ ሙዚየም ማቋቋም ችለዋል፡፡

‹‹አንድ ነገር ለማግኘት ሌላ ነገር ማጣት የግድ ነው›› እያሉ ለሥራቸው ውጤት የተሰማቸውን ሐሴት ይገልጻሉ፡፡

ከሰበሰቧቸው 1,200 መጽሐፍት መካከል 950ውን ዲጂታላይዝ ለማድረግ ችለዋል፡፡ 850 መጽሐፍትን ደግሞ ባሉበት ሁኔታ አድሰው አስቀምጠዋል፡፡ በሠሩት ሥራ ያለፈው ዓመት የበጐ ሰው ሽልማት ተሸላሚ እንደነበሩ ይታወሳል፡፡

ከአዲስ አበባ በስተ ምሥራቅ 525 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ሐረር ከአቶ አብዱላሒ ሙዝየም በተጨማሪ ሦስት ሙዚየሞች አሏት፡፡ የበርካታ መስህቦች ባለቤትም ናት፡፡ በሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተቆረቆረችው ጥንታዊቷ ሐረር፣ የሰላምና መቻቻል ከተማ በሚል ተሸልማለች፤ በዩኔስኮም ተመዝግባለች፡፡ በዩኔስኮ ከተመዘገቡ የኢትዮጵያ ቅርሶች አንዱ 3,334 ሜትር ስፋትና 12 ሜትር ከፍታ ያለው የጀጐል ግንብ ነው፡፡

ከከተማዋ ተጠቃሽ ሙዝየሞች አንዱ የሐረሪ ብሔራዊ ሙዝየም ነው፡፡ ሙዝየሙ የሐረሪ፣ አፋር፣ ሶማሌ፣ ኦሮምያና አማራ ቅርሶች ይገኝበታል፡፡ የሙዝየሙ አስጐብኚ ወ/ሮ ነጅሐ አቡበከር እንደሚናገሩት፣ ሙዚየሙ ጠቅለል ባለ መንገድ የየአካባቢውን ባህላዊ እሴቶችና ታሪክ ያሳያል፡፡ ከሐረሪ ውጪ ያሉ ክልሎች መገልገያዎች በሙዝየሙ ተሰባጥረው መገኘታቸው ለጐብኝዎች መልካም አጋጣሚ እንደሆነ አስጐብኚዋ ያስረዳሉ፡፡

ለዓመታት ጥቅም ላይ የዋሉ የዕለት ከዕለት መገልገያ ቁሳቁሶች በሙዝየሙ ይታያሉ፡፡ የእርሻ መሣሪያዎች፣ አልባሳት፣ ጌጣጌጥ፣ የጤና መጽሐፍትና በተለያዩ ክብረ በዓሎች ወቅት ጠቀሜታ ያላቸው ቁሳቁሶች በብሔራዊ ሙዝየሙ ከሚገኙ ጥቂቱ ናቸው፡፡

ወ/ሮ ነጅሐ፣ ቅርሶቹ ከአንድ መቶ ዓመት በላይ ዕድሜ እንዳላቸውና ኅብረተሰቡም አብዛኞቹን ቁሳ ቁሶች እንደማይጠቀምባቸው፣ ከጊዜ በኋላ እንደየዘመኑ የዕድገት ደረጃ ቁሳቁሶቹ ይዞታቸውን እየቀየሩ በሥራ ላይ እንደዋሉ ያስረዳሉ፡፡

በሐረር ከተማ ከሚገኙ ሙዝየሞች መካከል በሐረሪ ባህላዊ ሕንፃ አሠራር የተዘጋጀ ማዕከልም ይገኛል፡፡ በውስጡ በሐረሪ ባህል ለዕለት ከዕለት መገልገያነት የሚውሉ ቁሳቁሶችን መመልከት ይቻላል፡፡ ሙዝየሙ በሐረሪ ባህላዊ ቤት ውስጥ የሚገኙ ክፍሎችና በእያንዳንዱ የሚቀመጥ መገልገያ የሚያሳይ ነው፡፡ በሐረሪ ብሔራዊ ሙዝየም እንደሚገኙ ቁሳቁሶችም በዚህኛውም ሙዝየም ዛሬ ላይ ግልጋሎት የሌላቸው ቁሶች ይታያሉ፡፡

ሙዝየሙም ወደ 30 ዓመት ባስቆጠረው ሙዝየም፣ በተለያየ የዕድሜ ክልል የሚገኙ የአካባቢው ነዋሪዎች አለባበስ፣ በሐዘንና በደስታ ወቅት ያላቸውን አቀማመጥ ሥርዓትና መኖሪያ ቤትን ለማስጌጥ የሚውሉ ስፌቶች ከተመለከትናቸው መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በሐረሪ ከተማ ይኖር ለነበረው ፈረንሳያዊው ነጋዴ አርተር ራንቦ መታሰቢያነት የተሠራው ሙዚየም በፈረንሳያውያን ዘንድ ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጠው ነው፡፡ በጥንታዊ ቤት አሠራር የተዘጋጀው ሙዝየሙ፣ የራንቦን የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች፣ በሐረር በኖረበት ወቅት የተነሳቸውን ፎቶዎችና ለጥናትና ምርምር የሚሆኑ መረጃዎችን የያዘ ነው፡፡

በሙዝየሙ ውስጥ ካሉ ክፍሎች አንዱ ሥነ ግጥሞችና ፎቶ ግራፉ የሚታዩበት ጠባብ ክፍል ነው፡፡ ክፍሉ ጐብኝዎችን የበለጠ ይስባል፤ ከሌሎች ክፍሎች በተለየ ከራምቦ መንፈስ ጋር ያገናኘናል ብለው የሚያምኑ ጐብኝዎችም ጥቂት አይደሉም፡፡ በሙዚየሙ በተገኘንበት ወቅት ክፍሉን ይጎበኙ የነበሩ የአገር ውስጥና የውጭ ጐብኚዎች ገጥመውናል፡፡

በሐረር ስላሉ ሙዝየሞች የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ባለሙያ ረዳት ፕሮፌሰር አህመድ ዘካሪያን አነጋግረናል፡፡ በሐረር ከሌሎች ከተሞች በተለየ አራት ሙዚየሞች ከመቋቋማቸው ባሻገር ሙዚየሞቹ ዕድሜ ጠገብ እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡

በሙዝየሞቹ የቅርስ መደጋገም ስለሚታይ ይህ መስተካከል እንዳለበትና ዕድሳት ሊደረግላቸው እንደሚገባም ያሳስባሉ፡፡ የተለያዩ ብሔረሰቦች ቅርሶችን እንዲያካትቱም ይመክራሉ፡፡

በሐረር ከተማ የባህል ማዕከል እየተገነባ እንደሆነ ረዳት ፕሮፌሰር አህመድ ይናገራሉ፡፡ በተጨማሪ የአሚር አብዱላሒ መኖሪያ ቤትን ሙዚየም የማድረግ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ የሁለቱ መሳካት ከተማዋ ያሏትን ሙዚየሞች በዓይነት የተለያዩ ቅርሶች የሚጐበኙባቸው ያደርጋል፡፡ የአሚር አብዱላሒ መኖሪያ ቤት አሁንም የሚጐበኝ ሲሆን፣ ሙዚየም ከሆነ ከእሳቸው ጋር የተያያዙ ቅርሳቅርሶች ይካተታሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ወደ አቶ አብዱላሒ ሙዚየም የተጓዝንበትን ጠበብና ጠመዝማዛ መንገድ ጨምሮ ሐረር 359 መንገዶች አሏት፡፡

በከተማዋ የሚገኙ በርካታ ታሪካዊ ቦታዎችን ለመጐብኘት የሚጓዙ ሰዎች የሐረር ግንብ ሸዋበር፣ ፈላና በር፣ ኤረር በር፣ ሰንጋ በርና ቡዳ በር የሚባሉት አምስቱን በሮች ሳያዩ ይመለሳሉ ማለት አይቻልም፡፡

በግንቦቹ ከተከበቡት ቅርሶች በተጨማሪ ሰማንያ ሁለት ጥንታዊ መስጂዶችም በሥፍራው ይገኛሉ፡፡ ‹‹የፍቅር ከተማ›› በማለት ብዙዎች የሚያቆላምጧት ሐረር ጅብ፣ እንኳን ሳይቀር ከሰው እጅ የሚመገብባትም ናት፡፡

 

spot_img
Previous article
Next article
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ ሲኒመር ትሬዲንግ...

የባህር በር በቀጣናዊ ተዛምዶ ውስጥ

በበቀለ ሹሜ መግቢያ በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ማለቂያን ይዞ ዓብይ አህመድ በጠቅላይ...

ሥጋት ያስቀራል ተብሎ የሚታሰበው የጫኝና አውራጅ መመርያ

በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መልኩ በመደራጀት ማኅበረሰቡ ላይ እንግልትና...

ማወቅ ወይስ አለማወቅ – ድፍረት ወይስ ፍርኃት?

በአሰፋ አደፍርስ ወገኖቼ ፈርተንም ደፍረንም የትም አንደርስምና ለአገራችን ሰላምና ክብር...