Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትየምርጫውን ፋይዳ የሚፈታተኑ ስንክሳሮች

የምርጫውን ፋይዳ የሚፈታተኑ ስንክሳሮች

ቀን:

በበሪሁን ተሻለ

አገራችን በየአምስት ዓመቱ የምትደግሰው፣ አለመታደል ሆነና አሁንም ገና ፍጥርጥራችን አልሆን ብሎ ዝርዝሩንና ልኩን የማናውቀው የአገር ሀብት የሚከሰከስበት ምርጫ፣ አሁንም የሚገባውን ያህል ሙቀትና ድምቀት ሳያገኝ ለዘወትርና ለወጉ ያህልም ቢሆን የሚኖረውን ያህል መጨነቅና መጠበብ ሳያስከትል እነሆ መጋቢትን በማጠናቀቅ ላይ ነን፡፡ ከዚህ በኋላ የቀረው የአንድ ወር ተኩል ጊዜ ብቻ ነው፡፡ እናም በአጠቃላይ 2007 ዓ.ም. በመላ ወይም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳውን ካወጣበት ቀን ወዲህ ያለው ጊዜ፣ ወይም የምርጫ ቅስቀሳ ውድድሩ በይፋ ተጀመረ ከተባለ በኋላ ያለው ወቅት በእኔ በኩል ምርጫ ምርጫ አልሸት ብሎኛል፡፡

አንዳንዴ እንዲያውም፣ ዘንድሮ የምርጫ ዓመት መሆኑን የሚያስታውሰው የገዢው ፓርቲ የአንድ ወገን የሙሉ ጊዜ ሥራ ዘመቻና እንቅስቃሴ ነው፡፡ ገዢው ፓርቲ ከነደጋፊዎቹና ከነአጋሮቹ፣ በግልጽም ሆነ በሕግ፣ በተዘዋዋሪ መንገድም ሆነ በ‹‹ስሜት›› ከሚቆጣጠራቸው አካላት ጋር ሆኖ ‹‹ሁሉም ነገር ወደ ምርጫው ግንባር›› ብሎ ተነስቷል፡፡ በዚህ ምክንያት ‹‹እንኳን ልከህብኝ …… እቀራለሁ ወይ!›› የሚለው ሚዲያ፣ ቢሮክራሲ፣ ሲቪል ሰርቪስ፣ ፐብሊክ ሰርቪስ፣ ወዘተ መደበኛ ሥራውን በዚህ ምርጫ ቅኝት ያለከልካይ እያስኬደው፣ እያስነካው ነው፡፡

ሁሉም ነገር ወደ ምርጫው ግንባር በመባሉ፣ አለዚያም የተባለ ይመስል፣ የሕወሓት 40ኛ እና የኦሕዴድ 25ኛ ዓመት የምሥረታ ክብረ በዓላት የዚህ መድረክ ሆነው አላገለገሉም፣ የፕሮጀክቶች ምርቃት፣ የመሠረተ ድንጋይ የማኖር ሥነ ሥርዓት፣ የባለሥልጣናት ጉብኝት፣ የኮንዶሚኒየም የዕጣ ድልድል፣ የህዳሴው ግድብ አራተኛ የግንባታ ዓመት ለዚህ ዓላማ አልዋሉም፣ ኢሕአዴግ በመንግሥት ሥራው አጋጣሚ በእጁ በደጁ ያገኘውን ሁሉ አልተገለገለበትም ብሎ መወራረድ ይቸግራል፡፡

ወቅቱ ምርጫ ምርጫ አልሸት አለ ብለን ጀምረን ወቅቱ የምርጫ ወቅት መሆኑን የሚያስታውሰን፣ ከሌሎች መካከል እንዲህ ያለው ተግባር ነው ስንልና በምሳሌነት የገዢውን ፓርቲ ተግባሮች ስንጠቅስ፣ ይህ የኢሕአዴግ ‹‹ተረፍ›› አጠቃላይ የምርጫውን ‹‹ጎዶሎ›› ይሞሉትና ያካክሱታል ብለን አይደለም፡፡ እንዲያውም ውጤቱ በተቃራኒው ነው፡፡

ምርጫ በመጣ ቁጥር በሙቀቱና በድምቀቱ ውስጥ ገብተን፣ እየተጨነቅንና እየተጠበብን የእሱም አካልና አምሳል ሆነን ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ የሚፈቅድልንን ያህል የራሳችንን ጉዳይ በራሳችን መወሰን፣ የገዛ ራሳችን አዛዥ ናዛዥ እንድንሆን፣ ታሪክ እንድንሠራ እንፈልጋለን፡፡ ይኼ በሕገ መንግሥቱ የሕዝብ ሉዓላዊነት ድንጋጌ ሥር የሰፈረው የነፃነት መብታችን፣ የሉዓላዊነት ሥልጣናችን ምንዛሪ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶችን ማንነት ይደነግጋል፡፡ ሕዝብ ነው ይላል፡፡ ሕገ መንግሥቱም የሉዓላዊነታቸው መገለጫ ነው ይላል፡፡ ከዚህ በላይ አስፋፍቼና አብራርቼ ልናገር ሲል ደግሞ ሉዓላዊነታቸውም የሚገለጸው በሚመርጧቸው ተወካዮቻቸውና በቀጥታ በሚያደርጉት ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ አማካይነት ነው ይላል፡፡

ምርጫ በመጣ ቁጥር የምንጠይቀውም የዘንድሮ የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎትና ፈቃድ እንዴት ተገለጸ? በምን ፖሊሲ አማካይነትና በየትኛው ፓርቲ አምሳል ተገለጸ? የዚህ ምክንያት (አገራዊም ሆነ ዓለም አቀፋዊ) ምንድነው እያልን መሆን ነበረበት፡፡

ይህ ግን እስካሁን አልሆነም፡፡ በዚህ መንግሥት ኢትዮጵያ ውስጥ ምርጫ መካሄድ ከተጀመረ 20 ዓመት ቢሞላውም፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላማዊና ሕጋዊ ትግል አሁንም (ከ25 ዓመት ወዲህ) ዋጋ ቢኖረውም፣ ምርጫና የሕዝብ ፈቃድ ገና አልተገናኙም አልተዋወቁም፡፡

የተለየ ሐሳብ መግለጥ ቢያንስ በእንጀራ ገመድ ላይ አደጋ በሚያስከትልበት፣ ከዚህ አልፎ ሹም የሚፈልገውን አውቆ ሐሳብንና አስተያየትን ማስማማት፣ ሻል ከተባለም ዝም ማለት በሰፈነበት፣ መሽቆጥቆጥ፣ ኩርምት ማለት፣ አጎንብሶ ማለፍ፣ አንገትን መድፋት፣ አሁንም ገና ‹‹ኢትዮጵያዊ መለያችን›› ሆኖ በቀረበት፣ አድራጊ ፈጣሪነት ሕዝብን መፍራት ባልጀመረበት ምርጫ የሕዝብ ፈቃድ መገለጫ ነው ማለት የአገር ሕመምን አለማወቅ ነው፡፡

የእስካሁኑ ምርጫዎች ፋይዳም መገምገም ያለበት ወደዚሁ የሚደረገው ጉዞ ትክክለኛው መንገድ ስለመያዙ፣ በየጊዜው በሚመዘገቡት እንጥብጣቢ ድሎች አስተዋጽኦ ያደርጋል ተብሎና የኢትዮጵያን ሕዝብ ወደ ሰላማዊና ሕጋዊ ትግል አሸጋግሯል ተብሎ እንጂ፣ ምርጫና የሕዝብ ፈቃድ ኢትዮጵያ ውስጥ ተዋዶና አንድ ሆኑ ተብሎ አይደለም፡፡

ምርጫና የሕዝብ ፈቃድ እንዲዋደዱ ከተፈለገ፣ በምርጫ ማሸነፍ የሕዝብ ፈቃድ መገለጫ ነው ማለት እውነት ይሆን ዘንድ ከሁሉ አስቀድሞ ዴሞክራሲያዊ ፖለቲካዎች፣ ቢያንስ ቢያንስ ከአፍና ከተውኔት ይልቅ የአገር ወግ መሆን አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያን በ60ዎቹ ውስጥ ደርግ ወርዶ ‹‹ሕዝባዊ መንግሥት ይመሥረት›› አሉ ተብሎ የ‹‹ተሳቀባቸው››፣ በ80ዎቹ መጀመሪያ አጋማሽ ውስጥ ደርግ ሲወድቅ ወዲያውኑ ‹‹ሕዝባዊት ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ኢትዮጵያ›› ወይም ‹‹ፌዴራላዊት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን›› በሉ እናቋቁም ያልተባለው፣ ስለዚህም በቻርተሩ ከተወሰነው በላይ የሽግግር ዘመን ያስፈለገው ዴሞክራሲያዊ ፖለቲካ መጀመርያ መዘርጋት ስለሚያስፈልግ ነው፡፡ የመደራጀት ሐሳብን የመግለጽ ነፃነቶች በዚህ ውስጥ ይካተታሉ፡፡

በዚህም ምክንያት የሽግግር ዘመን ቻርተሩ፣ ዛሬ ሲያነቡት በሚያስደነግጥና በሚያስደንቅ ሁኔታ ‹‹የእምነት ሐሳብን የመግለጽ፣ የመደራጀት፣ በሰላም የመሰብሰብና የመቃወም ነፃነት አለው፤›› ሲል የእያንዳንዱን ሰው መብት አወጀ፡፡ መቃወም፣ ተቃውሞ ወይም ተቃዋሚ ማለት በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የሚያስጠቃ፣ ጥርስ የሚያስገባ፣ ከኢትዮጵያ ‹‹ሰፊ ሕዝብ›› ውጭ የሚያደርግ፣ ሲከፋና ‹‹አደጋ›› አለ ከተባለ ደግሞ ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር የሚያስፈርጅ ሆኗል፡፡ ሐሳብን የመግለጽ መብት፣ የመደራጀት መብት ዛሬም እንደ ቻርተሩ ዘመን በሕገ መንግሥቱ መሠረት (የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሠልፍ የማድረግ ነፃነትን ጨምሮ) የማንኛውም ሰው መብቶች ናቸው፡፡

የተጠቀሰውን የቻርተሩን የነፃነት ድንጋጌ ማንበብ ዛሬ ያስደንቃል ያስደነግጣል ያልኩበት ምክንያት፣ ዛሬም በተለይ ዛሬ መቃወም ብሎ መብት አለ እንዴ ብሎ የሚጠይቅ፣ የመደራጀት፣ ሐሳብን የመግለጽ፣ የመሰብሰብ መብትንና ነፃነትን ከኢትዮጵያዊነት ከዜግነት ጋር ብቻ የሚያስተሳስር ‹‹ንቃተ ህሊና›› በመስፈኑ ነው፡፡

ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት ለነፃ ምርጫ አንዱ ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡ መንግሥት የራሱን አስተሳሰብና ተግባር ጭራሽ ከውይይት በላይ አድርጎ በሚያይበት፣ የተለየና የሚቃረን ሐሳብን የማቅረብ ነፃነትን ጥቅሜ ብሎ ቀርቶ፣ የሕዝብ መብት ነው ብሎ ማድመጥን፣ መከራከርን፣ ቅዋሜ ሳይቋጥሩ መለየትን ፈጽሞ በማያቀበልበት ይልቁንም በተለመደውና ባረጀ ባፈጀው ‹‹ውሾች ይጮኻሉ…›› ተረቡ አማካይነት ማናናቁን መጠየፉን ሥራዬ ብሎ፣ መንግሥታዊ ሥራው አድርጎ ባስቀጠለበት አስተዳደር ውስጥ ከሁሉም በላይ ደግሞ መንግሥታዊ ኃላፊነትና ንብረት፣ እንዲሁም የሕዝብ ሀብት ለቡድንና ለፖለቲካ ሥራ መጠቀሚያነት ማዋልን የሚከላከልና የሚቆጣጠር ሥርዓት በሌለበት አገርና ሁኔታ ውስጥ ምርጫና የሕዝብ ፈቃድ አንድ ሊሆኑ አይችሉም፡፡

በዚህ ምክንያት 2007 የምርጫ ዓመት መሆኑን የሚያስትውሰን፣ በሚገርም ሁኔታ የአምስት ዓመቱ መጋቢት እንደዋዛ መገባደዱ፣ የምርጫውም ዓመት የኋሊት እየተቆጠረ መሆኑ አይደለም፡፡ በዚህ ውስጥ የሚታዩና የሚመሰከሩ የሚዲያው በተለይም የመንግሥት ሚዲያው ባህሪዎች ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ የምርጫ ፋይዳ የሚለካው ሕዝብን የሥልጣን ባለቤት ያደርጋል፤ የሕዝብ ሉዓላዊነት ዕውን ይሆናል ከሚባለው የመጨረሻው ግብ አንፃር አይደለም፡፡ ወይም ይኼኛው ፓርቲ አሸንፎ ያኛው ፓርቲ ከሥልጣን ይወርዳል አይደለም፡፡ የምርጫው ፋይዳ አንዳንዴም የፓርላማውን መቀመጫ ጥንቅር፣ የፓርላማውን ውሎና ውይይት ከማድመቅ አንፃር ሻል ያለ ቁጥር ያለው ተቃዋሚ ይኖራል ተብሎም ተስፋ የማይጣልበት አጋጣሚዎች አይተናል፡፡

ከዚህ ባነሰና መለስተኛ በሆነ ጥቅማ ጥቅሞችም የሚለካ ፋይዳ አለው፡፡ የሚዲያውን ባህል ማሻሻል፣ የሚዲያውን የምርጫ ወቅት የአጠቃቀም ሕግ መገንባት፣ በዚህ ውስጥ እኩይና ሰናይ፣ ነውርና በጎ የሚባል ልማድ ማቋቋም መቻል አንዱ የማይናቅ ፋይዳ ነው፡፡ እኛ ግን ለዚህ እንኳን አልታደልንም፡፡

ከምርጫዎች ሁሉ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ምርጫ ብሎ ዝም የሚባለው ምርጫ 97 ነበር፡፡ ድኅረ ምርጫው ባያምርም ምርጫው ሁሉንም ፍጥርጥራችንን በጎበኘበትና በመረመረበት ልክና መልክ ሚዲያችንንም ያን ያህል የምርና የእውነት አገላብጦ መርምሮ ነበር፡፡ የምርጫው ቀን ከመድረሱ በፊት የዛሬ አሥር ዓመት በመጋቢት ወር ምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤት ውስጥ የተካሄደው ውይይት ‹‹የመገናኛ ብዙኃንን የመጠቀም ነፃነት›› ነበር፡፡

በወቅቱ የተነሳው ጥያቄ ከዚያ በኋላ ሁልጊዜ የሚነሳው ዓይነት ጭምርም ነበር፡፡ ለምሳሌ አዳዲስ ፓርቲዎች የተመደበላቸው የአየር ሰዓትና ሚዲያውን የመጠቀም መብት አነስተኛ ነው መባሉ ያኔም የተነሳ መከራከሪያ ነበር፡፡ ስለዚህም ያኔ በነበረው የምርጫ ወቅት ሙቀትና ድምቀት፣ መጨነቅና ‹‹መጠበብ›› ልክ የክርክሩም መግለጫ ያን ያህል የጋለና የሰላ ነበር፡፡ ፓርቲዎች የአንደኛ ዲቪዚዮንና የሁለተኛ ዲቪዚዮን ዓይነት ምደባና ልዩነት ሊደረግባቸውም አይገባም ተባለ፡፡ ያኔ በነበረው ሙቀት፣ ግለትና ድምቀት ውስጥ የተፈጠረው ሥልጣኔ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችንና የግል ተወዳዳሪዎች ያለ አድልኦ በመገናኛ ብዙኃን ነፃ የአየር ጊዜና የጋዜጣ ዓምድ የማግኘትና የመጠቀም መብት አላቸው፡፡ የአጠቃቀሙ ሥርዓትም ከግል ዕጩዎች፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከራሳቸው ከመገናኛ ብዙኃንና አግባብ ካላቸው ሌሎች አካላት ጋር በመመካከር የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በሚያወጣው መመርያ ይወሰናል ማለት ድረስ አምሮበት ነበር፡፡

በወቅቱ ሥራ ላይ የነበረው የምርጫ ሕግ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያሉትን የመገናኛ ብዙኃን፣ የዕጩዎች ደጋፊ የሆኑት የፖለቲካ ድርጀቶችና የኅብረተሰብ ክፍሎች ያለአድልኦ የመጠቀም መብት እንዲሁም፣ ዕጩዎች በመገናኛ ብዙኃን ነፃ የአየር ጊዜ አግኝተው የመጠቀም መብት እንዳላቸው፣ በተለይም የአጠቃቀሙ ሥርዓት የማስታወቂያ ሚኒስቴር በሚያወጣው መመርያ መሠረት እንደሚወሰን ይደነግግ ስለነበር፣ ስብሰባው ውስጥ ኢሕአዴግን የወከሉት ተሳታፊ ይህንን ጠቅሰው ስለተከራከሩ ምርጫ 97 ‹‹ስለፍቅር በስመአብ ይቅር›› ማለት ድረስ ሊሄድ የነበረው ሳይሳካለት ቀረ፡፡

በምርጫ 97 ውስጥ የምርጫ የመጫወቻ ደንቦችን ለመቅረፅ ተደርጎ የነበው ጥረት ዋነኛ መገለጫ ከተሰጠው ወይም ከተመደበው የአየር ሰዓት ይልቅ፣ ይበልጥ አሳሳቢ የሆነ ሌላ የሚዲያ አጠቃቀም ችግር አለ ያለው ነበር፡፡

ይህም በአየር ሰዓት አመዳደብ ላይ የሚታይ አድልኦ አለ፡፡ ከዚህ የበለጠ ችግር የፈጠረውና የሚፈጥረው ከዚህ የምርጫ ቅስቀሳ ጊዜ ውጪ ያለውን የአየር ሰዓት ገዢው ፓርቲ ለምርጫ ቅስቀሳ ይጠቀምበታል፡፡ መላውን የሥርጭት ሰዓት የምርጫ ቅስቀሳ ክፍለ ጊዜ የሚል ርዕስ አይሰጠው እንጂ፣ የሚጠቀምበት ለምርጫ ቅስቀሳ ነው በማለት ድምፅ አግኝቶ የተስተጋባው የተቃዋሚ ተፎካካሪ ፓርቲዎች መከራከሪያ ነበር፡፡ መንግሥት የተመደበለትን የስድስት ደቂቃ ጊዜ ተጠቀመም አልተጠቀመም መላው የመንግሥት የመገናኛ ብዙኃን ተግባር የምርጫ ቅስቀሳ ሆኗል የሚለውን መከራከርያ፣ የመንግሥትና የገዢው ፓርቲ ተወካይ አጣጥለው የተከራከሩት መንግሥት ምርጫ መጣ ብሎ የመንግሥት ሥራውን አያቆምም፣ መንግሥት የልማት ሥራ አለው በማለት ነበር፡፡

የተቃዋሚ ፓርቲዎች ከዚህ አንፃር ያነሱት አፀፋ መከራከርያ ደግሞ በተለይ እንዲህ ባለ የምርጫ ወቅት ውስጥ በመንግሥት የሚዲያ አጠቃቀም ላይ ገደብ ሊበጅለት አይገባም ወይ? የመንግሥት መደበኛ ሥራ ከቅስቀሳው ጋር ተምታቷል፣ አንዱ ከሌላው አይለይም በማለት እንዲያውም ስብሰባውን የሚመሩትን የኢሌክሽን ሪፎርም ኢንተርናሽናል ተወካይን ጠየቁ፡፡ እስኪ በእናንተ አገር በሌላውም ዴሞክራሲያዊ አገር በምርጫ ወቅት ፕሮጀክት ይመረቃል? የመሠረተ ድንጋይ ይጣላል? ብለው እዩልኝ፣ ስሙልኝ፣ ፍረዱን አሉ፡፡

ከአሥር ዓመት በፊት በወቅቱ የተነሳው ጭብጥ፣ በተቃዋሚ ፓርቲዎችና በገዢው ፓርቲ መካከል የተደረገው ክርክር፣ ምርጫ ቦርድን የሚያግዘውና የሚያማክረው የኢሌክሽን ሪፎርም ኢንተርናሽናል ተቋም ተወካይ ያስረዱት፣ የዓለም አቋምና የእሳቸው ተሞክሮ ያስጨበጠው ዕውቀትና የግራ ቀኙ ክርክር የጫረው መነሻ ሐሳብ፣ ለኢትዮጵያ የምርጫ ሥርዓት ወደፊት መንደርደርያ ታላቅ የጥበብ መጀመርያ በሆነ ነበር፡፡ ምርጫ 2002 ይህንን ጥያቄ ‹‹ለማስቀጠል›› ቀርቶ ደግሞ ለማንሳት የታደለ አልነበረም፡፡ ታሞና ሲያገግም ከርሞ 2007 ላይ ከተፍ ያለው ምርጫም የተሻለ ዕድል አላገኘም፡፡

ይልቁንም የ2007 የፖለቲካ ፓርቲዎች የመገናኛ ብዙኃን አጠቃቀም መመርያና አሠራር አዲስና የባሰ ችግር ይዞ መጥቷል፡፡ ከዚህ ቀደም የምርጫ ወቅት የፓርቲዎች ወይም የግለሰብ ተወዳዳሪዎች የቅስቀሳ ፕሮግራምን የይዘት ሕጋዊነት የማረጋገጥ ኃላፊነት የሚዲያው አለመሆኑን ገልጬ፣ ሕጉ ራሱ ‹‹የሥርጭት ጊዜ የተሰጠው የፖለቲካ ድርጅት ወይም ዕጩ ተወዳዳሪ ለተሠራጨው ፕሮግራም ወይም መግለጫ ሕጋዊነት ኃላፊ ነው›› ማለቱን ጠቅሼ፣ አዲሱን ችግር አንስቼ ነበር፡፡ ችግሩ አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ የመንግሥት የመገናኛ ብዙኃን በተለይ፣ ከግሎችም አንዳንዶቹ ፓርቲዎች የሚያቀርቡትን ዝግጅት ወይም መግለጫ አስቀድመው እያዩና እየመረመሩ ይኼኛው ስም ያጠፋል ሌላው የተቋማትን ህልውና ይክዳል፣ ተግባራቸውን ያንቋሽሻል እያሉ ታርሞ እንዲመጣ አለዚያም ማስተላለፍ የማይችሉ መሆኑን እየገለጹ መመለሳቸውን፣ የአገር ምርጫ ዜና ሆኖ እየተነበበና እየተሰማ ነው፡፡

ሚዲያዎች የግልም ሆነ የመንግሥት እያንዳንዱ የሚዲያ መሠረታዊ አሃድ፣ የሚያወጣውን ወይም የሚያሠራጨውን ውጤት ሕጋዊነት ማረጋገጥ አለበት፡፡ ጉዳዩ በቀረበበት መልክ በምርጫ ወቅት ግን ይህ ግዴታ የሚዲያው አይደለም፡፡ በምርጫ ወቅት የይዘት ሕጋዊነትን የማረጋገጥ ግዴታ የሚዲያው መሆኑ ቀሪ የተደረገው ማንኛውም ሚዲያ ‹‹… በሕግ መሠረት ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶችና የምርጫ ዕጩ ተወዳዳሪዎች በምርጫ ወቅት ዓላማቸውንና ፕሮግራማቸውን ለሕዝብ እንዲያስተዋውቁ ወይም መግለጫ እንዲያስተላልፉ ነፃ የአየር ጊዜ መመደብ አለበት›› የሚል ሕግ ስላለ ነው፡፡ ሕጉ የሚዲያውን የይዘት ሕጋዊነት የማረጋገጥ ግዴታ ቀሪ ያደረገው ሚዲያው ነፃ የአየር ጊዜ ስለመደበ አይደለም፡፡ ሚዲያው ኤዲቶሪያል ሥልጣኑን ስላጣ ነው፡፡ የአየር ሰዓት የመስጠት ግዴታ አለብህ ስለተባለ ነው፡፡ በመልዕክቱና በመግለጫው ላይ ኤዲቶርያል ሥልጣን ስለሌለው ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ ዋናው ጥያቄና ጭብጥ የፖለቲካ ድርጅቶች ወይም የምርጫ ዕጩ ተወዳዳሪዎች ለሬዲዮ ‹‹ሀ›› ወይም ለቴሌቪዥን ‹‹ለ›› ያቀረቡት ዝግጅት የኢትዮጵያን ሕግ ይጥሳል? ስም ያጠፋል? ወይም (እንዲህ ያለ ጥፋት ካለ) ‹‹የተቋሙን ሕጋዊነትና ክብር በሚመጥን መልኩ›› ቀርቧል አልቀረበም? ወይም የፓርቲው ዓላማና ፕሮግራም ሕጋዊ ነው? ሕገወጥ? የሚለው አይደለም፡፡ ጥያቄው የቀረበውን ዝግጅት ይዘት ሕጋዊነት የማረጋገጥ ግዴታ የማነው? የፓርቲው ወይስ የሚዲያው ነው? የሚለው ነው፡፡

ሕጉና በሚዲያው ነፃነትና በነፃ ምርጫ ሥርዓት ላይ የተመሠረተው አሠራር ይህን ያደረገው የፖለቲካ ድርጅቶችና የዕጩ ተወዳዳሪዎች የዓላማና የፕሮግራም ማስተዋወቅ ሥራ፣ በእያንዳንዱ ሚዲያ ኤዲተሪያል ፈቃድ ላይ እንዳይመሠረት ነው፡፡ የይዘት ሕጋዊነትን የማረጋገጥ ግዴታው ግን (ለፓርቲው ተሰጠ እንጂ) እንዳለ ነው፡፡

የመንግሥት የመገናኛ ብዙኃንና ሌሎች ሚዲያዎች ጭምር ለሚሠራጨው/ ለተሰራጨው ፕሮግራም ወይም መግለጫ ሕጋዊነት ኃላፊው ሚዲያው መሆኑ ቀርቶ፣ ፓርቲው ወይም ዕጩ ተወዳዳሪው እንዲሆን መደረጉ ካልገባቸው ችግሩ ከዚህ ይጀምራል፡፡ ጉዳዩ ገብቷቸው ወንጀል/ጥፋት ሲሠራ ዓይተን ዝም ብለን አሳልፈን፣ ወደፊት ፓርቲው ይጠየቅ ማለት የሚያስችል ‹‹ህሊና›› የለንም የሚሉ ከሆነ ደግሞ እንዲህ ዓይነት ‹‹አርበኝነት›› በሌለ ሥልጣን የመገልገል ሕገወጥነት ነው፡፡ ይህ በሥልጣን አለአግባብ ከመገልገል የተለየ ነው፡፡ ሥልጣን ለራስ መስጠትና በሌለ ሥልጣን መገልገል ነው፡፡ የምርጫ ፋይዳ ደግሞ እንዲህ ዓይነት አድራጊ ፈጣሪነት ሕዝብን እንዲፈራ፣ እንዲቀር ማድረግ ላይ ነው፡፡ ወቅቱ የምርጫ ዓመት መሆኑን፣ ግንቦት 16 በምርጫ ካሌንደሩ መሠረት የኋሊት እየተቆጠሩ መሆኑን በዘነጋንበት በዚህ ወቅት ከምርጫው ድብርትና እንቅልፍ የሚያነቃንና ብንን የሚያደርገን፣ እንዲህ ያሉ ለኢትዮጵያ ምርጫ የቅርብም ሆነ የሩቅ ጊዜ ግብ የማይፈይዱ የተለያዩ የግል አካላት የአፄ በጉልበቱ ዕርምጃዎች ናቸው፡፡

መጀመሪያ ነገር ለፖለቲካ ድርጅቶችና ለምርጫ ዕጩ ተወዳዳሪዎች ነፃ የአየር ጊዜ ወይም የጋዜጣ ዓምድ እንዲመድቡ በሕግ የታዘዙ የመገናኛ ብዙኃንና የግል አካላት ናቸው፡፡ ከግል ባለቤትነት ውጪ ያሉት በመንግሥት ይዞታ ሥር የሚገኙት የአዲስ አበባም ሆነ የኢትዮጵያ ወይም የሌላ ክልል ኮርፖሬሽኖች፣ ኤጀንሲዎች፣ ወዘተ ባለቤትነታቸው የመንግሥት ስለሆነ ብቻ ወይም የመኪናቸው ታርጋ ኮድ 4 በመሆኑ ምክንያት የመንግሥት የአስተዳደር ሥራና ተግባር ፈጻሚዎች አይደሉም፡፡ እነሱ ግን የኢትዮጵያን ሕጎች የማስፈጸም ግዴታና ‹‹አርበኝነት›› አለብን ብለው ይህ ስም ያጠፋል ያኛው ክብር ይነፍጋል እያሉ የማያውቁበት ሥራ ውስጥ ገቡ፡፡

ሕግ የማስከበር የመንግሥት ሥልጣንና ተግባር ባለመብትነት የሚገኘው ከአርበኝነትና ከመንሰፍሰፍ ስሜት አይደለም፡፡ በሕግ ለዚያው የአገርን ሕግ የማውጣት ሕግና ሥርዓት ተከትሎ በወጣ ሕግ በመሰጠትና በመቀባት ነው፡፡ እንዲህ ያለ ሥልጣን የሰጣቸው ግዴታም ያቋቋመባቸው ሕግ ግን የለም፡፡ ሊኖርም አይችልም፡፡ ምክንያቱም ሕግ የማስፈጸም ተግባር የግለኛ አካላት ሥራ አይደለም፡፡ ይልቁንም ይህን ተግባር የሚፈጽሙት የይዘት ሕጋዊነት ኃላፊነትን ለፖለቲካ ድርጅቶች ወይም ለዕጩ ተወዳዳሪዎች የሰጠ አዋጅ እያለ ነው፡፡

በዚህ ድብርት በሰፈነበት የምርጫ ዓመት ውስጥ ድንገት ከእንቅልፍ ከሚቀሰቅሱን ጉዳዮች መካከል ሌላውና እስካሁን የመጨረሻው የናይጄሪያ ምርጫ 2015 ውጤት ነው፡፡ 

የናይጄሪያ ምርጫ ከሂደቱ ይልቅ ውጤቱ ብዙ ከእንቅልፍ የሚቀሰቅስ ጉዳይ አለው፡፡ ይህን ጽሑፍ ሳዘጋጅ የኢትዮጵያ ሚዲያ ውጤቱን እንዴት አድርጎ እንደሚዘግበው ገና አልሰማሁም አልታዘብኩም እንጂ፣ የምርጫ ውጤት በናይጄሪያ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው የሆነበት ምክንያት አለው፡፡ አንድ መንግሥት በምርጫ ሲወርድ ይህ የመጀመሪያ ጊዜው ነው፡፡

ሌላም የሚገርም ነገር አለው፡፡ በተለይ ኢትዮጵያ ውስጥ ሲሰሙት የሚገርመው (ስለዚህም ከእንቅልፍ የሚቀሰቅሰው) ሌላው ነገር ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት ናይጄሪያዊ መሐመዱ ቡሀሪ መሆናቸው ነው፡፡ ቡሀሪ በ1983 ዓ.ም. ሜጀር ጄኔራል መሀመድ ቡሀሪ እያሉ የሸሁ ሻጋሪን መንግሥት ገልብጠው ከሁለት ዓመት በኋላ በሌላ መፈንቅለ መንግሥት በሜጀር ጄኔራል ኢብራሂም ባባንጊዳ ከሥልጣን የወረዱ የናይጄሪያ ርዕሰ ብሔር ነበሩ፡፡ በ2015 የርዕሰ ብሔርነቱን ሥልጣን ያገኙት ግን በምርጫ ነው፡፡

ተመራጭ ፕሬዚዳንት መሀመድ ቡሀሪ አሸናፊነት የገለጸውን፣ የነፃው የናይጄሪያ የምርጫ ኮሚሽን ውሳኔን የተከተለው የፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን ምላሽም በምርጫ ወቅት የተኛን ሰው መላው አፍሪካንም ጭምር ከእንቅልፍ የሚቀሰቅስ ነው፡፡

ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን (ልብ አድርጉ አሁንም ዛሬም እስከ ግንቦት ድረስ ፕሬዚዳንቱ ጉድላክ ጆናታን ናቸው) ስልክ ደውለው ለተመራጩ ፕሬዚዳንት እንኳን ደስ ያለህ ማለታቸውና ሽንፈታቸውን መቀበላቸው ብቻ አይደለም ጉዳዩ፡፡ ደጋፊዎቻቸውንና ተከታዮቻቸውን እንዲረጋገጉ መልዕክት ማስተላለፋቸውና አደብ እንዲገዙ መንገራቸው አፍሪካ ውስጥ ያልተለመደ ጉዳይ ነው፡፡

በአንድ አገር ውስጥ በአንድ ጊዜ ሁለት ፕሬዚዳንት ስለሌለ አሁን ፕሬዚዳንቱ ጉድላክ ጆናታን ናቸው፡፡ ሕገ መንግሥቱ በዘረጋው ሥርዓት መሠረት የፕሬዚዳንትነት ምርጫ የሚካሄደው ያንን ሥልጣን የያዘው የመጨረሻው ሰው የሥልጣን ጊዜ ከመጠናቀቁ ከ60 ቀናት በማይበልጥ ከ30 ቀናት በማያንስ ጊዜ ውስጥ መሆን አለበት፡፡

ስለዚህም በምርጫና በሥልጣን ርክክብ መካከል ቢበዛ ከ60 ቀናት የማያልፍ አነሰ ቢባል ከ30 ቀናት ዝቅ የማይል የሽግግርና የርክክብ ጊዜ አለ፡፡

ምርጫ 97 እንዲህ ያለ ዝርዝርና ተፍታትቶ የተጻፈና የተሳለ የርክክብ አሠራር ባይኖረውም፣ የሥልጣን ርክክብ የሚያስከትል የምርጫ ውጤት አስመዝግቦ ነበር፡፡ የአዲስ አበባ አስተዳደርን ምክር ቤትና መንግሥት ያሸነፈውና ፒያሳ ላይ መንግሥት የሚመሠርተው፣ መላውን ማዕከላዊ መንግሥት ያሸነፈውና አዲስ አበባንም ያስተዳድር የነበረው የአራት ኪሎው መንግሥት አልነበረም፡፡

በዚህ ምክንያት ምርጫው አዲስ አበባ ላይ የሚከናወን የሥልጣን ርክክብ የሚያስከትል ውጤት ነበረው፡፡

ከሰኔ 23 ቀን 1997 ዓ.ም. ጀምሮ የፀናው ዓላማቸው ትርፍ ማግኘት ያልሆኑ የውጭ ድርጅቶችን፣ እንዲሁም እንቅስቃሴያቸው በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተሞች የሆነ ድርጅቶችንና ማኅበሮችን የመመዝገብ ሥልጣን ከአዲስ አበባ ተወስዶ ወደ ማዕከላዊ መንግሥት የተሰጠው በርክክቡ ወቅት ማዕቀፍ ውስጥ ነው፡፡

የአሠሪና ሠራተኛን ጉዳይ በሚመለከት በአዲስ አበባ ከተማ በፌዴራል መንግሥት ሥር የሚተዳደሩ ድርጅቶችን ጉዳይ የሚያይና የሚወስነው የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ ወደ ፌዴራል መንግሥት ከሰኔ 23 ቀን 1997 ዓ.ም. ጀምሮ ተዛወረ፡፡ ከዚሁ ቀን ጀምሮ በሌላ አዋጅ የሰነዶች ማረጋገጥና ምዝገባ ማሻሻያ ሕግ ወጥቶ በዚሁ ዘርፍ ያለውን የአዲስ አበባ መንግሥት ሥልጣን ልክ አስገባ፡፡ በዚያው ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት ባለሥልጣን መብቶችና ግዴታዎች ለፌዴራሉ የትራንስፖርት ባለሥልጣን ተላለፈ፡፡ የባለሥልጣኑ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሆኖ እንዲደራጅ ታወጀ፡፡ ይህ የሆነው ሐምሌ 30 ቀን 1997 ዓ.ም. በወጣ ሕግ ነው፡፡ እነዚህን አዋጆች ያወጣው ደግሞ በ1997 ዓ.ም. የሥራ ዘመኑን የሚፈጽመው በምርጫ 1997 ውጤት መሠረት 1998 መስከረም ላይ አዲስ ሥራ በሚጀምረው በአዲሱ ፓርላማ የሚተካው ተሰነባቹ ፓርላማ ነው፡፡

የአገራችን የኢትዮጵያ የምርጫ ፋይዳ መለኪያ ማን ያሸንፋል ማለት ድረስ ገና አልደረሰም የምለው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ በሚያሳዝን ሁኔታ ሥልጣንን በምርጫ አሸንፎ መረከብ የሚችል፣ ሥልጣንን በምርጫ ተሸንፎ ማስረከብ ፈቃደኛ የሆነ ኃይል ኢትዮጵያ ገና አምጣ የወለደች አይመስልም፡፡

ከዚህ ይበልጥ የሚያሳዝነው ደግሞ ምርጫችን በደረሰበት የዕድገት ደረጃ ክልል ውስጥ ማስመዝገብ የሚቻለውን እንጥብጣቢ ድልና ፋይዳ ለመቀዳጀት አለመቻላችን ነው፡፡ አሳዛኙን ጉዳይ ድርብርብ የሚያደርገው ሚዲያው የሐሳብ ትግል የሚካሄድበት፣ የተሻለው ሐሳብ አሸንፎ የሚወጣበት መድረክ መሆኑ ቀርቶ የዚህ አደናቃፊ መሆኑ ነው፡፡ ሚዲያው ከአባ ማሳ እሸት እየበላ ነው፡፡ ሚዲያው በደንባራ በቅሎ ላይ ቃጭል እየጨመረ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡ 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...