Tuesday, March 5, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልጉዞ ወደ ጠቢባኑ መንደር

ጉዞ ወደ ጠቢባኑ መንደር

ቀን:

ሐረር ከተማ የሚገኘውን ጄላን ወረዳ ለሁለት የሚከፍለውን አስፋልት ትተን ወደ መንደሮቹ ዘለቅን፡፡ ከአቧራማው ኮረኮንች ዳርቻ አነስተኛ መኖሪያ ቤቶችና የመቃብር ሥፍራ አሉ፡፡ ከፍ ወዳለ ኮረብታ ሲወጡ ከፊል ሐረር ወለል ብሎ ይታያል፡፡ ብዙም እንቅስቃሴ የማይስተዋልበት ዘዋራው ጄላን ወረዳ ውስጥ ካሉ ቅጥር ግቢዎች ወደ አንዱ ገባን፡፡

 ግቢውን ከሚያዋስኑት አጎራባች መኖሪያዎች ጋር የጋራ የሆነ ግዙፍ ዋርካ ይታያል፡፡ ዋርካውን የተጠለሉት አዕዋፋት ዝማሬ ለግቢው ልዩ ውበት ሰጥቶታል፡፡ በግቢው ካለው ዘመም ያለ የጭቃ ቤት አንዱ ክፍል  አንጋፋው ሠዓሊና ገጣሚ ገብረክርስቶስ ደስታ የተወለደበት ነው፡፡

በ1973 ዓ.ም. በ50 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ገብረክርስቶስ፣ ሐረር ካፈራቻቸው እውቅ የጥበብ ልሒቃን አንዱ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ሥነ ጥበብ አሻራቸውን ካሳረፉ ሠዓሊዎች አንዱ ከመሆኑም በላይ ግጥሞቹ በሥነ ጽሑፉ ሁነኛ ቦታ ይይዛሉ፡፡ የዚህ ታላቅ ሰው የቀድሞ መኖሪያ አሁን በተከራዮች ይዞታ ሥር ሲሆን፣ ጥበቃና እንክብካቤ ተነፍጎት ታሪካዊ ስፍራነቱን ጥያቄ ውስጥ ከቶታል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

አስጎብኚአችን የገብረክርስቶስ የእህት ልጅ አቶ ኃይሉ ሸዋሰገድ ከገብረክርስቶስ ጋር የሦስት ዓመት ዕድሜ ልዩነት አላቸው፡፡ ዘወትር እሱ የቀለም ትምህርት ይከታተልበት ከነበረው ትምህርት ቤት፣ እሳቸው ደግሞ ከአብነት ትምህርት መልስ በግቢው ይገናኙ ነበር፡፡ የቤቱ በረንዳው ላይ ከገብረክርስቶስ አባትና የአቶ ኃይሉ አያት እግር ሥር ሆነው ቅኔ ይማሩ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡

 ‹‹ይህን አስተካክሉ፤ ይሄኛው ጥሩ ነው፤ እያሉ ያስተምሩን ነበር፤›› በማለት ወቅቱን አቶ ኃይሉ ያስታውሳሉ፡፡ ግጥም ሲጻፍ ምን ዓይነት መንገድ መከተል እንዳለበት ለዓመታት አስተምረዋቸዋል፡፡ ገብረክርስቶስ በዘርፉ ስሙ እንደናኘ በደስታ የሚያስታውሱት አቶ ኃይሉም ግጥም ይጽፋሉ፡፡

ሥዕል መሣል ሲጀምር እንደ ቀለም ይጠቀም የነበረው ጥላሸትና ፅጌረዳ አበባ ነበር፡፡ ጥላሸት ፈረካክሶ፣ አበባ አድርቆ ከዛም በውኃ በጥብጦ ቀለም ካዘጋጀ በኋላ ከድግጣ ቅጠል ብሩሸ ሠርቶ ይሥል ነበር፡፡ ሐረር ውስጥ በኖረበት ወቅት በአካባቢው ካለ ኮረብታ ላይ ተቀምጦ ወደታች እየተመለከተ የሣለውን ሐረርን የሚያሳይ ሥዕል ያስታውሳሉ፡፡

ከእሳቸው የወጣትነት ትውስታዎች ዋነኛው ገብረክርስቶስ በጭቃ የሠራው የአፄ ቴዎድሮስ ሐውልት ነው፡፡ ቅርጹ በቤታቸው አቅራቢያ በሚገኝና ብዙ ጊዜ ለሥዕል በሚጠቀምበት ዋሻ ውስጥ ተቀምጦ ነበር፡፡ በቅርቡ ቅርጹ በአካባቢው በሚዘዋወሩ ሰዎች ሳቢያ መሰባበሩን በሐዘኔታ ይገልጻሉ፡፡ ዋሻውን ቆፍሮ ካዘጋጃቸው ቅርጾች አንዱ ቅዱስ ጊዮርጊስ በጦር ዘንዶ ሲወጋ የሚያሳይ ነው፡፡ የቅርጹ ልዩ ልዩ ክፍሎች በየጊዜው እየተሰባበሩ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ አሁን ዋሻው መገበያያ ስለሆነና አካባቢው ለከብቶች ግጦሽ ስለዋለ ለቅርጾቹ ጥበቃ ማድረግ አልተቻለም፡፡

ለቤቱና ዋሻው ጥበቃ ባይደረግም ቤተሰቦቻቸው የገብረክርስቶስን ግጥሞች በማሰባሰብ ጥናቶች እንደሚሠሩ ይናገራሉ፡፡ በስሙ የተሰየመ ዘመናዊ የሥነ ጥበብ ማዕከል ከጎተ (የጀርመን ባህል ማዕከል) አጠገብ እንደሚገኝም ይታወቃል፡፡

ገብረ ክርስቶስ ጀርመን አገር ሥነ ጥበብ ተምሯል፡፡ ሥራዎቹ እዛው ጀርመን፣ ግሪክ፣ ሴኔጋል፣ ብራዚልና በሌሎችም አገሮች ለዕይታ በቅተዋል፡፡ በጀርመን በሚገኝ ሙዚየም የነበሩ ሥራዎቹ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በስሙ በተዘጋጀው ጋለሪ ይገኛሉ፡፡     የገብረክርስቶስ ቤትና ይሥልበት የነበረው ዋሻ በሥርዓት ቢያዝ በሥዕልም ይሁን በሥነ ግጥም ያለውን ቦታ የሚያጎላ፣ ለሥራዎቹ ክብር የሚሰጥና ለጎብኚዎችም መስህብ መሆን የሚችል ነው የሚል አስተያየት ለሪፖርተር የሰጡት አካባቢውን ከጎበኙት አንዱ ደራሲ ኃይለመለኮት መዋዕል ናቸው፡፡

ዋሻው አሁን እንደሚታየው ቅርፆቹን ለአደጋ በሚያጋልጥ ሁናቴ መገበያያ መሆን እንደማይገባው ይናገራሉ፡፡ ሌሎች አገሮች የኪነ ጥበብ ባለሙያዎቻቸውን የሚዘክሩበትን መንገድ ሳይጠቅሱ አያልፉም፡፡ እንደ ምሳሌ ያነሱት እንግሊዛውያን ‹‹ፖየትስ ኮርነር›› በሚል የገጣሚዎቻቸውን መቃብር ሥፍራ ከልለው ማስጎብኘታቸውን ነው፡፡ የጀርመኑ ውልፍ ጋንግ፣ የሩሲያው ሊዮ ቶልስቶይና ዶስቶቨስኪ መኖሪያ የነበሩ ቤቶች ትልቅ ክብር ተሰጥቷቸው ይታያሉ፡፡

ቤቱ እንደ አገራዊ ቅርስነቱ ተጠግኖ ለእይታ መቅረብና ዋሻውም ታሪኩን የሚያስረዳ መግለጫ ተዘጋጅቶለት ሊጎበኝ ይገባል ይላሉ፡፡ አቶ ኃይሉ በበኩላቸው የተወለደበትን ቤት ቤተ መጻሕፍት ማድረግ ቢቻል ምኞታቸው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

አቶ ኃይለመለኮት ፈር መያዝ ያለባቸው ነገሮችን ለማስተካከል ቦታውን መጎብኘት አስፈላጊ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ቦታውን የጎበኙ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን በማጣቀስ ‹‹አንጋፋና ወጣት የኪነ ጥበቡ ባለሙያዎች ወደ ታሪካዊ ቦታዎች የሚያደርጉት ጉዞ ለቦታዎቹ ጥበቃ እንዲደረግ የሚያሳስብ ይሆናል፤›› ሲሉ ይናገራሉ፡፡

‹‹የዚህን ታላቅ ሰው የትውልድ ስፍራ መጎብኝት ለአገሩ ያበረከታቸውን ሥራዎች መዘከር ነው፤›› በማለት አቶ ኃይሉ የተሰማቸውን ሐሴት ይገልጻሉ፡፡ ከግጥሞቹ አንዱን ‹‹ሥጋው የኔ ገብሩ›› በስሜት ተሞልተው ካነበቡልን በኋላ ለአገሩ የነበረውን ጥልቅ ፍቅር ከሚያንፀባርቁ ግጥሞች ተጠቃሽ መሆኑን በትውስታ አውግተዋል፡፡

የገብረክርስቶስን ትውልድ ሥፍራ በጎበኘንበት ወቅት በቦታው የተገኙትና ጓደኛው የነበሩት ደራሲ አስፋው ዳምጤ በበኩላቸው፣ የተዋውቁበትን ቅፅበት አውስተዋል፡፡ በወጣትነታቸው ነው፤ አንድ ቀን እንግሊዝ ውሰጥ ሲዘዋወሩ ውለው እረፍት ለማድረግ ወደ አንድ ካፍቴሪያ ጎራ ይላሉ፡፡ በካፌው የጦፈ ክርክር ላይ ከነበሩ ሦስት ኢትዮጵያውያን አንዱ እንዲቀላቀሏቸው ይጋብዛቸዋል፡፡ ያ ሰው ገብረክርስቶስ ሲሆን፣ ያኔ ስለ ኪነ ጥበብና ፍልስፍና ሰዓታት የፈጀ ክርክር ማካሄዳቸውን ያስታውሳሉ፡፡

 ጠንካራ አቋም ያለው ሰው እንደነበር የሚናገሩት አቶ አስፋው፣ ‹‹ገብረ ክርስቶስ አመለካከቱ የተለየ ስለነበር ብዙ ጊዜ በሐሳቦች ዙሪያ ክርክር ያነሳ ነበር፤›› ይላሉ፡፡ በሥዕል በአብስትራክት ዘዬ ፈር ቀዳጅ መሆኑንና ‹‹መንገድ ስጡኝ ሰፊ›› የመሰሉ ግጥሞቹ ለሥነ ግጥም ያበረከተው አስተዋፅኦ አስረጂ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡

የገብረክርስቶስ ትውልድ ቀዬ የተጎበኘው የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር (ኢደማ) ‹‹ህያው የጥበብ ጉዞ 4፤ ወደ ፀሐይ መውጫ አገር›› በሚል ባዘጋጀው ጉዞ ነበር፡፡ አንጋፋና ወጣት ጸሐፍት ከአዲስ አበባ በስተምሥራቅ በሚገኙት ሐረርና ድሬዳዋ ያሉ ታሪካዊ ሥፍራዎችን ጎብኝተዋል፡፡  

የአንጋፋው ደራሲ መንግሥቱ ለማ የትውልድ አካባቢ በጉብኝቱ ከተካተቱ ይጠቀሳል፡፡ የመንግሥቱ አባት አለቃ ለማ ኃይሉ ያገለገሉበት የነበረው አደሬ ጢቆ የሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ተጠቃሽ ሲሆን፣ በመንግሥቱ ጽሑፎች ውስጥ የአካባቢው ተፅዕኖ ይስተዋላል፡፡ እንደ ምላሌ የሚጠቀሰው ‹‹ደማሙ ብዕረኛ›› ነው፡፡

 የመንግሥቱ አባት ከሚያገለግሉበት ቤተ ክርስቲያን ወደ ሌላ አጥቢያ ሄደው ቅኔ በሚያስተምሩበት ወቅት መንግሥቱ ተከትሏቸው እንደሚሄድ ይናገራሉ፡፡ ብርድና ጨለማ ሳይገታው ያደረገው ጉዞ ቅኔ ለማወቅ የነበረውን ጉጉት ያሳየ እንደነበር አሁን በቤተ ክርስቲያኑ የሚያገለግሉ ሊቃውንት ያወሳሉ፡፡ ከጎብኚዎቹ አንዱ የነበሩትና ‹‹የመንግሥቱ ደቀ መዝሙር ነኝ›› የሚሉት ገጣሚና ጸሐፌ ተውኔት አያልነህ ሙላቱ በበኩላቸው፣ በሥነ ጽሑፍ ሥራዎቻቸው የመንግሥቱን አስተዋጽኦ ያስረዳሉ፡፡

በሁለቱም ከተሞች የሥነ ጽሑፍ ምሽቶች የተዘጋጁ ሲሆን፣ ተስፋዬ ገሠሠ፣ አጥናፍ ሰገድ ይልማና ሌሎችም አንጋፋ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ተሞክሯቸውን ያካፈሉበትና ወጣቶች ሥራዎቻቸውን ያቀረቡበት ነበር፡፡ የሐረርና ድሬዳዋ አማተር ጸሐፊዎችና  የከፍተኛ ተቋማት ተማሪዎች ጥሩ የሚባሉ ግጥሞችና መነባንቦች  አስደምጠዋል፡፡ ወጣቶቹ ቀጣይነት ያላቸው መድረኮች ተሰናድተውላቸው የሥነ ጽሑፍ ሥራዎቻቸውን ቢያቀርቡ የበለጠ ፍሬያማ መሆን እንደሚችሉ ተመልክቷል፡፡

ሌላው የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት ቅኝት ነበር፡፡ ሐረር የሚገኘው የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት አነስተኛ የመጻሕፍት ክምችት ያለው ሲሆን፣ ከአካባቢው ነዋሪ  ቁጥር አንፃር ከተወሰነ ተጠቃሚ በላይ የሚያስተናግድ አይደለም፡፡ በአንፃሩ የድሬዳዋ የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት የተሻለ የመጻሕፍት ቁጥር አለው፡፡ የቤተ መጻሕፍት መጠን አነስተኛ ቢሆንም፣ አዲስ ቤተ መጻሕፍት እየተገነባ ስለሆነ የተሻለ የንባብ ቦታ እንደሚኖር ይገመታል፡፡ በቤተ መጻሕፍቱ ውስጥ የተለያየ ይዘት ያላቸው መጻሕፍት ተሟልተው ነዋሪዎች የንባብ ባህላቸውን የሚያዳብሩበት መንገድ መከፈት እንዳለበት አስተያየታቸውን የሰነዘሩ ነበሩ፡፡

ከዚህ ቀደም ‹‹ህያው የጥበብ ጉዞ ወደ ፍቅር እስከ መቃብር ሀገር›› በሚል ወደ አማራ ክልል፣ ‹‹ህያው የጥበብ ጉዞ ከቡስካ በስተጀርባ ወደ ድንግል ውበት ሀገር›› በሚል ወደ ደቡብ ክልል እና ‹‹የዓባይ ዘመን ህያው የጥበብ ጉዞ ወደ ፈላስፋው ዘርዐ ያዕቆብና ማህሌታይ ቅዱስ ያሬድ ሀገር›› በሚል ወደ ትግራይ ክልል ጉዞዎች ተካሂደዋል፡፡

 የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙሴ ያዕቆብ እንደሚናገሩት፣  ከጉዞው ዓላማዎች አንዱ የተለያዩ አካባቢዎችን ባህልና አኗኗር ለደራስያን በማስቃኘት ለጽሑፍ እንዲነሳሱ ማድረግ ነው፡፡ ደራስያን ወደ የተለያዩ አካባቢዎች እየተጓጓዙ ሲጎበኙ፣ ተሞክሯቸውን ሲያካፍሉና ሥራዎቻቸውን ሲያቀርቡ የየአካባቢው የሥነ ጽሑፍ ድባብ ይነቃቃል ብለው ያምናሉ፡፡ ሐረርና ድሬዳዋ ከተማ የተካሄዱትን የሥነ ጽሑፍ መርሐ ግብሮች በማጣቀስ፣ የንባብ ባህልን በማዳበር ረገድም ሚና እንደሚኖረው ያስረዳሉ፡፡

ወጣቶች የሥነ ጽሑፍ ሥራዎቻቸውን የሚያቀርቡባቸው መድረኮች እንዲስፋፉና የባህል ማዕከሎች እንዲጠናከሩ የማድረግ ዓላማቸውንም ይጠቅሳሉ፡፡ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና በሥነ ጽሑፍ ላይ ከሚሠሩ ማኅበራት ጋር የመግባቢያ ሰነድ መፈራረምና የማኅበሩን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ማስፋፋትን በዚህ ረገድ እንደሚጠቀስ ያስረዳሉ፡፡

በየአካባቢው በሚደረጉ ጉብኝቶች ወቅት የአንጋፋ ደራስያን ታሪክ አሻራ ያረፈባቸው  ቦታዎች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ማኅበሩ ምን እንቅስቃሴ እንደሚያደርግ ፕሬዚዳንቱን ጠይቀናቸዋል፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ ለችግሮቹ መፍትሔ ለማበጀት ዘላቂ ክትትል ይጠይቃል፡፡ እንደ ገብረክርስቶስ የትውልድ ስፍራ ያሉ የደራስያን እንዲሁም ሌሎች የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች አስተዋፅኦ እንዲወሳ መንገድ የሚከፍቱ ቦታዎች ፈር እንዲይዙ ርብርብ እንደሚያሻ ተናግረዋል፡፡  

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...