Saturday, July 13, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሕግ አግባብ ውጪ ንብረት ሸጧል ተብሎ ክስ ተመሠረተበት

ተዛማጅ ፅሁፎች

ባዜን እርሻና ኢንዱስትሪ ልማት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ለተበደረው ብድር በመያዣነት ያስያዘውን 10,000 ሔክታር መሬት ከሕግ አግባብ ውጪ በሆነ መንገድ ሸጦብኛል በማለት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ ክስ መሠረተ፡፡

ማኅበሩ ለፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቂርቆስ ምድብ ችሎት ያቀረበው የፍትሐ ብሔር ክስ እንደሚያስረዳው፣ ባዜን የእርሻና የኢንዱስትሪ ልማት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብድር ለመበደር ስምምነት ላይ ይደርሳል፡፡ ማኅበሩ ለሚበደረው ገንዘብ በጋምቤላ ክልል አኝዋ ዞን አርፔም ኦፔኖ ወረዳ የሚገኘውን 10,000 ሔክታር መሬት በመያዣነት ይሰጣል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከማኅበሩ ጋር በገባው ውል መሠረት ገንዘቡ ተመላሽ እንዳልተደረገለት (እንዳልተከፈለው) በመግለጽ፣ በቴሌቪዥንና በጋዜጣ የጨረታ ማስታወቂያ በማውጣት በጨረታ መነሻ ዋጋ 35,494,902.40 ብር አወዳድሮ ታኅሳስ 15 ቀን 2007 ዓ.ም. በ52 ሚሊዮን ብር መሸጡን ክሱ ያብራራል፡፡ ባንኩ በባንክ በመያዥያ ስለተያዘ ንብረት በተደነገገው አዋጅ ቁጥር 97/90 አንቀጽ 5 መሠረት ሊከተላቸው ይገቡ የነበሩ የሕግ ድንጋጌዎች ቢኖሩም፣ የሕግ ድንጋጌውን በመተላለፍ ግዙፍ የሥነ ሥርዓት ግድፈት መፈጸሙን ማኅበሩ በክሱ ዝርዝር አቅርቧል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመያዣነት የያዘውን ንብረት ጨረታ ማውጣት የነበረበት ንብረቱ በሚገኝበት በጋምቤላ ክልል መሆን ቢኖርበትም፣ ጨረታውን ያደረገው ግን የባንኩ ዋና መሥሪያ ቤት አዲስ አበባ በመሆኑ በአስገዳጅነት የተቀመጡትን የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ድንጋጌዎችን አለማክበሩን ይጠቅሳል፡፡ አዋጅ ቁጥር 97/90 የአንቀጽ ሁለት ድንጋጌ መሠረት የማይንቀሳቀስን ንብረት በሚመለከት ሬጅስትራር ንብረቱን መመዝገብ እንዳለበት የጠቀሰው ከሳሽ ማኅበር፣ በመያዣነት ያስያዘውን 10,000 ሔክታር መሬት ጨረታ ሲቀርብ እንደ ሬጅስትራር ሆኖ መመዝገብ ያለበት የጋምቤላ ክልል አበቦ ወረዳ አስተዳደር እንደነበር በክሱ ጠቅሷል፡፡ ነገር ግን ባንኩ ጨረታውን አዲስ አበባ በማድረጉ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 አስተዳደር ጽሕፈት ቤትን የጨረታው ታዛቢ ማድረጉ የአዋጁን መንፈስና ዓላማ የሚጋፋ መሆኑን ጠቅሷል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ52 ሚሊዮን ብር የሸጠውን 10,000 ሔክታር መሬት ማኅበሩ 101 ሚሊዮን ብር ሊሸጠው በመደራደር ላይ እንደነበር በክሱ የጠቀሰ ሲሆን፣ ይኼንኑ ድርድር የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንደሚያውቅም ጠቁሟል፡፡ በሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ሥር የሚገኘው አግሪ ሴፍት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በ101 ሚሊዮን ብር ሊገዛው እየተደራደረው እንደነበር ባንኩ እያወቀ ጨረታ በማውጣትና ራሱ አግሪ ሴፍት፣ ሳዑዲ ስታር አግሪካልቸዋል ዴቨሎፕመንት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርና የእነሱው አካል ለሆነው አንድ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ የሆኑ ግለሰብ በማጫረት የተፈጸመው የሽያጭ ተግባር ተገቢ ካለመሆኑም በተጨማሪ፣ በማኅበሩ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዳደረሰበት በክሱ ተገልጿል፡፡

ማኅበሩ በተደጋጋሚ ጨረታው እንዲሰረዝለት ለንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት ደብዳቤ በመጻፍ ማሳወቁን ጠቁሞ ምላሽ ሊያገኝ አለመቻሉን አስታውቋል፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 26553 ከሰጠው አስገዳጅ ትርጉም አኳያ ያቀረበው ክስ ምክንያት ያለው መሆኑን ገልጿል፡፡ በመሆኑም ባንኩ አዋጅ ቁጥር 97/90 (6)ን እና የፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ/445ን በመተላለፍ ጉዳት እንዳደረሰበት በመግለጽ ጨረታው እንዲሰረዝለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለቀረበበት የፍትሐ ብሔር ክስ በሰጠው ምላሽ እንደገለጸው፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 84353 በሰጠው አስገዳጅ ትርጉም ባንኩ በመያዣነት የያዘውን ንብረት በሐራጅ ሽጦ ዕዳውን በመሰብሰብ ተግባር ፍርድ ቤቶች ተቀብለው ለማየትም ሆነ ለመወሰን ሥልጣን የላቸውም፡፡

ማኅበሩ እንደ ውሉ ግዴታ ባለመክፈሉ በአዋጅ ቁጥር 97/90 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ሽያጩን ያከናወነ በመሆኑ ክሱ ተቀባይነት እንደሌለው በመጥቀስ፣ በቂ ኪሳራ ተቆርጦለት ክሱ ውድቅ እንዲደረግለት ጠይቋል፡፡ ማኅበሩ ከባንኩ 102,258,330 ብር ለመበደር መስማማቱን የጠቆመው ባንኩ በሊዝ በጋምቤላ ክልል ያገኘውን ቦታ የመጠቀም መብት በመያዣነት ማስያዙንም አረጋግጧል፡፡ በማስያዣነት የወሰደውን የሊዝ መብት በአዋጅ ቁጥር 97/90 መሠረት በተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት በጨረታ ለመሸጥ የ30 ቀናት ማስጠንቀቂያ መሰጠቱንም ጠቅሷል፡፡ ማኅበሩ በተሰጠው ማስጠንቀቂያ መሠረት ሊከፍለው ባለመቻሉ ሚያዝያ 25 ቀን 2006 ዓ.ም. በጋዜጣና ቴሌቪዥን ጨረታ ቢያወጣም በቂ ተጫራቾች ባለማግኘቱ፣ በድጋሚ ጨረታ አውጥቶ በ52 ሚሊዮን ብር መሸጡን አረጋግጧል፡፡ ጨረታውን ሳዑዲ ስታር አግሪካልቸራል ዴቨሎፕመንት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ማሸነፉንና የሽያጩም ገንዘብ ሙሉ በሙሉ ለብድር ዕዳው መክፈያነት መዋሉ ንግድ ባንክ አስረድቷል፡፡

በክልሉ ማጫረት ሲገባው አዲስ አበባ ማጫረቱን በሚመለከትም ማኅበሩ የጠቀሰው የሕግ ድንጋጌ የሐራጅ ሒደት መከናወን እንዳለበት የሚደነግግ አለመሆኑን ገልጿል፡፡ ማኅበሩ አግሪ ሴፍት በድርድር 101 ሚሊዮን ብር እንደሰጠው የገለጸ መሆኑን ያስታወሰው ባንኩ፣ ከ51 ሚሊዮን ብር በላይ አለማቅረቡን በመግለጽ፣ ማኅበሩ ያቀረበውን ክስ ተገቢና ከአግባብ ውጪ መሆኑን በመዘርዘር ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን መርምሮ ከበቂ ኪሳራ ጋር ከክሱ በነፃ እንዲያሰናብተው በማመልከት ምላሹን አጠቃሏል፡፡ በመያዣነት የተያዘውን 10,000 ሔክታር መሬት በ52 ሚሊዮን ብር እንደገዛው የተገለጸው ሳዑዲ ስታር አግሪካልቸራል ዴቨሎፕመንት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ጣልቃ ለመግባት ለፍርድ ቤቱ አመልክቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ መዝገቡን መርምሮ ብይን ለመስጠት ለመጋቢት 30 ቀን 2007 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች