‹‹የውዲቷ አገራችን አንድነት፣ ሰላምና ዕድገት ከምንም ነገር በላይ ስለሚበልጥ ቃሌን ጠብቄ ምርጫው ነፃና ፍትሐዊ እንዲሆን አድርጌያለሁ፡፡››
በቅርቡ በተካሄደው ምርጫ የተሸነፉት የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን ካደረጉት ንግግር የተወሰደ፡፡ ፕሬዚዳንት ጆናታንን ከ2.5 ሚሊዮን በላይ በሆነ ድምፅ ያሸነፉዋቸው የ72 ዓመቱ አዛውንት የቀድሞው ወታደራዊ መሪ (ጄኔራል) መሐሙዱ ቡሀሪ ናቸው፡፡ የ57 ዓመቱ ጆናታን በሥልጣን ላይ ሆነው በምርጫ የተሸነፉ የመጀመርያው ፕሬዚዳንት ሲሆኑ፣ ከምርጫው በፊት እሳቸው ቢሸነፉ ብጥብጥ ይነሳል ተብሎ ተሰግቶ ነበር፡፡ ነገር ግን እሳቸው፣ ‹‹የማንኛችንም ፍላጎት ከናይጄሪያውያን ደም አይበልጥም፤›› በማለት በገቡት ቃል መሠረት ምርጫው ነፃና ፍትሐዊ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡ በዚህ ተግባራቸውም በዓለም ዙሪያ ተሞግሰዋል፡፡ በምሥሉ ላይ የሚታዩት ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን ናቸው፡፡