Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትደሴቲቱ ማዳጋስካር የካፍን መንበረ ሥልጣን ተረከበች

ደሴቲቱ ማዳጋስካር የካፍን መንበረ ሥልጣን ተረከበች

ቀን:

  • ኢሳ ሐያቱ ለሽንፈታቸው ፊፋንና ተከታዮቹን ተጠያቂ አድርገዋል

አዲስ አበባ ታሪካዊ ክስተት የተከናወነበትን ጉባኤ አስተናግዳለች፡፡ ዓለም ከአዲስ አበባ የተደመጠውን ያልተጠበቀ ዜና ከዳር እስከ ዳር ተከታትላለች፡፡ ካሜሩናዊው ኢሳ ሐያቱ ለሦስት አሠርታት የነገሡበትን በትረ ሥልጣን ሳያስቡት ለማዳጋስካር ያስረከቡበት ሁኔታና ሽንፈታቸው ለዓለም መገናኛ አውታሮች ዋና ርዕስ ሆኗል፡፡ ማዳጋስካራዊ አህመድ አህመድ የካፍ የቀጣዩ አራት ዓመት ፕሬዚዳንት ሆነው ተመርጠዋል፡፡

በአዲስ አበባው 39ኛው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ጉባኤ ወቅት የተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ፣ በአፍሪካ እግር ኳስ እዚህ ግባ የሚባል ሚና የሌላትን ማዳጋስካርን የወከሉት አህመድ አህመድ ለአሸናፊነት የበቁበት ሒደት ለብዙ አገሮች እንደ ትንግርት ሆኖባቸው ታይተዋል፡፡ የ70 ዓመቱ ኢሳ ሐያቱ የሚብጠለጠሉባቸው፣ በክፉ የሚነሱባቸው በካፍ የቆዩባቸው ዓመታት ያከተመበትን ክስተት ያስተናገደችው አዲስ አበባ፣ የአሸናፊና ተሸናፊን የደስታ ፈንጠዝያና የድንጋጤ ስሜቶችን ለዓለም አሳይታለች፡፡

በአፍሪካ አገሮች የፖለቲካ ባለሥልጣናት ሳይቀር የኢሳ ሐያቱ የተንዛዛ የካፍ አገዛዝ ዘመን እንዲያከትም ብዙ ሲባል ቆይተዋል፡፡ ሐያቱ በሥልጣን ዘመናቸው ለአህጉሪቱ እግር ኳስ ከሠሩት ጥሩ ነገር ይልቅ፣ ከሙስናና መሰል ድርጊቶች ጋር በማገናኘት መታማታቸው ለመንበረ ሥልጣናቸው ማብቃት ዓይነተኛ ሚና መጫወቱ እንዳልቀረ ነው ብዙዎች የሚስማሙት፡፡ ለዚህ በማሳያነት የሚቀርበው ደግሞ አዲሱ የካፍ ፕሬዚዳንት የመሆን ሐሳቡም ሆነ ፍላጎቱ ኖሯቸው እንደማያውቁ፣ ነገር ግን በለውጥ ፈላጊዎች ጉትጎታ ወደ አህጉራዊ የካፍ አመራርነት ቦታ ለመምጣት የተነሳሱት አህመድ አህመድን በመጥቀስ የሚከራከሩ አሉ፡፡ ኢሳ ሐያቱና ደጋፊዎቻቸው ባልጠበቁት ዕጩ ከመንበራቸው መሰናበታቸው ያልተጠበቀ ያሰኘውም ይኼው ነው፡፡

ከደሴቲቱ ማዳጋስካር አንጋፋውን ተቋም ለመምራት የተወነጨፉት አህመድ አህመድ፣ የኢሳ ሐያቱን አመራርና የካፍን አሠራር በሰላ ትችት ሲኮንኑ የቆዩ መሆናቸውም ይነገርላቸዋል፡፡ ምክንያቱም እንደ ደሴት ከአፍሪካ እግር ኳስ ራሷን ነጥላ ጠንካራ ተሳትፎና ሚና ሳይኖራት 60 ዓመታት ያሳለፈችውን ማዳጋስካር ወደ አመራር ሰጪነት ያመጡት አህመድ አህመድ፣ በምርጫው ሒደት ከጋዜጠኞች እስከ ፖለቲከኞች የተባበረ የድጋፍ ኃይል እንደነበራቸው በምርጫው ካገኙት ወደ እጥፍ የሚጠጋ የድምፅ ብልጫ ይልቅ የአሸናፊነታቸው ዜና ሲበሰር በአዳራሹ የታየው ትዕይንት በቂ ማሳያ እንደነበር ታይቷል፡፡

ካፍን ለ29 ዓመታት ያስተዳደሩት ካሜሩናዊ ኢሳ ሐያቱ ለሽንፈታቸው የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) እና ተከታዮቹ፣ ዕድሜያቸውን ምክንያት በማድረግ በሠሩባቸው ደባ መሆኑን በይፋ ተናግረዋል፡፡ አዲሱ የካፍ ፕሬዚዳንት አህመድ አህመድ በበኩላቸው ካፍ የዕድሜውን ያህል ዕድገት ሳያሳይ መቆየቱን በመጥቀስ፣ በእሳቸው የአመራርነት ዘመን እንደሚያዘምኑት ጭምር ነው አጽንዖት ሰጥተው የተናገሩት፡፡

የ57 ዓመቱ ማዳጋስካራዊ አህመድ ካፍ በተቋም ደረጃ መታወቅ ከጀመረ ረዥም ዓመታት ማስቆጠሩ እንደ ስኬት ካልተቆጠረ በስተቀር፣ እግር ኳሱ ከሌሎች አህጉሮች አንፃር ሲታይ ብዙ እንደሚቀረው፣ ለዚህ ደግሞ ተቋሙ ሲከተለው የቆየው በሙስናና በጥቅማ ጥቅም የተሳሰረ አሠራር እንደሚጠቀስም ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን የግድ ለውጥ እንደሚያስፈልገው ከምርጫው አስቀድሞ በተሰጣቸው መድረክ ለጉባኤው በይፋ አስረድተዋል፡፡ ባልተጠበቀ የድምፅ ልዩነት 34 ለ20 የተሸነፉት ሐያቱ ለሽንፈታቸው ምክንያት ያደረጉት ፊፋ ፕሬዚዳንት ጣሊያናዊ ጅያኒ ኢንፋንቲኖ አፍሪካውያኑ ለውጥ ከፈለጉ ‹‹ጊዜው አሁን ነው›› ብለው ሁሉም የካፍ አባል አገሮች መምረጥ ያለባቸውን ከመወሰናቸው በፊት አንድ ጊዜ ሳይሆን፣ ሁለትና ሦስት ጊዜ መላልሰው አስበው ሊመርጡ እንደሚገባ ኢሳ ሐያቱ ለሚመሩት የካፍ ጉባኤ ማሳሰባቸው ትኩረት ስቦ ነበር፡፡

የምርጫው ውጤት ከታወቀ በኋላ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ጉባኤተኞች፣ የኢሳ ሐያቱ የአመራርነት ሚና ማብቃት እንዳለበት የሚጠቁም ነው፡፡ ምርጫው ከተጠናቀቀ በኋላ ውጤቱም ያሳየው ይህንኑ ነው፡፡ ይሁንና ካፍን ጨምሮ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ ለብዙ ዓመታት በመሥራት የሚታወቁት ቀደምት ጋዜጠኛው ፍቅሩ ኪዳኔ ውጤቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ከምርጫው ጀርባ የተሠራውን የምርጫ ቅስቀሳ ሒደት ይኮንናሉ፡፡

እንደ አቶ ፍቅሩ፣ ‹‹ለውጥን የሚጠላ ማንም ሰው ሊኖር አይችልም፡፡ ነገር ግን ከለውጡ ጀርባ የውጭ ኃይሎች ለለውጡ የነበራቸው ሚና የሚያሳዝን ነበር፤›› ብለው በአፍሪካ እግር ኳስ ይህ ነው የሚባል ስምና ዝና የሌላቸው እንደ ማዳጋስካር፣ ጂቡቲና ሴራሊዮን የመሳሰሉት ከፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ባልተናነሰ ለሥራ አስፈጻሚ አመራርነት እንዲበቁ የተደረገበትን አግባብ ይተቻሉ፡፡ መገናኛ አውታሮችን ጨምሮ ሁሉም እንደተከታተለው ግብፆች በጉባኤው የመጀመርያ ቀን ውሎ ከቴሌቪዥን መብት ጋር ተያይዞ ክስ ማቅረባቸውን ያስታወሱት አቶ ፍቅሩ፣ በፊፋ ምርጫ ወቅት ከብዙዎቹ የአፍሪካ አገሮች ድምፅ የሰጡት ማዳጋስካር፣ ኮንጎና ጂቡቲ ስለነበሩ በካፍ ምርጫ ከነዚህ አገሮች ውጪ ሌሎች አገሮች እንዳይመረጡ ሰፊ ቅስቀሳ ሲደረግ እንደነበርና ዕውን እንደሆነም ይናገራሉ፡፡

ኢሳ ሐያቱ ከዕድሜና መሰል ችግሮች ጋር ተያይዞ በካፍ ያላቸውን ሥልጣን እንዲለቁ የብዙ አገሮች ፍላጎት መሆኑን ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ፍቅሩ፣ ‹‹ዕድሜ ምክንያት ሊሆን አይችልም፡፡ ምክንያቱም ብራዚላዊ ጆን ሐቫላንጅ፣ የቀድሞ የፊፋ ፕሬዚዳንት ሴፕ ብላተር፣ የዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ (አይኦሲ) ፕሬዚዳንት  አንቶኒዮ ሳማራንሽ ዕድሜያቸው ከሐያቱ በላይ የነበሩ ናቸው፡፡ በመሠረቱ የዕድሜ ጣሪያ ገደብ የተጣለው ፊፋ ብራዚል ባስተናገደችው የዓለም ዋንጫ በሳኦፖሎ ባደረገው ስብሰባ ላይ ነው፡፡ በዚያ ስብሰባ የአገልግሎት ዘመኑ ለሦስት ዙር ብቻ እንዲሆን ነው ውሳኔ ያሳለፈው፡፡ ይህንኑ መነሻ በማድረግ የፊፋ አስተዳደራዊ ኮሚቴ ከሁለት ዓመት በፊት ፊፋ በብራዚል ያፀደቀውን ሕግ የአሁኑን የካፍ ጉባኤ ለመተቸት እንዲያመች ተደርጎ ቀርቧል፡፡ በአጠቃላይ የአሁኑ የካፍ ምርጫ በፊፋ ፍላጎት ብቻ እንዲጠናቀቅ የተሠራ ተንኮል ለመሆኑ መረዳት አያዳግትም፤›› በማለት ፊፋንና በዙሪያው ያሉትን ኃይሎች ተችተዋል፡፡ የሐያቱ ሽንፈት ሊመጣ የቻለውም ይህንኑ ተከትሎ እንደሆነ አቶ ፍቅሩ ይናገራሉ፡፡

ከ39ኛው የካፍ ጉባኤና ምርጫ ጎን ለጎን በአፍሪካ እግር ኳስ ብዙ ድርሻ ያላቸው ኢትዮጵያን ጨምሮ ብዙ አገሮች በካፍ የአመራርነት ሚና እንዲኖራቸው አልተደረገም፡፡ በአብዛኛው ለአመራር ሰጪነት የበቁት በአፍሪካ እግር ኳስ ስምና ታሪክ የሌላቸው ናቸው፡፡ ከዚህ አኳያና በተለይም ኢትዮጵያ ለወደፊቱ በካፍ ውስጥ ስለሚኖራት ድርሻ ምን ማድረግ ይጠበቅባታል? ለሚለው የሪፖርተር ጥያቄ አቶ ፍቅሩ፣ ‹‹ኢትዮጵያ የካፍ መሥራች አገር ስለሆነች ብቻ የተለየ ቦታ እንዲሰጣት አይጠበቅም፡፡ እንደሌሎች አገሮች ተወዳዳሪ ለመሆን መሥራት ይጠበቅባታል፡፡ ለዚህ ደግሞ እግር ኳሱን ጨምሮ በሌሎችም ስፖርቶች፣ ስፖርቱን የሚያውቁ ሰዎች ወደ ተቋማቱ ሲገቡና ጠንካራ ግንኙነት ሊያደርጉ የሚችሉበት ሁኔታ ሲመቻች ነው ለውጥ ሊመጣ የሚችለው፤›› ብለዋል፡፡

እንደዚያም ሆኖ ሲሉ ያከሉት አቶ ፍቅሩ፣ በአሁኑ ምርጫ ከኃላፊነታቸው የተነሱት ኢሳ ሐያቱ እንደ ኢትዮጵያ የመሰሉ አገሮች በካፍ ውስጥ ተገቢው ቦታ የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲኖር ያስቡ እንደነበር ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ ‹‹ማዳጋስካራዊው በመሀል ገብተዋል እንዴት ይሆናል? ወደፊት የምናየው ነው የሚሆነው፤›› ሲሉ አሳስበዋል፡፡

ስለ ቀጣዩ የአህመድ አህመድ አስተዳደር አስመልክቶም አቶ ፍቅሩ ለጊዜው ምንም ማለት እንደማይቻል፣ በሒደት ግን እንደሚታይ ጭምር ተናግረዋል፡፡ ‹‹አዲሱ የካፍ ፕሬዚዳንት ቃላቸውን የሚጠብቁ ከሆነ ለአባል ፌዴሬሽኖች ተገቢውን የፋይናንስ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ነው፡፡ እንዴትና በምን አግባብ የሚለውንም ወደፊት የምናየው ነው የሚሆነው፤›› በማለት ጭምር አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ሌላው ካፍ 60ኛ የምሥረታ በዓሉን ባከበረበት የአዲስ አበባው ጉባኤ፣ ዛንዚባርን የማኅበሩ 55ኛ አባል አድርጎ ተቀብሏታል። ለአፍሪካ እግር ኳስ ትልቅ ድርሻ ላበረከቱ ሁለት ክለቦች የኢትዮጵያው ቅዱስ ጊዮርጊስና የግብፁ አልሃሊን ሸልሟል፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ የቦርድ ሊቀመንበር አቶ አብነት ገብረመስቀል ተቀብለዋል፡፡ ከሁለቱ ክለቦች የቦርድ ሊቀመናብርት በተጨማሪ በስፖርት ጋዜጠኝነት ለአህጉሪቱ እግር ኳስ ለሠሩ አምስት የአፍሪካ ጋዜጠኞች ልዩ የክብር ሽልማትም አበርክቷል፡፡ ከኢትዮጵያ ለዚህ ልዩ ሽልማት የበቃው ጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...