ዱቄት በማምረትና በተለይም ለመንግሥት ተቋማት በማቅረብ የሚታወቀው አስትኮ የተመሠረተው በ1996 ዓ.ም. ነው፡፡ ገላን አካባቢ የሚገኘው ፋብሪካው ሥራውን የጀመረው ዱቄት በማምረት ሲሆን ፓስታና መኮረኒ ወደ ማምረቱም ተቀላቅሏል፡፡ መንግሥት የተመጣጠነ ምግብ ወይም በማዕድናትና በቫይታሚኖች የበለፀጉ ምግቦች አስፈላጊነትን አስመልክቶ ያወጣውን የተመጣጠነ ምግብ ፕሮግራም ተከትሎም ድርጅቱ የሚያመርተውን ዱቄት በቫይታሚንና በማዕድናት ማበልፀግ ጀምሯል፡፡ በቀጣይ ደግሞ የድርጅቱ ምርቶች የሆኑት አልታ እና ኖቫ ፓስታና መኮረኒ በማዕድናት በበለፀገው ዱቄት የሚመረቱ ይሆናል፡፡ አቶ ጸጋዬ ዋቅቶላ በድርጅቱ የንግድ መምሪያ ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ ምሕረት ሞገስ አነጋግራቸዋለች፡፡
ሪፖርተር፡- ድርጅቱ እንደተቋቋመ የስንዴ ዱቄት ለኅብረተሰቡ ማቅረብ ጀምራችሁ ነበር፡፡ በኋላ ግን አቅርቦቱን ወደ ተቋማት አድርጋችኋል፡፡ ምክንያቱ ምን ነበር? አሁንስ ምን ደረጃ ላይ ነው?
አቶ ጸጋዬ፡- ድርጅቱ በወቅቱ የሚያቀርበው የዱቄት ምርት የተጠቃሚው ፍላጎት ላይ መድረስ አልቻለም ነበር፡፡ በመሆኑም በግለሰብ ደረጃ ይሸጥ የነበረውን የስንዴ ዱቄት ወደ ተቋማት በማሸጋገር ለመከላከያ፣ ለፖሊስ ማቅረብ ጀመርን፡፡ በኋላም ተጨማሪ ማስፋፊያ አድርገን በ2000 ዓ.ም. ላይ ፓስታ ማምረት ጀምረናል፡፡ በ2006 ዓ.ም. ላይ ደግሞ መኮረኒ ማምረት ጀምሯል፡፡ ፋብሪካው እንደ ሞዴል ሆኖ የተተከለለት የስዊዘርላንድ ማሸን ነው፡፡ ዘመናዊ በመሆኑም ከአንድ ግብዓት 17 ዓይነት ዱቄት ያወጣል፡፡ ምርቱን ግን ለተጠቃሚው ማድረስ ከባድ ነው፡፡ የግብዓት እጥረት አለ፡፡ በመሆኑም ምርቱን ለመከላከያ ሠራዊት ብቻ እንሰጥ ነበር፡፡ በፓስታና በመኮረኒው ካልሆነ በስንዴ ዱቄት ገበያው ላይ አልተሳተፍንም፡፡ ሆኖም ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ መንግሥት ለዳቦ ጋጋሪዎች በፈጠረው የንግድ ትስስር በሁለት ክፍለ ከተሞች የሚገኙ የሸማቾች ማኅበራትና ዳቦ ጋጋሪዎች ዱቄት ከኛ ያገኛሉ፡፡ መከላከያ በየዕዙ ዱቄት እንዲያስፈጭ በመደረጉ በአሁኑ ሰዓት ዱቄት የምናቀርበው ለፌዴራል ፖሊስና ለአዲስ አበባ ፖሊስ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ፓስታና መኮረኒውስ ገበያ ላይ ወጥቷል?
አቶ ጸጋዬ፡- እነዚህ በቀጥታ ገበያ ላይ ነው የሚቀርቡት፡፡ በብዛት የምንሰጠው ለጅምላ አከፋፋዮች ሲሆን በሁሉም ክልሎች እናሰራጫለን፡፡ ምርቶቹን በማዕድናትና በቫይታሚኖች ከማበልፀጉ ጋር ተያይዞ ለጊዜው ማምረቱን አቁመናል፡፡
ሪፖርተር፡- በቀን ምርታችሁ ምን ያህል ነበር?
አቶ ጸጋዬ፡- በ24 ሰዓት ውስጥ የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ከሌለ ከ240 እስከ 250 ኩንታል ፓስታ እናመርታለን፡፡ መኮረኒ በ24 ሰዓት 360 ኩንታል እናመርታለን፡፡ ፍላጎቱም ከፍተኛ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በፓስታና መኮረኒ ያላችሁን ምርት የማስፋፋት ዕቅድ አላችሁ?
አቶ ጸጋዬ፡- አዎ፡፡ ማስፋፊያ ለመሥራት ከመንግሥት ቦታ አግኝተናል፡፡ ምርቶቻችንን አበልፅገን በአዲስ መልክ ለመቀጠል ሰፊ ሥራ ሠርተናል፡፡ ዝግጅታችንን ጨርሰናል፡፡ ዱቄቱን በማዕድንና ቫይታሚን ከማበልፀግ ጋር ተያይዞ አጠቃላይ በፋብሪካው የሚመረቱ ምርቶችን አስፋፍተን ለመሥራት ነው ያሰብነው፡፡ በጥቂት ወራት ውስጥ በሰፊው ገበያ ውስጥ እንገባለን፡፡ በዱቄቱም፣ በመኮረኒና በፓስታውም ከተቋማት አልፈን ለሕዝቡም እናቀርባለን፡፡
ሪፖርተር፡- በሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት በኩል ነው ለሕዝቡ የምታቀርቡት?
አቶ ጸጋዬ፡- እያሰብን ያለነው ፋብሪካው የራሱ የሆኑ ሱቆች በዋና ዋና ገበያ ማዕከላት እንዲኖሩት ነው፡፡ ቀጥታ ለተጠቃሚው የምናደርሰውም በዚሁ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በክልሎች ፋብሪካ ለመትከል የታሰበ ነገር አለ?
አቶ ጸጋዬ፡- ይኼኛውን አጠናክረን ከዓመት በኋላ ተጨማሪ ለመሥራት እናስባለን፡፡ ለማስፋፊያ ባገኘነው ቦታ ላይ ብስኩት የማምረት ዕቅድ አለን፡፡
ሪፖርተር፡- በኅብረተሰቡ በተለይም በእናቶችና በሕጻናት ላይ ለሚያጋጥመው የጤና እክል መንስዔ ከሆኑት አንዱ የተመጣጠነ ወይም በማዕድናትና በቫይታሚን የበለፀገ ምግብ አለማግኘት ነው፡፡ በመሆኑም መንግሥት ባወጣው የምግብ ፕሮግራም በተለይም ኅብረተሰቡ በብዛት የሚጠቀማቸው ስንዴ፣ ጨውና ዘይት በንጥረ ነገር እንዲበለፅጉ ወስኗል፡፡ ይህንን ተከትሎ ፋብሪካችሁ የሚያመርተውን የስንዴ ዱቄት በማዕድናትና በቫይታሚን ለማበልፀግ ዝግጅቱን መጨረሱን ሰሞኑን ይፋ አድርጋችኋል፡፡ ቢያብራሩልን?
አቶ ጸጋዬ፡- በአገር ውስጥ የስንዴ ዱቄትን በማዕድናትና በቫይታሚን አበልፅጎ በማቅረብ ፋብሪካችን የመጀመሪያው ይሆናል፡፡ ለዚህም ፋብሪካው ሲቋቋመ የተተከሉት ማሽኖች ከፍተኛ ሚና አላቸው፡፡ ማሽኖቹ ከአንድ የስንዴ ግብዓት 17 ዓይነት የዱቄት ውጤቶች ከማውጣታቸው ባለፈም ዱቄቱን በማዕድናትና በቫይታሚን ለማበልፀግ የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች አሏቸው፡፡ በመሆኑም በመንግሥትና የስንዴ ዱቄቱን የማበልፀጉን ሥራ የደገፉት ዓለማቀፍ ድርጅቶች ሥራውን ለመጀመር አስትኮን መርጠዋል፡፡ አስትኮ ያለበት ደረጃ ጥሩ ነው፡፡ ብዙ ምርቶችን ማውጣት የሚችል አቅም አለው፡፡ ከስዊዘርላንድ መጥተው የተገጠሙት የዱቄት ማምረቻ ማሽኖች አቅም አላቸው፡፡ ማሽኖቹን የተከለው የስዊዘርላንዱ ቡለር ካምፓኒም በየጊዜው የማሽኖቹን ጥገና ያደርግልናል፡፡ ማሽኖቹ ጥራት ስላላቸውና ፋብሪካውም የማምረት አቅሙ ከፍተኛ ስለሆነ የአሜሪካ የልማት ተራድዖ ድርጅት፣ አፍሪካን አሊያንስ ፎር ኢምፕሩቭድ ፉድ ፕሮስሲንግ፣ ቴክኖሰርቭ እንዲሁም ፓርትነርስ ኢን ፉድ ሶሊውሽንስ የተባሉት ድርጅቶች ፋብሪካችንን መርጠውት ላለፈው አንደ ዓመት ድጋፍ አድርገውልን የስንዴውን ዱቄት በማዕድናትና በቫይታሚን አበልፅጎ ለማቅረብ ዝግጅት አጠናቀናል፡፡ ይፋም አድርገናል፡፡ በቅርቡ ምርቱ ገበያ ላይ ይወጣል፡፡
ሪፖርተር፡- ረጂ ድርጅቶቹ ምንድን ነው ያደረጉላችሁ?
አቶ ጸጋዬ፡- ማይክሮ ኒውትረንቱን (ንጥረ ነገሩን) እነሱ ናቸው ያስመጡት፡፡ ከኬንያ፣ ከደቡብ አፍሪካ፣ ከአሜሪካ፣ ከአውሮፓ ባለሙያዎች በተለያየ ጊዜ እየመጡም ቴክኒካል ሥልጠና ሰጥተውናል፡፡ እንዴት መሠራት እንዳለበት አሳይተውናል፣ አሠልጥነውናል፡፡
ሪፖርተር፡- ከዚህ በኋላ ንጥረ ነገሩን እነሱ ያቀርቡላችኋል ወይስ ቀጥታ ከገበያ አወዳድራችሁ ትገዛላችሁ?
አቶ ጸጋዬ፡- ከዚህ በኋላ ንጥረ ነገሩን ገዝተን ነው የስንዴ ዱቄቱን የምናበለፅገው፡፡ በማዕድናትና በቫይታሚን የማበልፀጉ ሥራ በመንግሥትም ድጋፍ ያለው ስለሆነ ከውጭ በማስመጣቱ ረገድ ችግር ይገጥመናል ብለን አናስብም፡፡ አንዳንድ ምርምሮች ተደርገውና መስተካከል ያለባቸው አሠራሮች ተስተካክለው ወደፊት የምናመርታቸው ፓስታና መኮረኒ በንጥረ ነገር በበለፀገው የስንዴ ዱቄት ይሆናሉ፡፡
ሪፖርተር፡- ስንዴው በየትኞቹ ማዕድናትና ቫይታሚኖች ነው የሚበልፅገው?
አቶ ጸጋዬ፡- 12ቱም ዓይነት ቫይታሚኖች እንዲሁም ዚንክ፣ አይረንና ሌሎች ማዕድናትም ይኖረዋል፡፡ በኅብረተሰቡ ውስጥ የሰውነት መጫጫትን ያስቀራሉ፣ ጤናማና የተመጣጠነ ዕድገት እንዲኖር ያግዛሉ፡፡ የተባሉት ሁሉ ተካተዋል፡፡ በመንግሥት በኩል በኅብረተሰቡ የአመጋገብ ሥርዓት ውስጥ ወሳኝ ናቸው ብሎ የፈቀዳቸው ቫይታሚኖችና ማዕድናት ናቸው የሚገቡት፡፡
ሪፖርተር፡- የመንግሥት የፖሊሲ አቅጣጫ እንደመሆኑ ከመንግሥት ምን ትጠብቃላችሁ?
አቶ ጸጋዬ፡- ምርቱን በስፋት አምርተን ለማቅረብ መንግሥት በስንዴ አቅርቦቱ በኩል ሊያግዘን ይገባል፡፡ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ሚዲያውም ግንዛቤ በማስጨበጡ በኩል መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡ ዱቄቱን የምናበለፅገው በራሳችን መንገድ ተጨማሪ ጥቅም ለማግኘት ሳይሆን የመንግሥትን የሥርዓተ ምግብ ፕሮግራም ለማገዝ ነው፡፡ በመሆኑም በመንግሥትና በሚዲያው በኩል የምናገኘው እገዛ መጉላት አለበት፡፡ በሌላ በኩል ንጥረ ነገሮቹን ከውጭ ስናመጣ እንቅፋት እንዳይገጥመን ከወዲሁ ሊረዳን ይገባል፡፡ ንጥረ ነገሩን እስካሁን በዕርዳታ መጥቶ ነው ማበልፀግ የተጀመረው፡፡ ከዚህ በኋላ በራሳችን ሲሆን ከግብር እንዲሁም ተያያዥ የሆኑ ጉዳዮችን መንግሥት እንዲያይልን እንፈልጋለን፡፡
ሪፖርተር፡- በቫይታሚንና በማዕድናት የምታበለፅጉት የስንዴ ዱቄት ላይ የሚኖረው የዋጋ ልዩነት ቢነግሩን?
አቶ ጸጋዬ፡- ብዙ ወይም የተጋነነ የዋጋ ልዩነት አይኖርም፡፡ እንዳየነው ከሆነ ልዩነቱ በሳንቲም ደረጃ ነው የሚሆነው፡፡ እኛ የምንፈልገው ኅብረተሰቡ ምርቱን በደንብ እንዲያገኘው ነው፡፡ ከመንግሥት እገዛ የምንፈልገውም በማስተዋወቁ ላይ በስፋት እንዲሠራበት፣ የስንዴ አቅርቦቱን እንዲጨምር ነው፡፡ ዱቄት ከታክስ ነፃ ነው፡፡ ግን የስንዴ አቅርቦት ቀጥታ ከውጭ እንድንገዛ ቢፈቀድልን በማዕድናት የበለፀገ ምርት በስፋት ለኅብረተሰቡ ማቅረብ እንችላለን፡፡ አገር ውስጥ ያለው ስንዴ አገሪቷ ላላት ፍላጎት አይበቃም፡፡ በዛ ላይ ከጥራት ጋር የተያያዙ ችግሮች አሉ፡፡ ቆሻሻ መደባለቅ የሚገጥመን ችግር ነው፡፡ በአገራችን የነበረን ጥራቱን የጠበቀ ስንዴ ከእጃችን ወጥቷል፡፡ እሱን መመለስ ቢያቅተንም ያለንን ጥራቱን ጠብቀን መጠቀም አለብን፡፡ ከውጭ የሚመጣው ስንዴ ጥራቱ የተጠበቀ ነው፡፡ መንግሥት የዱቄት አምራቾች ስንዴ ቀጥታ ከውጭ እንዲያመጡ ቢፈቅድ በስንዴና በዱቄት በኩል እጥረት የሚባለው ነገር አይከሰትም ነበር፡፡ በግላችን ከአገር ውስጥ ሰፋፊ እርሻ ካላቸው እንገዛለን፡፡ ግን ዋጋው ውድ ነው፡፡ እጥረቱም አለ፡፡ መንግሥት የሚያቀርብልንን በጥቂት ቀናት ውስጥ ነው ፈጭተን የምንጨርሰው፡፡ ከውጭ የሚመጣው ስንዴ ሁሉን ወጭ ሸፍኖ እጃችን ሲገባ አገር ውስጥ ከምንገዛው የ100 ወይም የ200 ብር የዋጋ ልዩነት አለው፡፡
ሪፖርተር፡- ሠራተኞቻችሁ ድርጅቱ በአቅሙ ሙሉ ባለማምረቱና ለጊዜው የፓስታና መኮረኒ ምርቱን በማቆሙ ደስተኞች አይደሉም፡፡ ችግሩ ምንድን ነው? ምን ለማድረግ አስባችኋል?
አቶ ጸጋዬ፡- ፋብሪካችን የስንዴ ዱቄቱን በማዕድናትና በቫይታሚን ለማበልፀግ ሲያካሂድ በቆየው ሥራ ክፍተቶች ተፈጥረዋል፡፡ የዝግጅት ጊዜ ላይ ስለነበረን ነው፡፡ አሁን የምናመርተውን ዱቄት መጠን ጨምረን በቅርቡ በሰፊው እንገባበታለን፡፡ በቀን 1200 ኩንታል ዱቄት እናመርታለን፡፡ በቀጣዩ ዓመት ደግሞ ፓስታና መኮረኒውን በማዕድናት በልፅጎ ሙሉ ለሙሉ እንገባበታለን ብለን እናስባለን፡፡ ይህም ብዙ ማምረት እንችል ነበር ብሎ የሚቆጩትን 120 ሠራተኞቻችንን ጥያቄ ይመልሳል ብለን እናስባለን፡፡