Saturday, June 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ከኢሕአዴግ ጋር ለመወዳደር ይቅርና አብሮ ለመቆም የሚችል ፓርቲ እንደሌለ እናምናለን››

አቶ ረዳኢ ሃለፎም፣ የኢሕአዴግ የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ

አቶ ረዳኢ ሃለፎም በኢሕአዴግ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ ናቸው፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሶሺሎጂና ሶሻል አንትሮፖሎጂ በቢኤ ዲግሪ የተመረቁት አቶ ረዳኢ፣ በትግራይ ክልል በተለያዩ አካባቢያዊ አስተዳደሮች በመሥራት የሥራ ልምድ አካብተዋል፡፡ የክልሉ የማስታወቂያ ቢሮ ኃላፊ በመሆንም ሠርተዋል፡፡ ከ2001 ዓ.ም. እስከ 2006 ዓ.ም. በመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት አገልግለዋል፡፡ ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ የኢሕአዴግ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ በመሆንም  በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡ ሰለሞን ጎሹ በኢሕአዴግ የምርጫ ዝግጅትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ አቶ ረዳኢ ሃለፎምን አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. ለሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ኢሕአዴግ እንዴት እየተዘጋጀ ነው?

አቶ ረዳኢ፡- ኢሕአዴግ ሁሌ እንደሚያደርገው ምርጫዎች ሲኖሩ በቂ ዝግጅት ያደርጋል፡፡ ለምርጫ 2007 መዘጋጀት የጀመርነው የምርጫ ስትራቴጂ በማዘጋጀት ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሥነ ምግባር አዋጅ የስትራቴጂው አካል ሆኖ እንዲካተት አድርገናል፡፡ የምርጫ ማስፈጸሚያ ዕቅዶችም አሉን፡፡ ለከፍተኛ አመራሮችና ለኢሕአዴግ አባላት በተዋረድ ሥልጠናዎች ሰጥተናል፡፡ የቅስቀሳ ሥራዎቻችንም በሒደት ላይ ነው ያሉት፡፡

ሪፖርተር፡- የመጀመሪያው አምስት ዓመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ (GTPI) አፈጻጸም ገና አልተገመገመም፡፡ ነገር ግን በምርጫ ቅስቀሳችሁ ስለሁለተኛው ዙር ዕቅድ (GTPII) በመጥቀስ ላይ ናችሁ፡፡ ኢሕአዴግ ገዥ ፓርቲ ከመሆኑ አኳያ የምርጫ ስትራቴጂውና ለመራጮች በቀጣይ አምስት ዓመታት የምትሠሩትን ይህ ዕቅድ ይገልጸዋል?

አቶ ረዳኢ፡- ኢሕአዴግ የሕዝብ ፓርቲ ነው፡፡ ኢሕአዴግ እንደሚለውና በተግባርም እንደሚገለጸው የሕዝብን ፍላጎት በግንባር ቀደምትነት እየጠበቀና እየተደራጀ ነው የሚሄደው፡፡ ሕዝባዊ የሆነ ድርጅት በመሠረቱ ቅስቀሳው ቃል ላይ አይመሠረትም፡፡ ይህን አደርግልሃለሁ የሚለው ቅስቀሳ ብዙ ጊዜ ጤናማ አይደለም፡፡ ኢሕአዴግ የሚመርጠው በተግባር ይህን አከናውኛለሁ ነው፡፡ ስለዚህ በእስካሁኑ ሒደታችን ያስመዘገብናቸውን ስኬቶች ነው የምንገልጸው፡፡ ሕዝብ ኮንትራት ሰጥቶናል፡፡ በሰጠን ኮንትራት በቻልነው ያክል ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ነን፡፡ አገሪቱ ፈጣን ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉት ጥቂት አገሮች ተርታ እንድትሠለፍ አድርገናል፡፡ ጉድለቶችም ሲኖሩ እናርማለን፣ እያረምንም ነው፡፡ የሕዝብ አስተዋጽኦና የባለድርሻ አካላትን ግብዓት እየተጠቀምን ነው የምንሄደው፡፡ ስለዚህ ቅስቀሳው በአፈጻጸማችን ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ እግረ መንገዳችንን ግን እነዚህን ነገሮች እናጠናክራለን እንላለን፡፡ የመጀመሪያው አምስት ዓመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ (GTPI) እና ሌሎች ዕቅድና ፕላኖች ዋነኛ ዓላማቸው የኢትዮጵያን ህዳሴ ማረጋገጥ ነው፡፡ የኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ሌት ተቀን የሚራወጠው ይህን ለመፈጸም ነው፡፡ ኢሕአዴግ ግን ይህን አደርግልሃለሁ የሚለውን ቀብድ ወይም ድለላ አይመርጥም፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ የገዥው ፓርቲና የመንግሥት መስመር የተለየ ባለመሆኑ በቅስቀሳዎቹ የሚጠቀሱ ድርጊቶችን ጨምሮ በመንግሥት አቅም የተፈጸሙ ቢሆንም፣ እንደ ኢሕአዴግ ስኬቶች ይቀርባሉ በሚል ትተቻላችሁ፡፡ የእናንተ ምላሽ ምንድነው?

አቶ ረዳኢ፡- ትችቱ ሐሳብ ሆኖ በመቅረቡ ራሱ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን የተነሳው ሐሳብ ሚዛናዊና በተጨባጭ ማስረጃ የተደገፈ ነው ወይ ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ በአጠቃላይ በአደጉ አገሮችም ጭምር መንግሥት የሚያስፈጽመው የገዥው ፓርቲን ሐሳብ ነው፡፡ የዳበረ ዴሞክራሲ ባላቸው አገሮች የተለያዩ ፓርቲዎች እየተፈራረቁ ሥልጣን ስለሚይዙ በመንግሥትና በገዥው ፓርቲ መካከል ያለውን ልዩነት ለማወቅ አስቸጋሪ አይደለም፡፡ ለፓርቲውና ለመንግሥት ግልጽ ቢሆንም ለሕዝቡና ለሦስተኛ ወገን ታዛቢም ልዩነቱ የታወቀ ነው፡፡ በኢትዮጵያም የመንግሥትና የፓርቲ መስመር የተቀላቀለ አይደለም፡፡ ኢሕአዴግ ይህ እንዳይሆን ጥብቅ ጥንቃቄ ያደርጋል፡፡ የሚገናኙ ከሆነም በሕግ በተገደበና በውስጥ ዴሞክራሲያዊ አሠራር ከተወሰነ በኋላ ነው፡፡ ሆኖም አልፎ አልፎ በየደረጃው ይህንን ልዩነት የማያከብሩ ግለሰቦች ይኖራሉ፡፡ በጣም አልፎ አልፎ ይኼ ችግር በአደረጃጀትም ደረጃ ይከሰታል፡፡ ኢሕአዴግ እንደዚህ ዓይነት ችግሮች ሲከሰቱ እንዲታረሙ ያደርጋል፡፡

በቅድሚያ እንዳያጋጥሙ መርሆዎችን እናስቀምጣለን፡፡ ሲያጋጥሙ ደግሞ መርምረን መፍትሔ እናበጃለን፡፡ መንግሥትና ገዥው ፓርቲ አይገናኙ ሊባል አይችልም፡፡ መንግሥት የሚመሠርቱት እኮ የገዥው ፓርቲ አባላት ናቸው፡፡ እነዚህ አባላት ሁለት የተለያዩ ሚናዎችን ይጫወታሉ፡፡ በግለሰብ ደረጃ ግራ የሚጋቡ ቢኖሩም፣ ፓርቲው ለመንግሥትና ለፓርቲው ያላቸውን ሚና ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ሌላው ያው የኢሕአዴግ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ናቸው በመንግሥት እየተተገበሩ ያሉት፡፡ ስለዚህ ኢሕአዴግ በመንግሥትነት ያስመዘገበውን ስኬት መግለጹ ምንም ስህተት የለውም፡፡

ሪፖርተር፡- ከኢሕአዴግ የጥንካሬ ምንጮች አንዱ የአባላቱ ብዛት ነው ይባላል፡፡ አሁን ኢሕአዴግ ምን ያህል አባላት አሉት? ምን ያህሉስ በጥራት የሚያገለግሉና ከጥቅማቸው ባሻገር በፓርቲው ያምናሉ?

አቶ ረዳኢ፡- በእርግጠኝነት ከስድስት ሚሊዮን በላይ አባላት አሉን፡፡ አብዛኛዎቹ የኢሕአዴግ አባላት የአገሪቱን ልማት፣ ሰላምና ዴሞክራሲ ለማረጋገጥ የተሠለፉ ኃይሎች ናቸው፡፡ ለአገሪቱ ለውጥ ዋና ባለድርሻ ሕዝቡ ቢሆንም የኢሕአዴግ አባላትም ግንባር ቀደም ሆነው በመምራትና በመንቀሳቀስ የራሳቸው የማይተካ ሚና አላቸው፡፡ ከፓርቲው አባላት መካከል በተለያዩ ምክንያቶች የጥራት መጓደል ያለባቸው ግለሰቦች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ወደ ኢሕአዴግ የሚገባው ለመስዋዕትነት እንጂ ለጥቅም አይደለም፡፡ አንዳንድ ግለሰቦች ጥቅም አስበው ይገቡና ከገቡ በኋላ እንደሌለ ሲያረጋግጡ የሚለወጡበት ሁኔታ አለ፡፡ የኢሕአዴግ አባል መሆን ማለት የተለየ ጥቅም የሚያስገኝ ነገር አይደለም፡፡ ይህን ለመከላከል የአባላት የማጥራት ሥራ ይሠራል፡፡ የመጀመሪያው ሥራ ደግፎ ማብቃት ነው፡፡ እሱ የማይሳካ ከሆነና ኢሕአዴግ ለሰጠው ተልዕኮ የማይመጥን ከሆነ እንዲወጣ ይደረጋል፡፡ ለአባላት ሥልጠና በመስጠት አቅማቸውን እናጎለብታለን፡፡ ለኢሕአዴግ ዋናው የሥልጠና ማዕከል የጥናት ህዋሳቶች ናቸው፡፡ በዝቅተኛው እርከን ላይ የሚገኙ አደረጃጀቶች ናቸው፡፡ በተጨማሪ ለተወሰኑ ቀናት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ኮንፈረንሶችና መድረኮች እያዘጋጀን በጋራ ልምድ እንዲለዋወጡም እናደርጋለን፡፡ ርዕዮተ ዓለማዊ የሆኑ ክርክሮች የሚደረጉባቸው ሥልጠናዎችም ይሰጣሉ፡፡ 

ሪፖርተር፡- ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአንድ በኩል በጉዳያችን ውስጥ መንግሥት ጣልቃ እየገባብን ነው ይላሉ፡፡ በሌላ በኩል በገንዘብ አቅም ማጣት ምክንያት እንደ ተወዳዳሪ መዘጋጀት አልቻልንም ይላሉ፡፡ የኢሕአዴግ የገንዘብ አቅም የፖለቲካ መጫወቻ ሜዳው ላይ ጉልህ ሚና እንዲጫወት አድርጎታል?

አቶ ረዳኢ፡- የኢሕአዴግ ጥንካሬ ምንጭ መስመሩ እንጂ የገንዘብ አቅሙ አይደለም፡፡ የኢሕአዴግ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ተጨባጭ የሆኑና ለአገር በቀል የአገራችን ችግሮች መፍትሔዎች ናቸው፡፡ ይህን የሠራ ፓርቲ ሰውን ከጎኑ ማሠለፉ አይቀርም፡፡ የያዝከው ፖሊሲ የኃፍረት ምንጭ የሆነውን ድህነትንና ኋላቀርነትን የሚቀርፍ ከሆነ ጉልበት የሚሆንህ ሕዝብ ከጎንህ መሠለፉ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ሁለተኛ ያዘጋጀነውን ፖሊሲና ስትራቴጂ ሕዝቡ እንዲረዳውና ተገንዝቦት ይጠቅመኛል ያለ እንዲደግፍህ ማድረግ አለብህ፡፡ በዚህ ረገድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ዝቅተኛ አፈጻጸም ነው ያላቸው፡፡ አብዛኛዎቹ ተቃዋሚዎች የት እንዳሉ እንኳን ሳይታወቁ ምርጫ ሲደርስ ሲሰበሰቡና ሲበታተኑ ይሰማል፡፡ የፖለቲካ ሥራ የዕድሜ ልክ ሥራ እንደሆነ ሊገነዘቡ ይገባል፡፡ ይኼ ድክመታቸው በሌላ መሸፈን ያለበት አይመስለኝም፡፡ የገንዘብ ችግራቸውን ለመቅረፍ መንግሥት ለፖለቲካ ፓርቲዎች የሚሰጣቸው ድጎማ ቢኖር የተሻለ ይሆናል፡፡ በሙሉ አቅማቸው ስለማይሠሩ ብዙ አባላትን ማፍራት አልቻሉም፡፡ ድጎማ ራሱ በጀት መሆን አይችልም፡፡ የተወሰነ ነገር ነው ሊሸፍንልህ የሚችለው፡፡ በእኛ አገር በ2002 ዓ.ም. ነው የተጀመረው፡፡ ከዚያ በፊት ግን ፓርቲዎች ነበርን፡፡ በገንዘብ እጥረት የተነሳ የተሻለ ሚና መጫወት ያልቻሉ አንዳንድ ፓርቲዎች እንዳሉ እንረዳለን፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ፓርቲዎች የገንዘብ እጥረት እንዳለባቸው ያስመሰሉ እንጂ፣ መስመሩን ያልጠበቀ ገንዘብ እንደሚያገኙ እንገነዘባለን፡፡  

ሪፖርተር፡- የተቃዋሚ ፓርቲዎች የውስጥ ችግር ነው እንጂ፣ የፖለቲካ ምኅዳሩ ግን የጠራ አቋምና አማራጭ ይዞ ወደ ሕዝብ ለሚቀርብ ፓርቲ ምንም ዓይነት ሳንካ አይፈጥርም እያሉኝ ነው?

አቶ ረዳኢ፡- እኔ በግሌ እንዲሁም ፓርቲዬ ኢሕአዴግ በዚህ እናምናለን፡፡ ታግሎ ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ምንም ነገር ባልነበረበት፣ የጠራ አመለካከት ይዘው በዲሲፕሊን ለዓላማቸው ታማኝ ሆነው፣ ሚሊዮኖችን ከጎናቸው አሠልፈው ነው ያን ሰው በላ ሥርዓት የቀየሩት፡፡ በዚህ ረገድ ሁሉም ተቃዋሚዎች ተመሳሳይ ድከመት የላቸውም፡፡ ነገር ግን ሁሉም ማለት ይቻላል አምስቱንም ዓመት ሲጠቀሙ አይታይም፡፡ አንዳንድ ፓርቲዎች ከሥራው ይልቅ ከአንዱ ኤምባሲ ወደ ሌላው የሚዞሩበት ጊዜ ይበልጣል፡፡ ፓርቲዎች ከሕዝቡ ጋር ወርደው የሚገናኙበት ዕድል አሁንም አለ፡፡ ችግሮች እንኳን ቢኖሩ በትግል ማስተካከል ይቻላል፡፡  

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑና ታዛቢዎች የፖለቲካ ባህሉ ፅንፈኝነት እንደሚታይበት ይደመድማሉ፡፡ ኢሕአዴግ ሥልጣን ላይ በቆየባቸው 24 ዓመታት ይህ የፅንፈኝነት ባህርይ ላይ ለውጥ ታይቷል? ኢሕአዴግስ የዚህ ችግር አንዱ ተጠያቂ ነኝ ብሎ ገምግሞ ያውቃል?

አቶ ረዳኢ፡- በኢሕአዴግ እምነት ለውጦች አሉ፡፡ በዚች አገር የተለየ ሐሳብ ይዘህ አደባባይ መውጣት ይቅርና የተለየ አስበህ ይሆናል ተብለህ የምትረሸንበት ወቅት ነበር፡፡ ደርግ ከወደቀ በኋላ በመሣሪያ የተሸነፉ ኃይሎች የተለያዩ ሥልቶች ቀይሰው በሚዲያና በሌላውም ስም ከትጥቅ ትግሉ የማይተናነስ በጣም ፅንፈኛ የሆነ የትግል አቅጣጫ ተከትለው ነበር፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች አሁንም የሚፈለገው ደረጃ ላይ ባይደርሱም፣ እየቀነሱ መጥተዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ የቀነሱት ግን የፖለቲካ ፓርቲዎቹ አስተሳሰብ ስለተቀየረ አይደለም፡፡ ይልቁንም ሕዝቡ ፅንፈኝነት ይብቃኝ በማለቱ ነው፡፡ ስለዚህ ውጫዊ ሁኔታው አስገዳጅ ስለሆነ ሳይወዱ አንዳንዶቹ ለዘብተኛ ሆነዋል፡፡ የተወሰኑት ደግሞ ሰላማዊና ሕጋዊ ከሆነ መንገድ ውጪ አያዋጣም ብለው የቆረጡ አሉ፡፡ ይኼ ትልቅ ስኬት ነው፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅንም ተቀብለው የጋራ ምክር ቤት አቋቁመው የሚሠሩም አሉ፡፡ ከዚህ በፊት ተቃዋሚና ገዥ ፓርቲዎች ማዶ ለማዶ ሆነው ነበር የሚቀመጡት፡፡ ነገር ግን አሁንም ከፅንፈኝነት ያልወጡ ፓርቲዎች አሉ፡፡ ጦርነት የሚቀሰቅሱ፣ ለመንግሥት ተቋማት ዕውቅና የማይሰጡ፣ በሕግ አሸባሪ ተብለው የተፈረጁ አካላትን በአደባባይ ጀግኖች ናቸው ብለው የሚጠሩ ፓርቲዎች አሉ፡፡ ኢሕአዴግ ለዚህ ችግር መፍትሔ የሚያመጣ አካል እንጂ የፅንፈኝነት ምንጭ ነኝ ብሎ አያምንም፡፡

ሪፖርተር፡- የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በ2002 ዓ.ም. ከተቋቋመ በኋላ ያደረጋቸው እንቅስቃሴዎች ምን ያህል ስኬታማ ነበሩ? ዋነኛ ተቃዋሚ ነን የሚሉ ፖለቲካ ፓርቲዎችስ ምክር ቤቱን አለመቀላቀላቸው ምን ዓይነት ተፅዕኖ ፈጥሯል?

አቶ ረዳኢ፡- ምክር ቤት ያልገቡትን ፓርቲዎች ማን ነው ዋነኛ ተቃዋሚ ያደረጋቸው? ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲ እኩል እንደሆነ ኢሕአዴግ ያምናል፡፡ ኢሕአዴግ ልዩ የሚሆነው የመንግሥትነት ኃላፊነት የተሸከመ በመሆኑ ነው፡፡ አንዳንድ ፓርቲዎች ሌሎች ፓርቲዎችን በእኩልነት ለማየት ፈቃደኝነት የላቸውም፡፡ ነገር ግን ምክር ቤቱ በጣም ጥሩ ሥራዎችን እየሠራ ነው ያለው፡፡ አንደኛ ምክር ቤቱ ያቀፈው ሰላማዊ መንገድ የሚከተሉ ፓርቲዎችን ነው፡፡ ሁለተኛ አባላቱ የሚያቀርቡትን ቅሬታ ያስተናግዳል፡፡ መፍትሔ ማግኘት ብቻ ሳይሆን ለቀጣይ አሠራሮች ትምህርትም እንወስድበታለን፡፡ የተለያዩ ሐሳቦች ቀርበው የሐሳብ ፍጭት ተደርጎባቸው የጋራ ስምምነት የተደረገባቸው ይፀድቃሉ፡፡ ምክር ቤቱ ከዕድሜው አንፃር የሚቀረው በርካታ ነገር አለ፡፡ ነገር ግን በጋራ የአገሪቱ ችግሮች ላይ መወያየት መጀመራችን ትልቅ ነገር ነው፡፡ ከተቃዋሚዎች አሳማኝና ጠቃሚ ሐሳብ ሲነሳ ኢሕአዴግ ይቀበላል፡፡    

ሪፖርተር፡- ኢሕአዴግ በሥራ ላይ ያሉትን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ገምግሞ ዋነኛ ተገዳዳሪዬ ነው ብሎ የለየው ፓርቲ አለ?

አቶ ረዳኢ፡- ለይቶ አያውቅም፡፡ መለየትም አያስፈልግም፡፡ ለመለየትም መነሻ ሁኔታዎች የሉም፡፡ የኢሕአዴግ ዋነኛ ተገዳዳሪ ድህነትና ኋላቀርነት ነው፡፡ የራሱን ፖሊሲና ርዕዮተ ዓለም እንኳን በትክክል የማያውቅ የአገራችን ተቃዋሚን ተገዳዳሪ አድርጎ ለመውሰድ መነሻ የለንም፡፡ ኢሕአዴግን የሚያስጨንቀው የራሱ ድክመት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ተቃዋሚ ፓርቲዎች በቅርቡ ባወጧቸው የምርጫ ማኒፌስቶዎች ዴሞክራሲያዊ ተቋማትና የደኅንነት መሥሪያ ቤቶች ከኢሕአዴግ ተፅዕኖ ውጪ አይሠሩም ሲሉ ከሰዋል፡፡ በዚህ ላይ የእናንተ አስተያየት ምንድነው?

አቶ ረዳኢ፡- የአገራችን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ፕሮግራም አለን የሚሉት ያው ምርጫ ሲመጣ በሚያወጡት ማኒፌስቶ ነው፡፡ ይሁንና ማኒፌስቶዎቻቸው በማጥቆርና በመወነጃጀል ላይ ስለሚያተኩሩ ለመራጩ አማራጭ አያቀርቡም፡፡ በሌላው አካላት ጉድለት ላይ ነው የሚንጠለጠሉት፡፡ ኢሕአዴግ ቢጠፋ ኖሮ እነዚህ ተቃዋሚዎች ወዲያውኑ የሚጠፉ ናቸው፡፡ የእኛ አገር ማኒፌስቶ የክስ ፋይል ነው የሚመስለው፡፡ ምርጫ ቦርድ ነፃ አይደለም ይላሉ፡፡ ነፃ ምን ማለት ነው? ቦርዱ እኮ የመንግሥት አንድ አካል ነው፡፡ ምርጫ የሚያስፈጽም አንድ የመንግሥት አካል በመሆኑ ደሴት አይሆንም፡፡ እንዲያውም ቦርዱ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚመጣበት የፖለቲካ ተፅዕኖ የበረታ ነው፡፡ ኢሕአዴግ አድርጎታል ለሚሉት የፖለቲካ ተፅዕኖ ተጨባጭ ማስረጃ አቅርበው አያውቁም፡፡ ሕጋዊ ዕውቅና የሰጣቸውን ቦርድ ዕውቅና አንሰጠውም ለማለት ጊዜ ያልወሰደባቸው ፓርቲዎች አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- አንዳንድ የቦርዱ አባላት የኢሕአዴግ አባላት እንደነበሩ ማስረጃ አቅርበው ነበር፡፡ ይህ በእናንተ ዕይታ ነፃነትን ሊጋፋ አይችልም?

አቶ ረዳኢ፡- በሆነ ወቅት የኢሕአዴግ አባል የነበረ አሁንም የኢሕአዴግን መብት ያስከብራል የምንል ከሆነ፣ በአንድ ወቅት የኢሕአዴግ አመራር የነበሩና አሁን ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚመሩ አካላት የማንን መብት እያስጠበቁ ነው ብለን ልንጠይቅ ነው ማለት ነው፡፡ ይኼ የግለሰቦችን መብት የሚያጣብብ ነው፡፡ አባልነት ለዘለዓለም የሚቀጥል አይሆንም፡፡ አንድ ግለሰብ ሊለካ የሚገባው በተልዕኮው ነው እንጂ በኋላ ታሪኩ መሆን የለበትም፡፡

ሪፖርተር፡- ሰማያዊ ፓርቲና ሌሎች አካላት ኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች እንጂ የግለሰብ አባላት ስለሌሉት ኢሕአዴግን የሚወክል ዕጩ ሊኖር እንደማይችል ተችተዋል፡፡ አራቱ አባል ድርጅቶችም ከሚመሯቸው ክልሎች ውጪ የማይንቀሳቀሱ ክልላዊ ፓርቲዎች በመሆናቸው፣ በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ዕጩ ማቅረቡ ሕገወጥ ነው ብለዋል፡፡ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?

አቶ ረዳኢ፡- ሰማያዊ ቅሬታውን የጻፈው ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነው፡፡ ከኢሕአዴግ ተፅዕኖ ውጪ አይደለም ላለው አካል በኢሕአዴግ ላይ እንዲወስን መጠየቁ እርስ በርስ የሚጋጭ ነው፡፡ ኢሕአዴግ እንደ አገር አቀፍ ፓርቲ የተመዘገበ ፓርቲ ነው፡፡ የኢሕአዴግ አባል ፓርቲዎች ደግሞ ክልላዊ ናቸው፡፡ ስለዚህ ለሌሎች አገር አቀፍ ፓርቲዎች የተፈቀደው ሁሉ ለኢሕአዴግ ይፈቀዳል፡፡ አዲስ አበባና ድሬዳዋ ተጠሪነታቸው ለፌዴራል መንግሥቱ ነው፡፡ የሚተዳደሩት በኢሕአዴግ ኮሚቴ ነው፡፡ የኢሕአዴግ መተዳደሪያ ደንብ በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከመወዳደር የሚከለክለው አይደለም፡፡ የአገሪቱ የምርጫ ሕጎችም ይህንኑ መብት አይከለክሉትም፡፡ ሁኔታዎቹ ግልጽ ከሆኑ ሰማያዊ ፓርቲ ይህን ጥያቄ ለምን አነሳው? ምክንያቱም ከገባበት አጣብቂኝ ያወጣኛል ብሎ ስላሰበ ነው፡፡ አንደኛ የዘጠኝ ፓርቲዎች ትብብር አለኝ አለ፡፡ ብሔራዊ ቦርዱ ዕውቅና አልሰጠሁትም አለ፡፡ ሁለተኛ የሌሎች ፓርቲዎች አባላት በሰማያዊ ስም ይወዳደሩ አለ፡፡ ቦርዱ ሕጋዊ አይደለም አለው፡፡ ይኼ ቅሬታ የሠራውን ስህተትና ሕገወጥ ድርጊት አይሸፍንለትም፡፡ ነገር ግን ሕዝቡ እንዲህ በቀላሉ የሚጭበረበር አይደለም፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ አጭር ዕድሜ የተለያዩ ተቋማትን በማጠልሸት የተሞላ ነበር፡፡    

ሪፖርተር፡- የተለያዩ አጥኚዎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ ሕጉ፣ የፕሬስ ሕጉ፣ የሲቪል ማኅበራት ሕጉና የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ በዴሞክራሲያዊ ሒደቱ ላይ ጫና መፍጠራቸውን ይጠቁማሉ፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም በማኒፌስቶዎቻቸው እነዚህን ሕጎች እንደሚያስወግዱ አልያም መሠረታዊ ማሻሻያ እንደሚያደርጉ አመልክተዋል፡፡ ሁለቱም አካላት ሕጎቹ ከኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ጋር የሚጣጣሙ አይደሉም ይላሉ፡፡ ኢሕአዴግ በእነዚህ ሕጎች ይዞታ ላይ ለውጥ ሊያደርግ ይችላል?

አቶ ረዳኢ፡- አክራሪ ኒዮሊበራሎችና የእኛ አገር ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች በእነዚህ ሕጎች ዙሪያ ጋብቻ ፈጽመዋል፡፡ ማን የማንን አጀንዳ እንደሚያስተጋባ ይታወቃል፡፡ በተቃዋሚ አንደበት የሚነገሩ ግን የኢትዮጵያን ሕዝቦች የማይጠቅሙ አጀንዳዎች ናቸው፡፡ የሲቪል ማኅበራት ሕግ እኮ የተገኘውን ገንዘብ በብዛት በልማት ላይ ማዋል ያስፈልጋል ነው የሚለው፡፡ አሁን እኮ ማኅበራቱ በቁጥር ጨምረዋል፡፡ የሚዲያ ሕጉም የሚዲያ ቢዝነስን ለውጭ ኢንቨስትመንት የተከለከለ ዘርፍ ስላደረገው ነው የሚከራከሩት፡፡ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁም የሚያስደነብረው አካል አለ፡፡ ኢትዮጵያ የሽብር አደጋ የለበትም ብለው የሚከራከሩ ፓርቲዎች አሉ፡፡ ያከሸፍናቸው የሽብር አደጋዎች ተሳክተው ቢሆን ኖሮ ውጤቱ ምን እንደሚሆን ጎረቤቶቻችንን እነ ኬንያን ማየት ይበቃል፡፡ የውጭ ዜጎችም አዋጆቹን ሲተቹ በደፈናው ነው እንጂ አንቀጽ ጠቅሰው አይደለም፡፡ ከዚያም በላይ ጉዳዩ የሉዓላዊነት ጥያቄ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አጥኚዎችና ተቃዋሚዎች በተመሳሳይ የሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ አስፈላጊ እንደሆነ ይስማማሉ፡፡ ሕገ መንግሥቱ በሥራ ላይ በቆየባቸው 20 ዓመታት ማሻሻያ ተደርጎበት አያውቅም፡፡ ሕገ መንግሥቱ ራሱ የማሻሻያ ሥነ ሥርዓት ቢያስቀምጥም ኢሕአዴግ ማሻሻያን እንደ ሥርዓት መፍረስ ይወስዳል እየተባለ ይተቻል፡፡ ይህ አመለካከት እውነተኛ ፍላጎት በመያዝ ሕገ መንግሥቱ ተሻሽሎ የተለወጡ ነገሮችን እንዲይዝ የሚታገሉ ሰዎችን ተስፋ እያስቆረጠ መሆኑን የሚጠቁሙ አሉ፡፡ ኢሕአዴግ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያን ለምን ይፈራል?

አቶ ረዳኢ፡- የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የኢሕአዴግ ሳይሆን የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሕገ መንግሥት እንደሆነ በቅድሚያ ከግንዛቤ ውስጥ ሊገባ ይገባል፡፡ ሕዝቡ ይበጀኛልና ይጠቅመኛል እስካለ ድረስ እኔ ነኝ የማውቅልህ ማሻሻያ ይደረግበት ማለት ጤነኛ አይመስለኝም፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያን ሕዝቡ የጠየቀው መቼ ነው? የማሻሻያ ሒደቱን አክብሮ ከመጣ ቀዳሚው ደጋፊ ኢሕአዴግ ነው የሚሆነው፡፡ ኢሕአዴግ ግን እኔ አውቅልሃለሁ ብሎ ሕገ መንግሥቱን አያሻሽልም፡፡

ሪፖርተር፡- ከምርጫ 2002 በኋላ ነው ኢሕአዴግ የልማታዊ መንግሥትን ሞዴል መከተል የጀመረው፡፡ ይህ ሞዴል አብዮታዊ ዴሞክራሲን ተክቶ ነው እየሠራ ያለው ወይስ ጎን ለጎን እየሄዱ ነው?

አቶ ረዳኢ፡- ኢሕአዴግ የሚከተለው ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር ነው፡፡ አብዮታዊነት የልማቱና የዴሞክራሲው ተፈጥሮ ነው፡፡ አብዮቱ ልማትና ዴሞክራሲን ያጣምራል፡፡ ባለሀብቱ ሊሞላቸው ያልቻሉ የገበያ ጉድለቶችን መንግሥት ሊሸፍን ይገባል፡፡ ስለዚህ ልማታዊ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ተፈጥሮ ደግሞ ብዝኃነት አለው፡፡ ተፈጥሮአዊ ልዩነቶች አሉን፡፡ ስለዚህ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ ሁሉም ሊስተናገዱና ዕውቅና ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ሁለቱ ሲጣጣሙ መሠረታዊ ለውጥ ያመጣሉ፡፡ ቶሎ ማደግ ስለምንፈልግ ይኼ ያስፈልገናል፡፡ ሁሉም አንድ ላይ አሉ፡፡ የጠፋ ነገር የለም፡፡ ኢሕአዴግ አብዮታዊ ድርጅት ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- የልማታዊ መንግሥት ሞዴል የመንግሥት የልማት ሞዴል በመሆኑ የፓርቲ ርዕዮተ ዓለም ሊሆን አይችልም በማለት የሚተቹ አሉ፡፡

አቶ ረዳኢ፡- ይኼ ርዕዮተ ዓለም ለመንግሥት እንጂ ለፓርቲ አይሆንም የሚሉ አካላት ወይ በጉዳዩ ላይ በቂ ዕውቀት የላቸውም አልያም ሆን ብለው ማታለል ይፈልጋሉ፡፡ ልማታዊ መንግሥት ያለባቸው አገሮች እኮ በፓርቲ ነው የሚመሩት፡፡ ስለዚህ የፓርቲውን አስተሳሰብ የሚያስፈጽሙ ናቸው፡፡ ልማታዊ መንግሥታት በነበሩባቸው አገሮች ጠንካራ አሃዳዊ ፓርቲዎች ነበሯቸው፡፡ ስለዚህ ይኼ መሬት ላይ የሚረግጥ አስተያየት አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ኢሕአዴግ በተግባር ልማቱንና ዴሞክራሲውን እኩል እያስኬድኩት ነው ብሎ ያምናል?

አቶ ረዳኢ፡- እኩልነት እንደ ዕይታችን የሚወሰን ነው፡፡ ለኢሕአዴግ ልማት፣ ሰላምና ዴሞክራሲ የህልውና ጉዳይ ናቸው፡፡ መርጠን የምንፈጽማቸው ነገሮች አይደሉም፡፡ ከዚህ በላይ ክብደት ልንሰጥ አንችልም፡፡ ዴሞክራሲ እርግጥ ሒደት ነው፡፡ ይኼ ማለት ለነገ የምናሳድረው ነገር ይኖራል ማለት አይደለም፡፡ ትናንት ብዙ ያልተማሩ ሰዎች ነበሩን፡፡ ዛሬ ከ25 ሚሊዮን በላይ የተማሩ ሰዎች አሉን፡፡ እነዚህ ዜጎች የበለጠ ግንዛቤ ይኖራቸዋል፡፡ ስለዚህ ለመብታቸው የተሻለ ይታገላሉ፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህኛው ምርጫ ነባር አመራሮች ሙሉ በሙሉ ይተካሉ ተብሎ ነበር፡፡ ይህ ይፈጸማል?

አቶ ረዳኢ፡- መተካካት ሒደት በመሆኑ አይጠናቀቅም፡፡ አንድ ትውልድ የሚጓዘው ግን እስከተወሰነ ድረስ ነው፡፡ ሕዝባችን በየጊዜው የሚጠይቃቸውን አዳዲስ ጥያቄዎች ለመመለስና አዳዲስ አስተሳሰቦችን በአግባቡ ለማስተናገድ መተካካት ቀጣይነት ይኖረዋል፡፡ በምርጫ 2007 የሚጠናቀቅ መተካካት የለም፡፡

ሪፖርተር፡- በምርጫ 2002 አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ አባልና አንድ የግል ተወዳዳሪ ሲቀር ፓርላማውን ኢሕአዴግና አጋሮቹ አሸንፈዋል፡፡ በዘንድሮው ምርጫ ዕቅዳችሁ ምን ያህል ወንበር ለማሸነፍ ነው?

አቶ ረዳኢ፡- በምርጫ 2002 ተቃዋሚዎች ወደ ፓርላማ እንዳይገቡ በሕዝብ ተከልክለዋል፡፡ ከኢሕአዴግ ጋር ለመወዳደር ይቅርና አብሮ ለመቆም የሚችል ፓርቲ እንደሌለ እናምናለን፡፡ ይህ ከሠራነው ሥራ የመጣ መተማመን ነው፡፡ ነገር ግን ውሳኔው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነውና ለሕዝቡ እተወዋለሁ፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ18 ቀናት ግዢ መፈጸሚያ ብቻ እንደሚሆን አይኤምኤፍ ተነበየ

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ0.6 ወር ወይም...

ብሔራዊ ባንክ ለጥቃቅንና አነስተኛ ብድሮች ዋስትና መስጠት ሊጀምር ነው

ኢንተርፕራይዞችን ብቻ የሚያገለግል የፋይናንስ ማዕከል ሥራ ጀመረ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ...

የአየር መንገድ ተጓዦች በሻንጣ የሚያስገቡትን የልብስና የጫማ ብዛት የሚገድብ ረቂቅ መመርያ ተዘጋጀ

ከቀረጥ ነፃ ይገቡ የነበሩ ዕቃዎች 87 በመቶ እንዲቀንሱ ተደርጓል መንገደኞች...

አይኤምኤፍና ዓለም ባንክ በኢትዮጵያ የሁለትዮሽ የምንዛሪ ገበያ እንዳይኖር ሊመክሩ ነው

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አይኤምኤፍና ዓለም ባንክ በኢትዮጵያ ያለውን...