Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርት‹‹በአንዴ ቀነኒሳ በቀለን መተካት አይቻልም››

‹‹በአንዴ ቀነኒሳ በቀለን መተካት አይቻልም››

ቀን:

አቶ ዱቤ ጂሎ፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ጉዳይ ዳይሬክተር

ኢትዮጵያ በአዲስ አበባ የ12ኛው የአፍሪካ ወጣቶች ሻምፒዮና  ስድስት ወርቅ፣ 12 ብርና 10 ነሐስ በድምሩ 28 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ሦስተኛ ደረጃ በመሆን ማጠናቀቋ ይታወሳል፡፡ እንዲሁም ቻይና ጉያንግ በተደረገው በ41ኛው ዓለም አቀፍ የአገር አቋራጭ  ውድድር ላይ በሴቶች አምስት ወርቅ፣ ሦስት ብርና ሦስት ነሐስ ሜዳሊያ ማግኘት ችላለች፡፡ በወንዶች ምድብ ያሲን ሃጂና በሴቶች ለተሰንበት ግደይ የወርቅ ሜዳሊያ ሲያመጡ፣ ደራ ዲዳና እታገኝ ወልዱ የብርና የነሐስ ሜዳልያ አግኝተዋል፡፡ በዚህ ምድብ ኢትዮጵያ የግልና የቡድን ወርቅን አሳክታለች፡፡ በአገር ውስጥና በውጭ ከተደረጉት ውድድሮች የተገኘው ውጤት ለቀጣይ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ምን አመላካች ነገር አሳይቷል በሚልና በተያያዥ ጉዳዮች የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ጉዳይ ዳይሬክተሩን አቶ ዱቤ ጂሎን ዳዊት ቶሎሳ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ጊዜ አትሌቲክሱ ያለበት ደረጃ እንዴት ይገለጻል?

አቶ ዱቤ፡- እንደሚታወቀው በዓለም አቀፍ ደረጃ በተደረጉ ውድድሮች ላይ ኢትዮጵያም ባዘጋጀችው የወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮናም እንዲሁ በቻይናው የዓለም አገር አቋራጭ  ውድድሮች ላይ አትሌቶቻችን አመርቂ ውጤት ማምጣት ችለዋል፡፡ የአትሌቲክስ ደረጃም የሚለካው በአትሌቶች ውጤት በመሆኑ በታዳጊዎች፣ በወጣቶችና በአዋቂዎች ውጤት ማምጣት ተችሏል፡፡ በዚህ ውጤት መምጣት ፌዴሬሽኑ በስፋት ለአትሌቲክሱ ዕድገት ከአሠልጣኞች ጀምሮ እስከ አትሌቶች ድረስ ከላይ እስከ ታች ከክልሎችና ከማናጀሮች ጋር በመሆን ሰፊ ሥራ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡  

ሪፖርተር፡- በአዲስ አበባው የአፍሪካ ወጣቶች ሻምፒዮናም ሆነ በቻይናው የዓለም አገር አቋራጭ ውድድር የታየው ውጤት ወደፊት ለሚደረጉ እንደ ዓለም ሻምፒዮን ሆነ ኦሊምፒክ ዝግጅቶች ምን ያሳየው ፍንጭ አለ?

አቶ ዱቤ፡- በአፍሪካ ወጣቶች ሻምፒዮና ከዚህ በፊት በማንታወቅባቸው የአጭር ርቀትና የሜዳ ተግባር ላይ ተሳትፈን ሜዳሊያ አግኝተናል፡፡ ለወደፊት በሰፊው በነዚህ ዘርፍ ላይ ከተሠራ እንደረዥም ርቀት ሁሉ ዝናን ማትረፍ እንደምንችል አሳይቶናል፡፡ በቻይና ጉያንግ በተደረገው ውድድር ላይ አይደብልኤፍ ካዘጋጀው ስምንት ወርቆች አምስቱን ባማረ ውጤት ከ15 ዓመት በፊት በቤልጅግ ብራስልስ የነበረንን ውጤት የደገምንበት ነው፡፡ ይኼ ድል የበለጠ እንድንሠራ መነቃቃት ፈጥሮልናል፡፡   

ሪፖርተር፡- በሁለቱ ዓለም አቀፍ ውድድሮች የሴቶች የበላይነት ታይቷል፡፡ በሁለቱም ጾታ ተመጣጣኝ የሆነ ውጤት ማምጣት ያልተቻለበት ምክንያት ምንድን ነው?

አቶ ዱቤ፡- በሁለቱም ውድድሮች ላይ በይበልጥ የታየው በእርግጥ የሴቶች የበላይነት ነው፡፡ በጉያንግም በወጣት ሴቶች አንድ ኬንያ ነው የገባችው፣ በአዋቂ ሴቶችም ጥሩ ነበር፡፡ በወንዶቹ እጥረት አለ፡፡ ክፍተት እንዳለ ተገንዝበናል፡፡ እነዚህን ክፍተትም ለመቅረፍ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራን ነው፡፡ በተለይ በጉያንግ ውድድር ላይ እኛ ያዘጋጀነው በዓለም አገር አቋራጭ ልምድ ያለው አትሌት ኢማና መርጋ ነበር፡፡ ኢማና መርጋን በዚህ ውድድር ላይ በችግር ምክንያት ማሳተፍ አልቻልንም፡፡ ግን በዚህ ውድድር ላይ በተለይ በአዋቂ ወንዶች ሐጎስ ገብረሕይወት፣ ሙክታር እንድሪስ፣ አፀዱ ፀጋዬና ታምራት ቶላ ያደረጉት ፉክክር ጥሩ ነበር፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም በወጣቶች ያሲን ሃጂ አዲስና ተተኪ ነው፡፡  አዋቂዎችም፣ ወጣቶችም ያደረጉት ፉክክር ለወደፊት በትኩረት ከተሠራ ለዓለም ሻምፒዮና ጥሩ ውጤት ያመጣሉ ብለን እናስባለን፡፡

ሪፖርተር፡- በጉያንግ በወንዶቹ የተደረገው ውድድር ላይ የኢማና መርጋ ያለመኖር ውጤት ያሳጣን ወይስ መሠራት ያለባቸው ነገሮች በአግባቡ ስላልተሠሩ ነው?

አቶ ዱቤ፡-እኛ በመጀመርያ በውድድሩ ስንሳተፍ ቅድሚያ ዓላማችን ማሸነፍ ነው፡፡ ምክንያቱም በተለይ ከኬንያና ከተለያዩ አገሮች የተወከሉት አትሌቶች ፈጣን ናቸው፡፡ ስለዚህም የዛሬ ዓመት ሐጎስ ገብረሕይወትና ሙክታር የተወዳደሩት በወጣት ነበር፡፡ በዘንድሮ ውድድር ላይ ኢማናን ብናካትት የኬንያን አትሌቶች በከፊሉም ቢሆን መቋቋም ይቻል ነበር፡፡ በሌላ በኩል ኢማና ቢካተት ተቃራኒ አትሌቶች ልምዱን ስለማያውቁ የተወሰነ ተፅዕኖ መፍጠር ይችላል ብለን ስላሰብን ነው፡፡ ግን ወደፊት በወንዶች መሥራት እንዳለብን ግልጽ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በሴቶችስ የመጣው ውጤት በቂ ነው ማለት ይቻላል?

አቶ ዱቤ፡- በጉያንግ ውድድር ላይ በተለይ በስምንት ኪሎ ሜትር በአዋቂ ሴቶች ላይ ክፍተት ታይቷል፡፡ ይኼም የሆነው በማራቶን ውድድር ሲሳተፉ የነበሩና በአገር አቋራጭ ልምድ ያልነበራቸው ነበር የተካፈሉት፡፡ በተጨማሪም ለዚህ ውድድር ሕይወት አያሌውን ለማካተት ብንጥርም በአንዳንድ ችግር ምክንያት ስላልቻልንና ማጣሪያ ስናደርግ ያገኘናቸውና በአቅም ጉዳይ ያስቀረናቸው ወጣት አትሌቶች ነበሩ፡፡ በአጠቃላይ ግን እነዚህን አትሌቶችን ብናካት ኖሮ ስምንቱንም ወርቅ ማምጣት እንችል ነበር ብዬ እገምታለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ ውድድር ላይ ትምህርት በመውሰድ በተለይ በወንዶቹ ተተኪ ከማፍራት አንፃር ምን እየተሠራ ነው?

አቶ ዱቤ፡- ተተኪዎችን ከማፍራት አኳያ በትኩረት እየተሠራ ነው፡፡ የዚህም ማሳያ እንደ ሐጎስ፣ ሙክታርና አፀደን የመሳሰሉ አትሌቶች እየመጡ ነው፡፡ በአንዴ አትሌቶችን መተካት አይቻልም፡፡ አትሌቲክስ ከላይ ያለውና ከሥር የሚተካው እየተረዳዱ ሲመጡ ተተኪን ማፍራት ይቻላል እንጂ በአንዴ ቀነኒሳን የሚተካ መፍጠር አይቻልም፡፡ ሁሉም በሒደት ነው የሚከናወነው፡፡ ምክንያቱም አትሌቲክሱ ለረዥም ጊዜ የሚቆይበት ነገር አይደለም፡፡ ዕድሜና ጊዜ ይገድበዋል፡፡ ስለዚህ ቀስ በቀስ ልምድ ያላቸው አትሌቶች በመጠቀምና የተለያዩ ውድድሮችን በማሳተፍ ሰንሰለት ማበጀት ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- በአትሌቲክስ ቀጣይነት ያለው ውጤት ለማምጣት ማለትም እንደቀደምት አትሌቶች ጥሩነሽ ዲባባ፣ መሠረት ደፋር፣ ቀነኒሳ በቀለና ኃይሌ ገብረሥላሴን የመሳሰሉትን ዓይነት ለመፍጠር ምን ዓይነት ሥራ እየተሠራ ነው?

አቶ ዱቤ፡- እንዲህ ቀጣይነት ያለውን ውጤት ለማምጣት ወይም ከዚህ በፊት በተለይ በረዥም ርቀት በአዋቂ ሴቶች እነሰምበሪ ተፈሪና ዓለሚቱ ሐሮዬ እነመሠረትንና ጥሩነሽ እንዲተኩና በ10,000 እና በ5,000 ላይ ያለንን የበላይነት ለማስጠበቅ በትኩረት እየሠራን እንገኛለን፡፡ በተጨማሪም ፌዴሬሽኑ በረዥም ርቀት ብቻ ሳይሆን በአጭር ርቀትም ወደታች ወርዶ እየሠራ ይገኛል፡፡ በዚህም በብሔራዊ ደረጃ በሦስት ዘርፍ በታዳጊ፣ በወጣቶችና በአዋቂ ላይ በተጨማሪም በተመሳሳይ መልኩ በክልልም እየሠራ ነው፡፡ የዚህ ድምር ውጤት የቀድሞዎችን የሚተኩ ማፍራት ይቻላል ማለት

ነው፡፡    

ሪፖርተር፡- ለዓለም አቀፍ ውድድሮች ፌዴሬሽኑ በስም እንደሚመርጥ ይነገራል፡፡ አሁንስ የአትሌቶች ምርጫ በምን መልክ ይከናወናል?

አቶ ዱቤ፡- ከዚህ በፊት ከነበረው አትሌቶችን የመምረጥ ዘዴ በተለየ መንገድ ነው የሚመረጡት፡፡ በአሁኑ ሰዓት አትሌቶች በክልልም በክለብም እንዲሁም በማናጀሮች የሚሠለጥኑ አሉ፡፡ ሁሉም አትሌቶች አንድ ላይ በማሰባሰብ በተለያየ ውድድር ሜዳ ላይ በማወዳደር ያመጡት ሰዓት ታይቶና ተጠንቶ ብቁ የሆኑ ለዓለም አቀፍ ውድድሮች ይቀርባሉ ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በዓለም አቀፍ ደረጃ 10,000 ሜትር ውድድር እየቀረ ነው በመባሉ ተወዳዳሪ አትሌቶች ወደ ማራቶን እየገቡ ይገኛሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ለ10,000 አትሌቶችን ማግኘት እያሠጋ ነው ማለት ይቻላል?

አቶ ዱቤ፡- ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ማኅበር ውድድሩ ቀርቷል የሚል ነገር እስካሁን አላወጣም፡፡ ስለዚህ ውድድሩ በኦሊምፒክ ደረጃ መወዳደር ይቻላል ማለት ነው፡፡ በ10,000 አትሌቶች እጥረት አለ፡፡ አትሌቶችም የጠፉት በ10,000 ሜትር ላይ የታየው የመቀዛቀዝ ነገር ነው፡፡ መቀዛቀዙ ደግሞ ለኢትዮጵያ አትሌቶች መጥፋት ብቻ ሳይሆን ለተፎካካሪያችን ኬንያም ጭምር ነው፡፡ ምክንያቱም 10,000ን የተቆጣጠሩት ሁለቱ አገሮች ስለሆኑ፡፡ ስለዚህ እኛም በተቻለን መጠን ሕግ በሚፈቀድው መልከ በአገር አቋራጭ ላይ የሚወዳደሩ አትሌቶችንና ፈጣን የሆኑ የአስፓልት ላይ ተወዳዳሪዎች እንጠቀማለን፡፡

ሪፖርተር፡- አትሌቶች በብዛት ፌዴሬሽኑ ከሚሰጠው ሥልጠና ይልቅ በራሳቸው የግል አሠልጣኝ ነው የሚሠለጥኑት፡፡ እንደ ምክንያት የሚነሳ ነገር አለ?

አቶ ዱቤ፡- በአትሌቲክስ ሥልጠና ማንኛውም አትሌት የራሱ የሆነ አሠልጣኝ ሊኖረው ይችላል፡፡ ለምሳሌ ቀነኒሳ የራሱ የሆነ አሠልጣኝ ሊኖረው ይችላል፡፡ የግል አሠልጣኝ በየትኛውም ዓለም አትሌቶች የራሳቸው አሠልጣኝ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ብሔራዊ ቡድን የሚሠለጥኑ አትሌቶች አሉ፡፡ እኛ የግድ በብሔራዊ ቡድን ሠልጥኑ ማለት አንችልም፡፡ ግን የአገር ጉዳይ ከሆነ ማለትም በኦሊምፒክ ደረጃ ውድድር ካለ በፌዴሬሽኑ የመሠልጠን ግዴታ አለባቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ፌዴሬሽኑ ከማናጀሮች ጋር ያለው ግንኙነት በተለይ የአትሌቶችን ፍላጎትና ሕጋዊ የሆነ አካሄድን በተመለከተ ምን ይመስላል?

አቶ ዱቤ፡- እንደሚታወቀው ማናጀሮች ለአትሌቲክሱ ዕድገት ትልቅ ሚና ቢኖራቸውም በፌዴሬሽኑ ሕግ ግን መገዛት አለባቸው፡፡ ማናጀሮች ደግሞ በአንድ ጊዜ ከ60 እስከ 70 አትሌቶችን መያዝ ስለሚችሉ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ማሳተፍ ይችላሉ፡፡ በቅርቡ ጉዳዩን አስመልክቶ ውይይት አድርገናል፡፡ በውይይቱም በአገር ውስጥ የውድድር ፕሮግራም፣ በፀረ ዶፒንግ፣ በዕድሜ፣ በፎርጂድ የፓስፖርት ሥራ ላይና ዜግነትን በተመለከተ አንስተናል፡፡ በተለይም በውይይቱ ላይ አንድ አትሌት በዓመት ምን ያህል መሮጥ አለበት የሚለውን በዕውቀት ላይ በተመሠረተ መልኩ በሰፊው ተወያይተን ስምምነት ላይ ደርሰናል፡፡ ሌላው በፀረ ዶፒንግ ላይ ምንም እንኳን 98 በመቶ እርግጠኛ መሆን ቢቻልም ከፌዴሬሽኑ ጋር በመቆራኘት አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለብን ስምምነት ላይ ደርሰናል፡፡

ሪፖርተር፡- በሪዮ ዲጂኔሮ ለሚደረገው የኦሊምፒክ ጨዋታ ምን ዓይነት ዝግጅት እየተደረገ ነው?

አቶ ዱቤ፡- የኦሊምፒክ ጨዋታ ማለት የዓለም ትልቁ ዝግጅት ነው፡፡ ብዙ አገሮች በአራት ዓመት አንዴ በሚመጣው ውድድር ላይ ለመሳተፍ በቂ ዝግጅት ያደርጋሉ፡፡ የዓለም ሕዝብም ይኼን ውድድር በጉጉት ይጠብቃል፡፡ ስለዚህ ፌዴሬሽኑ ይኼን ከግምት ውስጥ በማስገባት ወደታች ወርዶ በተገቢው መንገድ ከአሠራር ጀምሮ እስከ አደረጃጀት ድረስ መሥራት አለበት፡፡ በተጨማሪም ለአሠልጣኞች ድጋፍ በማድረግና አትሌቶችንም በደንብ በማሠራት ለውድድር ማዘጋጀት አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...