Sunday, December 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

‹‹ላባጆ በነፃ››

ትኩስ ፅሁፎች

‹‹የበልግ ዝናብ ከሰማይ ቢጠፋ ከመሬት ፈልቆ መዝነቡ አልቀረም›› የሚለውን አነጋገር የሰማነው መጋቢት 29 ቀን 2007 ዓ.ም. ካዛንቺስ እንደራሴ (ራስ ሙሉጌታ ሰፈር) አካባቢ ድንገት የፈነዳው የውሃ ማስተላለፊያ ትቦ ያወናጨፈውን ውሃ ተከትሎ ነው፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች እንደተናገሩት የውሃ ክፍል ሠራተኞች ትቦውን አስተካክለው ከሄዱ በኋላ ክሥተቱ የተፈጠረው ወደ ስምንት ሰዓት ገደማ ነው፡፡ አጋጣሚውን የቤትና የንግድ አውቶሞቢሎች መኪናዎቻቸውን ለማፅዳት ተጠቅመውበታል፡፡ አንዳንዶቹም ‹‹ላባጆ በነፃ›› ብለዋል፡፡ (ፎቶ በሔኖክ ያሬድ)

**********

ለበጎ የመጣ ለክፉ ይተርፋል

አንድ ንጉሥ ወይን፣ በለስ፣ ሩማን፣ ትርንጎ የበቀሉበት የአትክልት ቦታ ነበረው ይህንን ቦታ ለባለ እኩል ሰጠው፡፡ ከጥቂት ቀን በኋላ ባለእኩሉ የሠራውን ለማየት ቢሄድ ያን አታክልት እሾህና አረም ውጦት አገኘ፡፡ በዚህ ንጉሡ ተናዶ ከመሬቱ ላይ ያለው ሁሉ እንዲነቀል ካዘዘ በኋላ በማኸሉ ሲያልፍ አንዲት ጽጌረዳ አገኘ፡፡ አበባዋን ቆርጦ ቢያሸት የአበባዋ ሽታ ቁጣውን አብርዶለት በርስዋ ምክንያት አታክልቱ ሁሉ ተረፉ፡፡

* * *

መሪና ተከታይ

አንድ ቀን የእባብ ጅራት ራስን እንዲህ አለው እስከ መቼ ድረስ ነው አንተ ፊት ፊት የምትቀድም? እኔም እኮ አንዳንድ ጊዜ ለመምራት እፈቅዳለሁ ራስም ይህንን ሰምቶ ጅራት ሊመራ እርሱ ሊከተል ፈቃዱ መሆኑን አስታወቀ ጅራትም እየመራ ወስዶ ከውኃው ውስጥ አገባው ከዚያ ሲወጡ ወስዶ ከእሳቱ ውስጥ ከተተው ከዚያ ሲወጡ ደግሞ ከሾኽ ውስጥ ጨመረው፡፡ ተከታይ ራስ መሪ ጅራት ፍጻሜው ጥፋት፡፡

* * *

ራስህን ቻል

ዶሮ ጫጩቶቹዋን ከእንቁላሉ እንደወጡ ከክንፎችዋ ውስጥ አግብታ ታሞቃቸዋለች፡፡ በፊት በፊታቸውም እየሄደች ጭራ ታበላቸዋለች፡፡ ጭልፊትም እንዳይወስዳቸው ወደማይገኙበት ቦታ ትወስዳቸዋለች፡፡ ካደጉ በኋላ ግን አንዱ የቀረባት እንደሆን ራስ ራሱን እየተከተከች ያውልህ አዛባ ቆፍረህ ብላ እያለች ታባርረዋለች፡፡

  • ካንዲት ኢትዮጵያዊት ተጻፈ ‹‹ምክርና ምሳሌ›› (1947)

********

የነፋስ ባህሪ

ነፋስ በቁሙ ረቂቅ ርጉዕ ህውክ ከሰማይ በታች በምድር ባራቱ ማዕዘን የመላ በገዛ ሀይሉ የሚታወክ የሚናወጥ የሚያረዝም የሚያሳድግ ሕይወትና ጤና የሚሰጥ፡፡ በዚህ በባህርየ ነፋስ ክፍለ ጊዜ ውስጥ ብር ብር እያለ (እየሮጠ) የሚሠራውን አያውቅም፡፡ ነፋሳዊ ባህሪ እየገፋፋ ማናቸውንም ነገር ያለፈቃድ ያሠራዋል፡፡

ነፋስ ከገለባ ፍሬን እንዲለይ ሕጻኑም ከክፉ መልካሙን የሚለይበት ወቅት ነው፡፡

አበው ‹‹ከአፋፍ ላይ ነፋስ ከአፍ ላይ እስትንፋስ›› እንዲሉ የሰው ልጅ በዘመኑ ሁሉ ሲተነፍስ ይኖራል ይህም በተፈጥሮ ባህርየ ነፋስ ለመኖሩ ምልክት ነው፡፡

ባህርየ ነፋስ ቢታመም ብርድ ብርድ ይለዋል፡፡ ብርድ መታኝ እንዲል ነፋስ የአየር እንቅስቃሴ ነፋስ ከየት እንደሚመጣ ወዴት እንደሚሄድ አይታወቅም፡፡ ነፋስ እንደአቅጣጫው በረከት ወይም እንቅፋት ሊሆን ይችላል፡፡ በከንዓን የምስራቅ ነፋስ መሬቱን ያደርቃል፡፡ ሃይለኛ ነው፡፡ የምዕራብ ነፋስ ወዛም ነው፡፡ የሰሜን ነፋስ ብርድ ያመጣል፡፡

  • መምህር አፈወርቅ ተክሌ ‹‹ቤተሰብና እንስሳት›› (2007)

**********

የፈላስፋው ወልደ ሕይወት ሐተታ

ስለቀሩት የሰዎች ትምህርታትና መጻሕፍትም ያለ ሐተታ ፈጥነን እናምናቸው ዘንድ አይገባንም፡፡ ከብዙ ሐተታ በኋላ ከልቡናችን ጋር የሚስማሙ መሆናቸውን አይተንና አውቀን እንቀበላቸዋለን እንጂ፡፡ ያም ልቡናችን በእርሱ እናምን ዘንድ እንደሚገባን ምስክር ይሆነናል፡፡ እውነት መሆኑን ልቡናችን የማያስረዳን ከሆነ ግን ማመን አይገባንም፡፡ ስለዚህ በችኮላ ሐሰት ነው እንበል፡፡ እውነት ወይም ሐሰት ቢሆን አናውቀውምና፡፡ ስለዚህ ‹‹ስለማናውቀው አናምነውም›› እንላለን እንጂ፡፡

‹‹ከእኛ በፊት የነበሩ ሰዎች እንዳመኑበት፣ በመጽሐፍ የተጻፈን ሆኑ ስለምን አታምንም?›› የሚሉኝ ቢኖሩ ‹‹ሐሰትን ይጽፉ ዘንድ በሚችሉ ሰዎች እጅ መጻሕፍት ስለሚጻፉ ነው›› ብዬ እመልስላቸዋለሁ፡፡ ዳግመኛም ‹‹አንተ ስለምን አታምንም?›› የሚሉኝ ሰዎች ቢኖሩ ‹‹እናንተስ ስለምን እንዳመናችሁ ንገሩኝ ብዬ እመልስላቸዋለሁ፡፡ ለማመን እንጂ ላለማመን ምክንያት አይፈለግምና፡፡ እናንተስ በተጻፈው ሁሉ ታምኑ ዘንድ ምን ምክንያት አገኛችሁ? የተጻፈው እውነት እንደሆነ ከሰዎች አፍ ሰምታችኋልና ከዚህ ብቻ በቀር ምክንያት የላችሁም፡፡ እናንተስ አታስተውሉምን? የተጻፈው እውነት ነው የሚላችሁ እውነት ቢሆን ወይም ሐሰት እነርሱም አላወቁትምና፡፡ እናንተ ከእነሱ ይህን እንደሰማችሁ እንዲሁም እነርሱም ከቀደምቶቻቸው ሰምተውታል እንጂ፡፡ እንዲሁም ሁላቸው በእግዚአብሔር ቃል ሳይሆን ሐሰት ይሆን ዘንድ በሚችል በሰው ቃል ያምናሉ፡፡ እንዲሁም እናንተ የልቡናችሁ ቃል ነው እንጂ እግዚአብሔር አልነገራችሁምና፡፡››

  • አለቃ ያሬድ ፈንታ ወልደ ዮሐንስ ‹‹ሐተታ ዘርዐ ያዕቆብ ወሐተታ ወልደ ሕይወት›› (2007)

**********

‹‹ሆሳዕና›› በምሥራቅ ‹‹ፋሲካ›› በምዕራብ

ያለፈው እሑድ መጋቢት 27 ቀን 2007 ዓ.ም. በዓለም ዙርያ ያሉ ክርስቲያኖች ሁለት በዓላትን አክብረዋል፡፡ የኢትዮጵያና የጁሊያን ቀን አቆጣጠር የሚከተሉ አገሮች ምሥራቅ አውሮፓዎች ኦርቶዶክሳውያን (ሩሲያ፣ ግሪክ፣ ኢየሩሳሌም፣ ሩማኒያ፣ ወዘተ) የሆሳዕና በዓልን ሲያከብሩ፣ የጎርጎሪዮሳዊውን ቀመር የሚከተሉ ምዕራቦችና ተከታዮቻቸው የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ በዓል ፋሲካን አክብረዋል፡፡

በኢትዮጵያ የሆሳዕና በዓል ከተከበረባቸው ቦታዎች አንዱ መንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ነው፡፡ ሕፃናት ‹‹ሆሳዕና በአርያም›› እያሉ ዘንባባ በመያዝ ዐውደ ምሕረቱን የዞሩትና ከፊታቸው አህያ ያስቀደሙት (ፎቶ) ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ውርንጭላ ላይ ሆኖ ኢየሩሳሌም የገባበትን ዕለት ለማስታወስ ነው፡፡ (ፎቶ በሔኖክ ያሬድ)

* * *

ሰው ብርቱ በማልማቱ

ያን ጊዜ በዚያን ዘመን

ልጅ ሆኜ ዓባይ ዓባይ ሲሉን

ቅርብ ነው ትንቢቱ ዛሬማ

ስናለማ ቀንና ጨለማ

ዳሩማ ያ ዘመን

ታገለ ታገለ አውድማም ቢሆን

ዳሩ ዳሩ ያ ጊዜ

ይጮህ ነበር ይቆረጥ ሲል ከደሞዜ

አባቴ የነገረኝ ትንቢቱ አይቀር

ቡልቻ ብዬ ዛሬ ዛሬ ላይ ደረስን ስንመረመር

ዓባይ ዓባይ ስንል በቅስና

በውስጡ ያለው ሀብት ባከና

ብለው ብለው ያን ጊዜ

ወርቅ ድንጋይ ከሰል ቢወጣ በጊዜ

መርምር ተመራመር ልጅ

ሲቆፈር ባይባክን እንኪለማ እስከ ደጅ

ወርቅ ይሁን ድንጋይ ከሰል

ነዳጅ ይሁን የጋዝ ቁልል

መልማቱ አይቀር እስከ ዛሬ

ለማ ለማ በርታ ያገሬ ትውልድ ዛሬ

ትንቢት አይቀር ወገን

መለስን አይቶ ገደለብን

መለስ መለስ ሲል ያኔ

ይጮህ ነበር ትናንትና በዘመኔ

ዳሩ ሰው ብርቱ

ቀመርህን አይተው ሲተርቱ

ተስፋዬ ደማሙ፣ መጋቢት 2007

- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች