Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ሸምዳጅና ኮራጅ

ሰላም! ሰላም! ዓለም ሰላም አጥታ በእኛ ‘ኬፍ’ መባባል የሚቆጣ ይኖራል እኮ። ምን ይታወቃል? ምቀኛ አያሳጣን ነው መቼስ። የቅናት ዛር የሰፈረበት ሁላ እንኳን በሰው ሰላም በሰው ኪስ ይቃጠል የለ? አንዳንዴ እኮ አለመፈጠርን የሚያስመኝ ከተፈጠርኩ ጀምሮ ያየሁት ትርጉም የለሽ ክፋት ተቆጥሮ የማይልቅ ሲሆንብኝ ነው። ዘንድሮ ቆጥራችሁ አይደለም ገና ሳትጀምሩት የሚያልቀው ገንዘብ ብቻ ሆኗል። በተረፈ ሌላው ጉድ የሚያልቅ አይደለም። እናም ሰላም በራቀን ልክ እኛም የምንመፃደቀው እንደ ግዳይ መቁጠር የጀመርነው ዕኩይ ዕኩዩን ሆነ። መቼ ዕለት አንድ ወዳጄ ከአንዱ ወደ አንዱ ድለላ ስከንፍ አግኝቶኝ “ጫረው!” አለኝ። ‘ፀብ አጫሪ መንገዱን አጣቦና ዓለምን አስጨንቆ ይዟት ሳለ ሌላ ፀብ ጫር ነው የሚለኝ?’ ብዬ ልሸሸው ስል፣ “የት ነው የምትሸሸው? ቨርጂኒያን አንቀጥቅጠናትማ እንዲህ በዋዛ አንላቀቅም። ና ቢራ ልጋብዝህ፤” አለኝ።

“ማን ናት ቨርጂኒያ? የትስ ናት እሷ?” ማለት። “አልሰማህም? ከእስር ቤት አምልጦ የቨርጂኒያን ፖሊስ ቁም ስቅሉን ያሳየው እኮ የእኛ አገር ሰው ነው። ሆሊውድ በ‘ፕሪዝን ብሬክ’ ሲያደነዝዘን እኛ ደግሞ በካሜራ ‘ቴክኒክ’ ሳንደገፍ በገሃድ ከእስር ቤት አምልጠን ፊልም ሠራንባቸው፤” ቢለኝ ምንም ሳልመልስ አፌን ከፍቼ ቀረሁ። ክፉም ደግም ሳይወጣኝ አንገቴን ነቅንቄ ጥዬው ሄድኩ። ተኝቶ መታከም ያለበት ሰው ቁጥር ከኢኮኖሚ ዕድገት አኃዙ በእጥፍ እየጨመረ እንደሆነ እርግጠኛ ሆኛለሁ። አሁን እስኪ ጦርነት ያላየ ትውልድ ልንተካ ለሰላም እየዘመርን፣ ዓባይን እየገደብን፣ ቢሰምርም ባይሰምርም የዴሞክራሲ ጭቃ እያቦካንና ማገር እየማገርን፣ ኢትዮጵያዊ ስለሆነ ብቻ ለአንድ ‘ማይክል ስኮፊል’ ቢራ እናጋጭ ይባላል? ኧረ በስንቱ እንቃጠል? የምድር ፀሐዮች የሰማዩዋን ሊያስቋት ምን ቀራቸው እናንተ! 

   አላመናችሁኝም መሰለኝ። ወትሮስ “ዕውነት የሚናገር ሰው ጓደኛ የለውም፤” አላሉም አፍሪካውያን ጠቃሾች? እውነቴን ነው የምላችሁ ይህቺን ጥቅስ እስከ ሸመደድኩባት ቀን ድረስ የመንጋነት እንጂ የመሪነት መንፈስ እንዳለን አላውቅም ነበር። ከነበር አፈንግጦ ‘የለም በዚያ አይደለም! ኑ በዚህ!’ ያለ አፍሪካዊ ‘ሶቅራጥስ እንዳለ ከድለላ በሚተርፈኝ ሰዓት መርምሬ ለማግኘት አንዳንድ መጻሕፍትን ሳገላብጥ ማንጠግቦሽ ታዝባኝ፤ “አንበርብር ተው ብዙ አታንብብ። ታብዳለህ! እኔ በኋላ ከኅብረተሰቡ የተገለለ ባል አልፈልግም። አርፈህ ቅስቀሳ አዳምጥ። ‘አሸነፍን’ ሲሉ ‘አበጃችሁ’ በል። ‘አልተሸነፍንም’ ሲሉ ‘እንዳላችሁ’ ብለህ እለፍ። ነገር አታምጣብኝ፤” ብላ አስፈራራችኝ። ያነበበና የተመራመረ ሁሉ የሥልጣን ሽሚያ ውስጥ ይገባል ያለው ማን እንደሆነ አላውቅም። ትንሽ ሰነባብታ ደግሞ፣ “እዚህ ቤት መጽሐፍ የሚባል ነገር ባይ የእኔና የአንተ ነገር አከተመ፤” አለችኝ። ካለመድኩት ብቸኝነት የለመድኩት፣ ምኑ ጣፍጦኝ እንደለመድኩትም እንዳላጣራ የተከለከልኩት አብሮነት ይሻለኛል ብዬ ለአንዱ አዟሪ ሸጥኳቸው። ደግሞ ለመሸጥ። እንኳን የራሴን የስንቱን ንብረትና እውነት ሳሻሽጥ አይደል እንዴ የኖርኩት? ታዲያስ!

እንዲያው እርሜን በተጋመሰ ዘመኔ እውነትን ፍለጋ ቆርጨ ብነሳ ተቃውሞ ከቤቴ መጀመሩ አስገርሞኝ ገመናዬን ለባሻዬ ልብ ሳዋየው “ደግ አደረገች” አለኝ። “ምነው አንተ የተማርክ ሰው አይደለህ? እንዴት እንዲህ ይባላል?” ስለው፣ በከፊል ይኼ የትምህርት ጥራት ጉድለት እንኳን በሚኒስትር ሹም ሽረት፣ በርዕየተ ዓለም ለውጥ በእንዶድ ቢያጥቡትም አይፀዳ እያልኩ፣ “መጻሕፍት ውስጥ ሐሳብ እንጂ እውነት ተገኝቶ አያውቅማ። ‘በተማረው ባሰ’ ‘ባነበበው ከረረ’ ሲባል የምትሰማው እኮ ሐሳብ ሸምድደን በሐሳብ ስለምንለያይ ነው። እውነት ግን አብራህ የተፈጠረች ናት። ህሊናህን ስትጠይቀው እውነትን ይጠራልሃል፤” ብሎ  የሚገባኝን አሳንሶ ያልገባኝን አብዝቶ አብራራልኝ። ‘ሐሳብ የሌለባት እውነት እንዴት ያለች ትሆን?’ ስል የሚያበላኝ ደላላነት ትቼ የሚያስርበኝን ፍልስፍና ሙጥኝ ልለው ሆነና ነገሩን ተውኩት። በባሻዬ ልጅ አስተያየት ግን ባይዘመርላቸውም ብዙ ሺሕ ሶቅራጥሶች አፍሪካ እንዳሉዋት አረጋገጥኩ። ማሰብና መናገር እየተከለከሉ አይመስላችሁም ያልዘመርንላቸው? 

እናላችሁ እንደምታውቁኝ ሥራ ላይ ንብ ነኝ። ኦ! ለካ ጊዜው የምርጫ ነው? የፖለቲካ አመለካከትና የምርጫ መብቴ እንደ ግለሰብ ይጠበቅልኝ አደራ። ደግሞ እንደሚገባኝ በላባችን እንደ ንብ ታትረን ማር መጋገር የከለከለን የለም። እና ደፋ ቀና ስል ባለሦስት ፎቅ ቪላ ላሻሽጥ፣ ከሻጩ ጋር አብሮ እንደኖረ ሰው ፍፁም ተግባባሁላችሁ። የእኛ ሰው ዝቅ ብላችሁ ጆሮ ከሰጣችሁት የጓዳ ታሪኩን ጨርሶ እትብቱ የተቀበረበትን አካባቢ ሁሉ ይጠቁማችኋል። ቪላውን ለማየት ቀጠሮ ይዘው ገዢዎች እስኪመጡ እንጫወታለን። “ይገርምሃል ዛሬ ጠዋት ሚስቴ ከእንቅልፏ ተነስታ ምን አማረኝ ብትለኝ ጥሩ ነው?” አለኝ። ግምቴ ቀረብ እንዲል እርጉዝ መሆኗን ጠየቅኩት። “ኧረ መሀን ነች፤” አለኝ። አምልጦት አይደለም። እንደነገርኳችሁ ጆሮ ካገኘን ሚስጥር አንቋጥርም። (ባናገኝም ለነገሩ ያው ነን) ‘ሰው ሁሉ የልቡን እንዲህ የሚናዘዝልኝ ከሆነ በጆሮ ጠቢነት ተመዝግቤ ጥሩ አበል ልሸቅል ይሆን?’ እያልኩ፣ “እርጉዝ ካልሆነችማ መገመት ይከብዳል፤” አልኩት። ልብ አድርጉ! ‘መሀን ከሆነችማ’ አላልኩም። በተዋወቅን ልክ መናናቅን መሻር ከእኔ ተማሩ። በትምህርት ጥራት መላሸቅ ብቻ አታሳቡ፡፡

ደንበኛዬ ቀጠለ። “ገና ከእንቅልፏ እንደተነሳች ‘ናይጄሪያዊ መሆን አማረኝ’ አትለኝ መሰለህ፤” ወዲያው ተቆጣ። “‘ጋዴሚት!’ ስንት አገር አለ። አውሮፓ ብትል አሜሪካ፣ ካናዳ። ናይጄሪያ ትለኛለች?” አፈጠጠብኝ። ‘እኔ ያልኩት አስመሰለው እኮ’ እያልኩ “ምነው አለች?” ስለው፣ “ምን እሷ ‘በሕይወቴ ዘመን በምርጫ ተሸንፎ ከቤተ መንግሥት ወጥቶ ከሕዝቡ የሚቀላቀል መሪ ሳታሳይ አትግደለኝ ነው’ የዘወትር ጸሎቷ፤” ብሎ ቤቱ ውስጥ ከእሱ አልፎ ለእግዜር የሚቀርበውን ሥለት ነገረኝ። እኔ አንዳንዴ ከዲሞክራሲ ነው ፍቅር የያዘን ፊት ሲቀያየር ከማየት እላለሁ። የገባችሁ እንድታስረዱኝ ቁጥሬን እንዳልናገር ለማንጠግቦሽ ወሬ አቀባዩ ብዙ ነው። መላ ያጣ ነገር!

 ያልኳችሁን ቤት አሻሽጬ አንድ ሎቤድ ላከራይ ስንከራተት ስልኬ ‘ቻርጅ’ ጨረሰች። እኛ ደላሎች ሳንቀጣጠር የምንገናኝባት የሰርክ መሰብሰቢያችን ወደሆነችው ካፌ ተጣደፍኩ። ስደርስ አንዱ ደላላ ወዳጄ ፈንጠር ብሎ ብቻውን ተቀምጦ ደብዳቤ ይጽፋል። ሌሎቹ ተሰብስበው ያሽካካሉ። ወደሚያሽካኩት ተጠግቼ በአንደኛው ሞባይል ወደቀጠርኩት ተከራይ እየደወልኩ፣ “ምን እየጻፈ ነው?” አልኳቸው። “ለሞባይሉ ደብዳቤ እየጻፈ ነው። አትረብሽው፤” ብሎ አንደኛው እንባው እስኪያቀር ይስቃል። “ስልኩ በመጥፋቱ የስንት ሚሊየን ብር ሥራ እንዳመለጠው ብታውቅ እንዲህ አታላግጥም፤” ይላል ከጎኑ ኮስተር ባዩ ወዳጃችን። ከደንበኛዬ ጋር ተቀጣጥሬ ‘ቻርጅ’ እስካደርግ የሚጽፈውን ለማንበብ አጠገቡ ተቀመጥኩ። “ከኑሮ ፅዋ እኩል ተግተን፣ ሚሊየነር ሆኜ የደላላነት ጫማዬን ልሰቅል ስል ጥለሽኝ በመጥፋትሽ አዝኛለሁ፤” ሲል ይጀምራል። “… እነሆ ‘ወንዝ በሌለበት ድልድይ እንሠራለን’ ማለት የለመደ ውሸታም ሲያስለቅሰኝ እንዲኖር ፈቅደሽ፣ ድህነቴን በሥራ ሳይሆን በርዕዮተ ዓለም ምርጫ አመልጠው ይመስል በወሳኜ ሰዓት ከዳሽኝ። መቼም ከዚህ አገር ‘ኔትወርክ’ ጋር የዋለች ሞባይል መጥፋት እንጂ ሌላ ምንም ተምራ እንደማትመጣ የታወቀ ነው። ለሁሉም እንደ ሥራው ይሰጠዋል። ስንቱ በሙስና ሚሊየነር ተብሎ ታፍሮና ተከብሮ እየኖረ እኔ በላቤ ሳያልፍልኝ በድህነት እንድኖር ፈረድሽብኝ። ግን አንቺም? አብረን ብዙ አይተን ገና ለገና ሚሊየነር ሆኖ ‘አይፎን’ ይደርብብኛል ብለሽ ጠርጥረሽ? ሳትነግሪኝ ገብቶኛል። ብደርብስ መደረብ በእኔ አልተጀመረ? ደግሞ በዚህ ጊዜ ማን ነው የማይደርበው? ግድ የለም …” እያለ ይቀጥላል። እንግዲህ የሞባይል ቀፎ በጠፋ ቁጥር የአርባ ቀን ዕድልን በደብዳቤ መተቸት ከጀመርን የወረቀት ዋጋ ከነዳጅ ዋጋ መጨመር በላይ ሊያሳስበን ነው። ተሳሰቡማ አልተባልንም አሉ፡፡

በሉ እንሰነባበት። ‘ኮሚሽኔን’ ተቀባብዬ ጥሜን ልቆርጥ ወደ ግሮሰሪያችን አመራሁ። ሰው እንደ ወትሮው ገደብ በጣሰ ብስጭትና ንዴት ይጨልጣል። የባሻዬን ልጅ ደወልኩለት። ጥቂት ቆያይቶ ከተፍ አለ። ጨለጥ ጨለጥ አድርጎ ሲደርስብኝ፣ “የእኛ ነገር እንዲህ በንዴትና በብስጭት ብርጭቆ ሥር ተጎልቶ ማምሸት ሆነ በቃ?” ስለው “ተወኝ የዛሬው ያስጠጣል፤” አለኝ። “አንተ ደግሞ ምን ሆንክ?” አልኩት፡፡ “አባዬ ደከመ ብለውኝ ነፍሴን ሸጬ ቤት ስደርስ ሬዲዮ ጆሮው ሥር አስጠግቶ ይቁነጠነጣል። ደህና መሆኑን ስጠይቀው እሱ ከእኔ በልጦ ‘ዝም በላቸው ‘አፕሪል ዘ-ፉል’ ነው! ሟርተኛ ሁላ!” ብሎ ዘጋኝ። ማን ይኼን ደረቅ የውሸት ቀን እንደጀመረው?” ብሎ ሲበሳጭ ባሻዬ አንድ ነገር ቢሆኑ ኮረንቲ ካልጨበጥኩ እንደሚል አረጋገጥኩ። ያኔ አጠገቡ ካልሆንኩ መብራት እንዲጠፋ መብራት ኃይል መደወል ነው። አብሩት ስንል እንጂ አጥፉት ብንል አይሰሙንም ብላችሁ ነው?

የባሻዬ ልጅ ተናግሮ እንዳበቃ አንድ ጎልማሳ ድምፁን ከፍ አድርጎ፣ “እኔ ቤትህ ተቃጠለ ቶሎ ድረስ ብለው እግዜር ያሳያችሁ ሥራ ትቼ ስደርስ ‘የውሸት ቀን ነው’ አሉኝ። መቼ የእውነት ቀን አለና ነው የውሸት ቀን ያስፈለገን?” ተናግሮ ሳይጨርስ፣ “አንተም ሞኝ ነህ። ተቃጠለ ሲሉህ ምን ልታተርፍ ትሄዳለህ? ወይስ እንደ ደመራ ወዴት እንደሚወድቅ ልታይ ነው?” አለው አጠገቡ የተቀመጠ። ሁለቱ ሲበሻሸቁ ሌላው፣ “እኔ አለሁ አይደል? በእኔ ቤት ‘ዛሬ የውሸት ቀን ነው ማንም አይሸውደኝም’ ብዬ እጮኛዬ የምሯን አረገዝኩ ስትለኝ ‘ሂጂና የምታታልይውን አታይ’ ብዬ የተቆራረጥኩት፤” አለ። ሌላ አንድ ሰካራም ተነስቶ ደግሞ፣ “ለማንኛውም ዛሬ መንግሥት ባወጣው መግለጫ ‘ምርጫው ለዛሬ አምስት ዓመት ተሸጋግሯል’ ብሏል፤” ሲል ውሸቱ ያፈጠጠ ነበርና ሁሉም ገፈታትሮ አስወጣው። ሁካታው ሲያይል ለማርገብ የግሮሰሪዋ ባለቤት፣ “ፀጥታ! ዛሬ የፈለጋችሁትን ያህል ጠጡ ሒሳብ በእኔ ነው!” አለ። ቤቱ በአንዴ ረጭ አለ። ሁሉም እውነት መስሎት ዓይን ዓይኑን አየው። “ቀልደኛ ሁላ! እናንተን በነፃ አጠጥቼ ‘ቫት’ ምን ልከፍል ነው?” ብሎ ወዲያው ጢማችንን አበረረልን። እኔና የባሻዬ ልጅ ስለውሸት ቀን ገጠመኞች እያነሳን ስንጫወት አመሸን። ግን ማን ይሙት እውነት እንጂ ውሸት መቼ ተወደደብንና ለሐሰት ቀን ሲቀጥሩ አብረን እንደመራለን? ድንቄም ‘ግሎባላይዜሽ!’ እያልን አመሸን፡፡ የሆነስ ሆነና እስከ መቼ ነው ሸምዳጅና ኮራጅ ሆነን የምንዘልቀው? መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት