Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

ጊዜው እንዲህ ሳይራቀቅ ይቅርታ መላ ቅጡ ሳይጠፋ፣ ወላጆቻችን ኪሳቸው ውስጥ ሃያ ብር ካለ ዓለም አበቃላት ይባል ነበር፡፡ ያኔ ድሮ ያኔ፡፡ በተለይ በበዓል ሰሞን እኔ ነኝ ያለ ሙክት በአሥር ብር ተገዝቶ ተጎትቶ ሲመጣ የሠፈሩ ሰው የመጀመርያ ጥያቄ ‹‹በስንት ብር ተገዛ?›› የሚል ነበር፡፡ በእርግጥ አሁንም ይህ ጥያቄ እንዳለ ነው፡፡ መልሱ ቢለያይም፡፡ አባታችን ታዲያ ኮራ ብሎ፣ ‹‹ይኼ የወጣበትን ዋጋ ብትሰሙ ታብዳላችሁ፡፡ ቢቀርባችሁ ይሻላል፤›› ብሎ ትከሻውን እየሰበቀ ወደ ቤት ሲገባ ይገርመን ነበር፡፡ ያኔ በአሥር ብር አንዳች የሚያህል ሙክት መገዛቱ ሲሰማ ከመግረም አልፎ ያስደነግጥ ነበር፡፡ በእርግጥ ዛሬ በአሥር ብር አንድ ፍንጃል ሻይ ሲገዛ የያኔዎቹ ኖረው ቢሰሙ ከመደንገጥ በላይም ይሆኑ ነበር፡፡ እንኳንም አልኖሩ፡፡

አባቴ በጊዜው የታወቀ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር ነበር፡፡ እናቴ ደግሞ ነርስ፡፡ በዚያን ዘመን የሁለቱ ድምር ደመወዝ ከ500 ብር ባይበልጥም፣ ኮራ ያለ ኑሮ እንኖር ነበር፡፡ እኔ፣ አምስት ወንድሞቼና እህቶቼ በወቅቱ አጠራር ‹‹የቅንጦት›› የሚባል አስተዳደግ ነበረን፡፡ በዙሪያችን ያሉ ጎረቤቶቻችን ግን በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ስለሚገኙ የአሥር ብር ሙክት ብርቃቸው ነበር፡፡ በእርግጥ በዚያን ዘመን ትንሿ አምስት ሳንቲም ሳትቀር ትልቅ ዋጋ ነበራት፡፡ ከሠፈራችን ካዛንቺስ ተነስታ በፒያሳ አቆራርጣ መርካቶ ትዘልቅ የነበረችው የከተማ አውቶቡስ የደርሶ መልስ ቲኬት ዋጋ 0.25 ሳንቲም ነበር፡፡ እኛ ደግሞ በአምስት ሳንቲም አምስት ደስታ ከረሜላዎች፣ ወይም ሁለት የማር ከረሜላዎች ገዝተን ከጓደኞቻችን ጋር እንካፈል ነበር፡፡ እኛ ቤት የተገዛውን ሙክትም ጎረቤቱ ጭምር ይስተናገድበት ነበር፡፡ በነበር ቀረ እንጂ፡፡

እየጎረመስን ስንመጣ ወላጆች ‹‹ደጉ ጊዜ እንደ ዋዛ አለፈ›› ብለው ሲያጉረመርሙ ሰምተናል፡፡ ለምሳሌ እናቴ በትልቅ ዘንቢሏ ከመርካቶ አጭቃ ያመጣቻቸው ሸቀጦች 12 ብር ወጣባቸው ብላ ስትንገበገብ አይረሳኝም፡፡ ዛሬ የአሥር ሳንቲም ፌስታል ስንት የወጣበትን ትይዝ ይሆን ብዬ ሳስብ እንደ ሞኝ ያስቀኛል፡፡ አባቴ ከጓደኞቹ ጋር ስድስት ኪሎ ግብፅ ኤምባሲ አካባቢ የሚገኝ ታዋቂ ክትፎ ቤት ጣባ ሙሉ ክትፎ በልቶ ሦስት ብር በመክፈሉ ሲነጫነጭ አስታውሳለሁ፡፡ በእነሱ ወጣትነት ጊዜ ክትፎ ሃምሳ ሳንቲም ነበር፡፡ በእርግጥ ያንገበግባል፡፡ እኔ እንኳ በአቅሜ በአሥር ብር ግርማ ክትፎ ቤት የበላሁበትን ጊዜ እንዴት እረሳለሁ? ‹‹ድሮ ቀረ›› ዓይነት ወሬ ለማድራት ሳይሆን፣ ጊዜ ሲለዋወጥ አስከትሎ የሚመጣው ጓዝ ግን ያስገርመኛል፡፡

ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀን ወጥተን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሥራ በጀመርኩበት ሰሞን ብሔራዊ ቴአትር አካባቢ የሚገኝ ምግብ ቤት ምሳ ስንበላ የገጠመኝ አይረሳኝም፡፡ እኔና ሦስት የሥራ ባልደረቦቼ ምሳ እየበላን ሳለ አንድ ዝንጥ ባለ አለባበሳቸው ዓይን የሚያርፍባቸው ሰው ትክ ብለው ያዩናል፡፡ ‹‹ጌታዬ ምን እንታዘዝ?›› በማለት ጥያቄ አቀረብኩላቸው፡፡ ‹‹እዚያ ባንክ ቤት ውስጥ አውቃችኋለሁ፡፡ አይ እናንተ ዕድለ ቢሶች፡፡ ይኼ አውሬ ደርግ የሚባል መጥቶ ነው እንጂ እናንተ እኮ በአሁኑ ጊዜ ባለመኪና መሆን ነበረባችሁ፤›› ሲሉን በመገረም ተያየን፡፡ ሰውየው ፈገግ እያሉ፣ ‹‹አያችሁ ከዩኒቨርሲቲ ግራጁዌት ያደረጉ የባንክ ሠራተኞች እኮ ድሮ ቢፈልጉ ከሴፌሪያን ወይም ከፊያት አሊያም ከአንዱ ውኃ የመሰለች መኪና ወዲያው በክሬዲት ያገኙ ነበር፡፡ አሁን ድርቅ ሆኗል፡፡ በሉ አይዞአችሁ በርቱ…›› ብለው ተሰናበቱን፡፡ በእኛ ቤት የባንክ ባለሙያ በመሆናችን የወላጆች ቤት ውስጥ ሆነን ስንዘንጥ፣ የቀድሞዎቹ ለካ ቤትና መኪና በክሬዲት ያገኙ ነበር? ወይ ጊዜ፡፡ ዛሬስ? የዛሬዎቹ ያውቁታል፡፡ ከነችግሩና ከነጫናው፡፡

ጊዜ እየነጎደ ሲሄድ ከትናንት ዛሬ፣ ከዛሬ ደግሞ ነገ መክበዱ ለምን ይሆን እላለሁ፡፡ በእርግጥ የወደፊቱ ትውልድ ከእኛ የተሻለ ያገኛል የሚል ተስፋ በውስጤ አለ፡፡ አሁን ላይ ሆኜ የትናንቱንና የዛሬውን ሳነፃፅር የተሻሉ ነገሮች እንዳሉ ይሰማኛል፡፡ ነገር ግን የዛሬዎቹ ወጣቶች (ብዙኃኑ) የትራንስፖርት ችግር፣ የመኖሪያ ቤት ችግርና ዘና የሚያደርግ የወር ገቢ አለማግኘታቸው ምን ያህል እንደሚጎዳቸው ሳስብ እሳቀቃለሁ፡፡ ሥራ አጥተው የሚንገላቱትና የማይፈልጉትን እየሠሩ ተከፍተው የሚኖሩትን ሳይም እናደዳለሁ፡፡ ጊዜ ጊዜን እየተካ ሲሄድ ዛሬ ከትናንት ካልተሻለ ነገ እንዴት ብሩህ ሊሆን ይችላል የሚለውም ያሳስበኛል፡፡ በርካታ ጥያቄዎችን ያጭርብኛል፡፡

እኔም ወግ ደርሶኝ ሃምሳዎቹን እያጋመስኩ ባለሁበት ወቅት በጊዜ ሒደት ውስጥ የተለዋወጡ የኑሮ ስንክሳሮችን ሳስባቸው ይገርሙኛል፡፡ አባቴ ‹‹ባትሰሙ ይሻላችኋል፡፡ ዋጋው ያሳብዳችኋል…›› ያለለት የዚያን ዘመኑ ሙክት እኩያ ዛሬ ከአራት ሺሕ ብር በላይ ይጠራበታል፡፡ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ከተለያዩ አቅጣጫዎች በመነሳት ትንታኔ በማቅረብ የዋጋ ለውጥ እርግጥ መሆኑን ቢነግሩንም፣ የአገራችን ወልጋዳ የግብይት ሥርዓት የፈጠረው መንገብገብ ግን ትከሻችንን እያወላገደው መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ ሰፊ ለም መሬት፣ በአፍሪካ ወደር የሌለው የውኃ ሀብትና ከፍተኛ ቁጥር ያለው መሥራት የሚችል ሕዝብ ይዘን ሥጋ፣ እንቁላል፣ ቅቤና ወተት ብርቅ ሲሆኑብን ማየት ያሳፍራል፡፡ አብዛኞቹ የአፍሪካ አገሮች እነዚህን ምግቦች ከድንች እኩል በአነስተኛ ዋጋ አግኝተው ሲመገቡ፣ የስንዴ ዱቄትና ዘይት ብርቅ ሆኖብን ስንሠለፍ ማየት ያማል፡፡ ሕመሙም አጥንት ድረስ ዘልቆ ይሰማል፡፡

ከጊዜ ጋር እያሰናሰልኩ ያነሳሁት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ በብዙ ነገሮች ከአፍሪካ ኋላ መቅረታችን ያበሳጨኛል፡፡ ቅኝ ያልተገዛንበትና የአውሮፓን ወራሪ ኃይል ያንበረከክንበትን አኩሪ ታሪካችንን እንደ ተረት እየተረትን መተኛታችን ሳያንስ፣ በአገር ብሔራዊ ጉዳይ እንኳ መግባባት አንችልም፡፡ ብዙዎቻችን ከራሳችንና ከብጤዎቻችን ፍላጎትና ጥቅም በላይ የአገር ጉዳይ ስለማያሳስበን የዛሬን ፈተና ተቋቁመን ለነገው አገር ተረካቢ ትውልድ አናስብም፡፡ ጥቅማችን ዕይታችንን እየጋረደው የሰው መብት አናከብርም፡፡ ወገንን ከራስ ጥቅምና ፍላጎት በማሳነስ ሁሌም በጠባቡ ማዕዘን ውስጥ ነው የምናስበው፡፡ ራስ ወዳድነት የከፋበት ዘመን፡፡ በጊዜ ሒደት ውስጥ ብዙ ነገሮች ሲለዋወጡ ራሳችንን እንደ ወቅቱ ሁኔታ መለዋወጥ ካልቻልን እንደ መርግ የሚከብዱ ሸክሞቻችን ይበዛሉ፡፡ መላ ቅጡ በጠፋበት ዘመን ውስጥ ብንሆንም አገርና ወገንን እናስብ፡፡ ለነገው ትውልድ የሚመች አገር እንፍጠር፡፡ ከህሊና ሙግትም ራሳችንን ነፃ እናውጣ፡፡

(ኤ.አ.፣ ከገርጂ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...