Saturday, September 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተለየ ሁኔታ የመምህራንን ወይም የተመራማሪዎችን ነፃነት የሚሸረሽር ነገር ብዙም ያለ አይመስለኝም››

ዶ/ር አድማሱ ፀጋዬ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት

ዶ/ር አድማስ ፀጋዬ አሥረኛው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሲሆኑ፣ ዩኒቨርሲቲውን ላለፉት አራት ዓመታት በፕሬዚዳንትነት በመምራት ላይ ይገኛሉ፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ከመሆናቸው ቀደም ብሎ የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲን እንዲሁ ለሦስት ዓመታት ያህል በፕሬዚዳንትነት አገልግለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በዩኒቨርሲቲው የአካዴሚክ ኦፊሰር፣ የአስተዳደርና የልማት ምክትል ፕሬዚዳንት፣ የአካዴሚክና የምርምር ፕሬዚዳንት በመሆንም አገልግለዋል፡፡ በአገር ውስጥ በቀድሞው ሐዋሳ መለስተኛ እርሻ ኮሌጅና በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ሲሆን፤ ሁለተኛና የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ደግሞ ኔዘርላንድ ከሚገኘው ዋገኒገን ዩኒቨርሲቲ በእንስሳት ተክል ላይ ባደረጉት ጥናት አግኝተዋል፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መተግበር ጀምሬያለሁ በሚላቸው አዳዲስ አሠራሮችና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ነአምን አሸናፊ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር ሒደቱን በተመለከተ አዳዲስ ሥራዎችን እያከናወንኩ ነው በማለት ከመግለጽ ባለፈ፣ እርስዎ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ከሆኑ በኋላ የተደረጉ በርካታ ማሻሻያዎች እንደተከናወኑ ተገልጿል፡፡ ከዚህ አንፃር እርስዎ ወደ ፕሬዚዳንትነት ከመጡ በኋላ የተከናወኑ አዳዲስ ነገሮችን ቢያብራሩልኝ?

ዶ/ር አድማሱ፡- በለውጥ ፕሮግራም ውስጥ መጀመርያ ያደረግነው ነገር ቢኖር በአጠቃላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን አደረጃጀት በደንብ በማየትና በመፈተሽ ከዚህ በፊት የነበሩ የተንዛዙ አሠራሮችን መቀየር ነው፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ የትምህርት ፕሮግራሞችንና የአስተዳደር ሥራዎችን እንደገና ለማደራጀት የሠራናቸው ሥራዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ከዚህ በፊት ወደ 15 የሚሆኑ የትምህርት ፕሮግራሞች በቀጥታ ከአካዴሚክ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ጋር ይገናኙ ነበር፡፡ የዕዝ ሰንሠለቱ በጣም ረዥም ነበር፡፡ ይህንን ለማስተካከል በጣም አጠር ያለ የእዝ ሰንሠለት እንዲኖር ፕሮግራሞችን፣ ማዕከላትንና የትምህርት ክፍሎችን በሞላ በኮሌጆች ሥር በማደራጀት አሥር ኮሌጆች እንዲኖሩ፣ በአጠቃላይ ሁሉም ፕሮግራሞች በኮሌጆች ሥር እንዲሆኑና እነሱም በቀጥታ ተጠሪነታቸው ለአካዴሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት እንዲሆን የማድረግ ሥራ ተሠርቷል፡፡ ከዚህ በፊት ግን በአካዴሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ሥር በጣም ብዙ የተለያዩ ቢሮዎች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ ቺፍ አካዴሚክ ኦፊሰር፣ ቀጥሎ ዳይሬክተር፣ ከዚያ ደግሞ ኦፊሰሮች እያለ ነው ወደ ኮሌጅ የሚወርደው፡፡ ከዚያ በመቀጠል ደግሞ ፋካልቲ አለ፣ የትምህርት ክፍል አለ፡፡ በጣም ረዘም ያለ የአሠራር ሥርዓት ነበር የነበረው፡፡ እነዚህ በአካዴሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ሥር ያሉት ዳይሬክተሮች የትምህርት ክፍሉ አባላት ናቸው፣ ኦፊሰሮቹም እንዲሁ፡፡

በአጠቃላይ እነዚህ ምርምሩን ትተው ነው የማስተማር ሥራ ሲሠሩ የነበረው፡፡ አሁን በአዲሱ አደረጃጀት የትምህርት አካባቢውን ብንመለከት አካዴሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት አለ ከዛ በታች ዳይሬክተር አለ፡፡ ከዚያ በቀጥታ ወደ ኮሌጅ ነው የሚሄደው፡፡ ከኮሌጅ በታች ደግሞ የትምህርት ክፍሎች ነው ያሉት፡፡ ሌላው ከዚህ በፊት አንዳንድ ተቋማት ነበሩ፡፡ እንደገና ደግሞ የምርምር ተቋማት በአጠቃላይ የምርምር ሥራቸውን አቁመው በቅድመና በድኅረ ምረቃ ፕሮግራሞች ላይ በማተኮር ወደ መማር ማስተማሩ ሒደት ውስጥ ነበሩ፡፡ በአዲሱ አደረጃጀት መሠረት ተቋማት ራሳቸውን ችለው ምርምር ላይ እንዲያተኩሩ የሚያስችል ሁኔታ ተደራጅቷል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ እነዚህ የምርምር ተቋማት ሙሉ በሙሉ ምርምር ላይ ትኩረት አድርገው ለአገሪቱ ችግር ፈቺ የሆነና የሚጠቅሙ የምርምር ርዕስ ላይ አተኩረው ሥራቸውን ይሠራሉ ማለት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም እያንዳንዱ ኮሌጅ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር ተደርጓል፡፡ የአካዴሚክ ሕጋችንን በደንብ አድርገን እንደገና አሻሽለናል፡፡ እናም እያንዳንዱ ኮሌጅ የራሱ የሆነ አካዴሚክ ነፃነት አለው፡፡ የሰው ኃይልና የፋይናንስ አስተዳደር ነፃነት አለው፡፡ ለምሳሌ ከዚህ በፊት የአካዴሚክ ማዕረግ ሲሰጥ የተባባሪና የረዳት ፕሮፌሰር ማዕረግ በሞላ ወደ ማዕከል እየመጣ ነበር ሲፀድቅ የነበረው፡፡ አሁን ግን በአዲሱ አሠራራችን መሠረት ኮሌጆች ናቸው ሁሉን ነገር የሚጨርሱት፡፡ በመሆኑም ዕድገት በኮሌጅ ደረጃ ነው የሚያልቀው፡፡ የሙሉ የፕሮፌሰርነት ማዕረግ ብቻ ነው ወደኛ የሚመጣው፡፡

ከዚህ ሌላ አንድ ዩኒቨርሲቲ ታዋቂ የሚሆነው የምርምር ዩኒቨርሲቲ ሲሆን ነው፡፡ ለዚህም የምርምር ምክትል ፕሬዚዳንት ቢሮን እንደገና በማደራጀት በዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስር ላይ እንዲያተኩር በማድረግ፣ በተለይ ለተመራማሪዎች የተለያዩ የምርምር ማበረታቻዎች በማዘጋጀታችን የምርምር ሥራችን ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ መጥቷል፡፡ አንድ ተመራማሪ በታወቁ የምርምር መጽሔቶች (ጆርናሎች) ላይ ካሳተመ የሚሰጠው ማበረታቻ አለ፡፡ ለምሳሌ ባለፈው ዓመት ከሦስት ሚሊዮን ብር በላይ ለተመራማሪዎች ማበረታቻ ሰጥተናል፡፡ ስለዚህ እነዚህ ዓይነት ነገሮች ተመራማሪውን እያበረታቱት ይገኛሉ፡፡ የድጋፍ ሰጪ ሠራተኞችን በተመለከተ ከዚህ በፊት እንደሚታወቀው ዩኒቨርሲቲው ከ50 እና ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑት ድጋፍ ሰጪዎች የኮንትራት ሠራተኞች ናቸው፡፡ እነዚህ የድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ደግሞ ከ20 እስከ 25 ዓመታት በኮንትራት ሲሠሩ የነበሩ ናቸው፡፡ የጡረታ መብትም አልነበራቸውም፡፡ በዚህም ምክንያት የሲቪል ሰርቪሱ ሕግ ተግባራዊ አይሆንም ነበር፡፡ በዚህም በኩል በገንዘብ፣ በሰው ኃይልና በንብረት አስተዳደር አያይዝም ይህንን ጉዳይ ለማስተካከል በከፍተኛ ደረጃ ሥራ ተሠርቷል፡፡

ከሲቪል ሰርቪስና ከትምህርት ሚኒስቴር እንዲሁም ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ጋር በመነጋገር ከዚህ በፊት ለ20 እና ለ30 ዓመታት በኮንትራት የሠሩ ሠራተኞች ብቁ ከሆኑና ለሥራው የሚመጥኑ ከሆነ፣ እየተወዳደሩ ወደ ቋሚ ሠራተኝነት እንዲቀየሩ ለማስፈቀድ ብዙ ጊዜ ወስዶብናል፡፡ በዚህ ሁኔታ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እነዚህ እስከ 30 ዓመታት የቆዩ የኮንትራት ሠራተኞችን እያወዳደርን ወደ ቋሚ ሠራተኝነት እንዲዛወሩ ተደርጓል፡፡ ከዚያም በኋላ በአጠቃላይ በአሁኑ ጊዜ የሲቪል ሰርቪሱን ሕግን ተግባራዊ በማድረግ ሕጉን እየከተልን ነው፡፡ የገንዘብ አስተዳደርን በተመለከተ እንዲሁ ነው፡፡ በጣም ለረዥም ዓመታት ኦዲት ያልተደረጉ ሒሳቦች ነበሩ፡፡ ኦዲትም ቢደረጉ እነዚያ ሒሳቦች ላይ ኦዲተሮች አስተያየት መስጠት አልቻሉም ነበር፡፡ ይህን ወደኋላ በመሄድ በአንዳንዶቹ ከ1978 ዓ.ም. ጀምሮ እነዚህን ሒሳቦች የማስተካከል ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከሞላ ጎደል ሒሳቦቹ እየተስተካከሉ ለኦዲተሮች የማቅረቡ ሥራ እየተጠናቀቀ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አደረጃጀትን መቀየርና ማስተካከል ላይ ያተኮሩ በርካታ ሥራዎችን መሥራታችሁን ገልጸዋል፡፡ ብዙ ጊዜ እንዲህ ዓይነት የአደረጃጀትና የአሠራሮች መቀያየር ሲኖር የሚፈጠር ተቃውሞ ይኖራልና ከዚህ አንፃር እናንተን የገጠሙዋችሁ ፈተናዎች ምን ነበሩ?

ዶ/ር አድማሱ፡- አንደኛ የውስጥ አሠራሩን ለመቀየር የተከተልነው አካሄድ አሳታፊ ነበር፡፡ በአጠቃላይ ይህን ሥራ የሠሩት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የነበሩ፣ አሁንም ያሉ ሠራተኞች ናቸው፡፡ ስለዚህ የሚጠበቀውን ያህል ፈተና አልነበረውም፡፡ ነገር ግን የትምህርት ክፍሎችን በተለይ ጉልህ ሆነው የሚታዩ አንዳንድ ለብቻቸው የነበሩ ተቋማት ወደ ኮሌጅ ለማሰባሰብ በምንጥርበት ጊዜ ከአንዳንድ መምህራንም፣ ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞችም ትልቅ የሆነ ተቃውሞ ነበር፡፡ ያንንም በየጊዜው ውይይት በማድረግ፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ከጊዜ በኋላ ያለውንም ውጤት እያዩት ተቃውሞው እየቀነሰ መጥቷል፡፡ አሁንም ቢሆን ተቃውሞ አለ፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ የትምህርት ክፍሎች ለምንድነው ብቻችንን የማንሆነው? የሚሉ ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡ እኛ ደግሞ በውይይትና በሌሎች እያደጉ ባሉ አገሮች ያለውን የአካዴሚክ አደረጃጀት በማምጣትና በመወያየት እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ችለናል፡፡ አሁንም ቢሆን ጉዳዩ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የተቋጨ አይደለም፡፡ በየጊዜው የሚከለሱ ነገሮች አሉ፡፡ ይህን አደረጃጀት ተግባራዊ ስናደርግ አንድ በጣም ያጋጠመን ችግር ግን የሰው ኃይል እጥረት ነው፡፡ ምክንያቱም ኮሌጆች ራሳቸውን እንዲችሉ በምናደርግበት ጊዜ የራሳቸው የግዥ፣ የፋይናንስና የንብረት አስተዳደር ሠራተኞች ያስፈልጉዋቸዋል፡፡ አሁን በምንከፍለው ደመወዝ እነዚህን ብቁ ሠራተኞች ማግኘት አልቻልንም፡፡ በየጊዜው ሠራተኞች እየለቀቁ ይሄዳሉ፡፡ ስለዚህ ለኮሌጆች የሰጠነውን ራስን በራስ የማስተዳደር ሥልጣን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ አልቻልንም፡፡

ሪፖርተር፡- ለበርካታ ጊዜያት ኦዲት ያልተደረገ ሒሳብን ኦዲት በማስደረግ ላይ መሆናቸሁን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ አንፃር ለበርካታ ዓመታት ኦዲት ያልተደረገው የዩኒቨርሲቲው ሒሳብ ክፍተት ምን ይመስላል? በገንዘብስ ምን ያህል ጉድለት ያሳያል?

ዶ/ር አድማሱ፡- ያገኘነው ክፍተት ምንድን ነው? ለምሳሌ በመረጃዎች አመዘጋገብ ላይ በጣም ከፍተኛ ክፍተት ነበር፡፡ የክፍያዎች አለመወራረድ ነበር፡፡ ይህንን በተለያዩ ጊዜያት ኦዲት ለማድረግም ተሞክሮ ኦዲተሮች አስተያየት ለመስጠት አንችልም ብለው የተዋቸው ነገሮች ናቸው ብዙዎቹ፡፡ አሁን እነዚህን ወደኋላ ሄደን በደንብ አድርገን ዓይተን በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ውሳኔ የሚፈልጉ አሉ፡፡ በእኛ ሥልጣን ውሳኔ የሚሰጥባቸው ነገሮች አሉ፡፡ በእነዚያ ላይ ውሳኔ እንሰጣለን፡፡ ለቦርዱ የሚቀርቡ አሉ፣ ለመንግሥት የሚቀርቡም አሉ፡፡ አሁን ያንን ሁሉ እያስተካከልን አንድ ቦታ ላይ መቆም መቻል አለበት ብለን እየሠራን ነው፡፡ ወደኋላ ያለው እንግዲህ ኦዲት እየተደረገ ነው፡፡ ነገር ግን አንዳንድ መረጃዎችን ማግኘት አልቻልንም፡፡ አንዳንድ ጊዜ በቦታው የነበሩ ኃላፊዎችና የሒሳብ ሠራተኞች የሉም፡፡ አመዘጋገቡ የተመሰቃቀለ ነው፡፡ ያንን ሁሉ እያስተካከልን ነው፡፡ አሁን ባለንበት ሁኔታ በአጠቃላይ እስከ 2006 ዓ.ም. ድረስ ያለው ሒሳብ ተዘጋጅቶ ኦዲት እየተደረገ ነው፡፡ ይህን ስናደርግ በጣም የተቸገርነው የሙያተኞች አለመኖር ነው፡፡ የምንሰጠው ደመወዝ እጅግ በጣም አነስተኛ ስለሆነ አንድ ሠራተኛ ለስድስት ወራት የሚሆን አገልግሎት ሲኖረው ዩኒቨርሲቲውን ይለቃል፡፡

ሪፖርተር፡- ለተፈጠረው የፋይናንስ አስተዳደር ችርግና የኦዲት አለመደረግ ተጠያቂው ማን ነው?

ዶ/ር አድማሱ፡- ተጠያቂ ሊሆን የሚችለውን አካል ማወቅ የሚቻለው አጠቃላይ የኦዲት ሥራው ከተጠናቀቀ በኋላ ኦዲተሮች በሚሰጡት አስተያየት ነው፡፡ አሁን የራሳችንን የውስጥ ሥራ ሠርተናል፡፡ ለኦዲት ዝግጁ አድርገናል፡፡ ስለዚህ ኦዲተሮች አጠናቀው ሪፖርት በሚያደርጉበት ጊዜ ተጠያቂ የሚሆን አካል ካለ ያን ጊዜ ነው የምናውቀው፡፡

ሪፖርተር፡- በዩኒቨርሲቲው ተደጋጋሚ ግንባታዎች እየተካሄዱ ነው፡፡ ተጠናቀው ለአገልግሎት ዝግጁ የሆኑ ነገር ግን ሥራ ያልጀመሩ ሕንፃዎችም አሉ፡፡ ሌሎች አዳዲስ ግንባታዎችም በመካሄድ ላይ ናቸው፡፡ ተጀምሮ ለረዥም ጊዜ ሳይጠናቀቅ የቆየው የሪቻርድ ፓንክረስት መታሰቢያ ቤተ መጻሕፍት ግንባታም እንዲሁ አለ፡፡ ግቢው ውስጥ የሚካሄዱ ግንባታዎች የሚጠናቀቁት መቼ ነው? በግቢው የሚገኙ ክፍት ቦታዎች ሁሉ ሕንፃ እየተሠራባቸው ነውና ለዓይን ማረፊያ የሚሆን ቦታስ አያሳጣውም ወይ?

ዶ/ር አድማሱ፡- በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንደሚታወቀው እንደ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች የማስፋፋት ሥራ በስፋት አልተከናወነም፡፡ አዳዲስ ግንባታዎች አሉ፡፡ በተለይ በከፍተኛ ደረጃ ብዙ ግንባታዎች ያሉን በሠፈረ ሰላም ካምፓስ ነው፡፡ ከዚህ በፊት የተጀመሩ ግንባታዎች ነበሩ፡፡ በስድስት ኪሎና በአምስት ኪሎ የዶርሚተሪ፣ እንዲሁም በአራት ኪሎ ደግሞ የቤተ መጻሕፍት ግንባታዎችን ሲያከናውን የነበረው ማገር ኮን የተባለ ድርጅት ነበር፡፡ ያ ድርጅት እነዚህን ግንባታዎች ማጠናቀቅ ባለመቻሉ ውሉን አቋርጠን ጨረታ እያወጣን ነው፡፡ ምክንያቱም የገንዘብ አቅሙ በጣም ደካማ ነው፡፡ ብዙ ገንዘብ ከዚህ በፊት ወስዶ በዚያም መጨረስ አልቻለም፡፡ ስለሆነም ኮንትራቱን አቋርጠን አንድ ሁለት ጊዜ ጨረታ ብናወጣም ያንን ሥራ ለመሥራት ፈቃደኛ የሆኑ ኮንትራክተሮችን ለማግኘት አልቻልንም፡፡ አሁን የዕቃ ግዥ ኤጀንሲን አስፈቅደን በውስን ጨረታ እንደገና ጨረታ እያወጣን ነው፡፡

የዚህ የሪቻርድ ፓንክረስት መታሰቢያ ቤተ መጻሕፍት የሚገነባው ለኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ነው፡፡ የቤተ መጻሕፍቱ ግንባታ ከእኛ ቁጥጥር ውጪ ነው፡፡ ሼክ አል አሙዲ የሚያሠሩት ነው፡፡ ከሚድሮክ ጋር በተለያዩ ጊዜያት ውይይት አድርገናል፡፡ ከዚያም ብዙ ጊዜ ለማግኘት አልቻልንም፡፡ ግንባታውን መጨረስ አልቻሉም፡፡ ከተጀመረ ረዥም ጊዜው ነው፡፡ ኮሚቴም አቋቁመን መጨረስ ካልቻሉ እኛ በጀት ይዘን ማስጨረስ እንደምንችል አሳውቀናል፡፡ ይህንን እንግዲህ ለቦርድም አቅርበናል፡፡ በጀት አስይዘን እኛው መጨረስ አለብን ብለን ወስነን ለቦርድ አቅርበናል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በሚድሮክ እንደ አዲስ አደረጃጀት አለ ስለተባለ አንድ ዕድል ተጠቅመን በተወሰነ ደረጃ እነርሱን ለማግኘት እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ ከዚህ ጐን ለጐን ደግሞ የጨረታ ሰነድም እያዘጋጀን ነው፡፡ ምክንያቱም እነርሱ በአጭር ጊዜ የማይጨርሱልን ከሆነ እኛ ተረክበን በራሳችን በጀት ጨረታ አውጥተን አወዳድረን ለማጠናቀቅ ወስነናል፡፡ ግንባታቸው ያለቁትና አገልግሎት መስጠት ያልጀመሩትን  ሕንፃዎችን በተመለከተ ሥራ ለመጀመር የዘገዩበት ምክንያት የተለያዩ ሲሆን፣ አንደኛው የመብራት ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት አዲሱ የመዝገብ ቤት ሕንፃና የቤተ መጻሕፍት ሕንፃ እንዲህ ዓይነት ችግር አለበት፡፡ ግቢው ከግንባታ መቼ ነፃ ይሆናል ለሚለው፣ እኛ ግቢውን ከግንባታ ነፃ ማድረግ አለብን ብለን አናስብም፡፡ ምክንያቱም በሌሎች ከፍተኛ ተቋማት ላይ ያለው የማስፋፋት ሥራ በዩኒቨርሲቲው መካሄድ አለበት ብለን እናምናለን፡፡ ምክንያቱም ሁሉም ካምፓሶች የማስፋፋት ሥራ ይፈልጋሉ፡፡ በዚህም መሠረት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በመነጋገር በ68 ሔክታር መሬት በተለያዩ ካምፓሶች የማስፋፋትሥራ ለመሥራት ተፈቅዶልናል፡፡

ሪፖርተር፡- ዩኒቨርሲቲውን የምርምር ማዕከል ለማድረግ እየሠራችሁ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡ ነገር ግን የሚካሄዱት ምርምሮች ችግር ፈቺ ካለመሆናቸውም በተጨማሪ፣ ድግግሞሽና የመቀዳዳት ልማድ ይታይባቸዋል የሚባል ነገር አለ፡፡ ከመጀመርያ ዲግሪ ጀምሮ እስከ ዶክትሬት ዲግሪ ድረስ የተማሪዎችን ምርምር ለአገር ጠቃሚ ከማድረግ አንፃር ዩኒቨርሲቲው ምን እየሠራ ነው?

ዶ/ር አድማሱ፡- እነዚህ የምርምር ሥራዎች ከአገሪቱ የዕድገት አቅጣጫዎች ጋር መያያዝ አለባቸው፡፡ ለዚህም ቅድሚያ የሚሰጣቸው ምርምሮች ዝርዝር አውጥተናል፡፡ በአጠቃላይ በዶክትሬት ዲግሪ ይሁን በሁለተኛ ዲግሪ የሚሠሩ ምርምሮች ቅድሚያ በሚሰጣቸው ጉዳዮች መሠረት ነው መሄድ ያለባቸው ብለን እየገመገምን፣ በዚህ መሠረት የማይሄዱ ከሆነ እንዳይጀመሩ እናደርጋለን፡፡ ግን እዚህ ላይ አሁን በተለይ በማኅበራዊ ሳይንስ አካባቢ የሚሠሩ ምርምሮች አሉ፡፡ እነዚህን ለማስተሳሰር አንድ የምርምር ተቋም አቋቁመናል፡፡ ከዚህ በፊት እየተደረገ የነበረው ምንድነው? ማኅበራዊ ሳይንስ ውስጥ የተመዘገቡ የዶክትሬት ወይም የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎች በራሳቸው ፍላጎት የራሳቸውን የምርምር ጥያቄ አምጥተው ከፕሮፌሰሮች ጋር ተነጋግረው የሚሠሩት ምርምር ነው የነበረው፡፡ ይህ ደግሞ ለአገሪቷ የሚጠቅም ቢሆንም በተደራጀ ሁኔታ በአጭር ጊዜ የአገሪቷን ችግር የሚፈታ አልነበረም፡፡ በሳይንስና በጤና በጣም ብዙ ምርምሮች አሉ፡፡ በተለይ በሳይንስ በታወቁ መጽሔቶች ላይ የሚታተሙ ምርምሮች ተሠርተዋል፡፡ አንዳንድ የጥናት ቡድኖች አጥኚዎቻቸውን ወደዚህ እየላኩ ነው፡፡ የዚህ ዩኒቨርሲቲ ውጤትና በከፍተኛ ደረጃ በሚታወቁ መጽሔቶች ላይ ማሳተም እንዴት ነው እየጨመረ የመጣው የሚለውን ለማጥናት እየመጡ ነው፡፡ መታተም ብቻ ሳይሆን ከታተሙ በኋላ ምን ያህል ፕሮፌሰሮች አልያም ተቋማት ናቸው ያንን አንብበው የተጠቀሙበት? የምርምር ውጤቶች አንድ መጽሔት ላይ ሊታተሙ ይችላሉ፡፡ ማንም ካላነበባቸውና አንብቦ ደግሞ ለሌላ ሥራ ካላዋላቸው ጠቃሚ አይደሉምና በዚያም በጣም ጠቃሚ ምርምሮች በሳይንሱ ዘርፍ አሉ፡፡ የምርምር ውጤቶችን በተመለከተ ትንሽ ችግር ያለብን በኢንጂነሪንግና በማኅበራዊ ሳይንስ መስክ ነው፡፡ በእነዚህ መስኮች የምርምር ሥራዎች አነስ ብለው ይታያሉ፡፡ እነዚህን እንግዲህ ለማበረታታት ሥርዓት ዘርግተናል፡፡ እነርሱም በቂ ካልሆኑ ከልሰን እንዴት ማበረታታት አለብን የሚለውን በጋራ እያየን ነው ያለነው፡፡

ሪፖርተር፡- በአገሪቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን በተመለከተ ከተለያዩ አካላት የሚነሳው አንዱና ዋነኛው ጉዳይ የማስተማር ነፃነት (Academic Freedom) ነው፡፡ ከዚህ አንፃር በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያሉ መምህራን የማስተማር ነፃነት እንዴት ይገለጻል?

ዶ/ር አድማሱ፡- እንግዲህ በማስተማር ነፃነት ላይ ብዙ ጊዜ የሚነሱ ጉዳዮች አሉ፡፡ ለምሳሌ ከካሪኩለም ቀረፃ አንፃር በአጠቃላይ የመምህራን ምርምር የመሥራት ነፃነትና የመከራከር ነፃነት መታየት መቻል አለበት፡፡ እንግዲህ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተለየ ሁኔታ የመምህራንን ወይም የተመራማሪዎችን ነፃነት የሚሸረሽር ነገር ብዙም ያለ አይመስለኝም፡፡ አንዳንድ ጊዜ የተሳሳተ ግንዛቤ ያላቸው የማስተማር ነፃነትን ለሌላ ጉዳይ ለመጠቀም የሚፈልጉ አሉ፡፡ በተለየ ሁኔታ በጣም ጠበቅ አድርጎ በዚህ መንገድ ነው መሄድ ያለብህ፣ በዚህ ነው መሥራት ያለብህ እንዲህ ነው የሚባል ነገር እስካሁን አልነበረም፡፡ ነገር ግን መኖር አለበት ብዬ ነው የምገምተው፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለአገር ጥቅም ወይም ለዕድገታችን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ከተፈለገ ሥርዓት መምጣት አለበት፡፡ የማስተማር ነፃነት ከሥርዓት ውጪ አይደለም፡፡ የተወሰነ ሥርዓት አለ፡፡ በዚያ ሥርዓት መሠረት መሠራት ያለበት ጉዳይ መሆን አለበት ብዬ ነው የማምነው፡፡

ሪፖርተር፡- ቀደም ሲል እንደገለጹት የአንድ መምህር ተባባሪ ወይም ረዳት ፕሮፌሰርነት ማዕረግ በኮሌጅ ደረጃ እንደሚፀድቅ፣ የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ደግሞ ወደ ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ይመጣል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ዩኒቨርሲቲው ለእነዚህ ማዕረጎች ያስቀመጣቸው መሥፈርቶች ምን ምን ናቸው?

ዶ/ር አድማሱ፡- የሴኔት ሕጋችን ላይ መሥፈርቱ አለ፡፡ አንደኛው የምርምር ወረቀቶችን ማሳተም መቻል አለበት፡፡ ለምሳሌ ፕሮፌሰር ለመሆን አምስት የምርምር ውጤቶችን ማሳተም ይኖርበታል፡፡ ሁለተኛ ደግሞ እነዚህ ኅትመቶች ታዋቂ በሆኑ መጽሔቶች ላይ መታተም አለባቸው፡፡ የመጽሔቱን ታዋቂነት ደግሞ የትምህርት ክፍሉ ወይም ኮሌጁ ማረጋገጥ አለበት፡፡ ሌላው ደግሞ እነዚህ ወረቀቶች በሁለት የውጭ ገምጋሚዎች ይገመገማሉ፡፡ ምን አዲስ ነገር አመጡ የሚለው ጉዳይም በሁለት የአገር ውስጥና በሁለት የውጭ ገምጋሚዎች መገምገም አለባቸው፡፡ ይህ እንግዲህ የምርምር ኅትመቶችን በተመለከተ ነው፡፡ ሌላው የተማሪዎች ግምገማ አለ፣ የሥራ ባልደረባ ግምገማ አለ፣ የኅብረተሰብ አገልግሎት አለ፡፡ ያ ሁሉ ተደማምሮ ነው ለዕድገት የሚያበቃው፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ የፕሮፌሰርነት ማዕረግ ጋር በተገናኘ ዶ/ር መረራ ጉዲና የሚያነሱት ጥያቄ አለ፡፡ ዩኒቨርሲቲው ጡረታዬን ካላማራዘሙ በተጨማሪ የፕሮፌሰርነት ማዕረጌንም ከልክሎኛል የሚል ጥያቄም ያነሳሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የዩኒቨርሲቲው ምላሽ ምንድነው?

ዶ/ር አድማሱ፡- እንግዲህ ከላይ እንደገለጽኩት የዕድገት ጥያቄዎች በኮሌጅ ይታዩና ሴኔቱ ያቋቁመው የሴኔት ቋሚ ኮሚቴ ያየዋል፡፡ በዚህ መንገድ ይቀርብና በደንብ ይገመገማሉ፡፡ በሚገመገሙበት ጊዜ አንደኛ አንዳንድ ጊዜ ለምሳሌ አንድ ፕሮፌሰር ለመሆን ጥያቄ የሚያቀርብ ሰው መጽሐፍ አሳትሜያለሁ ይላል፡፡ ለዚህ ነጥብ ይሰጠዋል፡፡ እንደገና ደግሞ ወረቀቶችን በታወቁ መጽሔቶች ላይ አውጥቻለሁ ይላል፡፡ ያን መጽሐፍ በመጻፉ ነጥብ ሰጥተነዋል፡፡ እንግዲህ መጽሐፉ ውስጥ ያለው ነገር ደግሞ በሌላ መጽሔት ስላሳተመ ነጥብ አይሰጠውም፡፡ ይህ ማለት ምን ማለት ነው? ለአንድ ሥራ ሁለት ነጥብ አይሰጥም ማለት ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ በነገራችን ላይ እንዲህ ዓይነት ነገሮችን የሚያየው ኮሚቴው ነው፡፡ የዶ/ር መረራ ጉዳይም በኮሚቴዎች እጅ ነው ያለው፡፡ ስለዚህ የአሠራር ሥርዓቱ ግልጽ ስለሆነ ቅሬታ ቢኖራቸው እንኳን ቅሬታቸው የሚታይበት ክፍል አለ፡፡

ሪፖርተር፡- ለስምንት ወራት ያህል ዩኒቨርሲቲው ደመወዛቸውን እንዳልከፈላቸውም ይገልጻሉ፡፡ ለዚህስ ዩኒቨርሲቲው የሚሰጠው ምላሽ ምንድነው?

ዶ/ር አድማሱ፡- እንግዲህ እኛ በዚህ አልተከፈለኝም በተባለው ደመወዝ ላይ ዶ/ር መረራ ያው የጡረታ ጊዜያቸው እንዳልተራዘመ ተነግሯቸዋል፡፡ ቀደም ብሎ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ከዚያ በኋላ ሠርተው ያልተከፈላቸው ካለ እንዴት ሊሠሩ ቻሉ የሚለውን ነገር በደንብ ማየቱ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ጡረታ እንደሚወጡ ቀደም ብሎ ተነግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ ዶ/ር መረራ አንድ የዶክትሬትና አራት የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን እያማከሩ እንደሆነ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል፡፡ ታድያ ተማሪዎቹን ማን መደበላቸው?

ዶ/ር አድማሱ፡- እንግዲህ ይህንን ዝርዝር ጉዳይ እኛ አናውቅም፡፡ ዋናው ነገር ሕግና ሥርዓቱን ማስከበር ነው፡፡ ደመወዝ እንዴት ይከፈላል? የት ላይ ያቆማል? ጡረታ እንዴት ይራዘማል? የሚለውን ጉዳይ በተመለከተ ነው ባለው አሠራር የምንሄደው፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚሁ ጋር በተያያዘ ዩኒቨርሲቲው ከዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ጋርም ውዝግብ ውስጥ ገብቷል፡፡ የእርሳቸውስ ጉዳይ ከምን ጋር የተያያዘ ነው?

ዶ/ር አድማሱ፡- የዶ/ር ዳኛቸውም ጉዳይ ከጡረታ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ አንድ መምህር ለሰባት ዓመታት ካገለገለ በኋላ ዩኒቨርሲቲው የሚሰጠው የአንድ ዓመት የምርምር ፈቃድ አለ፡፡ የምርምር ፈቃድ የሚሰጠው ለምንድነው? በአጠቃላይ ምርምር ሠርቶ የራሱን ዕውቀት አዳብሮ እንደገና ተመልሶ ያስተምራል ከሚል ታሳቢነት የሚሰጥ ፈቃድ ነው፡፡ በመሆኑም የጡረታ ጊዜው ላልተራዘመለት ሰው ይህ ፈቃድ አይሰጠውም፡፡ ስለዚህ እኔ እስከማውቀው ድረስ የዶ/ር ዳኛቸው ጉዳይም ከዚያ የተለየ አይደለም፡፡ የእነዚህ መምህራን ጉዳይ ልዩ የሚያደርገው ምን እንደሆነ አልገባኝም፡፡ ምክንያቱም በርካታ መምህራን ከጤና ሳይንሱም ከሳይንሱም በዚህ አሠራር የጡረታ ጊዜያቸው ያልተራዘመላቸው አሉ፡፡

 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች