Sunday, June 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

‹‹ንግድ ምክር ቤቱን ውጭ ሆነህ ስታየውና ውስጥ ገብተህ ስትመለከተው የተለየ ነው›› አቶ ሞላ ዘገየ፣ የሕግ ባለሙያ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

አቶ ሞላ ዘገየ የሕግ ባለሙያ ናቸው፡፡ በእርሳቸውና በቤተሰቦቻቸው የተቋቋመ ሞላ ዘገየና ቤተሰቦቻቸው የተባለ ድርጅትም አላቸው፡፡ ባለፈው ዓመት በተካሄደና በፍርድ ቤት ታግዶ በነበረው የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ በተካሄደው ምርጫ የቦርድ አባል ለመሆን በከፍተኛ ድምፅ ከተመረጡት ሁለት ተመራጮች መካከል አንዱ ናቸው፡፡ ንግድ ምክር ቤቱን ለአንድ ዓመት ቦርድ በመሆን አገልግለዋል፡፡ በድጋሚ በተደረገው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫ ላይ ግን አልተሳተፉም፡፡ ለምን እንዳልተሳተፉና በአጠቃላይ የንግድ ምክር ቤቱን እንቅስቃሴ በተለይም የአንድ ዓመት ቆይታቸው ምን እንደሚመስል የሚያብራሩበትን ቃለ ምልልስ ከዳዊት ታዬ ጋር አድርገዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በፍርድ ቤት ውሳኔ እንደገና በተደረገው ምርጫ ላይ አብዛኛዎቹ የቦርድ አባላት በድጋሚ ተወዳድረው ሲመረጡ እርስዎ አልተካተቱም፡፡ ለምን አልተወዳደሩም?

አቶ ሞላ፡- በአጋጣሚ ከኢትዮጵያ ውጭ ስለነበርኩ ብኖርና ብጠቆም ልመረጥ እችል ይሆናል፡፡ ግን ለሕክምና ውጭ አገር ስለነበርኩ በጠቅላላ ጉባዔው ላይም አልተሳተፍኩም፡፡

ሪፖርተር፡- ለአንድ ዓመት በቦርድ አባልነት ንግድ ምክር ቤቱን አገልግለዋል፡፡ ቆይታዎ እንዴት ነበር? ምንስ ሠርተናል ብለው ያምናሉ?

አቶ ሞላ፡- ሁሉም እንደሚያውቀው ለአንድ ዓመት የሥራ ላይ የነበረው ቦርድ  ጠንካራ ነበር፡፡ ፕሬዚዳንቱ ቅንና ለሥራ ተነሳሽነት ያላቸው ናቸው፡፡ ሌሎችም የቦርድ አባላት አንዳንድ ውስንነት ይኖራቸው ይሆናል እንጂ የቦርድ አባላቱ ጠንካራና ሊሠሩ የሚችሉ ናቸው፡፡ ስንመርጥ የገነባው ቃል አለ፡፡ በግሌ ላደርግ የሚገባኝን በወቅቱ አቅርቤያለሁ፡፡ ለምርጫ ስንቀርብ የተናገርኩን ቃል በቃል አስታውሳለሁ፡፡ ‹‹እኔ የሕግ ባለሙያና የቢዝነስ ኢንተርፕረነር ነኝ፡፡ የዝቅተኛውንና የመካከለኛውን ነጋዴ ችግር በጽሕፈት ቤቱ በኩል እያስጠናሁ ከመንግሥት ጋር እደራደራለሁ፡፡ ችግሩ በድርድር ካልተፈታ በፍርድ ቤት እሟገታለሁ፤›› ብዬ ነበር ቃል የገባሁት፡፡ ነገር ግን ንግድ ምክር ቤቱን ውጭ ሆነህ ስታየውና ውስጥ ገብተህ ስትመለከተው የተለየ ነው፡፡ የንግድ ምክር ቤቱ የጽሕፈት ቤት አደረጃጀት ዘመናዊ ነው፡፡ ፕሮፌሽናል ነው፡፡ ፕሮፌሽናል ጸሐፊም አለው፡፡ ነገር ግን በአጀንዳ ቅደም ተከል ረገድ ችግር አለ፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ዓይነት ችግር?

አቶ ሞላ፡- ችግሩ አዲስ የተመረጠው ቦርድ የራሱን አጀንዳ ለመቅረፅ ያለመቻሉ ነበር፡፡ አጀንዳውን የሚቀርፀው ጽሕፈት ቤቱ ነው፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ቦርዱ የራሱን አጀንዳ ቀርጾ በነጭ ወረቅ ላይ አስፍሮ ጽሕፈት ቤቱን ይህንን ፈጽም ማለት ያለመቻሉን ነው እንደ ችግር የማስበው፡፡ መሥራት የነበረብንን ያህልም አልሠራንም፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ከሆነ ንግድ ምክር ቤቱን በነጋዴው ሳይሆን በጽሕፈት ቤቱ ነው የሚመራው፤ ጽሕፈት ቤቱ የበላይ እየሆነ ነው የሚለውን አስተያየት አያጠናክርም?

አቶ ሞላ፡- እንግዲህ የበላይ ነው የሚለው ቋንቋ ትንሽ ከበድ ይላል እንጂ የሚመስል ነገር ሊኖረው ይችላል፡፡ እውነት ለመናገር ግን የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ ጠንካራ ናቸው፡፡ ለምሳሌ የንግድ ልዑካን ወደ ውጭ በሚሄዱበት ጊዜ የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ ገለጻ ሲያደርጉ ብትመለከት የንግድ ምክር ቤት ጸሐፊ አይመስሉም፡፡ እንደ አንድ የመንግሥት ኃላፊ የአገሪቱን የኢንቨስትመንት ዕድልና ተያያዥ ጉዳዮች በሚገባ ያቀርባሉ፡፡ ኢንቨስትመንት እንዲመጣ ይተጋሉ፡፡ ይህ የሚያሳይህ የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቅም እንዳለባቸው ነው፡፡ ይህ ከበጎ ነገር በመነሳት ነው፡፡ ነገር ግን በቦርድ ላይ ይኼ ነው የማይባል ተፅዕኖ ያሳድራሉ፡፡ ነገሩ ከበጎ ስሜት በመነሳት ይሆናል ተፅዕኖ የሚያደርጉት፤ በተለያዩ ጉዳዮች ወጠሩን፤ አጀንዳዎቹ እያመጡ ያዙን፡፡ ትናንት በተቀረፁ አጀንዳዎችና ለነጋዴው ይጠቅማሉ ብለው በሚያቀርቡልን አጀንዳ ተወጥረን የራሳችንን አጀንዳ መቅረፅ ስላልቻልን ጽሕፈት ቤቱ የበላይ መሰለ፡፡ በሌላ በኩል ስታየው ደግሞ ዋና ጸሐፊው በጎ ጐን አላቸው፡፡ የኮሙዩኒኬሽን ሰው ናቸው፡፡ አንድ ዓመት ብንቀጥልና ሥራውን በደንብ እየተለማመድን ብንሔድ ኖሮ የራሳችንን አጀንዳ (የቦርዱን አጀንዳ) ቀርፀን ቅደም ተከተል አስይዘን እንዲፈጸም ለማድረግ እንችል ነበር፡፡ አልሆነም፡፡ ምን ሠራችሁ ለሚለው ጥያቄም ጽሕፈት ቤቱን የሚያጠናክሩ አንዳንድ ጉዳዮችን ከመወሰን በቀር ይኼነው የምልህ የለም፡፡

ሪፖርተር፡- በአሠራሩ ግን አንድን ተቋም የመምራት፣ አጀንዳ የመቅረፅና አመራር የመስጠቱ ኃላፊነት የቦርዱ ነው ወይስ የጽሕፈት ቤቱ?

አቶ ሞላ፡- የቦርዱ ነው፡፡ በሕጉም በአዋጁም የተቀመጠው አጀንዳ የመቅረፅ ኃላፊነት ያለበት ቦርዱ ነው፡፡ ቦርዱ አጀንዳውን ካልቀረፀውስ? የራሱ አጀንዳ ከሌለውስ? ችግሩ ያለው እዚያ ላይ ነው፡፡ እኛ ተመርጠን ስንገባ ወደ ሥራ የገባነው ቀጣይነት ያለውና ተከታታይ ጉዳዮች ላይ ነው የገባነው፡፡ እኛ ግን ማድረግ የነበረብን የንግዱን ኅብረተሰብ የሚጠቅም አጀንዳ ማመንጨት የሚችል የጥናትና የምርምር ተቋም በማቋቋም ከዚያ በሚገኘው ግብዓት እንዲሁም የራሳችንን አጀንዳዎች ቀርፀን ሥራ ላይ ማዋል ነበረብን፡፡   ዘግይቶም ቢሆን ግን የጥናትና የምርምር ተቋም ተቋቁሟል፡፡ ቀደም ብሎ ይህ ተቋም ቢኖር ኖሮ የነጋዴውን ችግር ለይተህ ያለውን ችግር መፍታት ይችል ነበር፡፡ ግን ይህ አልሆነም፡፡ ስለዚህ አሁን እንደታየው ውስጡ ስትገባ ወሳኝ አጀንዳዎችን ለማየት ጊዜ አልነበረም፤ አንድ ዓመት በጣም አጭር ነው፡፡ ሳታስበው ያልቃል፡፡ የምንሰበሰበው የተወሰነ ጊዜ ነው፤ ይህንንም ስብሰባ የአንተ ባልሆነ አጀንዳ ላይ ነው የምትነጋገረው፤ ምናልባት ቅድሚያ በማይሰጠው ነገር ላይ ነው የምትወያየው፡፡ ስለዚህ ብዙ አጀንዳዎች ቀድሞ የነበሩ በመሆናቸው ጊዜ ወሰዱ፡፡

      ከዚህ አንፃር ይህንን ጽሕፈት ቤት ሊቆጣጠር የሚችል ቦርድ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ያ ባለመሆኑ ነው ጽሕፈት ቤቱ በቦርዱ ላይ የበላይነት ያለው የሚያስመስለው፡፡ ቦርዱ በአዋጅና በመመርያ የተሰጠውን ሥልጣን ሊጠቀምበት ይገባል፡፡ ቦርዱ ይህንን ሥራ ብሎ ለጽሕፈት ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቶ ማሠራት አለበት፡፡ እንዲህ ሥራ ተብሎም አልሠራም ያለበትን አጋጣሚ አውቅም፡፡ ይህ ቢሆን ኖሮ ጽሕፈት ቤቱ የበላይ ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ሲባል ግን የጽሕፈት ቤቱ ጥንካሬና አደረጃጀት ማድነቅ ያስፈልጋል፡፡ አመራር በመስጠት በኩል እንዲሁም አጀንዳ የመቅረፅ ሥራ የቦርዱ መሆን አለበት፡፡ በዚያ በተደራጀ ጽሕፈት ቤት በኩል ዓላማውን ማስፈጸም ያለበት ቦርዱ ነው፡፡ ቦርዱ የነጋዴውን ችግር በቅደም ተከተል ለይቶ አስቀምጦ በዚያ ላይ ትኩረት አድርጎ ለጽሕፈት ቤቱ አስፈጽም ብሎ አመራር መስጠት ነው፡፡ አስፈጽም የተባለውን ሥራ ካላስፈጸመም ዕርምጃ ይወሰዳል፤ እንቢ ሊል አይችልም፡፡ እንቢ ካለ ሊባረር ይችላል፡፡

 ሪፖርተር፡- አሁንም የጽሕፈት ቤቱ የበላይነት ይታያል ይባላል?

አቶ ሞላ፡- ይኼ መስተካከል አለበት፡፡ አቶ ኤልያስም ሆነ አሁን ያለው ቦርድ አቅም እንዳላቸው እርግጠኛ ነኝ፡፡ በቦርድ አባል በነበርኩበት ጊዜ ይህንኑ ጽሕፈት ቤቱ ላይ የሚነገረውን ይዘን በዚህ ጉዳይ ተነጋግረናል፡፡ በቃለ ጉባዔም ተይዞ እንዲታይ ተደርጎ ነበር፡፡ አልጨረስነውም፡፡ በመሃል የአቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ ክስ መጣ እንጂ በጽሕፈት ቤቱ ጉዳይ ላይ እየተነጋገርንበት ነበር፡፡ ሁሉም የቦርድ አባላት ማለት ይችላል፤ ኧረ ይህንን ጽሕፈት ቤት መምራት ያለብን እኛ ነን በማለት መነጋገር ጀምረን ነበር፡፡ አጀንዳም ተይዞበት መነጋገር ጀምረን ነበር፡፡ ይህ ግን እውን ሳይሆን እንደተባለው የፍርድ ቤቱ ክስ ሲመጣ ነገሮች ተከፋፈሉና አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ገባን፡፡ የፍርድ ቤቱ ጉዳይ ዱብ ዕዳ ሆነ፡፡ በነገራችን ላይ የፍርድ ቤቱ ጉዳይ እኮ እኛን አይመለከተንም ነበር፡፡ በፍፁም አይመለከተንም፡፡   

ሪፖርተር፡- እንዴት አይመለከተንም ሊሉ ቻሉ?

አቶ ሞላ፡- ምክንያቱም አቶ ኢየሱስ ወርቅ ወደ ፍርድ ቤት እንዲሄዱ ያደረጋቸው ውሳኔ የተላለፈው በቀድሞ ፕሬዚዳንት አቶ አያሌው ዘገየ ቦርድ ነው፡፡ ውሳኔውን የወሰነው እኛ አይደለንም፡፡ አቶ ኢየሱስ ወርቅ ወደ ጠቅላላ ጉባዔ እንዳይገቡ ያደረገው፤ ወደ ጠቅላላ ጉባዔ እንዳይገቡ የከለከሉበትን ስብሰባ የመሩት አቶ አያሌው ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- እናንተ በዚያ ጠቅላላ ጉባዔ ከተመረጣችሁ በኋላ ግን የቀድሞ ቦርድ ያስተላለፈውን ውሳኔ ትክክል ነው ብላችሁ እየተከራከራችሁ ነበር?

አቶ ሞላ፡- ያ የቦርዱ ውሳኔ ቃለ ጉባዔ አለ፡፡ በንግድ ምክር ቤቱ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት የተደረገ ውሳኔ ስለመሆኑ መርምረናል፡፡ ውሳኔው አግባብ ነው አልን፡፡ ምክንያቱም በመተዳደሪያ ደንቡ ውስጥ የተቀመጠ በመሆኑ ነው አግባብ ነው ያልነው፡፡ ይህን ውሳኔ የያኔው ቦርድ በሥራ ላይ አውሎታል፡፡ ትክክል አይደለም ብለን የምንቀለብስበት ምክንያት አልነበረም፡፡ አቶ ኢየሱስ ወርቅም መክሰስ የነበረባቸው አቶ አያሌውንና የቀድሞ ቦርድ አባላትን ይመስለኛል፡፡ የቀድሞውን ቦርድ ያሳለፋችሁት ውሳኔ አግባብ አይደለም፡፡ በተለይም ፕሬዚዳንቱን ማስፈጸሙ ሕገወጥ ነው፤ ያላግባብ የተወሰነ ነው ብለው ሊከሱ ይችሉ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ይህንን የቀድሞ ቦርድ ውሳኔ ደግሞ እኛ እናስፈጽማለን አላላችሁም?

አቶ ሞላ፡- አላስፈጸምንም፡፡ እናስፈጽማለንም አላልንም፡፡ መጀመርያውኑ የተፈጸመ ጉዳይ ነው፡፡ ስብሰባ እንዳይገቡ የሚለውን ውሳኔ የወሰነው በአቶ አያሌው የሚመራው ቦርድ ነው ስብሰባውን የመራው፡፡ ወደ ስብሰባ እንዳይገቡ ያገዳቸውም በአቶ አያሌው የሚመራው ቦርድ ነው፡፡ እኛ እኮ ከኋላ የመጣን ሰዎች ነን፡፡ የቀድሞ ቦርዱ የወሰነውን ውሳኔ የእኛ ቦርድ አስፈጽሞት ቢሆን ኖሮ እኛ መከሰስ ነበረብን፡፡ ነገር ግን ስብሰባ እንዳይገቡ የተደረገው በቀድሞ ቦርድ ነው፡፡ ስለዚህ አቶ ኢየሱስ ወርቅ ከእኛ ጋር ጉዳይ የላቸውም መክሰስ ያለባቸው የቀድሞውን ቦርድ ነው የምለውም ለዚህ ነው፡፡ በሌላ በኩል ግን ይህ የፍርድ ቤት ጉዳይ በአግባቡ ቢያዝ ውጤቱ ሊለወጥ ይችል እንደነበር እገምታለሁ፡፡ እዚህ ላይ አቶ ኢየሱስ ወርቅ ፍርድ አግኝተውም በድጋሚው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ አልተገኙም፡፡ ይህ መሆን አልነበረበትም፡፡

ሪፖርተር፡-  በፍርድ ቤት ትዕዛዝ በድጋሚ በተደረገው ምርጫ ላይ የተለያዩ አስተያየቶች ሲሰነዘሩ ነበር፡፡ አንድን ቡድን በድጋሚ ለማስመረጥ የተሠራ ሥራ አለ ይባላል፡፡ የጽሕፈት ቤቱም እጅ አለበት የሚል አስተያየት አለ?

አቶ ሞላ፡- እሱን እንግዲህ በወቅቱ እኔ ስላልነበርኩ አላውቅም፡፡ እኔ የሚሰማኝን ስሜት ከመናገር ወደኋላ የምል አይደለሁም፡፡ እውነት ለመናገር ዝርዝር ነገሩን አላውቅም፡፡ ነገር ግን የሚመስል ነገር ሊኖር ይችላል፡፡ በተጨባጭ ግን ማረጋገጥ አልችልም፡፡ ሌላው እዚህ ጋር ማንሳት የምፈልገው ነገር አለ፡፡ እኔ ቦርድ ውስጥ ስገባ አማላጅ መሆን እፈልግ ነበር፡፡ በመንግሥትና በንግዱ ኅብረተሰብ መሀል ድልድይ መሆን እፈልግ ነበር፡፡ አንድ ምሳሌ ልንገርህ ብዙ ነጋዴዎች ከታክስና ከግብር ጋር በተያያዘ ታስረዋል፡፡ ይህ የንግድ ምክር ቤቱ ጉዳይ ጭምር ነው፡፡ አባላቱ ታስረዋል፡፡ እርግጥ ብዙዎቹ ፍርድ ቤት ቀርበው ተፈርዶባቸዋል፡፡ በመንግሥት በኩል የታክስና የግብር ሕግ በየጊዜው ይለዋወጣል፡፡ እንኳን ለንግዱ ኅብረተሰብ ይቅርና ለእኛም ለሕግ ባለሙያዎች ጭምር የሕግ አስተያየት ለመስጠት የምንፈተንበት ነገር አለ፡፡ የታክስና የግብር ሕጎች ይቀያየራሉ፡፡ የግብር አስከፋይ መሥሪያ ቤት ሠራተኞቹም ቢሆኑ የራሳቸው ክፍተት ሊኖርባቸው ይችላል፡፡ ስለዚህ በመንግሥትም በኩል ጥርት ያለ አስተማማኝ የሆነ አንድ ወጥ የሆነ አሠራር መኖር አለበት፡፡ በነጋዴውም በኩል ደግሞ እንዲሁ፡፡ ስለዚህ ብዙዎቹ ችግሮች ናቸው ብዬ የማስበው በሁለቱም ወገን ካለ ክፍተት ነው፡፡ በእኔ እምነት እነዚህ ነጋዴዎች ተራ የማጭበርበር ሥራ ለመሥራት አስበው ሳይሆን ባለው ክፍተት አጋጣሚ የተፈጠሩ ሁኔታዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እኔ ሕግ አይከበር የምል ሰው አይደለሁም፡፡ ነገር ግን ጉዳዩ ሊመረመር ይገባል የሚል እምነት ስላለኝ ነው፡፡ መንግሥት ማህሪ ነው፡፡ መንግሥት ሆደ ሰፊ ነው፡፡ ይህ የመንግሥት ባህሪ ነው፡፡ እኔ ካለኝ ልምድ እንደማውቀው የመንግሥት ኃላፊዎችን ጠጋ ብለህ ነገሩን ብታስረዳ ያዳምጣሉ፡፡ ነገሩን ሊመረምሩ ይችላሉ፡፡ መፍትሔ ሊያበጁ የሚችሉ ስለመሆኑም አውቃለሁ፡፡

ስለዚህ እነዚህ የታሰሩ ሰዎች ምን ይደረጉ ብትለኝ በመንግሥትም በኩል እንዲህ ዓይነት ችግር አለ፤ በነጋዴውም በኩል እንዲህ ዓይነት ችግር አለ ተብሎ ነገሩን መመልከት ያሻል፡፡ ቆይቶ ሁላችንም ሥርዓቱን አውቀነውና ተረድተን፣ መኖር እስከምንጀምርበት ድረስ መሸጋገሪያ ሁኔታ መኖር አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ በዚህ የተነሳ ለምሳሌ ይህን ያህል ዓመት ተብሎ የተፈቀደላቸው አሉ፡፡ እኔ ሳስብ የነበረው (በወቅቱ ለቦርዱም በግልጽ አላቀረብኩም) እነዚህ ነጋዴዎች በገንዘብ ይቀጡ ነው፡፡ የእነሱ መታሰር ጉዳት አለው፡፡ አንዳንድን ነጋዴ ስታስረው የሠራተኛ መበተን ይመጣል፡፡ ነገ ሳይንቲስት፣ ዶክተር ወዘተ ሊሆኑ የሚችሉ ልጆችን የሚያሳደግ ሠራተኛ በመሆኑ የእሱ ሥራ ማጣት ችግር ይፈጥራል፡፡ መንግሥትም ነጋዴዎቹን በማሰሩ ማግኘት የሚገባውን ግብርና መዋጮ ያጣል፡፡ መንግሥትም ተበድሏል፡፡

      በእኛ አገር ሁኔታ ተቋማዊ የሆነ አካሄድ የለም፡፡ ብዙው ተቋም የሚቀጥለው ባለቤቱ ሲኖር ነው፡፡ ባለቤቱ ወሳኝ በመሆኑ የነጋዴዎች መታሰር ያስተዳድሩ የነበሩትን ተቋም ቀጣይ እንዳይሆን ያደርገዋልም የሚል ሥጋት አለኝ፡፡ ይህ ሊታይ ይገባል፡፡ ንግድ ምክር ቤቱም ይህንን ማየት አለበት፡፡ እኔ የበለጠ የገረመኝ ጋዜጠኛ፣ ፖለቲከኛና ሌላው ቢታሰር ሁሉም ይጮሃል፤ ነጋዴው ሲታሰር የሚጮህ መጥፋቱ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ ምንድን ነው መደረግ ያለበት?

አቶ ሞላ፡- በእኔ እምነት በንግድ ምክር ቤቱ መደረግ ያለበትና እኔ በቦርዱ ውስጥ በነበርኩበት ወቅት ሳላሳካ የቀረሁት ጉዳይ ነው፡፡ የእነዚህን ሰዎች ዝርዝር ወስዶ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በግልጽና በድፍረት ሄዶ አለማነጋገራችን ነው፡፡ አሁንም ግን ይህንን መረጃ ይዞ መንግሥትን መለመን፤ መለመን፤ መለመን ያስፈልጋል፡፡

ቦርድ ውስጥ በነበርኩበት ወቅት ይህንን የታሰሩ ነጋዴዎች ጉዳይ እንዳንነጋገርበት በሌሎች አጀንዳዎች ተወጠርን፡፡ ሌሎች ይቀርቡልን የነበሩ አጀንዳዎች ወጠሩን፡፡ ነገር ግን እኔ በበኩሌ አንዱ አጀንዳዬ ይኼ ነበር፡፡ ለምን መሰለህ ለግለሰቦቹም ላዝን ይገባል፡፡ እስር ምን እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ እኔ ያለኃጤያቴ ዘጠኝ ዓመት ታስሬ አይቼዋለሁ፡፡ እስር ማለት ጠንቅቄ አውቃለሁ፡፡ ስለዚህ ወንጀለኞች አይቀጡ አልልም፡፡ ወንጀለኛ መቀጣት አለበት፡፡ ነገር ግን ይህ የተለየ ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ የታሰሩ ነጋዴዎች ሁለተኛ ዕድል ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ አሁንም በታክስና በግብር ምክንያት የተፈረደባቸውና የታሰሩ ሰዎች ሁለተኛ ዕድል ሊሰጣቸው ይገባል የሚል የጠነከረ እምነት አለኝ፡፡ እኔ እነዚህ ሰዎች የፖለቲካ ነገር ከጀርባቸው ከሌለባቸው መንግሥትም ይህንን ካረጋገጠ መንግሥት ጉዳዩን ሊመለከት ይችላል፡፡ እርግጠኛ ነኝ፡፡

ሪፖርተር፡-  ነገሩ እርስዎ እንዳሉት ሊሆን የሚችል ከሆነና አሁን የጠቀሱልኝ ችግር አሳሳቢ መሆኑን ካመኑበት ጉዳዩ ትኩረት እንዲያገኝ አሁንም ቢሆን ለንግድ ምክር ቤቱ ማሳወቅ አይቻልም?

አቶ ሞላ፡- እሞክራለሁ፡፡ በተለይ በምክር ቤቱ ቦርድ አማካይነት ይኼ ጉዳይ ቢቀርብ ኖሮ መንግሥት የሚለውን ብሰማ ደስ ባለኝ ነበር፡፡ ይህንን ሳላደርግ በመውጣቴ እፀፀታለሁ፡፡ ይቆጨኛል፡፡ ይህንንም የማደርገው ለይምሰል ወይም ርካሽ ተወዳጅነት ለማግኘት ሳይሆን የማምንበት ስለሆነ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ካገኘሁ መንግሥትን መለመን ጉዳዩን እንዲመለከተው ማቀራረብ እፈልጋለሁ፡፡ አሁን ሽማግሌ ነኝ፡፡ መሸምገልም አለብኝ፡፡ ደግሜ የምናገረው ግን መንግሥትም ቢሆን ከጀርባ ምንም ነገር ከሌለ ጉዳዩን በመረጃ ካቀረብክለት ይሰማል፡፡ ያያል፡፡

ሪፖርተር፡- የንግድ ምክር ቤቱ 15,000 አባላት አለን ይላል፡፡ በትክክል ዓመታዊ መወዋጮዋቸውን ከፈሉ የሚባሉት ደግሞ 4,000 አባላት ናቸው፡፡ ከሁሉም በላይ ግን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ነጋዴዎች ያለበት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ አብዛኛው ነጋዴ የንግድ ምክር ቤቱ አባል  አይደለም፡፡ እንደውም አሉ የሚባሉትም እየወጡ ነው፡፡ ትላልቅ ኩባንያዎችም አይታዩበትም የሚለው አስተያየትም ጎልቶ ይወጣል፡፡ ይህን አካሄድ እንዴት ያዩታል?

አቶ ሞላ፡- አንድ ተቋም አባላቱ ሊቀርቡትና ሊጠጉት የሚሉችት ትርጉም ያለውና አባላትን የሚደግፍ ሥራ ሲሠራ ነው፡፡ እንደ አንድ አባል ያለብህን ችግርህን ሲፈታልህ ነው፡፡ ንግድ ምክር ቤቱ አንድ አባሉ ተቸግሮ ድርጅቱን ሲዘጋ ተቸግሮ ፈቃዱን ሲመልስ፣ ወዘተ ካልደገፈው፣ ችግርህ ምንድነው ካላላው ምን ይሠራል? የነጋዴውን ችግር ዓይቶ አማላጅ ሆኖ ከመንግሥት ጋር አቀራርቦ ችግርህን ሲፈታ ካላየኸው ምን ይሠራልሃል? እኔ በነበርኩበት ወቅት በዚህ ጉዳይ በአጀንዳ ይዘን ሁልጊዜ እንነጋገራለን፡፡ የአባላቱን ቁጥር እንዴት እንጨምር? እያልን ተነጋግረናል፡፡ የአባላቱን ቁጥር ለመጨመር ደግሞ መፍትሔው አንድና አንድ ብቻ ነው፡፡ ይህም የአባላትን ጥቅም ማስከበር አባላት ጥቅም የሚያገኙበትን ነገር ማቅረብ ነው፡፡ ይህ ከሆነ አባላት ይጎርፋሉ፡፡

ሪፖርተር፡- የንግድ ምክር ቤቱን ጉዞ እንዴት ያዩታል?

አቶ ሞላ፡- አሁን ጥሩ የሆነው ነገር የምርምር ተቋሙ ተቋቁሟል፡፡ በዚህም ተቋም አማካይነት ዋና ዋና ናቸው የተባሉ የነጋዴው ችግሮች ተለይተው በአስቸኳይ ተጠንቶ ጥናቱ ያስገኘውን ውጤት በመያዝ ለሚመለከተው ክፍል ማቅረብ ያሻል፡፡ ይህንንም ወጥሮ ይዞ ጽሕፈት ቤቱ እንዲያስፈጽም ማድረግ ነው፡፡ ለምሳሌ የመሬት ሊዝን እንውሰድ ሁላችንም በያለንበት ሊዝ ችግር አለው እንላለን፡፡ የሆነውን ያልሆነውን እንነጋገራለን፡፡ በጥናት የተደገፈ ነገር ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ዙሪያ ያለው ችግር ይህ ነው ብለህ ጥናትህን ይዘህ ቀርበህ እንዲስተካከል መጠየቅ ትችላለህ፡፡ ካላስተካከልክ መንግሥትም እኮ ሊከሰስ ይችላል፡፡ በጥናት የተደገፈ ተጨባጭ መረጃ አቅርቤ ጉዳዩ የሚመለከተው የመንግሥት የሥራ ኃላፊ፣ ወይም ንግድ ሚኒስቴር፣ ገቢዎችና ጉምሩክ ወይም ሌላ መንግሥትዊ ተቋም ዘንድ ሄዶ ጉዳዩ ይመለከተዋል የተባለው ተቋም በጥናት ለተደገፈው ችግር መፍትሔ በሚሰጥ ሁኔታ ጉዳዩን አልፈጽምም ካለ ሕግ ጥሷል ማለት ነው፡፡ ይህ ከሆነ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ይዤው እሄዳለሁ፡፡ መረጃ ይዘህ ከሆነ መንግሥትን በመክሰስህ የሚወጣብህ ነገር የለም፡፡

      እኔ ከአንዴም ሁለት ሦስቴ ትልልቅ የመንግሥት ተቋማትን ከስሻለሁ፡፡ ይህንን በማድረጌ ያስፈራራኝ የለም፡፡ የቀጣኝ የለም፡፡ ፈቃዴም አልተነጠቀም፡፡ ብዙ ሰው ግን ያስፈራሃልል፡፡ ይህም የወጣው እንዲህ ዓይነቱ ነገር ስላልተለመደ የተከሰተ ነው፡፡ ስለዚህ ይኼ ቦርድ ካለፈው ተምሮ ይሠራ፡፡ የተጀመሩ አንዳንድ ሥራዎች ያሉ በመሆኑ እነሱንም ያስፈጽም፡፡ የምርምር ተቋሙን በቶሎ ሥራ ማስጀመር አለበት፡፡ በዚህ ተቋም የሚገኘው የምርምር ውጤት መሠረት የነጋዴው ችግር የፖሊሲ ችግር ከሆነ እሱን ማሳየት፤ የአፈጻጸም ችግር ከሆነም ይህንኑ በማመላከት መፍትሔ እንዲመጣ ማድረግ ይችላል፡፡ ነገር ግን ይህንን አላደረግንም፡፡ እንደው እዚህ ላይ አንድ ነገር ላንሳ፡፡ ለአንገብጋቢ ጉዳዮች መፍትሔ ያለመፈለጉ ችግር በተለያየ መንገድ ይገለጻል፡፡ አንዱ አንዳንዶች ንግድ ምክር ቤቱን የሙጥኝ ብለው የሚይዙት እኮ እንዲህ ዓይነቱን ሥራ ከመሥራት ይልቅ የግል ጉዳያቸው ስለማያስቡ ነው፡፡ ሌላው ንግድ ምክር ቤቱ ብዙ የውጭ ጉዞ ዕድሎች አሉት፡፡ ይህ ዕድል ብዙን ጊዜ የሚታደለው በጽሕፈት ቤቱ ነው፡፡ ይህ አሠራር መቀየር አለበት፡፡ ይህም ሥልጣን ለቦርዱ መሰጠት አለበት፡፡ ከዚያ አካባቢ ያለመጥፋታቸው ጥቅም ስላለው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በንግዱ ምክር ቤቱ አመራር ላይ በመቀመጥ ምን ዓይነት ጥቅም እየተገኘበት ነው ይላሉ?

አቶ ሞላ፡- ለምሳሌ ወደ ውጭ የመሄድ ዕድል ይኖርሃል፡፡ የቢዝነስ ልዑክ ተብሎ እዛ ውስጥ ትካተትና ትሄዳለህ፡፡ ውጭ በመሄድህ ደግሞ ለአንተ ቢዝነስ የሚሆኑ ግንኙነቶች ታፈራለህ፡፡ ይኼኔ የነጋዴውን ነገር ትተውና የራስህን ቢዝነስ ታመቻቻለህ፡፡ ቦርድ ውስጥ መሆንህ በልዩ ልዩ መንገድ ባለሥልጣናትን ትተዋወቃለህ፡፡ እዚህም ስለመረጠህ ነጋዴ ችግር ሳይሆን የምታወራው የአንተን ቢዝነስ እንዴት እንደምታሳልጥ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሥራ በሁሉም ባይሆን በተወሰኑ ሰዎች ይፈጸማል፡፡ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ራሳቸውን ለማስተዋወቅ ሲንቀሳቀሱ የነበሩም አሉ፡፡ እንደውም አንዳንዶቹ ከትቢያ ተነስተው ራሳቸውንና ቢዝነሳቸውን ያስተዋወቁ ናቸው፡፡ ቦታውን የሚፈልጉም አሉ፡፡ ስለዚህ ይህን ቦርድ ምክር ቤት እንዲያደርግ ከተፈለገ ከእንዲህ ዓይነቱ ነገር መፅዳት አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- እንዲህ ዓይነቱ ችግር የሚታወቅ ከሆነ እንዳይደገም ምን መደረግ አለበት ይላሉ?

አቶ ሞላ፡- ነጋዴው አመራሮቹን ሲሰይም ምርጫው ላይ መጠንቀቅ አለበት፡፡ ብልጣብልጦችን መከላከል አለበት፡፡ ነጋዴው ይህንን ተቋም ማጠናከር አለበት፡፡ ለዝቅተኛው፣ ለመካከለኛውም ሆነ ለከፍተኛው ነጋዴ ይኼ ተቋም ይጠቅመዋል፡፡ ትልቅ ተቋም ነው፡፡ የሚያስመስሉ ሰዎችን ሳይሆን በአግባቡ የሚመሩትን መምረጥ አለበት፡፡ በጣም አዋቂ ነጋዴዎች እኮ አሉ፡፡ ጠንካራ የሚባሉ ነጋዴዎችም አሉን፡፡ እነዚህን ወደ አመራር ማምጣት ያስፈልጋል፡፡ የንግዱ ኅብረተሰብም በእርሱ ጉዳይ በሚመከርበት ስብሰባ መገኘት አለበት፡፡ ከውጭ ሆኖ ማማት አይጠቅምም፡፡

      እኔ እኮ ውጭ ከማወራ እስቲ ልምከር ብዬ ነው የገባሁት፡፡ ሌሎችም እንዲህ ማድረግ አለባቸው፡፡ የራሳቸውን ጥቅም ለመጠበቅ ከሚሯሯጡ መላቀቅ አለብን፡፡ አሁንም ቢሆን እኮ ምክር ቤቱ የተለዩ ሥራዎች ይሠራል፡፡ ግን አመራሩ ጠንካራ መሆን አለበት፡፡ መንግሥትም ጆሮ የሚሰጥህ ጠንካራና በአግባቡ የምትሠራ ስትሆን ነው እንጂ ለግል ጥቅም በመሯሯጥ አይደለም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች