በዐሥራ ሰባተኛው ምእት ዓመት የኖረው ኢትዮጵያዊ ፈላስፋ ዘርዐ ያዕቆብና የደቀ መዝሙሩ ወልደ ሕይወት ፍልስፍናዊ ሐተታዎች አዲስ የአማርኛ ትርጉም ለሕትመት በቃ፡፡
ከ400 ዓመታት በፊት የነበሩት የአክሱም ተወላጁ ዘርዐ ያዕቆብ (ሁለተኛ ስሙ ወርቄ) እና የእንፍራንዝ (ጎንደር አካባቢ) ተወላጁ ወልደ ሕይወት (ሁለተኛ ስሙ ምትኩ) ሐተታዎች ከግእዝ ቋንቋ ወደ አማርኛ የተረጐሙት አለቃ ያሬድ ፈንታ ወልደ ዮሐንስ ናቸው፡፡
‹‹ሐተታ ዘርዐ ያዕቆብ ወሐተታ ወልደ ሕይወት- የኢትዮጵያ ፍልስፍና›› የሚል ርእስ ያለው መጽሐፉ ከመጋቢት 28 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ገበያ ላይ ውሏል፡፡
በመጽሐፉ ቀዳሚ ቃል ላይ እንደተመለከተው፣ ፈላስፋው ዘርዐ ያዕቆብ በዚህ አጭር ሐተታው ውስጥ ብዙ ጥያቄዎችን በማንሣት የፈጣሪን ህልውና መርምሯል፤ መኖሩንም አረጋግጧል፡፡ የቅዱሳት መጻሕፍትን ትምህርት ትክክል መሆን አለመሆናቸውን በተመለከተ ዝርዝር ጥናት ያደረገ ሲሆን በተለያዩ ሃይማኖቶች፤ በተለይም እርሱ በነበረበት ዘመነ በነበሩት በአይሁድ፤ በክርስትና እና በእስልምና ላይ ጥልቅ ምርምር አድርጓል፡፡
አሁን ለንባብ የበቃው ይህ የሁለቱ ፈላስፋዎች አዲስ የአማርኛ ትርጉም ኢኖ ሊትማን እ.ኤ.አ. በ1904 ያሳተመው የግእዝ እትምን በመጠቀም ያቀረቡት አለቃ ያሬድ፣ የግእዙን ሐተታ መሠረት ሳይለቅ አገባቡንና የአጻጻፍ ስልቱን በአቻ አማርኛ እንዲቀርብ ማድረጋቸው በመግቢያው ተመልክቷል፡፡
‹‹ሐተታ ዘርዐ ያዕቆብ ወሐተታ ወልደ ሕይወት- የኢትዮጵያ ፍልስፍና›› የመሸጫ ዋጋው 55 ብር ሲሆን፣ አከፋፋዩ ቡክ ላይት መጻሕፍት መደብር መሆኑ ታውቋል፡፡
አለቃ ያሬድ ቀደም ሲል ያዘጋጇቸውና ለንባብ ያበቋቸው መጻሕፍት፡- ስለኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠርና ሥነ ፈለክ የሚያወሳው ‹‹ባሕረ ሐሳብ የቀመርና የሥነ ፈለክ ምሥጢር››፣ በአራቱ ወቅቶች ላይ የተመሠረተው ‹‹መጽሐፈ ግጻዌ ሐዲስ››፣ ‹‹ፍኖተ ግእዝ ዘመናዊ›› እና በሁለት ቋንቋዎች የተዘጋጀው ‹‹የንግግር ሥርዓቶችና አገባቦች- Rules & Forms of Speech›› ናቸው፡፡