Friday, June 9, 2023

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መራዘምና አለመራዘም በአንድ ወር ውስጥ ይወሰናል

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በሥራ ላይ የሚቆይበት ጊዜ ከ20 ያነሱ ቀናት ቢቀሩትም፣ የመራዘሙና አለመራዘሙ ጉዳይ ከአንድ ወር ጥናት በኋላ እንደሚወሰን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ አስታወቁ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመንግሥታቸውን የስድስት ወራት ሥራ አፈጻጸም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሐሙስ መጋቢት 7 ቀን 2009 ዓ.ም. ባቀረቡበት ወቅት፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከአምስት ወራት በፊት ተከስቶ የነበረውን ፀጥታ መደፍረስ ቀድሞ ወደነበረበት ሁኔታ መቀየር መቻሉን ገልጸዋል፡፡ አሁንም ቢሆን ሙሉ ለሙሉ ችግሮች ተቀርፈዋል የሚባልበት ጊዜ ላይ አለመደረሱን አክለዋል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኮማንድ ፖስት ባደረገው ግምገማ ወደ መደበኛው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለማሸጋገር የሚያስችል መመርያ ተዘጋጅቶ ሥራ መጀመሩን አስረድተዋል። ‹‹ወደ መደበኛ የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመመለስ የሚከናወነው ተግባር በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የመጣውን ሰላምና መረጋጋት የሚያሳይ ነው፤›› ብለዋል።

‹‹በአገሪቱ የተፈጠረው ሰላምና መረጋጋት ተጠናክሮ የቀጠለ ቢሆንም፣ አሁንም ለፀጥታ ሥጋት የሚሆኑ ክስተቶች ሙሉ ለሙሉ ተወግደዋል ማለት አይደለም፤›› በማለት፣ አልፎ አልፎ ፀጥታ ለማደፍረስ የሚደረጉ ችግሮች በተለየዩ ቦታዎች እየተስተዋሉ መሆኑን ለምክር ቤቱ አስረድተዋል፡፡

‹‹በአውራ ጎዳናዎች ላይ መኪና አቁሞ መዝረፍና መስታወቶች መስበር፣ በጥቂት ቦታዎች የትምህርት ተቋማት ውስጥ የመማርና ማስተማር ሒደቱን ማስተጓጎልና ረብሻ ለመፍጠር መሞከር፣ በአንዳንድ አካባቢዎች በግለሰቦችና በድርጅቶች ቅጥር ግቢ ውስጥ ቦምብ መወርወርና የመሳሰሉት ተግባራት ይንፀባረቃሉ፤›› ብለዋል፡፡

እነዚህ ክስተቶች በውስን አካባቢ የተከሰቱ ቢሆንም ከሕዝቡ ጋር ተጨማሪ ውይይት በማካሄድና በተግባር እነዚህን ሒደቶች ለማምከን ተጨማሪ የተጠናከሩ ሥራዎች እንደሚሠሩ ተናግረዋል።

‹‹በእነዚህ ጉዳዮች ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለአንድ ጊዜ ቢራዘም የተደላደለና እጅግ አስተማማኝ የሆነ ሰላም ለማረጋገጥ ይቻላል የሚለው ሐሳብ፣ በሕዝብ ውስጥ እንደሚንሸራሸር ለመገንዘብ ችለናል፤›› ሲሉም አስረድተዋል፡፡

ይሁን እንጂ በጥናቱ በተሰበሰበ የሕዝብ አስተያየት መሠረት ከ82 በመቶ በላይ በጥናቱ የተሳተፈ ሕዝብ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሙሉ ለሙሉ ወይም በከፊል እንዲቀጥል የሚል አስተያያት መሰጠቱንም ለምክር ቤቱ ገልጸዋል፡፡

ነገር ግን ጥናት ስላሉት ጉዳይ ዝርዝር ማብራሪያ ባይሰጡም፣ ኮማንድ ፖስቱ ግን ቀደም ብሎ ጥናት እያካሄደ ስለመሆኑ ገልጾ ነበር፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ፀንቶ በሚቆይበት በቀጣዩ የአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ጥናት በማካሄድ ውጤቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ሊፀድቅ እንደሚችል ጠቁመዋል።

የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬታሪያት ኃላፊና የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ በበኩላቸው ረቡዕ መጋቢት 6 ቀን 2009 ዓ.ም. በመኮንኖች ክበብ በጠሩት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተናገሩት፣ ኮማንድ ፖስቱ መመርያ ቁጥር አንድና ቁጥር ሁለትን በማውጣት የተሰጠውን ኃላፊነት ሲወጣ መቆየቱን አስታውሰው፣ መመርያ ቁጥር 3 በማስታወቅ ተጨማሪ ክልከላዎች መነሳታቸውን ይፋ አድርገዋል።

ከእነዚህ ክልከላዎች መካከል በትልልቅ ተቋማት አካባቢ ተጥሎ የቆየው ሰዓት ዕላፊ እንዲቀር መደረጉ ተካቶበታል፡፡

በእነዚህ ቦታዎች ላይ ሰዓት ዕላፊ ተላልፎ በተገኘ ማንኛውም ሰው የጥበቃ ወይም ሕግ አስከባሪ አካላት አስፈላጊውን ዕርምጃ እንዲወስዱ የተሰጣቸው ሥልጣንም እንዲቀር ተደርጓል።

በተመሳሳይ ክልከላዎችን ተላልፎ የተገኘ ማንኛውም ሰው ላይ የሕግ አስከባሪዎች ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በቁጥጥር ሥር ማዋል፣ አዋጁ ተፈጻሚነቱ እስኪያበቃ ኮማንድ ፖስቱ በሚወስነው ቦታ እንዲቆይ ማድረግ፣ ተገቢውን የተሃድሶ ሥልጠና ወስዶ እንዲለቀቅና ወደ ፍርድ ቤት የሚቀርበውን እንዲያቀርብ የሚለውም አንቀጽ መቅረቱን ገልጸዋል፡፡

‹‹ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በማናቸውም ሰዓት ብርበራ በማድረግ ማንኛውም ወንጀል የተፈጸመበት ወይም ሊፈጸምበት የሚችል ንብረት መያዝም እንዲቀር ሆኗል፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

በተጨማሪም በማንኛውም ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥን፣ ጽሑፍ፣ ምሥል፣ ፎቶግራፍ፣ ቴአትርና ፊልም የሚተላለፉ መዕልክቶችን ለመቆጣጠርና ለመገደብ የተጣለው መብት እንዲቀር መደረጉን ጠቁመዋል።

የሕግ አስከባሪዎች የተዘረፉ ንብረቶችን ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በመፈተሽ ለባለቤቶቹ እንዲመለሱ የማድረግ ሁኔታም እንዲቀር ከተረደጉት መካከል ናቸው።

ከዚህ ሌላ የጦር መሣሪያ ወይም ማንኛውንም የግልም ሆነ የመንግሥት ንብረት የዘረፈ፣ ለሕገወጥ ተግባራት ድጋፍ ያደረገና አቅራቢያው ለሚገኝ የሕግ አስከባሪ መመርያ ቁጥር አንድ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በአሥር ቀናት ውስጥ እንዲመልስና እጁን እንዲሰጥ የሚለው አንቀጽም ቀርቷል።

ወረቀት በመበተን፣ አድማ በማድረግ የተሳተፈና ያነሳሳ፣ ሰው የገደለ፣ ማንኛውንም ንብረት ያቃጠለና ማንኛውንም ወንጀል ፈጽሞ እጁን ለሰጠ የተሃድሶ ትምህርት በመስጠት የመልቀቅ ዕርምጃ በዚህ መመርያ ቀሪ ሆኗል።

ነገር ግን በመመርያ ቁጥር 1 ከተወሰኑት ክልከላዎችና ዕርምጃዎች በስተቀር፣ በመመርያ ቁጥር 2 መሠረት ራስን ለመከላከል በሕግ አስከባሪዎች ስለሚወሰድ ዕርምጃ፣ በብርበራና በፍተሻ ወቅት ስለሚከናወኑ ተግባራት እንዲሁም በመመርያ ቁጥር 1 ላይ የተመለከቱ ክልከላዎችና ዕርምጃዎች ተፈጻሚነት ይቀጥላል።

አቶ ሲራጅ እንደገለጹት፣ ክልከላዎቹ በዋናነት እንዲቀሩ የተደረጉት በአገሪቷ የተረጋጋ ሁኔታ በመፈጠሩ፣ ኢንቨስትመንትን ለማበረታታትና ለገጽታ ጭምር ጥቅሙ የጎላ መሆኑ ስለታመነበት ነው።

ሁከትና ብጥብጡ በመቀነሱና ‹‹አሁን ያሉትን ችግሮች በመደበኛ የሕግ ማስከበር ሥርዓት መቆጣጠር›› እንደሚቻል መታመኑም፣ ለዕገዳዎቹ መነሳት ሌላኛው ምክንያት ነው በማለት አቶ ሲራጅ ለጋዜጠኞች አብራርተዋል፡፡

በተቃራኒው ደግሞ እነዚህን መመርያዎች ሽፋን በማድረግ አንዳንድ የሕግ አስከባሪ አካላትም ሆኑ ሌሎች ፀጥታ አስከባሪ በመምሰል ኅብረተሰቡን እያጭበረበሩ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ከደቡብ ሱዳን በሚመጡ ታጣቂዎች በጋምቤላ አካባቢዎች ስለሚፈጸሙ ጥቃቶች የተጠየቁት የመከላከያ ሚኒስትሩ፣ የሁለቱ አገሮች መሪዎች አስፈላጊውን ዲፕሎማሲያዊ ውይይት በማድረግ የፀጥታ ሥጋቱን በጋራ ለመዋጋት እየሠሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከዲፕሎማሲያዊ ጥረቱ ባሻገር የአገር መከላከያ ሠራዊት በበኩሉ ታጣቂዎችን ለመከላከል በርካታ ሥራዎች እየሠራ መሆኑን ገልጸው፣ ከእነዚህም ውስጥ ወደ ደቡብ ሱዳን ለመሻገር የሚያስችል የድልድይና የመንገዶች ግንባታዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በተለይም የድንበር አካባቢው ጫካ የበዛበትና ረጅም ወንዝ ያለበት በመሆኑ፣ የመከላከያ ሠራዊት ፈጥኖ ዕርምጃ መውሰድ የሚያስችሉትን ድልድዮች እየሠራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -