Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርየቅማንት ብሔረሰብ የማንነትና የአስተዳደር ጥያቄ – ሔግል በአማራ ክልል

የቅማንት ብሔረሰብ የማንነትና የአስተዳደር ጥያቄ – ሔግል በአማራ ክልል

ቀን:

በውብሸት ሙላት

መጋቢት ወር 2007 ዓ.ም. የመጀመሪያ ሳምንት ለቅማንት ብሔረሰብ አንድ የምሥራች ዜና ተበሰረ፡፡ በይፋ ብሔረሰብ እንደሆኑና ለዓመታት የታገሉለትን የራሳቸውን አስተዳደር የመመሥረት ጥያቄ አዎንታዊ መልስ አገኘ፡፡ በእርግጥ ይገባናል ያሏቸውን ቀበሌዎች በሙሉ ባያገኙምና እነዚህ ቀበሌዎች በተራቸው በአንድነት ወረዳ ይሁኑ ዞን ወይንም ሌላ  ባይታወቅም፡፡

ይህ ጽሑፍ የቅማንትን ብሔረሰብ የማንነት ይታወቅልኝ ጥያቄና መልሱን ከሕገ መንግሥቱ አንፃር ይመረምራል፡፡ በተለይም በፌደራሉና በአማራ ክልል አንቀጽ 39 ላይ ከተገለጹት መሥፈርቶች አንፃር ያብራራል፡፡ መሥፈርቶቹ መግባቢያ ቋንቋ፣ ተመሳሳይ ባህልና ልማድ፣ የጋራ ህልውና አለን ብሎ ማመን፣ ተያያዥ በሆነ መልክዓ ምድር መኖርና የሥነ ልቦና አንድነት ናቸው፡፡ የስልጤ ብሔረሰብን በተመለከተ ከዓመታት በፊት ከተሰጠው ውሳኔ ጋርም ያነፃፅራል፡፡ በመጨረሻም ለብሔረሰብነት ወይም ብሔርነት ዕውቅና ማግኘት የተለየ ቋንቋና ባህል መኖር አስፈላጊ መሆን ወይንም አለመሆኑንና ተያያዥነት ባላቸው አካባቢዎች የመኖርን የግዴታ መሥፈርትነትን ይፈትሻል፡፡  

- Advertisement -

በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት መሠረት በዋነኛነት የራስን ዕድል በራስ መወሰን የሚችሉት ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ናቸው ካልን እስካሁን ዕውቅና ያላገኙት ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ለመሆን ወይንም ዕውቅና ለማግኘት ጥረት ማደረጋቸው አይቀሬ ሒደት ይሆናል፡፡ ይህ ወደ ብሔርነት፣ ብሔረሰብነት ወይም ሕዝብነት የሚደረግን ጉዞ ነው የማንነት ጥያቄ በማለት በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የምናየው፡፡ ከአንቀጽ 39 በረከት ተቋዳሽ ለመሆን፣ ለሉዓላዊ የሥልጣን ባልተቤትነትም ዕውቅና የመጀመሪያው ዕርምጃ ነው፡፡

ጥቂት ነጥቦች ስለቅማንት ብሔረሰብና የብሔረሰብነት መለያዎች

አንባቢ ሊረዳው እንደሚችለው በፌደራሉ ሕገ መንግሥት፣ ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ የሚሉት ቃላት ግልጽ የሆነ ልዩነት ባይኖራቸውም፣ ከዚህ ጽሑፍ ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያለው የአማራ ክልል ሕገ መንግሥትና ሌሎች የክልሉ ሕጎች ግን አማራን ብሔር፣ በክልሉ ውስጥ የሚገኙትን አዊ፣ ኽምራ፣ አርጎባና ኦሮሞን ደግሞ ብሔረሰቦች በማለት ስለሚጠራቸው፣ እኔም ቅማንትን ጥያቄ ማቅረባቸውን ስገልጽ ማኅበረሰብ፣ ከዚያ ውጪ ግን ብሔረሰብ በማለት፣ ወጥ በሆነ መንገድ የተጠቀምኩት ከዚሁ አንፃር ነው፡፡ የሦስቱን አንድነትና ልዩነት መጻፍ የዚህ መጣጥፍ ዓላማ ስላልሆነ በሌላ ጽሑፍ (መጽሐፍ) ስለምመለስበት ለአሁኑ ትቸዋለሁ፡፡

ስለቅማንት ሲነሳ አንድ የሚገርም ክስተትን ማንሳት ተገቢ ነው፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ በ1987 ዓ.ም. የቤት ቆጠራ ወቅት በኢትዮጵያ 84 ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ነበሩ፡፡ በ1999 ዓ.ም. ደግሞ 85 ሲሆኑ በ1987 ዓ.ም. ከነበሩት አምስቱ ይቀሩና ሌሎች ስድስት ተጨምረዋል፡፡ የቅማንት ሕዝብ ብዛትም በ1987 ዓ.ም. 172,327 ሲሆን፣ በ1999 ዓ.ም. የሕዝብና ቤት ቆጠራ ሪፖርቱ ላይ ግን አልተካተተም፡፡ የሚገርመው በአሥራ ሁለት ዓመታት ልዩነት አምስት ብሔረሰቦች ጠፍተው ስድስት መጨመራቸው ሲሆን፣ በተለይ የቅማንት ደግሞ ይኼን ያህል ቁጥር ኖሮት አለመካተቱ የበለጠ ይገርማል፡፡ በአማራ ክልል ከሚኖሩት ብሔረሰቦች ወይጦና ቅማንት በዚህ ሪፖርት ውስጥ አልተካተቱም፡፡ የቅማንት አለመካተት የማንነት ይታወቅልኝና በራስ የመተዳደር ጥያቄውን አፋጥኖታል፡፡ ለምን ቢሉ? አማራ ተደርጎ ተቆጠረም አልተቆጠረም የቅማንት ሕዝብ መኖሩ ሀቅ ሆኖ ሳለ፣ በሕዝብና ቤት ቆጠራ ወቅት የተሳሳተ ማንነት በመስጠት አማራ ናችሁ መባላቸው ህልውናቸውን መካድ፣ እያሉ እንደሌሉ ማድረግ ከጭቆና ተለይቶ የሚታይ ስላልሆነ ነው፡፡

ሌላው የሚደንቀው የሽግግር መንግሥቱ ዕውቅና የሰጠው ለ63 ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ብቻ መሆኑና እስካሁን ድረስ በፌደሬሽን ምክር ቤት ተወካይ ያላቸው እየተሻሻለና እያደገ መጥቶ እንኳን፣ ገና ሰማንያ አለመሙላቱ ነው፡፡ በመሆኑም የሕዝብና ቤት ቆጠራ ሪፖርትን እንኳን ብንወስድ 85 ብሔረሰቦች አሉ፡፡ የፌደሬሽን ምክር ቤት ግን እነዚህን ሁሉ ገና አላወቃቸውም፡፡ ወይም እንደ ብሔረሰብ አልቆጠራቸውም፡፡ በእርግጥ ያሉ በሕግ ግን የሌሉ ሆነዋል፡፡ በተለይ በ1987 ዓ.ም. ቆጠራ ላይ የተካተቱትንና ኋላ የተዘለሉትን፣ አሊያም ብሔረሰቡ ራሱ ብሔረሰብነቱን የተወውን ብንደምረው 90 ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ እዚህ ላይ የሕዝብና ቤት ቆጠራ ለአንዳንድ ፖለቲካዊ ፋይዳዎች እኛም አገር እየዋለ ይሆን እንዴ? ብለን መጠየቃችን አይቀሬ ነው፡፡

የቆጠራ ሪፖርቱ (ውጤቱ) የማንነት ወይም የብሔር ፖለቲካ ላይ ተፅዕኖ ስለሚኖረው በብዙ አገሮች ሆን ተብሎ ወደሚፈልጉት ድምዳሜ ላይ እንዲደርስ ይደረግ እንደነበር ታሪክ ምስክር ነው፡፡ ቀደም ሲል አሜሪካኖች ዘርን፣ ኦቶማን ቱርኮች፣ ሩሲያና ፖላንድ ብሔርን በፈለጉት መጠን እንዲያሳያቸው ተደርጎ ይከናወን ነበር፡፡ ሃይማኖትንም በተመለከተ እንዲሁ ይደረግ ነበር፡፡ መብለጥ የለበትም የሚሉትን ሀቁ ምንም ይሁን ምን፣ ሪፖርት ላይ በሚገለጽ ቁጥር እንዲያንስ አድርገውታል፡፡ የእኛን አገር ጉዳይ ለአሁኑ ትቼዋለሁ አንባቢ ራሱ እንዲመልሰው፡፡

በሪፖርቱ መሠረት ቢያንስ ከአማራ ክልል ሁለት፣ ከኦሮሚያም ሁለት ብሔረሰቦች ሲቀነሱ፣ ደቡብ ክልል ላይ ደግሞ ተጨምረዋል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ድርጊቶች የተፈጸሙት በድንገት፣ በቸልተኝነት ወይም ሆን ተብሎ ይሁንም አይሁንም ያልታሰበ ችግር ሊያስከትሉ እንደሚችሉ መታወቅ አለበት፡፡ የብሔረሰቦችንም ግንኙነት በእጅጉ ያሻክራል፡፡ ለዚህ ደግሞ የቅማንት ጉዳይ ዋቢያችን ነው፡፡

ወደ ጥንተ-ነገሬ ልመለስና ቅማንት የራሱ የሆነ የጋራ የትውልድ አመጣጥ አፈ ታሪክ ያለው በጭልጋ፣ በላይ አርማጨሆና በጎንደር ከተማ፣ ወጥ ባይሆንም፣ ተያያዥነት ባለው አካባቢና በሌሎች የሰሜን ጎንደር ወረዳዎች የሚኖር፣ የራሱ የሆነ ባህልና ልማዳዊ ሥርዓቶችና በሰፊው የሚግባቡበት የተለየም ቋንቋ ቢሆን የነበረው ብሔረሰብ ነበር፡፡ በተራዘመው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነታቸው እየከሰመና እየተዋጠ ይሂድ እንጂ የራሳቸው ሃይማኖትም ነበራቸው፡፡ የተለየ የዘር ግንድ እንዳላቸው፣ ትክክልም ይሁን ስህተት ማረጋገጥ ባይቻልምና ባያስፈልግም፣ ክብረ ነገሥትና የአለቃ ታዬ፣ የኢትዮጵያ ታሪክ፣ የሚሉትን መጽሐፍት ይመለከቷል፡፡ አንድ የዘር ግንድ አለን ብሎ ማሰብና የጋራ ጠላት እንዳላቸው መቁጠር ለጋራ የሥነ ልቦና መፈጠርና የተለየ ማንነትን ለማሳደግ ወሳኝ ጉዳዮች እንደሆኑ የዚህ ዘርፍ ማዕምር የሆኑት እነ ዎከር ኮኖር ያስረዳሉ፡፡ የወል ሥነ ልቦና ያለው ማኅበረሰብ ነው ብሔር ወይም ብሔረሰብ ሊሆን የሚችለው፡፡ የብሔሩን ቋንቋ ባያውቅም፣ ባህሉን ቢረሳውም፣ ከብሔሩ ርቆ የትም ቢኖርም የብሔር ተዓማኒነቱን ግን መቼም ላይተው ይችላል፡፡ ቅማንትኛ ቋንቋን የማይችሉ ይልቁንም በአማርኛ አፍ የፈቱ፣ ሕገ ልቦና ይባል የነበረው ሃይማኖት ትተው ክርስትናና እስልምናን የተቀበሉ፣ ባህላቸውንም የማያውቁ ሆነው የቅማንት ብሔርተኞች ግን ሞልተዋል፡፡ ለዚህም ጭምር ነው የሕገ መንግሥታችን አንቀጽ 39(5) ላይ የተቀመጡት መሥፈርቶች ፍተሻ ያስፈልጋቸዋል የሚያሰኘው፡፡ ሕጉ ሌላ፣ ነባራዊ ሁኔታው ሌላ፣ ‹‹ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ›› እንዲሉ!

የቅማንትን ባህልና ልማዶችን በተመለከተ አንድ ጥናት ከሌሎች የተለየ ባህል መኖርን እንደ አንድ ሕገ መንግሥታዊ ቅድመ ሁኔታ የሚያስመስል ሐተታ ያቀርብና ቅማንቶች ከኦርቶዶክስና ከእስምልና እምነት ተከታዮች በተለየ መልኩ ከተራራና ዛፍ ሥር የሚከናወን ሃይማኖታዊ ሥርዓታቸውን ስለሚፈጽሙ፣ እንዲሁም የበዓል ቀናቸው ቅዳሜ ስለሆነ ባህላቸው ልዩ ነው ይላል፡፡ በመሆኑም ሰፋ ያለ የጋራ ፀባይነት ያለው ባህል ወይም ተመሳሳይ ልምዶች አላቸው በማለት ለመደምደም ይሞክራል፡፡ ጥናት አድራጊው አንድ ወይም በጣት የሚቆጠሩ የአምልኮ ቦታዎችን እንደ ምሳሌ በመውሰድ፣ ቃለ መጠይቅ ካደረገላቸው 226 ሰዎች ውስጥ ሦስት የሕገ ልቦና (የቅማንቶች ነባር ሃይማኖት)፣ 218 የኦርቶዶክስ፣ ሦስት የፕሮቴስታንት አንድ ደግሞ የእስልምና እምነት ተከታይ መሆናቸውን ገልጾአል፡፡ እነዚህ ሰዎች የሚያደርጓትን አንዲት ሃይማኖታዊ ሥርዓት ብቻ መዝዞ በማውጣት የተለየና ሰፋ ያለ የጋራ ፀባይ የሚያንፀባርቅ ባህል አላቸው ብሎ ከመደምደም ይልቅ  የላቸውም ቢል ተዓማኒነት ነበረው፡፡

ነገሩ ባህልና ልማድ ምን ማለት ናቸው? ሕገ መንግሥቱስ አንድ ብሔር ከሌላው የተለየ ባህልና ልማድ ያስፈልጋል ብሏልን? መለያየቱና ተመሳሳይነቱስ ከላይ እንደቀረበው አንዲት ዘሃ ብቻ በመምዘዝ ሊጠቃለል ይችላልን? ልዩ መሆን አለበት ቢባል እንኳን መለየት ያለባቸው ከየትኛው ብሔር ነው? አብሮ ከሚኖረው? በሌላ ቦታ ከሚኖረው? ባህልህ ከሌላ ብሔር ጋር ስለተመሳሰለ ብሔር አይደለህም ማለትስ ይቻላልን? ይህ ዓይነቱ አካሄድ የማንነት ይታወቅልኝን ጥያቄ ማቅለልና ትርጉም አልባ ማድረግ ይሆናል፡፡ የተለየ ባህልና ልማድን ሕገ መንግሥቱ በግልጽ እንደ ቅድመ ሁኔታ አይጠይቅም፡፡ ይልቁንስ የማንነት ጥያቄ አቅራቢው ሰፋ ባለሁኔታ የሚጋራቸው ባህሎችና ልማዶች ያሉት መሆኑን እንጂ! አመጋገባቸው፣ አለባበሳቸው፣ ሃይማኖታቸው፣ አስተራረሳቸው፣ ወዘተ ከሌላ ጋር ስለተመሳሰለ ብሔር አይደሉም፣ ስለማይመሳሰል ብሔር ናቸው ማለት የዘመናዊነትን፣ የሉላዊነትን (የግሎባላይዜሽን)፣ የቴክኖሎጂና የመሳሰሉትን ተፅዕኖ ከግምት ውጪ በማድረግ አለመለወጥን፣ ከሌሎች ጋር አለመቀላቀልና አለመዋሀድን በስህተት ታሳቢ ማድረግ ነው፡፡

ቅማንቶች የራሳቸው ቋንቋ አላቸው ከማለት ይልቅ ነበራቸው ማለት ይቀላል፡፡ አሁን ያለው የተናጋሪው ብዛት በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ነገር ግን ቢያንስ በአማርኛ ይግባባሉ፡፡ ዋናው ልዩ የሚያደርጋቸውና ከፊት ለፊት ያለው መለያቸው፣ ብሎም መመለስ ያለበት የጋራ ማንነታቸውና የሥነ ልቦና አንድነታቸው ነው፡፡ ይህንን የጋራ ሥነ ልቦናና የወል ማንነት ለመፍጠር ደግሞ ከአንድ የጋራ የዘር ግንድ አለን ብለው ማመናቸው ነው ወሳኙ ብለናል፡፡ እናም ራሳቸውን ‹‹ቅማንት ነን›› ብለው ካሰቡ ሌላ ሊሆኑ አይችሉም፣ ‹‹ሌላ ናችሁ›› ማለትም አይቻልም፣ ቅማንት ስለመሆናችሁ ‹‹አናውቅም ወይም አማራ እንጂ ቅማንት አይደላችሁም›› ማለት ከሞራል አንፃርም ስህተት ነው፡፡

ቻርለስ ቴለር የተባለው የዘርፉ ምሁር አንድ ማኅበረሰብ አማናዊ ማንነቴ ‹‹ይኼ ነው›› ሲል ዕውቅና መንፈግ ወይም ያልሆነውንና ነኝ ላላለው ሌላ የማንነት ዕውቅና መስጠት ያለውን የሞራል ዳፋ አሳምሮ አቅርቦታል፡፡ ሲበዛም የጭቆና አንዱ ፈርጁ ነው ይለናል፡፡ ለዚህ ነው የሥነ ልቦናው መሥፈርት ወሳኝ የሚሆነው፡፡

ጉዳዩ እንዲህ ከሆነ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39(5) እና ሌሎች ሕጎች ላይ የተቀመጡትን አንድን ማኅበረሰብ ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ የሚያሰኙ መሥፈርቶቹ ላይ ጥያቄ ከማንሳታችንና ለቅማንት ብሔረሰብ ከዚህ አንፃር እንዴት መልስ እንደተሰጠ ከማየታችን በፊት፣ የማንነትን ፖለቲካዊና ፍልስፍናዊ መሠረቶች ጨረፍ አድርገን እንይ፡፡ ለሕግ መሠረቱ ብዙ ጊዜ ፖለቲካና ፍልስፍና ስለሆኑ፡፡

የማንነት ፖለቲካዊና ፍልስፍናዊ መሠረቶች

የአንድ ማኅበረሰብ የማንነት ጥያቄ የሚያያዘው ዕውቅና ከማግኘት፣ ከአማናዊነት (Authenticity)፣ በልዩነት ከመታወቅና እኩል ክብር ከመቀዳጀት ጋር ነው፡፡ አማናዊነት የሚያመለክተው አንድ ማኅበረሰብ ማንንም ለመምሰል ሳይጥር እውነተኛው ራሱን መሆንን ነው፡፡ የራሱን አመጋገብ፣ አለባበስ፣ አጠቃላይ አኗኗር ዘዬ ተከትሎ መኖር ነው፡፡ ‹‹የሠለጠነ›› ለመባል ሌላ ብሔርን መምሰል፣ ወዘተ አማናዊ የሆነ ባህርይ አይደለም፡፡ ማስመሰል ነው፡፡ በመሆኑም የማንነት ጥያቄ አማናዊ የመሆን ግስጋሴ ነው፡፡ የስልጤ ማኅበረሰብ የማንነት ይታወቅልኝ ጥያቄ ሲያነሳ ያደረገው አማናዊ ማንነቴ ስልጤ እንጂ፣ ጉራጌ አይደለም ነበር ያለው፡፡ አማናዊ ማንነቱን የሚያውቀው ደግሞ ራሱ ቡድኑ ወይም ብሔሩ (የቅማንት ብሔረሰብ ራሱ) እንጂ ሌላ አይሆንም ማለት ነው፡፡

የዕውቅናን ነገር ጀርመናዊው ፈላስፋ ሔግል በአለቃና በምንዝር (ባርያ) ተምሳሌት የጻፈው የበለጠ ይገልጸዋል፡፡ ከላይ ከቀረበው ሃቲት ለየት ባለ መልኩ፡፡ እንዲህ ነበር ያለው፡፡ አንድ ሰው ራሱ ማን እንደሆነ የሚባንነውና የሚያውቀው ሌላ ሰው ያንን ማንነቱን ሲነግረው ነው ይላል፡፡ አለቃው ምንዝሩን ‹‹ምንዝር›› ሲለው ነው ምንዝርነቱን የሚያውቀው፡፡ ምንዝሩም አለቃውን በአለቃነት ዕውቅና ሲሰጠው ነው ‹‹አለቃ ነኝ›› የሚለው ነው ሔግል ያለው፡፡ ልክ እንደዚሁ ሁሉ አዎንታዊ በሆነ መልኩ አንድ ብሔር፣ ብሔርነቱን ሌላው ዕውቅና ሲቸረው ነው ማንነቱ የሚታወቀው፡፡ ለዚያም ነው የማንነት ጥያቄ ሲቀርብ በውስጠ ታዋቂነት ያለው ፍለጎት ‹‹እኛ›› መሆናችንን ዕወቁልን የሚል መልዕክት ያለው የሚሆነው፡፡ ሌሎችም ለአማናዊው የብሔሩ ማንነት ዕውቅና መስጠት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህንን ማንነትህን ‹‹አላውቅም›› ማለት ወደ ግጭትና ጥላቻ ከመግፋት ውጪ አያፋቅርም፣ አያዋድድም፡፡

የጉራጌ ልሂቃን ረዘም ላለ ጊዜ ‹‹ስልጤ ጉራጌ እንጂ የተለየ ስልጤ የሚባል አማናዊ ማንነት የለውም፤›› ማለታቸው በሁለቱ ወገኖች መካከል ቅሬታ ከመፍጠር በዘለለ ቢያንስ በወቅቱ አላዋደዳቸውም፡፡ በተለይ ከቡታጅራው ኮንፈረንስ በኋላ የፌደሬሽን ምክር ቤት እስከሚወስን ድረስ ግንኙነታቸው የበለጠ እየሻከረ መሄዱ መነሻው ምንም ሳይሆን፣ ‹‹በስልጤነታችን ዕወቁን፣ አናውቃችሁም›› የሚለው እሰጥ አገባ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ከዕውቅና ማግኘት ላይ የሚመነጨው ሌላው ፀጋ ደግሞ እኩል ክብር መቀዳጀት ነው፡፡ ሌላውን መስሎ መኖሩን ትቶ፣ ራሱን ሆኖና እኩል የብሔርነት ክብር አግኝቶ፣ ብሔርነት ከሚያስገኛቸው ትሩፋቶች ተቋዳሽ መሆንን ያስችላል፡፡ ራስን ማስተዳደር፣ በፍትሐዊነት በየተቋማቱ መወከል፣ ወዘተ ቅማንትም ከአሁን በኋላ ቢያንስ በፌደሬሽን ምክር ቤት፣ በክልል ምክር ቤትና በሌሎች ተቋማት በፍትሐዊነት የመወከል መብትን ያገኛሉ፡፡

ልዩ መሆንም አንድ የማኅበረሰብ አባላት እንደ ቡድን እኛ ራሳችን እንደምናስበው  እንጂ እናንተ እንደምትስሉን አይደለንም፡፡ እናንተ ለእኛ ካላችሁ አመለካከት የተለየ ማንነት ነው ያለን፡፡ ልዩ ነን፡፡ ማንነታችንን እናንተ ሳትሆኑ እኛው ራሳችን እናውቀዋለን፡፡ ይልቁንስ እኛ የምንለውን ተቀበሉን የሚል መልዕክት ያዘለ ነው፡፡ ይህ ሥነ ልቦናዊ ጉዳይ ነው፡፡ ይህንን መካድ ነው የበለጠ የሚከፋው፡፡

ሔግል በአለቃና በምንዝር ምይይጡ (Master-Slave Discourse) እንዳስቀመጠው የሚመስል፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ያለው አባተ የቅማንት ሕዝብን በተመለከተ በኢቢሲ ሲናገሩ እንደሰማናቸው፣ ‹‹የቅማንት ብሔረሰብ በተለይ በጭልጋና በላይ አርማጭሆ አካባቢ የሚገኙ ሲሆን፣ እነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች ራሳቸውን ቅማንት ነን ይላሉ፡፡ ሌሎቹም ቅማንት ናችሁ ይሉዋቸዋል፡፡ በእርግጥ የቅማንትነይ ቋንቋን የሚናገሩት ሰዎች ቁጥር አናሳ ቢሆንም›› የሚል መልዕክት የያዘ ነበር (ቀጥታ ጥቅስ አይደለም!)፡፡ በመሆኑም እንደ ሔግል አባባል ሁሉ በአካባቢው የሚኖረው አማራ በቅማንትነታቸው ያውቃቸዋል፡፡ ቅማንቶችም የአካባቢውን ሕዝብ ሌላ ስለመሆናቸው (ለአማራነታቸው) ዕውቅና ሰጥቷል ማለት ነው፡፡ ስለሆነም የቅማንት ሕዝብ አለ ማለት የሚል ድምዳሜ ነው ከአቶ ያለው ንግግር የምንረዳው፡፡ አንዱ ሌላውን በተለየ አቋሙ (Status) ዕውቅና መቸሩ ለራሱም የተለየ ማንነትና ለሌላውም ልዩ መሆን ማረጋገጫ ነው ማለት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ዓይነቱ ውሳኔና አረዳድ ከሕገ መንግሥቱ ጋር አብሮ ይሄዳልን? የሚለው አጠያያቂ ቢሆንም፡፡

ማንነትን ማን ይወስን? የቅማንትንስ ማን ወሰነ?

የማንነት ጥያቄ ለማን ነው የሚቀርበው? ወይም በሌላ አገላለጽ የማንነትን ጥያቄ የመጨረሻ ወሳኙ ራሱ የማኅበረሰቡ አባላት ቢሆኑም ጥያቄው መቅረብ ያለበት ለፌደሬሽን ምክር ቤት ወይስ ለክልል ነው? የሚል ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ግልጽ የሆነ መልስ ስለሌለው የፌደሬሽን ምክር ቤት የስልጤን ጉዳይ ባየበት ወቅት፣ የማንነት ጥያቄ ዙሮ ዙሮ ዋና ዓላማው ራስን ማስተዳደር ስለሆነ ይህን ጥያቄ የመፍታት ሥልጣን በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 52(2)(ሀ) መሠረት የክልል ምክር ቤት ነው በማለት ወስኗል፡፡

የማንነት ይታወቅልኝ ጥያቄ ብሔርን መሠረት ያደረገ አስተዳደራዊ ተቋማት ከመመሥረት (ቀበሌ፣ ወረዳ፣ ዞን) እንዲሁም ክልል ከማቋቋምም ይቀድማል፡፡ እነዚህን ጉዳዮች የመወሰን ሥልጣን የክልል ከሆነ የማንነትማ ወደ ፌደራል ተቋማት በቀጥታ ሊሄድ አይችልም፡፡ እነዚህ የአስተዳደር እርከኖችን የማቋቋምም ያለቋቋምም የክልሎች ሥልጣን ነው፡፡ ይሁን እንጂ በክልሉ ምክር ውሳኔ ወይም በሚሰጣቸው ምላሾች ቅር የተሰኘ ወገን የመጨረሻ ውሳኔ ለማግኘት ወደ ፌደሬሽን ምክር ቤት ሊሄድ ይችላል፡፡ ይህንን በስልጤ ጉዳይ ከተሰጠው ውሳኔም፣ ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 62(3) ላይም መረዳት ይቻላል፡፡

እዚህ ላይ የማይታለፍ አንድ ጥያቄ አለና እሱን እናንሳ፡፡ የፌደሬሽን ምክር ቤት የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጣል ሲባል ምን ማለት ነው? ከፊት ለፊቱ ሲታይ በእርግጥ በይግባኝም ይሁን በአቤቱታ ወደ ሌላ አካል ሊቀርብ አይችልም ማለት ነው፡፡ በዚህ ተቋም ውሳኔ ከተሰጠ አከተመ፣ የመጨረሻ ነው እንደ ማለት ነው፡፡

ይሁን እንጂ ትርጉሙ በዚህ ብቻ የሚቆም አይደለም፡፡ ምክንያቱም በክልል ምክር ቤት አንድን ማኅበረሰብ፣ ብሔር ወይንም ብሔረሰብ ለመሆን ማሟላት ያለባችሁን በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39(5) ላይ ከተዘረዘሩት አምስት መሥፈርቶች የተወሰኑትን አላሟላችሁምና ሕዝበ ውሳኔ ማድረግ አያስፈልግም ተባሉ እንበል፡፡ በውሳኔው ቅር በመሰኘት ይግባኛቸውን ወደ ፌደሬሽን ምክር ቤት ይዘው መጡ፡፡ በዚህ ጊዜ የፌደሬሽን ምክር ቤቱ ሁለት የውሳኔ አማራጮች አሉት፡፡ የክልል ምክር ቤቱን ውሳኔ ሊሽረውም ሊያፀናውም ይችላል፡፡ ከሻረው ሕዝበ ውሳኔ ሊካሄድ ይችላል፡፡ አስቸጋሪው ጉዳይ የሚመጣው ሲያፀናው ነው፡፡ ማለትም ‹‹ብሔር ወይም ብሔረሰብ መሆን አትችሉም›› ሲባሉ ነው፡፡ ‹ነኝ› በሚለው ማንነቱ ዕውቅና አያገኝምና! የመንጃ ማኅበረሰብ የማንነት ጥያቄና የደቡብ ክልል የብሔረሰቦች ምክር ቤትና የፌደሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ በዚህ ጉዳይ ላይ ተጠቃሽ ነው፡፡ የቅማንት ብሔረሰብ ግን ምንም እንኳን አጭር የማይባል ጊዜ ቢፈጅበትም፣ ሕዝበ ውሳኔ ማካሄድ ሳያስፈልገው ለብሔረሰቡ ህልውና ዕውቅና በመስጠት አስተዳደራዊ ተቋማት መመሥረት ላይ ብቻ ትኩረት ማድረግን ምክር ቤቱ የመረጠ ይመስላል፡፡ በመሆኑም የዕውቅናው ጥያቄ ይግባኝ የሚያስብል አይደለም፡፡ አልተካደምና! በነገራችን ላይ አቶ ያለው አባተ ስለ ቅማንት የተናገሩትን ወስደን ለመንጃ ማኅበረሰብ ብናውለው ኖሮ፣ መንጃዎች ራሳቸውን መንጃ የሚሉ ሲሆን፣ ካፋና ሸካም በመንጃነታቸው (በእርግጥ የጋራ የሆነ አንድ የዘር ግንድ ቢኖራቸውም!) ስለሚያውቋቸው ውሳኔው በተቃራኒው ይሆን ነበር፡፡ አንቀጽ 39(5) ላይ ከተዘረዘሩት መሠረቶች አኳያ ግን ብሔር ወይም ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ መሆን አልቻሉም፡፡

ሌላው ጉዳይ የጥያቄ አቅራቢው ማንነት ነው፡፡ ‹ማንነቴ ይታወቅልኝ› በማለት መጠየቅ የሚችለው ራሱ ማኅበረሰቡ ነው፡፡ አስቸጋሪው ማኅበረሰቡ ወይም ሕዝቡ የሚባለው ማን ነው? መቼም ሁሉም ሕዝብ በአንድነት ተሰባስቦ ይጠይቃል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ስለሆነም የዚያ ማኅበረሰብ ልሂቃን ሊያቀርቡ ይችላሉ፡፡ ለአብነት የቅማንትን የማንነት ይታወቅልኝ ጥያቄ 120 አባላት ያሉት የኮሚቴ አባላት ናቸው ወደተለያዩ ተቋማት ያደረሱት፡፡ ዋናው ነገር ማኅበረሰቡን ይወክላሉን? የሚለው ነው፡፡ ይህንን ማረጋገጥ ደግሞ ከባድ ነው፡፡ ማለትም የአብዛኛው ፍላጎት ስለመሆኑ የማስረዳት ሸክሙ የማን ነው? ጥያቄው የቀረበለት አካል ራሱ በተለያዩ ሥልቶች ማስጠናት አለበት ወይስ ጥያቄ ያቀረቡት ሰዎች? የስልጤ ጉዳይ ሲወሰን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያምን ጨምሮ ይህንኑ ጥያቄ አንስተውት ነበር፡፡

ለዚህ ጥያቄ መልስ የሚሆን በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ግልጽ ድንጋጌ የለም፡፡ ይሁን እንጂ ከላይ በተገለጸው ጉዳይ ማጠቃለያ ‹‹…ጥያቄውን ማንም ሊያቀርብ እንደሚችል ሆኖም ጥያቄው ትክክለኛ የሕዝብ ጥያቄ መሆን አለመሆኑ በሒደት በሚሠሩ ሥራዎች የሚወሰኑ፣ የሚነጥሩና የሚለዩ መሆናቸውን…. መረጋገጥ አለበት›› በማለት ተደምድሟል፡፡ በውሳኔው ሐተታ ላይ ግለሰቦችም፣ በቡድን የተደራጁ ሰዎችም፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሊያቀርቡ እንደሚችሉ የተገለጸ ሲሆን፣ እነዚህ አካላት ሊያቀርቡ አይችሉም የሚል ተቃውሞም አልተነሳም፡፡ ይሁን እንጂ የሕዝብ እውነተኛ ጥያቄ ስለመሆኑ ጥያቄው የቀረበለት ምክር ቤት ማጣሪያ ሊያደርግ እንደሚችልም መገንዘብ ይቻላል፡፡

ሌላው የሕዝብ ጥያቄ ስለመሆኑ ወይም አለመሆኑ በሚመለከት ከስልጤ ጉዳይ መገንዘብ የሚቻለው የማስረዳት ሸክሙም ወደ መንግሥት እንደዞረ ሲሆን፣ የፌደሬሽን ምክር ቤትን ለማጠናከር በወጣው በአዋጅ ቁጥር 251/1993 አንቀጽ 21 መሠረት ግን ከማኅበረሰቡ አባላት አምስት በመቶ የሚሆነው ጥያቄውን መደገፋቸውን ለማሳየት ስም፣ ፊርማና አድራሻ መግለጽ አለባቸው ስለሚል የሕዝብ ጥያቄ መሆኑን የማስረዳት ሸክሙ ወደ ጥያቄ አቅራቢዎቹ ተመልሷል ማለት ነው፡፡ የቅማንትን እንደ ምሳሌ ብንወስድየማኅበረሰቡ አባለት በአሁኑ ወቅት 200,000 ይሆናሉ ቢባል እንኳን ወኪሎቻቸው ቢያንስ የ10,000 ሰው ፊርማ አያይዘው ለክልሉ ምክር ቤት ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል ማለት ነው፡፡

ብዙ ጊዜ ጥያቄ አቅራቢዎች ቁጥራቸውን ከፍ በማድረግ አጋንኖ ማቅረብ የተለመደ በመሆኑ ይኼ ጉዳይ መወሳሰቡ አይቀሬ ነው፡፡ ለምሳሌ ሕገ መንግሥቱ ሲፀድቅ የስልጤ ተወካዮች የብሔረሰቡን ቁጥር ወደ 3.5 ሚሊዮን እንደሚሆን ይናገሩ ነበር፡፡ የቅማንትም ወደ 900 ሺሕ እንደሚደርሱ ይናገራሉ፡፡ ይህ የአምስት በመቶ መሥፈርት ስም፣ ፊርማና አድራሻ ጥያቄ አቅራቢዎቹ ከገለጹት ሕዝብ ላይ ወይስ ከምን ላይ ነው የሚሰላው? ማንነታቸው በይፋ ዕውቅና ሳያገኝ፣ በተለይ ደግሞ በሕዝብና ቤት ቆጠራ ላይካተቱ ስለሚችሉ ለሥሌቱ መነሻው ምን ሊሆን እንደሚችልም አስቸጋሪ ነው፡፡ የቅማንትን ልዩ የሚያደርው ደግሞ በ1999 ዓ.ም. የሕዝብና ቤት ቆጠራ ሪፖርት ላይ ስላልተገለጸ ይህ የአምስት በመቶ ሥሌትን አስቸጋሪ ማድረጉ ግልጽ ይመስላል፡፡

ጥያቄው የሚቀርበው ደግሞ በቅድሚያ ለክልል ምክር ቤት ነው፡፡ ምክር ቤቱም ጥያቄው ከቀረበበት ጊዜ ጀምሮ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ምላሽ መስጠት አለበት፡፡ ከላይ የጠቀስነው አዋጅ አንቀጽ 20(2) እና 22 እንደሚደነግገው በክልሉ ምክር ቤት በሁለት ዓመት ውስጥ መልስ ያላገኘ ማኅበረሰብ በቀጥታ ለፌደሬሽን ምክር ቤት ጥያቄውን ማቅርብ ይችላል፡፡ የአማራ ክልል ምክር ቤት የቅማንትን ጥያቄ በዚሁ ጊዜ ውስጥ ባይመልስም፣ በመጨረሻ ግን ሥልታዊ በሆነ መንገድ አስተዳደራዊ ጥያቄው ላይ ትኩረት በመስጠት መልስ ሰጥቷል፡፡ እግረ መንገዱን ለብሔረሰቡ ዕውቅና በመስጠት፡፡

የተለየ ቋንቋ አስፈላጊነት

አንድ ማኅበረሰብ የብሔርነት ዕውቅና ሲያቀርብ ጥያቄውን በሚያቀርብበት ወቅት አባላቱ የሚግባቡበት የተለየ ቋንቋ መኖርን ሕገ መንግሥቱ እንደ መሥፈርት ይወስደዋል ወይ? ለዚህ ጥያቄ መልስ ለመስጠት ሕገ መንግሥቱ ሲረቀቅ የነበረው እሳቤ ምን ነበር የሚለውንና አሁን ያለው አዝማሚያ ምን እንደሚመስል ማየት ተገቢ ነው፡፡ በመጀመሪያ የሕገ መንግሥቱን እሳቤ እንይ፡፡ ሲረቀቅ ታሳቢ ያደረገው ከአንድና ከዚያ በላይ የሆኑ ብሔረሰቦች አንድ ቋንቋ ሊኖራቸው እንደሚችል ነው? ወይስ አንድ ቋንቋ ካላቸው አንድ ብሔር እንደሆኑና እንደሚሆኑ ነውን? የሽግግር መንግሥቱ 63 ብሔሮችን፣ ብሔረሰቦችንና ሕዝቦችን በአዋጅ ሲዘረዝር ቋንቋቸውን ብቻ መሠረት በማድረግ ነበር፡፡ የሥነ ልቦና አንድነት፣ የጋራ ማንነትና ሌሎች መሥፈርቶችን ከግምት ያስገባ ነበር ማለት አይቻልም፡፡ ምንም እንኳን በደርግ ጊዜ የተቋቋመውን የብሔረሰቦች ጥናት ምርምር ተቋም የጥናት ውጤትን እንደ ግብዓት ቢወሰድም የብሔሮችን፣ ብሔረሰቦችንና ሕዝቦችን ማንነት የተወሰነው በሕዝቡ ሳይሆን በሽግግር መንግሥቱ ምክር ቤት ነበር፡፡ መለያው ደግሞ ቋንቋ ነበር፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 46 ክልል ለመመሥረት የተቀመጡት መሥፈርቶች አሰፋፈር፣ ፈቃደኛነት፣ ማንነት ጋር አንዱ ቋንቋ ነው፡፡ የተለየ ቋንቋ የሚጠይቅ ባይሆን ኖሮ መቼም ቋንቋ የሌለው ሕዝብ ስለማይኖር እንደ መሥፈርት አይገባም ነበር፡፡ ክልሎችም ሲመሠረቱ ወሳኙ መሥፈርት ቋንቋ ነው፡፡ የተለያየ ቋንቋ ላላቸው ብሔሮች የተለየ ክልል እንዲመሠርቱ ነው እሳቤው፡፡ ቢያንስ በዛ ያለ ቁጥር ላላቸው፡፡ ለምሳሌ ከታሪክ አኳያ ስናይ በተለይ ከሰገሌ ጦርነት በኋላ የወሎና የሸዋ ሕዝብ እንደ ጠላት ነበር የሚተያየው፡፡ ቢያንስ አንድ ዓይነት የሆነ የማንነት ሥነ ልቦና አላቸው ማለትም አይቻልም፡፡ ሰሜን ሸዋ ከወሎ ጋር አንድ የሚያደርገው ቋንቋው ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የሕገ መንግሥቱ ፍላጎት የተለየ ቋንቋ እንዲኖር ነው ማለት ይቻላል፡፡

ባለፉት 20 ዓመታት የነበረውን የማንነት ፖለቲካን ደግሞ እንይ፡፡ ስልጤ የራሱ ቋንቋ ስለነበረው ዕውቅና አግኝቷል፡፡ ወይጦዎችና ትግረ ወርጂዎች በቋንቋቸው እየተጠቀሙ ስላልሆነ ወይም የተናጋሪው ቁጥር ስለቀነሰ፣ ጉጂ ኦሮሞዎች ከሌላው ኦሮሞ ከፍተኛ የዘየ ልዩነት ያለው ቋንቋ ቢኖራቸውም ከሕዝብ ቆጠራ ሪፖርትም ወጥተዋል፡፡ የመንጃ ማኅበረሰብ ከቋንቋቸው አንፃር የካፋና የሸካ ብሔረሰቦች ውስጥ ያሉ ጎሳዎች እንጂ ራሳቸውን የቻሉ ብሔረሰብ አይደሉም በማለት የደቡብ ክልል የብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝቦች ምክር ቤት ወስኗል፡፡ የፌደሬሽን ምክር ቤትም ውሳኔውን አፅድቆታል፡፡ ከእነዚህ አድራጎቶች አንፃር አሁንም የተለየ ቋንቋ መኖር ቅድመ ሁኔታ ነው ማለት ይቻላል፡፡

ሁለት ተቃራኒ የሆኑ ድምዳሜዎች ላይ አርፈናል፡፡ ከሞራልና ከፍልስፍና እንዲሁም ሕገ መንግሥቱ ላይ ከተጻፈው ዓረፍተ ነገር አንፃር ቋንቋ ቅድመ ሁኔታ አይደለም፡፡ ሕገ መንግሥቱ ሲፀድቅ ታሳቢ ካደረገውና አሁን እየሆነ ካለው የማንነት ፖለቲካ አንፃር ደግሞ የተለየ ቋንቋ መኖር ግድ ነው፡፡ የትኛው ትክክል ነው ከተባለ መልሱ የፖለቲካው ንፋስ ሁለቱንም ትክክል ሊያደርጋቸው ይችላል ነው፡፡

በአንድ ወቅት ወላይታ፣ ጋሞ፣ ጎፋና ዳውሮ ብሔረሰቦች ቋንቋዎቹ መሠረታዊ ልዩነት የላቸውም በማለት ‹‹ወጋጎዳ›› በማለት አንድ የጽሑፍ ቋንቋ በመቅረፅ ሁሉም በዚሁ ብቻ እንዲማሩ ተጀምሮ ውጤቱ አስከፊ እየሆነ ሲመጣ ቀሪ ሆኗል፡፡ እነዚህ ቋንቋዎች አንድ ናቸው፡፡ ልዩነታቸው የዘዬ ብቻ ነው ከተባለ የተለየ ቋንቋ መኖር ግድ አይደለም ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም አራቱም የተለያዩ ብሔረሰቦች እንደሆኑ ቀጥለዋልና፡፡ የወቅቱ ፖለቲካ በአንድነታችሁ ቀጥሉ የሚያስብል አልነበረም፡፡ የቅማንት ብሔረሰብም በቅማንትነይ የሚግባቡት በጣት የሚቆጠሩ ሰዎች ቢሆኑም የሚያግባባቸው የተለየ ቋንቋ መኖርን የክልሉ ምክር ቤት እንደ መሥፈርት አለመውሰዱን መገንዘብ ይቻላል፡፡ በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ ለሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ የማንነት ይታወቅልኝ ጥያቄ ያቀረቡት የባህረ ወርቅ መስመስ ማኅበረሰብ የሚናገሩት አማርኛ በመሆኑ፣ የደንጣ ቡደም ክንቺቺላ ደግሞ ከከንባታና ከሀዲያ ሕዝቦች የተለየ ቋንቋ ስለሌላቸውም ይመስላል እስካሁን ድረስ ዕውቅና ስለማግኘታቸው ይህ ጸሐፊ አያውቅም፡፡ የፖለቲካው አውሎ ንፋስ አስገዳጅ አልነበረም ማለት ይቻላል፡፡

የማንነት ጥያቄ ለሚያነሱ ልክ እንደ ራያ ማኅበረሰብ የተለየ ቋንቋ ለሌላቸው፣ ለቅማንት ብሔረሰብ የተሰጠው ውሳኔ ትልቅ ትምህርት የሚሆን ይመስላል፡፡ በግድ በተለየ ቋንቋ መግባባትን፣ የተለየ ባህልና ልማድ እንዳላቸው ማረጋገጥን ቅድመ ሁኔታ አላደረገምና!በወቅቱ የሚፈጠረው ፖለቲካዊ ንፋስ እንደተጠበቀ ሆኖ! ይሁን እንጂ፣ ገደብ በሌለው ሁኔታ የአንድ አካባቢ ማኅበረሰብ ባሻው ጊዜ እየተነሳ ብሔር ነኝ የሚል ከሆነ፣ ብሔር ከመሆን የሚመነጩ የራስን ክልል፣ ዞንና ወረዳ እናቋቁም፣ በተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ እንወከል የሚሉ ማለቂያ የሌላቸው ውስብስብ ችግሮችን እንደሚያስከትል ግልጽ ነው፡፡ ስለሆነም የፌደሬሽን ምክር ቤት አስማሚና አስታራቂ መፍትሔ መሻት አለበት፡፡

  • ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...