በአዲስ አበባ ከተማ ያለውን የመኪና ማቆሚያ (ፓርኪንግ) ችግር ለመፍታት፣ ለግል ባለሀብቶች መሬት በልዩ ሁኔታ እንደሚቀርብ ተገለጸ፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታው ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የመኪና ማቆሚያ የሚገነባባቸው ቦታዎች ተለይተው ታውቀዋል፡፡
እነዚህን ግንባታዎች በግል ባለሀብቶችና በመንግሥት የማልማት ዕቅድ መያዙን የገለጹት አቶ አባተ፣ ለግል ባለሀብቶች መሬት በልዩ ሁኔታ ይሰጣል ብለዋል፡፡ በኅዳር 2004 ዓ.ም. የከተማ ቦታ በሊዝ ስለመያዝ የወጣው አዋጅ፣ በዋነኛነት መሬት የሚተላለፈው በጨረታ እንደሚሆን ይደነግጋል፡፡
የአዲስ አበባ አስተዳደርም ይህንን አዋጅ ለማስፈጸም ያወጣው ደንብና መመርያ፣ በዋነኛነት መሬት የሚተላለፈው በጨረታ እንደሆነ ይደነግጋል፡፡ ነገር ግን ለከተማው ጠቃሚ ለሆኑ ፕሮጀክቶች መሬት በልዩ ሁኔታ እንደሚስተናገድ የሚገልጽ በመሆኑ፣ አስተዳደሩ የመኪና ማቆሚያ የሚገነባባቸውን ቦታዎች በልዩ ሁኔታ እንደሚያስተናግድ ተገልጿል፡፡ በዚህ መሠረት ባለሀብቶች የተለዩትን ቦታዎች በማየት ሊመረጥ የሚችል ፕሮጀክት ቀርፀው ከመጡ አስተዳደሩ መሬት እንደሚሰጥ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ይህንን ግንባታ ለማካሄድ የግል ባለሀብቶች ፍላጎት ካላሳዩ ደግሞ አስተዳደሩ በራሱ አቅም ግንባታ እንደሚያካሂድ ተገልጿል፡፡ አቶ አባተ እንዳሉት፣ የመኪና ማቆሚያ ግንባታዎችን ለማካሄድ የከተማው መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ዲዛይን እንዲሠራ መመርያ ተሰጥቶታል፡፡
አስተዳደሩ በአዲስ አበባ ከተማ 20 የመኪና ማቆሚያ ሕንፃዎች እንዲገነቡ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ አቶ አባተ እንዳሉት፣ ቦታዎቹ ተለይተው ለግንባታ ዝግጁ ሆነዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍተኛ የትራንስፖርት መጨናነቅ እየተፈጠረ በመሆኑ፣ ለትራንስፖርት መጨናነቁ ከሚቀርቡ ምክንያቶች ውስጥ የመኪና ማቆሚያ ቦታ እጦት ተጠቃሽ ነው፡፡ በተለይ አስተዳደሩ እንዲለሙ ባደረጋቸው ካዛንቺስ፣ ኤድና ሞልና ሰንጋተራ አካባቢዎች ከፍተኛ የትራንስፖርት መጨናነቅ በመፈጠሩ፣ በእነዚህ አካባቢዎች የመኪና ማቆሚያ ሕንፃዎች ይገነባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡