Wednesday, June 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከፍተኛ ኤሌክትሪክ የሚጠቀሙ ኢንቨስተሮች ችግራቸውን መንግሥት እንዲፈታላቸው ጠየቁ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚጠቀሙ ኢንቨስተሮች በኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ምክንያት እየደረሱባቸው ያለውን ችግር የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር እንዲፈታላቸው ጥያቄ አቀረቡ፡፡

መጋቢት 29 ቀን 2007 ዓ.ም. በሚኒስቴሩ የተሰበሰቡት እነዚህ ኢንቨስተሮች፣ ከኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ በተጨማሪ ‹ፓወር ፋክተር ኮኔክተር› እንዲገጠምላቸው ከሁለት ዓመት በፊት ክፍያ ቢፈጽሙም፣ እስካሁን እንዳልተገጠመላቸው ለሚኒስቴሩ ማስታወቃቸውን በስብሰባው ላይ የተገኙ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ቅሬታ አቅራቢዎቹ በዋናነት የሚያነሱት በኃይል መቆራረጥ ምክንያት በርካታ ሥራዎች እየተስተጓጎሉባቸው ከመሆኑም በላይ፣ ለንብረት ውድመትም እየተጋለጡ መሆኑን ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ቪጂላንስ ኦፊሰር አቶ ኪሮስ ሐዱሽ ይህ ችግር መኖሩን ለሪፖርተር ገልጸው፣ የችግሮቹ መነሻዎችንና መንግሥት እየወሰደ ያለውን ዕርምጃ ጨምረው አስረድተዋል፡፡ አቶ ኪሮስ እንዳሉት፣ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ በዋናነት በተፈጥሮ አደጋ፣ በሰው ሠራሽ፣ በሕገወጦችና የኤሌክትሪክ ጭነት ማስተናገድ ባልቻሉ ማሰራጫዎችና ማከፋፈያ መስመሮች አቅም ማነስ ነው፡፡ ሕገወጥ የተባለው ፈቃድ ሳይኖራቸው ከፍተኛ ኤሌክትሪክ የሚጠቀሙ ግለሰቦች መኖራቸው ነው፡፡ እነዚህ ግለሰቦች ከዋና መስመር ኤሌክትሪክ በመጥለፍ ከባድ ማሽኖች የሚያንቀሳቅሱ መሆናቸውን አቶ ኪሮስ ገልጸዋል፡፡ በሰፊው እየተከሰተ ያለው ችግር ደግሞ በአዲስ አበባና ዙሪያዋ የሚገኙ የኤሌክትሪክ ማከፋፈያና ማሰራጫ ጣቢያዎች እርጅና ምክንያት የሚፈለገው ኃይል በታሰበለት ቦታ መድረስ ያለመቻሉ ነው፡፡

ድርጅቱ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ሕገወጦችን ሥርዓት ከማስያዝ ጀምሮ ማሰራጫና ማከፋፈያ መስመሮችንም በአዲስ በመቀየር ላይ ነው በማለት አቶ ኪሮስ ጨምረው ገልጸዋል፡፡ ባለፈው ማክሰኞ በተካሄደው ስብሰባ የጨርቃ ጨርቅ፣ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች፣ የብረታ ብረት፣ የወረቀት፣ የምግብ፣ የአበባና በአጠቃላይ በኤክስፖርት ዘርፍ የተሰማሩ የፋብሪካ ባለቤቶች ተገኝተዋል፡፡ በዚህ ስብሰባ የተሳተፉ ኢንቨስተሮች በኃይል መቆራረጥ ምክንያት ከፍተኛ ችግር እየደረሰባቸው መሆኑን ስብሰባውን ለመሩት የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ አቶ ዓለማየሁ ተገኑ መግለጻቸው ታውቋል፡፡

በስብሰባው የተገኙ ኢንቨስተሮች ከፍተኛ የኃይል መቆራረጥ በሥራቸው ላይ ችግር ከማስከተሉም በላይ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃላፊዎችና ሠራተኞች የሚደርስባቸውን ችግር እንደማይፈቱላቸው ለሚኒስትሩ  ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ኢንቨስተሮች ‹ፓወር ፋክተር ኮሬክተር› እንዲገጠምላቸው ከሁለት ዓመት በፊት ክፍያ ቢፈጽሙም፣ መሣሪያው ሊገጠምላቸው ባለመቻሉ የሚያገኙትን ኃይል በአግባቡ ለመጠቀም እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡

አቶ ዓለማየሁ ችግሮች በሚነሳባቸው አካባቢዎች የሚገኙ የሥራ ኃላፊዎች ምላሸ እንዲሰጡ ከማድረጋቸውም በተጨማሪ፣ አርኪ ምላሽ ያላቀረበ የሪጂን ኃላፊ በአፋጣኝ ለኢንቨስተሮች ጥያቄ ምላሽ ሰጥቶ ሪፖርት እንዲያቀርብላቸው ትዕዛዝ መስጠታቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ለ‹ፓወር ፋክተር ኮኔክተር› ችግርም አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ ሚኒስትሩ ትዕዛዝ ሰጥተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የሥነ ምግባር ችግር አለባቸው በተባሉ የድርጅቱ ሠራተኞች ላይ ምርመራ ተደርጎ ዕርምጃ እንዲወሰድ ማዘዛቸው ታውቋል፡፡

አቶ ዓለማየሁ ችግሮችን ለመቅረፍ የማከፋፋያና ዋና ማሰራጫ ጣቢያዎችን አቅም ከማሳደግ ባሻገር፣ ለትልልቅ ፕሮጀክቶች ራሱን የቻለ ማከፋፈያ ጣቢያ እንደሚተከል ማሳወቃቸውን ምንጮች ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በበኩሉ በአዲስ አበባና በዙሪያዋ እየተከሰተ ያለውን ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ለማስቀረት በ160.6 ሚሊዮን ዶላር የጀመረውን ፕሮጀክት በሚቀጥለው ወር እንደሚያጠናቅቅ አስረድቷል፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት የውጭ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ገብረ እግዚአብሔር ታፈረ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በአዲስ አበባ አሥር ማከፋፈያ ጣቢያዎች በ100 ሚሊዮን ዶላር እየተገነቡ ነው፡፡

‹‹የተወሰኑት ተጠናቀው ሥራ የጀመሩ ሲሆን፣ በሚያዝያ ወር ቀሪዎቹ ተጠናቀው ወደ ሥራ ይገባሉ፤›› በማለት አቶ ገብረ እግዚአብሔር ገልጸዋል፡፡ የማሰራጫ መስመሮች ደግሞ በ60.6 ሚሊዮን ዶላር እየተገነቡ በመሆናቸው፣ እነዚህ ፕሮጀክቶች በአጠቃላይ ሥራ ሲጀምሩ የነዋሪዎችም ሆነ የኢንቨስተሮች ችግር ይፈታል በማለት አቶ ገብረ እግዚአብሔር ጨምረው ገልጸዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች