Monday, September 25, 2023

መላ ኢትዮጵያን ሐዘን ያስቀመጠው አሳዛኝ ክስተት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

አቶ በሪሁን ማስረሻ ይባላሉ፡፡ ዕድሜያቸው ስድሳዎቹ መጨረሻ አካባቢ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ስድስት ልጆች ቢወልዱም የ‹‹ቆሼ›› በሚባለው የቆሻሻ ማስወገጃ ሥፍራ አደጋ ከመከሰቱ በፊት አራት ልጆች ብቻ ነበሯቸው፡፡ ሁለቱ (አንድ ወንድና አንድ ሴት) ልጆቻቸው የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ሲሆኑ፣ ሁለቱ ደግሞ የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች ነበሩ፡፡ ዕድሜያቸው ከገፋ በኋላ ሚስት እንዳገቡ የሚናገሩት አቶ በሪሁን ባለቤታቸውን ካጡ ገና ሦስት ዓመታቸው ነው፡፡ ቆሼን መተዳደሪያ አድርገው መኖር ከጀመሩ ከሃያ ዓመታት በላይ ቢያስቆጥሩም፣ ዛሬ ሲያዩዋቸው ግን ሰውነታቸው ጃጅቷል፣ ጉልበታቸው ዝሏል፡፡ ቁጭ ብለው ስለዋሉ አደጋው ከመከሰቱ ሃያ ደቂቃዎች በፊት ትንሽ ጉልበታቸውን ለማዝናናትና አየር ለማግኘት ከቤታቸው ይወጣሉ፡፡ በዘመዶቻቸው ድጋፍና ዕርዳታ፣ እንዲሁም ሁለቱ ትላልቅ ልጆቻቸው በትርፍ ሰዓት እየሠሩ ከሚያመጡላቸው ገንዘብ በስተቀር ሌላ መተዳደሪያ ገቢ የላቸውም፡፡

ባለቤታቸው ካረፉ በኋላ ጉልበታቸው መድከሙን የሚናገሩት አቶ በሪሁን ፊታቸው ላይ ጥልቅ ሐዘን ይነበባል፡፡ ‹‹በአጋጣሚ ብወጣ አራቱን ልጆቼን አጣሁ!›› እያሉ ሲቃ በተናነቀው ድምፅ ሲያነቡ በአካባቢያቸው የነበሩ ሰዎች አብረዋቸው እያነቡ ያፅናኑዋቸው ነበር፡፡  በወቅቱ የቆሻሻውን ክምር ሰው ቢሆን ኖሮ አይቀጡ ቅጣት ይፈጽሙት እንደነበርም ሲናገሩ ተሰምተዋል፡፡

አቶ በሪሁን አራቱ ልጆቻቸው ከቆሻሻው መርግ ጋር አብረው እንደተቀበሩ አውቀዋል፡፡ በደከመ አንጀታቸውና እንባ በሌላው ዓይናቸው (ከመድከምና ከመዛላቸው የተነሳ) መሬት ላይ በተደጋጋሚ እየተነሱ ይወድቃሉ፡፡ ሲደክማቸው ደግሞ የቆሼን የተደረመሰ ቆሻሻ ትኩር ብለው እያዩ የሲቃ እንባ ያነባሉ፡፡ ባረጀ ዕድሜያቸው፣ በላመ ጉልበታቸው ይህ ሁኔታ ወዴት እንደሚወስዳቸው ግራ የተጋቡ ይመስላሉ፡፡ አሁንም ግን ያንን የተናደ የቆሻሻ መርግ ጥግ አድርገው ተቀምጠዋል፡፡

በ1956 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቦታ ከዚህ በፊት ረጲ ወይም ፉሪ ነበር ተብሎ የሚጠራው፡፡ ይህ ቦታ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ‹‹ቆሼ›› እየተባለ የሚጠራ ሲሆን በ37 ሔክታር መሬት ላይ ያረፈ ሰፊ የቆሻሻ መጣያ ሥፍራ ነው፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የነበሩት አፄ ኃይለ ሥላሴ ቦታውን ለቆሻሻ መጣያነት የመረጡበት ዋነኛ ምክንያት፣ ከመናገሻ ከተማቸው አዲስ አበባ በጣም ሩቅና በነዋሪዎች ላይ ምንም ዓይነት አደጋ አያስከትልም ተብሎ ታስቦ እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

እንደ ዋዛ ለቆሻሻ መጣያነት የተመረጠው ይህ ሥፍራ ዛሬ ከአንድ መቶ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ሞትና ምክንያት ሆኗል፡፡ ይህ የቆሻሻ ማስወገጃ ሥፍራ ዓመታትን ከማስቆጠሩ የተነሳ ከሜዳማነት ወደ ተራራማነት ተቀይሯል፡፡ ይህንን ሰው ሠራሽ የቆሻሻ ተራራ ተገን አድርገው በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ዜጎች እንደሚኖሩ አሁን ያለው የአካባቢው ገጽታ አመላካች ነው፡፡

ከቆሻሻው ክምር ሲቀናቸው ጌጣ ጌጦችና የታሸጉ ምግቦች፣ ሳይቀናቸው ደግሞ ቆሻሻውን በተለይም ፕላስቲክ ነክ የሆኑትን በመሰብሰብና በመሸጥ ልጆቻቸውን እያስተማሩ ከፍተኛ ደረጃ ያደረሱ ወገኖች እንዳሉ ብዙዎች ይናገራሉ፡፡

‹‹ቆሼ›› በአንድ በኩል የዝንብ መንጋና የሽታ ገጸ በረከቱን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የገቢ ማስገኛ ምንጭ በመሆን በዙሪያው ከሚኖሩ ወገኖች ጋር እጅና ጓንት ሆኖ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡

ይህ ሥፍራ በአሁኑ ወቅት በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ክልል ውስጥ ይገኛል፡፡ የሰሞኑ አሳዛኝ ክስተት ከተፈጠረበት ሥፍራ ሆኖ ወደ አራቱ አቅጣጫ ለተመለከተ በምዕራብ በኩል ተደርምሶ የገባውና አሁንም ድረስ የሚደረመስ የሚመስለው የቆሻሻ ሰንሰለት፣ በሰሜንና በምሥራቅ በኩል ከናዳው የተረፉና ሌሎች መኖሪያ ቤቶች ሲገኙ፣ በደቡብ በኩል ደግሞ በላፍቶ ክፍለ ከተማ ውስጥ የሚገኘው ባዶና ከአደጋ ሥጋት ነፃ የሆነ ሜዳማ አካባቢ ይታያል፡፡ በዚህ ሥፍራ አሁንም ከመርጉ ከተረፉ ቤቶች ምሥልና ሁኔታ መረዳት እንደሚቻለው ከላስቲክና ከሸራ ተወጥረው የተሠሩና ዕድሜ ጠገብ የቆርቆሮ ቤቶች አሉ፡፡ አለፍ ሲል ደግሞ የአደጋው ሰለባና አሁንም ድረስ መትረፋቸው የሚያስደንቅ ዘመናዊ ቤቶች አሉ፡፡

ሥፍራው በቆሻሻው ክምር ምክንያት ተራራማ የሆነ የመሬት አቀማመጥ ቢኖረውም፣ በዙሪያው ላሉ ነዋሪዎች መጥፎ ሽታን ከማደል ባሻገር ለሞትና ለተለያዩ ጉዳቶች ሲዳርጋቸው እንደቆየ የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡

ከጅምሩ ጀምሮ ብዙ ችግሮች እንዳሉበት ይነገር የነበረው የቆሼ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ሥፍራ፣ ቅዳሜ መጋቢት 7 ቀን 2009 ዓ.ም. ምሽት 1፡30 ሰዓት ሲሆን ግን እሱን ተገንና መጠጊያ አድርገው በዙሪያው ይኖሩ በነበሩ ዜጎች ላይ የጭካኔ ብትሩን አሳረፈባቸው፡፡ ብዙዎቹ እንደገለጹት ለዓመታት ተሸክሞት የነበረውን የቆሻሻ መርግ እንደ ዶፍ አወረደባቸው፡፡ እንደ ዘንዶ አፉን ከፍቶ በላቸው፡፡ እሱን ተገንና መከታ አድርገው ይኖሩ የነበሩ ዜጎች ለዘለዓለሙ አሸለቡ፡፡

‹‹ልጆቼን እንዳላሳደግኩብህ፣ እንዳላስተማርኩብህ ዛሬ ምነው ቆሼ ጨከንህብን?›› እያሉ ያለቅሳሉ የ52 ዓመቷ ወይዘሮ ሰናይት ቸኮል የተባሉ እናት፡፡

ሙሉ ቤተሰባቸውን ያጡ አባት ደግሞ በእስተርጅና ብቻቸውን እንዲቀሩ ቆሼ እንደፈረደባቸው በእንባ ተሞልተው ይናገራሉ፡፡ ዕድሜያቸው እንደገፋና 60ዎቹ መጨረሻ አካባቢ እንደሚገኙ የሚያሳብቅባቸው እኚሁ ሰው የሚተዳደሩት በልመና ነው፡፡ ልመና ውለው ወደ ቤታቸው ሲገቡ ግን ቤታቸው ያገኙት  የቆሻሻ መርግ ነው፡፡ ሙሉ ልጆቻቸውንና (ሦስት ተማሪ ልጆቻቸውን ጨምሮ) ባለቤታቸውን በሞት ተነጥቀዋል፡፡ በሽምግልና ዘመናቸው ጉሮሮአቸው በለቅሶ ደርቆ ልባቸው በሐዘን አርሮ መናገር ስለማይችሉ በምልክት ስለሚናገሩ ስማቸውን መናገር አይችሉም፡፡ እንደምንም ብለው ድምፅ ሲያወጡ፣ ‹‹ፈጣሪ ምን በደልኩህ እኔን ወደኋላ አስቀረኸኝ?›› እያሉ ያለቅሳሉ፡፡

አሥራ አንድ ቤተሰቦቿን አጥታ ብቻዋን የቀረችው ወጣት ፌቨን ይርዳው የወጣትነት ዕድሜዋ በሐዘን ተበርዞ ዕድሜው እንደገፋ ሰው መናገር ተቸግራለች፡፡ ፊቷ ላይ የሚነበበው የሲቃና የለቅሶ ሁኔታ የሐዘኗን መበርታት ያሳያል፡፡ ጉሮሮዋ ደርቋል፣ ፊቷ ጠውልጓል፡፡

‹‹እኛ እኮ የምንኖረው ቆሻሻ ውስጥ ነው፡፡ ወይ ከዚህ ቦታ አንሱን ወይ ቆሼን አንሱልን እያልን ስንጮህ ኖረናል፡፡ ዛሬ ግን ስናልቅ መጣችሁ አይደል?›› በማለት በወቅቱ አካባቢውን በማየት ላይ የነበሩ የወረዳ አመራሮች ላይ ንዴቷን ገልጻለች፡፡ ‹‹የዛሬው መምጣታችሁ ምን ፋይዳ አለው?›› ካለች በኋላ፣ ‹‹ቆሼ አሳድጎ በላን፤›› እያለችም ስታነባ ተደምጣለች፡፡

ሌላኛዋ ተጎጂ ደግሞ ወይዘሮ አልጋነሽ ጥበቡ ይባላሉ፡፡ በአንድ የግል ትምህርት ቤት አስተማሪ ናቸው፡፡ እዚህ ሠፈር ከገቡ ገና ሦስት ወር ነው የሆናቸው፡፡ ወይዘሮ አልጋነሽ ፀሐይዋ የሰማዩን አድማስ አጋምሳ ቁልቁል ማየት ስትጀምር ቅዳሜ መጋቢት 2 ቀን 2009 ዓ.ም. ከሥራ ቦታቸው ወደ ቤታቸው ተመለሱ፡፡ ቤታቸው እንደ ደረሱ አፋቸው ላይ ምግብ ጣል ካደረጉ በኋላ ወደ አራስ ጎረቤታቸው ቤት ሄዱ፡፡ የሄዱትም አራስ ጎረቤታቸውን ለመንከባከብ ነበር፡፡ አሁን ፀሐይዋ ጉዞዋን አጠናቅቃ አዲስ አበቤዎችን ወደ ቤታቸው እንዲገቡ ፊቷን ስታጠቁር የወይዘሮ አልጋነሽ ባለቤትም ከዋሉበት ወደ ቤታቸው ተመለሱ፡፡ ቤት ገብተው ባለቤታቸውን ባለማግኘታቸው አራስ ጎረቤታቸው ቤት እንደሚኖሩ በመገመት ወደ እዚያ አቀኑ፡፡ እንዳሰቡትም እዚያ አገኟቸው፡፡ ወይዘሮ አልጋነሽ ቡና አፍልተው አራስ ጎረቤታቸውን እያጫወቱ እያለ ከእሳቸው ቤት ለቡና ቁርስ የሚሆን ለማምጣት ወደ ቤታቸው ሄዱ፡፡ ቤታቸው ደርሰው ሊወጡ ሲሉ ግን የሚያዩትና የሚሰሙትን ማመን አቃታቸው፡፡ በሰከንዶች ልዩነት ባለቤታቸውን፣ አራስ ጎረቤታቸውን ከጨቅላ ልጃቸውና የአራስ ጎረቤታቸውን ባለቤት አጡ፡፡ አራቱንም ግለሰቦች ከንፋስ የፈጠነ የቆሻሻ ናዳ ሰለባ ሆኑ፡፡

ከዛሬ ሦስት ወራት በፊት በቤተሰቦቻቸውና በዘመዶቻቸው፣ ‹‹ጋብቻችሁን የአብርሃምና የሳራ ያድርገው›› ተብለው የተዳሩት ሙሽራ ባለቤታቸው ዛሬ በሕይወት የሉም፡፡ ወይዘሮ አልጋነሽ በዚያ በቆሻሻ በታፈነ ሠፈር ብቻቸውን ቀርተዋል፡፡ በወጣትነት ዕድሜያቸው ከባለቤታቸው ጋር ጠንክረው ሠርተው፣ ልጆች ወልደውና ሀብት አፍርተው ለመኖር አቅደውት የነበረው በሙሉ ዛሬ ባዶ ሆኖባቸዋል፡፡

ሌላዋ ሐዘንተኛ የለበሱት ልብስ ሙሉ በሙሉ ጥቁር ነው፡፡ በወገባቸው መቀነት የሚመስል ጥቁር ሻሽ አስረዋል፡፡ ሲናገሩ ድምፃቸው በትንሹ ነው የሚሰማው፡፡ በእጃቸው አንድ ፎቶ ይዘዋል፡፡ ከወዲያ ወዲህ እያሉና ፎቶውን እያነሱ እየጣሉ ያለቅሳሉ፡፡ ሲያለቅሱና ሲጮሁ ድምፃቸው ብዙም ባይሰማም የያዙት ፎቶ የሰባት ዓመት ዕድሜ ያለው ሕፃን ልጅ እንደሆነ በለሆሳስ በሚመስል ድምፅ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

‹‹እናቱና አባቱ በዚህ ናዳ አልቀዋል፡፡ ልጁ እስካሁን አልተገኘም (እስከ ረቡዕ ምሽት ድረስ ነበር)፡፡ እባካችሁ የልጄን ጓደኛ ፈልጉልኝ፡፡ የሰባት ዓመት ልጄ በጓደኛው መሰወር አልቅሶ ሊሞትብኝ ነው፡፡ ልጄ ነው፡፡ የልጄ ጓደኛ ነው፡፡ እባካችሁ ልጄን. . .›› እያሉ ያለቅሳሉ፡፡

ይህ መላ ኢትዮጵያን ሐዘን ያስቀመጠ አሳዛኝ ክስተት ሳምንት ቢያልፈውም ተጎጂዎች በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ በሚገኘው የወጣቶች ማዕከል ጊዜያዊ መጠለያ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ ቁጥራቸው የበዛና ከአደጋው የተረፉ ዜጎችም እስከ ዛሬ ድረስ አደጋው በደረሰበት የቆሻሻ ክምር አካባቢ እየኖሩ ነው፡፡

ይህንን አሰቃቂ ችግር በጊዜያዊነት ለመፍታት መንግሥት፣ ዕርዳታ ድርጅቶችና ግለሰቦች ባደረጉት ጥረት ወደ ጊዜያዊ መጠለያ የገቡ፣ ከገቡ በኋላም የምግብ፣ የልብስና የመኝታ አገልግሎት እንዲያገኙ የተደረገ ቢሆንም ገና ብዙ ሊሠሩ የሚገባቸው ጉዳዮች እንዳሉ ግን በጊዜያዊ መጠለያ ማዕከሉ ሪፖርተር ያገኛው ግለሰቦች ይናገራሉ፡፡

ሪፖርተር ይህንን ዘገባ ለመሥራት በተንቀሳቀሰ ጊዜ በጊዜያዊ የመጠለያ ክፍሉ የሚገኙ ተጎጂዎችንም ጎብኝቷል፡፡ በአራት በተወጠሩ ሸራዎችና በሕንፃ ውስጥ ባሉ ሁለት ክፍሎች ተጎጂዎች እንዲያርፉ ተደርጓል፡፡ ከአሥር ቀን አራስ ጀምሮ እስከ 82 ዓመት ዕድሜ ድረስ ያላቸው አዛውንቶች እንደተጠለሉም ለማወቅ ተችሏል፡፡ በየቀኑ የሚገቡ ተጎጂዎች እንዳሉም የጊዜያዊ መጠለያ ማዕከሉ አስተባባሪና የኮልፌ ክፍለ ከተማ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሀብታሙ ተስፋዬ ይናገራሉ፡፡ እንደ አቶ ተስፋዬ ገለጻ፣ በዚህ ጊዜያዊ የመጠለያ ማዕከል የሚገኙ ተጎጂዎች በቀጣዩ ለአደጋ ይጋለጣሉ ተብለው የተለዩና መጠለያቸውን በአደጋው ያጡ ናቸው፡፡

አስተባባሪው ይህን ይበሉ እንጂ ተጎጂዎች ግን ጊዜያዊ መጠለያው ውስጥ ተጎጂ ያልሆኑ ዜጎችም እንዳሉ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በፊት ቤትና ንብረት ያልነበራቸው ግለሰቦች ዝም ብለው ሲገቡ፣ በተቃራኒው ደግሞ ተጎጂ ሆነው ቤትና ንብረታቸውን ያጡ  ወገኖች ድጋፍ እየተደረገላቸው እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡ ሪፖርተር በሥፍራው ያገኛቸው ወይዘሮ ራድያ መሐመድ በዚህ ሥፍራ ከአሥር ዓመታት በላይ እንደኖሩ ይናገራሉ፡፡ አንድ ልጅ እንዳላቸውና ኤችአይቪ በደማቸው ውስጥ እንዳለ ገልጸዋል፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ የሚኖሩት አደጋው በተከሰተበት ሥፍራ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

የወይዘሮ ራድያ ቤት የሚገኘው አደጋው በተፈጠረበት አካባቢ በመሆኑ አሁንም ለሌላ አደጋ ተጋላጭ ነው፡፡ የቤታቸው ጣሪያም በቆሻሻው መርግ ተጎድቷል፡፡ ‹‹መንግሥት ማንሳትና ጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ ማስገባት ያለበት ማንን ነው?›› በማለት አስተያየታቸውን በጥያቄ የሚጀምሩት ወይዘሮ ራድያ፣ ካለባቸው ችግር ባሻገር የሰሞኑ ጉዳይ እንዳሳሰባቸው ይናገራሉ፡፡ ‹‹እኛስ ዜጋ አይደለንም?›› ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡ ‹‹እስከ ዛሬ ድረስ በአንድ ሰው ድጋፍ ነው ያለሁት፡፡ እሷም ጋዜጠኛ ነች፡፡ እሷ ባትረዳኝ ሌላ የሚደርስልኝ ወገን የለም፡፡ ልጄንም ማሳደግ አልችልም ነበር፡፡ ኤችአይቪ በደሜ ውስጥ እያለ ማንም ሰው ግን ቀርቦ ሊረዳኝና ሊያፅናናኝ የሞከረ አልነበረም፡፡ ዛሬ ደግሞ ጎጆዬ ፈረሰ፡፡ ታዲያ ካሁን በኋላ የት ልግባ?›› እያሉ በማልቀስ እንባቸው ከፊታቸው ላይ የማይጠፋው ወይዘሮ ራድያ አሁንም ሐሳብ ገብቷቸዋል፡፡

አሁን እየተወሰዱ ያሉ ጊዜያዊ መፍትሔዎች መልካም እንደሆኑ የሚናገሩ ቢኖሩም፣ በቋሚነት የሚኖሩበት ሁኔታ ሊታሰብበት እንደሚገባ ይጠይቃሉ፡፡

ረቡዕ መጋቢት 6 ቀን 2009 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ ከቀትር በኋላ ለተጎጂ ቤተሰቦች የቀብር ማስፈጸሚያ የሚሆን አሥር አሥር ሺሕ ብር ከሰጡ በኋላ ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት እንደተናገሩት፣ መንግሥት ከተጎጂ ቤተሰቦች ጎን ይቆማል፡፡

ይህ መላ አገሪቱን የሐዘን ማቅ ያላበሰው አሳዛኝ ታሪክ ለሦስት ቀናት ያህል ብሔራዊ የሐዘን ቀን እንዲታወጅ ምክንያትም ሆኗል፡፡ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ይህ ብሔራዊ የሐዘን ቀን መታወጁ ጥሩ እንደሆነ ቢገልጹም፣ በመዘግየቱ ግን ቅር መሰኘታቸውን አልሸሸጉም፡፡ የሐዘን ቀኑ መታወጅ የነበረበት አደጋው በደረሰ ማግሥት ጀምሮ ነበር ይላሉ፡፡

በአዲስ አበባ ውስጥ የአደጋ ሥጋት ተብለው  ከተለዩ ሥፍራዎች መካከል የተጠላለፉ የኤሌክትሪክ ገመዶች፣ ለማስፋፊያና ለልማት ተብለው ተቆፍረውና በአፈር ሳይሞሉ የሚቀሩ ጉድጓዶችና ቦዮ፣ እንዲሁም የቆሻሻ ማስወገጃ ሥፍራ ‹‹ቆሼ›› ይገኙበታል፡፡ በእነዚህ የአደጋ ሥጋት በነበሩ ጉድጓዶችና ሌሎች ጉዳዮች ከዚህ በፊት ብዙ ዜጎች ሕይወታቸውን አሳዛኝ በሆነ ሁኔታ እንዳጡ ይታወቃል፡፡

በተለያዩ ጊዜያት የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር እነዚህን ችግሮች ለይቶ ለመፍታት እየተንቀሳቀሰ ቢሆንም ቅሉ ቆሼ በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ያደርሷል ተብሎ በጥናት ይፋ የተደረገው ግን የጎርፍ አደጋ ነበር፡፡ በእርግጥም ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት በጎርፍ በደረሰ አደጋ የሰዎች ሕይወት ጠፍቷል፣ ንብረት ወድሟል፡፡ ይሁን እንጂ ነዋሪዎች በተደጋጋሚ አቤት ብለንበታል የሚሉት የቆሻሻው ክምር ተናደና ለ115  ዜጎች ሕልፈተ ሕይወት ምክንያት ሆኗል፡፡ ይህ ቁጥር ማተሚያ ቤት እስከገባንበት ዓርብ ምሽት ድረስ ለውጥ አላሳየም፡፡

ቆሼ ትናንት ይህንን ያህል ሰው ሕይወት ቢቀጥፍም ግን ቆሻሻው እንደሚናድ ይመስላል፡፡ በጎንና በጎን የቀረው የቆሻሻ ክምር ለሁለተኛና ለሦስተኛ ጊዜ አደጋ ማስከተሉ እንደማይቀር ሥጋታቸውን የሚገልጹት፣ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ አሁንም እንደ ሥጋት የሚያነሱት ይህንኑ ነው፡፡ ይህንን በተመለከተ የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ የወረዳ አንድ የምክር ቤት አባል የሆኑና ለተጎጂዎች ድጋፍ ሲያደርጉ ሪፖርተር ያገኛቸው አቶ አማኑኤል እንብዛ ‹‹አሁንም ቁልቁል ሊናድ የሚመስለው የቆሻሻ ክምር ሌላ አደጋ እንዳያስከትል እየሠራን ነው፤›› ብለዋል፡፡ የተከመረውን ቆሻሻ ተጨማሪ ጉዳት እንዳያደርስ በቁፋሮ ማሽኖች በመታገዝ ለማስተካከል እየተሠራ መሆኑን አክለዋል፡፡

የቆሻሻ ክምር ተደርምሶ አደጋ ከማድረሱ በፊት መከላከል ይቻል ነበር በማለት ብዙዎች መንግሥትን ይወቅሳሉ፡፡ በአካባቢው በየጊዜው እየተናደ አደጋ የሚያደርሰው የቆሻሻ ተራራን መከላከል ወይም በጥናት ላይ የተመሠረተ መፍትሔ መፈለግ አለመቻል አላስፈላጊ መስዋዕትነት ያስከፍላል ሲሉም ይናገራሉ፡፡ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ባለፈው ዓርብ ምሽት ባወጣው ሳምንታዊ የአቋም መግለጫ፣ አደጋው አስደንጋጭና የኢትዮጵያዊያንን ልብ የሰበረ ነው ብሎታል፡፡ መንግሥት ለዘላቂ መፍትሔ ትኩረት በመስጠት የአጭርና የረጅም ጊዜ ዕቅድ አውጥቶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል ብሎ፣ በአንድ በኩል ከአደጋው የተረፉት ወገኖች በቋሚነት ወደ ተረጋጋ ሕይወት የሚመለሱበትን ሁኔታ ያመቻቻል በማለት ገልጿል፡፡

ሕይወታቸው በአደጋው ያለፉ ዜጎች በተለያዩ ቦታዎች እንደየ ሃይማኖታቸው የቀብር ሥነ ሥርዓት ተካሂዶላቸዋል፡፡ መንግሥትም ለቀብር ማስፈጸሚያ የሚሆን ለተጎጂ ቤተሰቦች በቤተሰብ ሺሕ ብር የሰጠ ሲሆን፣ በጊዜያዊ መጠለያ ማዕከል ለሚገኙ ዜጎች ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ግለሰቦች፣ ክልሎች፣ መንግሥታዊ ድርጅቶችና የግል ድርጅቶች፣ እንዲሁም ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ለአደጋው ተጎጂዎች ዕርዳታ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -