በዓለማችን በርዝማኔው ወደር የሌለው የውኃ ተፋሰስ የዓባይ ወንዝ ወይም ናይል የአፍሪካ አኅጉርን አንድ አሥረኛ እንደሚሸፍን ይነገርለታል፡፡ ማለትም የዓባይ የውኃ ተፋሰስ 3,038,100 ካሬ ኪሎ ሜትር የሚሸፍን በአሥራ አንድ አገሮች የሚገኙ ከ400 ሚሊዮን በላይ የሆኑ ሕዝቦች ሀብት ነው፡፡
ይሁን እንጂ ኢፍትሐዊነት በነገሠበት የአጠቃቀም ሥርዓት የተፋሰሱ ተጋሪ የሆነችው ግብፅ ለብዙ ሺሕ ዓመታት የተፋሰሱ ውኃ ዋነኛ ተጠቃሚ ሆና ቆይታለች፡፡
በቅርቡ በአዲስ አበባ ሒልተን ሆቴል ተካሂዶ በነበረው የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታን የተመለከተ የሙህራን ሲምፖዚየም ላይ የጥናት ጽሑፋቸውን ያቀረቡት የውኃ (ሃይድሮ) ፖለቲካ ተመራማሪና ተንታኝ የሆኑት ታዋቂው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር ዶ/ር ያቆም አርሳኖ፣ በተፋሰሱ ያለውን ኢፍትሐዊ የውኃ አጠቃቀም እንደሚከተለው ገልጸውት ነበር፡፡ ‹‹የዓባይ ተፋሰስ የውኃ ገብነትና የበርሃማነት ሁለት ተቃራኒ ጫፎችን በአንድ የሚያስተሳስር ቢሆንም፣ ሁለቱን ጫፎች በአንድ ማስተሳሰርና የጥቅም ተጋሪ ማድረግ አዳጋች ሆኖ ለዘመናት ቆይቷል፤›› በማለት፡፡
ይህ በዓለማችን በርዝማኔው ወደር የሌለው የውኃ ተፋሰስ የ400 ሚሊዮን ሕዝቦች የጋራ ሀብት እንደመሆኑ መጠን የጋራ ባለቤቶቹ የሆኑት ሕዝቦች በፍትሐዊነትና አንዱ በአንዱ ላይ ጉዳት ባለማድረስ ሊጋሩት የሚችሉት ሀብት መሆኑ እሙን ነው፡፡
ኢትዮጵያ ለዚህ ተፋሰስ የአንበሳውን ድርሻ ማለትም 86 በመቶውን የምታበረክትና የ90 ሚሊዮን ሕዝቦች አገር ብትሆንም፣ ይህንን ሀብቷን ከሦስት ሺሕ ዓመት በላይ ሳትጠቀምበት ቆይታለች፡፡ ኢትዮጵያ የዓባይን ተፋሰስ የመጠቀም ጽኑ ፍላጐቷን ለበርካታ መቶ ዓመታት ስታንፀባርቅ ብትቆይም፣ በተለያዩ ምክንያቶች በዋናነትም በአቅም ማጣትና በውጭ የፖለቲካ ተፅዕኖ ተገድባ የኖረች አገር ናት፡፡ የተለያዩ የኢትዮጵያ መንግሥታትና ነገሥታት ተፋሰሱን የማልማት ጽኑ ፍላጐታቸውን በሚገልጹበት ወቅት ዘንግተውት የማያውቁትና እስካሁንም ጽኑ የሆነው አቋም፣ በተፋሰሱ ተጋሪ አገር ሕዝቦች ላይ ጉዳት ያለማድረስ መርሆ እንደሆነ ታሪካዊ ማስረጃዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ መምህሩ ዶ/ር ያቆብ ይህንኑ ተንትነው ያስረዳሉ፡፡ ኢትዮጵያ በ1894 ዓ.ም. የዓባይ ተፋሰስንም ሆነ ገባሪ ወንዞችን ፍሰት ላለመግታት በይፋ ቃል ገብታ እንደነበር ይጠቅሳሉ፡፡ ግብፅና ሱዳን በ1949 ዓ.ም. ተፋሰሱን በብቸኝነት ለመጠቀም በድብቅ ሲደራደሩም፣ በከፍተኛ ተቃውሞ መግለጫ አውጥታ እንደነበር ይኸውም መግለጫ ኢፍትሐዊ አጠቃቀምን የሚቃረንና ኢትዮጵያም የተፋሰሱን ውኃ በወቅቱ ለነበረው ትውልድም ሆነ ለመጪው ትውልድ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንደምታለማው የሚገልጽ እንደነበር ዶ/ር ያቆብ ያስረዳሉ፡፡
ከዚህ ባለፈም ግብፅ በ1972 ዓ.ም. ከዓባይ ተፋሰስ የምታገኘውንና በታላቁ የአሰዋን ግድብ የሚንጣለለውን ግዙፍ ውኃ በካናል (በቦይ) ወደ ሲናይ በረሃ በመውሰድ ለማልማት አዘጋጅታው የነበረውን ዕቅድ በመቃወም በወቅቱ በሌጐስ ተካሄዶ ለነበረው የተባበሩት መንግሥታት ጉባዔ አቤቱታ በማሰማት ፍትሐዊነትን ብትጠይቅም፣ በወቅቱ የነበረው የግብፅ መንግሥት ምላሽ ‹‹ኢትዮጵያ የግብፅን የመጠቀም መብት ካልተቀበለች ገደል ልትገባ ትችላለች፤›› የሚል አሳፋሪ ምላሽ እንደነበር ዶ/ር ያቆብ በሲምፖዚየሙ ላይ አስታውሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት በመጋቢት ወር 2003 ዓ.ም. የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታን ይፋ ባደረገበት ወቅትም ለፍትሐዊ አጠቃቀም ለዘመናት ሲንፀባረቅ የቆየውን የኢትዮጵያ ጽኑ አቋም ያልዘነጋ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከአዲስ አበባ በ850 ኪሎ ሜትር በሚርቀው በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ውስጥ በምትገኘው ጉባ መንደር እውን እየሆነ ያለው የዓባይ ውኃ ልማት ፕሮጀክትን ለመገንባት ተወጥኖ የነበረው በ1956 ዓ.ም. እንደነበር ያስታወሱት ዶ/ር ያቆብ፣ ከቀድሞው ዕቅድ እጅግ ብዙ እጥፍ ሆኖ ዛሬ ላይ የኢትዮጵያን የተፋሰሱ ተጋሪነት ሊያረጋግጥ እየተቃረበ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ይፋ ሆኖ ወደ ትግበራ መግባት በዘመናት የቆየውንና የአንድ አገር የብቻ ሀብት መስሎ የሚታየውን ፖለቲካዊ አስተሳሰብና እምነት በመቀየር ላይ ጉልህ ምልክት እንደሆነ የተለያዩ ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ተንታኞች ይገልጻሉ፡፡
‹‹በአንድ አገር የበላይነት ሥር ወድቆ ዘመናትን ያስቆጠረውን የፖለቲካ ቅኝት የቀየረ፤ የሰሜንና የምሥራቅ አፍሪካን የውኃ ፖለቲካ ወደ ፍትሐዊነት ያሸጋገረ በአኅጉራችንና በኢትዮጵያ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ምልክት ነው፤›› ሲሉ ዶ/ር ያቆብ የህዳሴውን ግድብ ይገልጹታል፡፡
የአፍሪካ የውኃ ማማ የምትባለውን ኢትዮጵያንና በዓባይ ተፋሰስ ሀብት ላይ ተስፋዋን የሰነቀች የበርሃ ጫፍ ላይ ያለችውን ግብፅ ከዚህ ወዲህ በፍትሐዊነት መርህ የሚያስተሳስር መቀነት እንደሆነም ሌሎች ይገልጹታል፡፡
የታላቁ ህዳሴ ግድብ የዘመናት የኢፍትሐዊነት ቀንበርን በመስበር ኢትዮጵያንም ሆነ ሌሎች የተፋሰሱ ተጋሪ አገሮችን ነፃ ከማውጣት ባሻገር ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ፋይዳው ምንድን ነው?
የህዳሴው ግድብ ከፖለቲካ ሚዛንነቱ ባሻገር
ከሱዳን ድንበር 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከአዲስ አበባ በስተምዕራብ ነቀምትና አሶሳ ከተሞችን በማቋረጥ በ850 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ጉባ በምትባል መንደር አንድ መለስተኛ ከተማ ተመሥርቷል፡፡ በሰንሰለታማና ድርብርብ ተራሮች ተከቦ ከባህር ወለል በ650 ሜትር ከፍታ ላይ በተመሠረተው የጉባ መለስተኛ ከተማ ውስጥ ዘጠኝ ሺሕ ሰዎች ለአንድ ዓላማ ከትመዋል፡፡
በዚህ መለስተኛ ከተማ እንደማንኛውም ከተማ ሁሉም ነገር አለ፡፡ ባንኮች፣ የሕክምና ማዕከላት፣ ፖሊስ ጣቢያ፣ የመዝናኛ ማዕከላት፣ የትራፊክ ጽሕፈት ቤትና የመሳሰሉት፡፡ በዚህ መለስተኛ ከተማ ሁሉም ነገር ቢኖርም ግን ሁሉም ነገር በሥርዓትና በከፍተኛ ዲሲፕሊን ነው የሚፈጸመው፡፡ በዚህ መለስተኛ ከተማ መዝናኛ ቦታዎች ቢኖሩም፣ ማንኛውም ሰው ከምሽቱ 12 ሰዓት በፊት ቢራ ለመጠጣት አይፈቀድለትም፤ የመዝናኛ ቦታዎችም እንዳይሸጡ ይገደዳሉ፡፡ በዚህ መለስተኛ ከተማ ጫት መግባት አይችልም ሲቅም የተገኘም በዚህ መለስተኛ ከተማ የመጨረሻ ቆይታው ይሆናል፡፡
ይህ ሁሉ የሚሆነውና 24 ሰዓት ሙሉ ከተማዋ እንቅስቃሴ ውስጥ ሆና የምትታየው ኢትዮጵያ በዚህ መንደር ልታቆመው ያሰበችውን የህዳሴ ግድብ እውን ለማድረግ ነው፡፡ ይህ ግድብ ከሦስት ዓመት በኋላ ማለትም በ2011 ዓ.ም. ሲጠናቀቅ 145 ሜትር ከፍታ የሚኖረው ግድብ፣ 1.8 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚኖረውና አጠቃላይ ውኃ ለመያዝ ዝግጁ የሚሆን 1,874 ካሬ ኪሎ ሜትር ቦት ይፈጠራል፡፡ ይህም ማለት 1,874 ካሬ ኪሎ ሜትር ላይ የሚንጣለል 74 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ ውኃ የሚይዝ ሰው ሠራሽ ሀይቅ ይፈጠራል፡፡
ይህንን በቀላሉ ለማስረዳት ያህል የህዳሴው ግድብ ከፍታ ማለት ስድስት የአክሱም ሀውልት ከግማሽ ድምር ቁመትን ያክላል፡፡ ውኃው የሚያርፍበት 1,874 ካሬ ኪሎ ሜትር ማለት ደግሞ 156 ሺሕ የእግር ኳስ ሜዳዎችን ያክላል ማለት ነው፡፡ የሚይዘው ውኃ ደግሞ በኦሎምፒክ ደረጃ የሚገነቡ 29 ሚሊዮን የመዋኛ ገንዳዎች የሚይዙትን የውኃ መጠን ያክላል፡፡
የዚህ የውኃ መጠን መሠረታዊ ዓላማ ኃይል የማመንጨት ቢሆንም፣ ለተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለሚሰጡ ልማቶች ግን ማዋል ይቻላል፡፡
ከስፔን እስከ ቱርክ
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግንባታው በተያዘለት የጊዜ ገደብ ከሦስት ዓመት በኋላ ቢጠናቀቅም፣ የታቀደውን የኃይል አቅርቦት ለማመንጨት ግድቡ በሙሉ አቅሙ መያዝ ያለበትን የውኃ መጠን መሙላት ይኖርበታል፡፡ በሙሉ አቅሙ ማመንጨት ሲጀምር ግን ስድስት ሺሕ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይልና በአማካኝ 15,692 ጊጋ ዋት በሰዓት ኢነርጂ በዓመት በማመንጨት ለአገር አቀፍ የኤሌክትሪክ ትስስር ሥርዓት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ይታመናል፡፡ ይህ በመሆኑም አሁን ያለውን አገራዊ የኤሌክትሪክ ሽፋን ከ54 በመቶ ወደ 75 በመቶ ከፍ ማድረግ ይቻላል፡፡
ሰሞኑን ተካሂዶ በነበረው የሙህራን ሲምፖዚየም ላይ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚፈጥረው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን የተመለከተ ጥናታዊ ጽሑፍ የቀረቡት የቀድሞው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበሩት አቶ ምሕረት ደበበ፣ የህዳሴው ግድብ የኢትዮጵያን የኃይል ፍላጐት ከማረጋገጡ በላይ ኢትዮጵያን በዓለም የኃይል አቅርቦት ገበያ የሚያስተዋውቅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዚህም የተነሳ ኢትዮጵያን እንደ ምሥራቅ አፍሪካ የኤሌክትሪክ ኃይል ማዕከል ያስተዋውቃታል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በምሥራቅ አፍሪካ ፓወር ፑል ውስጥ እየተሳተፈች መሆኑንና ይህንን እውን ለማድረግ ከወላይታ እስከ ኬንያ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መንገድ እየተገነባ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይህ መሆኑም ኢትዮጵያን በአካባቢያዊ የኃይል ኔትወርኮች ማለትም ከደቡብና ከሰሜን አፍሪካ የፓወር ኔትወርኮች ጋር እንድትገናኝ እንደሚያደርጋት ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ከህዳሴው ግድብ የሚመነጨው ኃይልን በሱዳን – ግብፅ – ሊቢያ – ሞሮኮና ስፔን ድረስ መሸጥ እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡ በሌላ መስመር በሱዳን – ግብፅ – ጆርዳን – ሶሪያና ቱርክ ድረስ የኤሌክትሪክ ኃይል ማቅረብ ይችላል፡፡
አቶ ምሕረት የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለዓለም ገበያ ቢቀርብ ምን ያህል ገቢ እንዲሁም የጂዲፒ አስተዋጽኦ ይኖረዋል የሚለውን ተንትነው አስቀምጠዋል፡፡
ከግድቡ የሚመነጨው ኃይል በአምስት የአሜሪካ ሳንቲም በኪሎ ዋት ሰዓት ማለትም በአሁኑ ወቅት ለጂቡቲ እየተሸጠ ባለበት ምጣኔ ለዓለም ገበያ ቢቀርብ፣ በዓመት 765 ሚሊዮን ዶላር ማግኘት እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡
ከላይ የተጠቀሰው የመሸጫ ዋጋ ለኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ላላት ጂቡቲ የተሰጠ በመሆኑ ትክክለኛውን የዓለም ገበያ ዋጋ አያንፀባርቅም፡፡ በአሁኑ ወቅት የዓለም ገበያ ለኤሌክትሪክ ኃይል በኪሎ ዋት ሰዓት የሚሰጠው አማካኝ ዋጋ 20 የአሜሪካን ሳንቲም መሆኑን የገለጹት አቶ ምሕረት፣ በዚህ የዋጋ ተመን መሠረት ከህዳሴው ግድብ የኃይል ሽያጭ 3.06 ቢሊዮን ዶላር በዓመት ማግኘት እንደሚቻል ይኸውም በጂዲፒው ላይ የስድስት መቶኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡ ይህ ከሆነ የህዳሴው ግድብን እውን ለማድረግ የሚጠይቀውን 4.38 ቢሊዮን ዶላር ከሞላ ጐደል ከሁለት ዓመት ባነሰ ጊዜ መመለስ ይቻላል፡፡
የዓሳ ሀብት ልማት
በኢትዮጵያ የዓሳ ፍላጐትና ምርት አለመጣጣም የተነሳ የነፍስ ወከፍ የኢትዮጵያውያን ዓመታዊ የዓሳ ፍጆታ 40 ግራም ብቻ እንደሆነ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ 38 ሺሕ ቶን ዓሳ በዓመት እንደሚመረት በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የዓሳ ሀብት ልማት ላይ ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ዮሴፍ ተክለ ጊዮርጊስ ይገልጻሉ፡፡
የህዳሴው ግድብ እውን መሆን በራሱ ይህንን የዓሳ ምርት ፍላጐትና አቅርቦት መካከል ያለ አለመጣጣም በመቅረፍ ረገድ አስተዋጽኦው የጐላ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡ እንደሳቸው አባባል በአሁኑ ወቅት በዓባይ ተፋሰስ ውስጥ ዘጠኝ ዓይነት የዓሳ ዓይነቶች ይገኛሉ፡፡
በዚህ ተፋሰስ ውስጥ ካሉት የዓሳ ዓይነቶች መካከል በትንሹ ከአምስት ኪሎ ግራም እስከ አሥር ኪሎ ግራም የሚመዝኑ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ አምባዛ የሚባለው የዓሳ ዓይነት እስከ ሃያ ኪሎ ግራም እንደሚመዝን፣ በጣም ተወዳጅና ጣፋጭ የሚባለው በዚሁ ተፋሰስ የሚገኝ ዓሳ ናይል ፐርች የሚባለው ሲሆን፣ እስከ 100 ኪሎ ግራም ሊመዝን እንደሚችል ዶ/ር ዮሴፍ በጥናታቸው ገልጸዋል፡፡ አንድ ኪሎ ግራም የናይል ፐርች ዓሳ በኢትዮጵያ እስከ 300 ብር ያወጣል፡፡
የህዳሴው ግድብ የሚያጠራቅመው ውኃ ምንም ዓይነት ሰው ሠራሽ ጣልቃ ገብነት ሳይጨመርበት በዓመት 6,540 ቶን ማግኘት እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡ በዚህ የህዳሴ ግድብ ውኃ ላይ በሰው ሠራሽ መንገድ የዓሳ ልማት ማካሄድ ከተቻለ ደግሞ በዓመት 30 ሺሕ ቶን ዓሳ ማለትም በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የሚመረተውን ዓሳ መጠን እጥፍ ሊያደርገው እንደሚችል ዶ/ር ዮሴፍ በጥናታቸው ጠቁመዋል፡፡ በዚህም መሠረት ከግድቡ ውኃ የሚለማ የዓሳ ሀብትን ወደ ውጭ በመላክ እስከ 100 ሺሕ ዶላር ዓመታዊ ገቢ ማግኘት ይቻላል፡፡
ቱሪዝም
በዓለማችን የቱሪዝም መስህብ ከሆኑ ኃይል ማመንጫ ግድቦች ግንባር ቀደም ተጠቃሹ የአሜሪካው ሁቨር ዳም ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ1935 በኔቫዳና አሪዞና ግዛቶች ድንበር ላይ በሚፈሰው ኮሎራዶ ወንዝ ላይ በቅንፍ ዲዛይን የተገነባ ግድብ ነው፡፡
ይህ ግድብም በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ ግዙፍ የኢንጂነሪንግ ጥበብ ውጤትና ወሳኝ ብሔራዊ ክስተት ተብሎ ተመዝግቧል፡፡ የዚህን ግድብ የምሕንድስና ጥበብና የያዘው ውኃ የሚፈጥረው ምቹ አየር ለመጐብኘት በዓመት ሰባት ሚሊዮን ጐብኚዎች ይታደማሉ፡፡
ይህንኑ ዓይነት የቱሪዝም እንቅስቃሴ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ መፍጠር እንደሚቻል የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሰሞኑን በግድቡ ስፍራ ለተገኘው የጋዜጠኞች ቡድን አስረድተዋል፡፡ ጐብኚዎችን በግድቡና በኃይል ማመንጫ ቤቶች ውስጥ ለውስጥ በማስጐብኘት ገቢ ማግኘት መታሰቡን የሚገልጹት ሥራ አስኪያጁ፣ የኢንጂነሪንግ ተቋማት ትምህርታዊ ጉብኝት የሚያደርጉበት ሁኔታ እንደሚፈጠር ገልጸዋል፡፡
በምሽት ደግሞ በውኃው ላይ የተለያዩ ሰው ሠራሽ ቀለማማ ብርሃኖችን በመፍጠርና ከተለዋዋጭ ብርሃኖቹና ከውኃው ፍሰት ጋር የሚቀናጅ ማጀቢያ ሙዚቃ በማከል የጐብኚዎችን ቀልብ ለመግዛት መታሰቡንም ተናግረዋል፡፡
በአካባቢው የሚከማቸው የውኃ መጠንንና ተራራማው መልክዓ ምድር አዕዋፍን በመሳብ የቱሪስቶችን ቀልብ ሊገዛ እንደሚችልም ገልጸዋል፡፡ የህዳሴ ግድቡና ቱሪዝም በሚል ጥናት ያካሄዱት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህሩ ዶ/ር ሙሉጌታ ፍስሃም ግድቡ ከፍተኛ የቱሪዝም ሀብትን ማግኘት እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡