Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

‹አልተግባብቶም!›

እነሆ መንገድ! ከስቴዲየም ወደ ቄራ ልንጓዝ ነው። ጋቢና የተቀመጠ ተሳፋሪ በስልኩ ያወራል። “ስማ ባንተ ቤት ሰው መርጠህ ልብህ ውልቅ ብሏል። እኔ እያለሁ እስኪ ምን ሌላ ጋ ያስኬድሃል? ‘ሥጋ ሞኝ ነው’ አለ ያገሬ ሰው። ይኼው ለገንዘብ ብለህ የእጅህን አገኘህ፤” ይላል። ከጀርባው የተሰየመ ጎልማሳ፣ “እውነት ነው! ሥጋ ሞኝ ነው። ታዲያ የበሬ አይደለም። የሰው ነው ሞኝ፤” ይላል አጠገቡ ለተቀመጠች ቀዘባ። ወጣቷ፣ “መቼም ሰብቶ ከመታረድ የእኛ ይሻላል፤” ስትለው መሀል መቀመጫ የተቀመጠች መነጽር ያደረገች ወይዘሮ፣ “ቅድም በሬዲዮ ስለመላላጫና ስለፈረሰኛ ሲያወሩብን ዋሉ። አሁን ደግሞ እዚህ ስለሥጋ። ሥጋና ደሙን ሰጥቶ ሞቶ ሊነሳ ቀናት ሲቀረው ምናለበት በወሬ ባታስፈስኩን?” ስትል ትነጫነጫለች። ከጎኗ የተቀመጠ ቀበጥባጣ ወጣት ደግሞ፣ “አይገርምም? ከዘንድሮ የምርጫ ቅስቀሳ የሥጋ ቤት ማስታወቂያ ደመቀ እኮ፤” እያለ ንዴቷን ያባብሳል።

“እርግጠኛ ነኝ ቀጣዩ የዓለም ጦርነት የሚነሳው በሥጋ በልና በ‘ቬጂቴሪያን’ መሀል ነው” ብላ ደግሞ አጠገቤ የተቀመጠች የዩኒቨርሲቲ ተማሪ መሳይ ፌስቡክ ገጽ ላይ ስትለጥፍ እታዘባለሁ። ጥቂት ቆይታ ‘ኮሜንት’ ስታበጥር ወደ ሌላ የማይ መስዬ በጎንዮሽ ሰረቅ አደርጋለሁ፡፡ “የሃይማኖት አክራሪዎችና የፖለቲካ ሴረኞች ሸር ሳያንሰን ደግሞ የሥጋ በሎች የጦርነት ታሪክ ሊጸፍብን? አይደረግም፤” ሲል አንዱ ሌላው በመቀጠል “እህል ከመሬት መስሎኝ የሚበቅል። ሥጋም ቢሆን ከመልካም የግጦሽ ሳር ነው የሚሰባው። እናም በእህል ለመጣላት እንደ መሬት በሊዝ የመንግሥት ነው እስኪባል መጠበቅ አለብን?” ይላል። ምድረ ጦር ጠማኝ እጅ ለእጅ እንደማይያያዝ አውቆ በቃላት ጠረባ አንዱ ሌላውን አፈር ድሜ ሲያስግጥ ማየቱ ቴክኖሎጂን የሚያስረግም ሲሆንብኝ፣ ጆሮዬን መጨረሻ ወንበር ወደተቀመጡት ጣል አደረኩ። ሲናገሩ እንጂ ሲያዳምጡ መቼ ይገኛሉ?

“እሺ እዚያ ጥግ” ወያላው ጉዞ ከመጀመራችን ያጣድፈናል። መጨረሻ ወንበር ከተቀመጡ አንድ አዛውንት ሌላ ሦስቱ ይተዋወቃሉ። የሚጫወቱት ስለኬንያው የአልሸባብ ጥቃት ነው። “የአበራሽን ጠባሳ ያየ ‘አይስቅም’ ሆኖብኝ እንጂ እኔስ ሳቅ ሳቅ ይለኛል፤” ይላል አንደኛው። “ዋ ሰው ሲሞት የሚስቅ ቀጣዩ ሟች ብቻ ነው ይባላል። አይደል አባት?” አዛውንቱን ለፍርድ ያስገቡዋቸዋል። “ይባላል!” ይመልሳሉ ባጭሩ።  “እኔ እኮ የምስቀው በሟቾች አይደለም። ምን ነክቷችኋል? ምንድነው የምድሩ አልበቃ ብሎ በሰማይ ቤት ስም ማጥፋት?” አለና “እኔ ሳቅ ሳቅ ይለኛል ያልኩት የአልሸባብ ኬንያ ላይ እንደልቡ መሆን ነው። እዚህማ አያስባትም፤” ሲል አዛውንቱ አቋረጡት፡፡ “እግዜር ሲጠብቅ ነዋ ልጄ። ሁሉንም እሱ ሲጠብቅ ነው። ‘እሱ ከተማን ካልጠበቀ ጠባቂ በከንቱ ይደክማል’ ይላል መጽሐፉ። ምህላችን እያስጨነቀው ለቅሷችን ዙፋኑ ሥር እንደ ባህር ተንጣሎ እያየ እንዲያ ላለ የሽብር ጥቃት እንዴት አሳልፎ ይስጠን? ቦምብ ስለማንሰማ ጥይት ስለማይጮህብን እንጂ በቀን ሦስቴ ካለመብላት የከፋ ሽብርስ አለ?” አሉት።

ነገሩ እየተያያዘ እንደ ሰደድ እሳት ወዴት እንደሚያመራ ወጣቶቹ ገብቷቸው አዛውንቱን ሊያናግሩ ይተነኩሳሉ። “እውነት ነው እንግዲህ ጦሙም አለቀ። መብላት ስናስብ ያሰብነውን ያህል መብላት እንደማንችል ትዝ ሊለን ነው፤” አለ በሾፌሩ ትይዩ መስኮቱ አጠገብ የተቀመጠ። ጓደኛው ተቀበለና፣ “መንግሥት ሳይቸግረው ሃይማኖትና ፖለቲካን ለያይቶ እንጂ የተጀመሩት ልማቶች በሰላምና በታቀደላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ በሚል ሌላ ሁዳዴ ማሳወጅ ነበረበት፤” ብሎ ብቻውን ሳቀ። ሳቁ በትንታ ሲቆራረጥ ተሳፋሪዎች ደንግጠው ወደሱ ዞሩ። ጓደኛው ደረቱን እየደቃ፣ “አይዞህ ይህን ሳቅማ እንደጀመርከው ትጨርሰዋለህ! ይኼኔ እያለቀስክ ቢሆን ትን ባላለህ?” ይለዋል። ተሳፋሪዎች ፈገግ ይላሉ። እውነት ግን የለቅሶ ትንታ የሌለው ለምድነው? ለመልካም ነገር እጅ ያጠራት ዓለም!

እየተጓዝን ነው። ወያላው ሒሳብ ሰብስቦ እንዳበቃ ያስተዋለው ከወይዘሮዋ አጠገብ የተቀመጠው ወጣት፣ “እሺ ምዕመናን አንዴ ትኩረታችሁን ወደኔ!” ሲል አንቧረቀ። አጠገቤ ያለችውን በቆረጣ አያለሁ። “ጋይስ ተንቀሳቃሽ ‘ቸርች’ ተከፈፈተ እንዴ?” ብላ ትለጥፋለች። ‘ኮሜንት’ ይግተለተላል። ለጊዜው ቀልቤን ወደ ወጣቱ መልሻለሁ። “ያው እንደምታውቁት መጪው ዓመት በዓል ነው። ይህ ዓመት በዓል ሃይማኖታዊ አንድምታው የጎላ እንደመሆኑ የተቸገሩትን ለመርዳት የቻልነውን ያህል እጃችንን መዘርጋት አለብን። ‘ስጡ ይሰጣችኋል’ ይላል። እኔ አላልኩም እሱ ነው። እና አሁን . . .” ጉሮሮውን ትንሽ ያፀዳዳና ይቀጥላል።  “. . . እና አሁን እኛ በአካባቢያችን የሚገኙ አረጋውያን አቅመ ደካሞችን ለዓመት በዓል መዋያ የሚሆን ነገር ለማድረግ መዋጮ እየሰበሰብን ነው። የተቻላችሁን እጃችሁን ብትዘረጉ እግዚአብሔር ከማያልቀው በረከቱ ይዘግንላችኋል፤” ብሎ እንዳበቃ ‘የተቻላችሁን’ ሲል የነበረው ሰውዬ ‘ከሃያ ብር በታች አልቀበልም’ ማለት ጀመረ።

ይኼን ጊዜ ጎልማሳው “20 ሳንቲምም 20 ብርም ስጦታ ነው። ኧረ ለመሆኑ ግን አንተ ማን ትባላለህ? እስኪ የወከለህን ማኅበር ወረቀት አሳየን?” ብሎ አፈጠጠበት። ያላሰብነውና ያልጠረጠርነው ነገር መምጣጡ ገብቶናል። “ሳያዩ የሚያምኑ ብፁአን ናቸው’ አላለም መድኃኔዓለም?”  አለ ወጣቱ። ሊሰጥ አሰፍስፎ የነበረ ሁላ የጎልማሳው ጥርጣሬ ተጋባበት። ጭራሽ መጨረሻ ወንበር ከተቀመጡት አንደኛው፣ “ዝም ብለህ እኮ የበርጫ ሙሉልኝ ምናምን ብትለን ካለን እንሰጥህ ከሌለንም የእኛን እናስቅምህ ነበር፤” አለው። ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ሦስተኛው ሰማይ ደርሶ የመጣ ይመስል የነበረው የወገን ደራሽ ቀልቡ ተገፎ ወያላውን አውርደኝ ብሎ ጮኸበት። ታክሲዋ ልትቆም ዳር እስክትይዝ ሳይታገስ በሩን ከፍቶ ዘሎ ወረደ። ወይዘሮዋ፣ “እግዜር እኛ በስምህም የሚነግዱትን እንዲህ አሽቀንጥረን እንደምንጥል እባክህ አንተም በስማችን የሚነግዱ ፀረ ሕዝቦችን አሽቀንጥረህ ጣልልን፤” ብላ አጉተመተመች። ነገር ጉኖ ጉኖ ፖለቲካ ካልሆነ አይዘንብም ማለት ነው በቃ?

በወረደው አጭበርባሪ ምትክ ሁለት እናቶች ተሳፍረዋል። ስለዋሉበት ገበያ እያወሩ ነው። “እንዲያው ስለስምንተኛው ሺሕ ፍካሬ ኢየሱስ ሲናገር በቃ ተስፋ የለውም ነው የሚለው አንቱ!” አንዳኛቸው ይጠይቃሉ። “እርስዎ ደግሞ ገና የጀማሪ ጥያቄ መጠየቅ ይወዳሉ። ምን ሆነው ነው ግን? ስምንተኛው ሺሕ ማለት ገበያው እንጂ ሌላ ምን ሆነና፤” ይመልሳሉ የወዲያኛዋ። “ታዲያ እንዲህ ከሆነማ መድኃኔዓለም እስከ መቼ እየተወለደ፣ ተገርፎ፣ ተሰቅሎ፣ ተነስቶ ያርጋል? እኛ እንኳን ዶሮና እንቁላል መግዛት ከብዶናል። ለምን መጥቶ አይገላግለንም?” ከወዳጃቸው ገርጀፍ የሚሉት እናት ከአጠያየቃቸው ማስመሰል የሚያውቁ አይመስሉም። “ሰዓቱዋ ቀኑዋ ስትደርስ ይመጣል። አንቺ ዶሮና እንቁላል ለአንድ ፋሲካ መሸመት ከበደሽና ምፅአት መቅረብ አለበት? ሆሆ! እንኳን የላይኛው የታችኞቹም አላዘኑልን፤” ቆፍጠን ብለው ወዳጃቸውን እየተቆጡ የወዲያኛዋ መለሱ።

በመሀል ገና ጉዟችን ሳይጀመር በስልክ ይነጋገር የነበረው ተሳፋሪ “ወዲያ! ቁም ነገር የሚባል አታውራኝ አሁን። ቁም ነገር ነው የሰለቸኝ። ቁም ነገር በማውራት ቢሆንማ በስብሰባ የምናጠፋው ጊዜ ተደምሮ የትና የት ባደረሰን ነበር?” ይላል። እንዲያ ሲል በስልክ የሚያናግረው ደንበኛው ሳቀ መሰል “ግድ የለም እጠብቅሃለሁ ተረጋግተህ ሳቅህን ጨርስ!” ሲል ሰማነውና ደነገጥን። “እንዴ ይኼ ሰውዬ እስካሁን በስልክ እያወራ ነው?” መጨረሻ ወንበር ከተመቀጡት ወጣቶች አንደኛው አዳንቆ ጠየቀ። “ምን ይታወቃል ‘ቴሌ’ ጉደኛውና ተዓምረኛው እንደ ‘ፍሪ ስኮላርሺፕ’፣ ‘ፍሪ ኔትወርክ’ ማደል ጀምሮ ይሆናላ፤” ቢል ጎልማሳው ተሳፋሪው የምፀት ሳቁን ለቀቀው። ‘ነፃው ቀርቶብኝ ላቤን ባልነጠቀኝ’ ይሉት ምፀት መሆኑ ነው! ጉድ እኮ ነው!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ወያላውና ሾፌሩ ለዓውደ ዓመት ከማን ብር ተበድረው ዘና ሲሉ እንደሚያነጉ እየተቀባበሉ ይጫወታሉ። መጨረሻ ወንበር የተቀመጡት ወጣቶች ስለሚደግፏቸው የአውሮፓ ቡድኖች ሲነዛነዙ ቆይተው ‘የእኔ ቡድን አሠላለፍ ይበልጣል አይበልጥም!’ እየተባባሉ ታክሲዋን ‘ቴክኒክና ታክቲክ’ ክፍል አስመስለዋታል። መሀላቸው የተቀመጡት አዛውንት ከዘራቸውን እየቆረቆሩ ሩቅ ያስባሉ። ከሾፌሩ ጀርባ የተቀመጡት ጎልማሳና ኮረዳ ‘ሕዝብ በፍቅር እንጂ በልማት ብቻ አይሸነፍ/ይሸነፋል’ ይከራከራሉ። እሷ ፋሲካን ተገን አድርጋ መሲሁን እንደ ምሳሌ እያነሳች፣ “ገና ለገና ሞተን እንኑር አንኑር ሳናውቀው ዘመናችንን በእሱ አምነን እንድንፈጽም ያደረገን ፍቅር እንጂ ሌላ አይደለም፤” ትላለች። ጎልማሳው አዳምጦ ሲያበቃ፣ “ኳሷ መሬት ሳለች እንደ ፕላቶናዊቷ ‘ዩቶፒያ’ የማይጨበጥ ምስሌ በአስረጂነት አትሰንቅሪ፤” ብሎ ይቆጣታል። ከእነሱ ጀርባ ወይዘሮዋ አጠገቧ ከተቀመጡት እናቶች ጋር በሸመታ ዙሪያ ሲጫወቱ የቅመምና በርበሬ ወሬያቸው ጆሮ ይለበልባል። በአጠቃላይ ታክሲያችን ተንቀሳቃሽ የጫጫታ አዳራሽ ሆናለች።

ድንገት መራገፊያችን ላይ ደርሰን ወያላው “መጨረሻ!” ሲል አጠገቤ የተቀመጠችዋን ወጣት ፌስቡክ (‘ፌስቡክ’ ሳይሆን ‘ፌስሃውስ’ ቢባል እንዴት ደግ ነበር ግን? አንዳንዱ ውሎ አዳሩ መቼ ልቡና ቤቱ ይመስላል ‘ሎግ ኢን’ ካለ?) ስቃኝ፣ “ታክሲ ሲሳፈሩና ኢቲቪ ሲከፍቱ ‘ኢርፎን’ ጆሮዎ ላይ መሰካትዎን አይዘንጉ” ብላ ለጥፋለች። ‘ኮሜንት’ ይግተለተላል። “ታክሲም የመንግሥት ሆነ?” ሲል ሌላው ከሥር፣ “ምን የመንግሥት ያልሆነ አለ? ነፍስህም ስለማትጨበጥ እንጂ ታሪክ እናይ ነበር፤” ብሎ ‘ኮምቷል’። ልወርድ ስዞር ከደጅ ታክሲ ይጠብቅ የነበረ መንገደኛ ታክሲያችንን ሲያይ እየተሻኮተ መጥቶ በሩን አንቆ ቆመ። ወያላው፣ “ሳይወርዱ እንዴት ብላችሁ ነው የምትገቡት?” ይላል። የሚሰማው የለም። ሾፌሩ ተበሳጭቶ፣ “ኤጭ ሥልጣን መሰላችሁ እንዴ? የምን ግብ ግብ ነው አስወርዷቸዋ መጀመርያ” ይላል። አይሰሙትም። ጥቂት እንደተጉላላን አዛውንቱ ከመቀመጫቸው ተነሱና፣ “ኧረ በህማማት የለም መገፋፋት!” አሉ። መንገዱ ተለቀቀ። በፍጥነት ወረድን። ጎልማሳው “አዳሜ በህማማት መንገድ ሲለቀቅለት ሥልጣንም የሚለቀቅለት መስሎት ጉድ እንዳይሆን” ሲል አዛውንቱ ሰምተውት ከት ብለው ሳቁና፣ “በህማማት ምርጫን እንዳማልህ ነው? ሞኝህን ፈልግ ብለውት” ሸመጠጡ። የዘንድሮ ወሬ በነገር እየተቆሰቆሰ ሲግለበለብ ‘አልሰማሁም’ ከማለት ይልቅ ‘አልተግባብቶም’ ብሎ ‘መሸወድ’ ሳይቀል አይቀርም፡፡ መልካም ጉዞ! 

    

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት