በመጪው ግንቦት አጋማሽ በመላው አገሪቱ የሚካሄደው አምስተኛው ዙር አገር አቀፍ ምርጫ በሰላም ተጀምሮ በሰላም እንዲፈጸም ሁሉም ወገኖች ጥረት እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጠየቀች፡፡
ሚያዝያ 4 ቀን 2007 ዓ.ም. የሚከበረውን የትንሣኤ በዓል ምክንያት በማድረግ ብፁዕ እምብፁዓን ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን፣ በመንበረ ካርዲናል መጋቢት 28 ቀን ባስተላለፉት መልዕክት፣ መጪው አምስተኛ ዙር አገር አቀፍ ምርጫ በሰላም ተጀምሮ በሰላም እንዲፈጸም የሁሉም ትብብር አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
‹‹ለተፈጻሚነቱ መንግሥት፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ሕዝብ የሚያደርጉትን ጥረት እያደነቅን ለዚህም መላው ምዕመኖቻችንና መላው ሕዝባችን በፀሎት እንዲተባበር አሳስባለሁ፤›› ብለዋል፡፡
ካርዲናል ብርሃነየሱስ አያይዘውም፣ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ሰላምና ፍቅር እንዲነግሥ ሁላችንም በዘርና በሃይማኖት ሳንከፋፈል በኅብረት እንደምንጸልይና እንደምንኖር ሁሉ በብዙ የዓለም ክፍል በመለያየት በጦርነት በስቃይ በግድያና በስደት ለሚገኙ ሕዝቦች ሁሉ በተለይ በአንዳንድ አገሮች ውስጥ ክርስቲያኖች ብቻ ስለሆኑ የሚደርሰው ስደትና አሰቃቂ ግድያ እንዲያቆም እንድንጸልይ አደራ እላለሁ ብለዋል፡፡
በትንሣኤ በዓል አጋጣሚም ምዕመናን ለድሆችና ረዳት ለሌላቸው የአቅማቸውንና የችሎታቸውን ያህል እንዲረዱና እንዲመግቡም ካርዲናሉ ጥሪ ሳያቀርቡ አላለፉም፡፡
ዓመታዊው የትንሣኤ በዓል ጎርጎርዮሳዊ ቀመርን በሚከተሉ የዓለም አገሮች ባለፈው እሑድ መጋቢት 27 ቀን የተከበረ ሲሆን፣ በኢትዮጵያና የጁሊያን ቀመርን በሚከተሉት የዓለም ኦርቶዶክሳውያን ዘንድ በዓሉ ሚያዝያ 4 ቀን ይከበራል፡፡