Thursday, November 30, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የፖለቲካው ዓውድ ከስሜታዊነት የፀዳ ድርድር ያስፈልገዋል!

ኅብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያ ከዘጠና ሚሊዮን በላይ የሚሆነው ሕዝቧ ተሳስቦና ተከባብሮ የሚኖርባት አገር ናት፡፡ በርካታ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ማኅበረሰቦች በልዩነታቸው ውስጥ አንድነትን አፅንተው የሚኖሩባት ኢትዮጵያችን የተለያዩ ፍላጎቶችን ለማስተናገድ ዴሞክራሲን የህልውናዋ መሠረት ማድረግ አለባት፡፡ የተለያዩ ፍላጎቶችን አቻችሎና አግባብቶ እንደ አገር መቀጠል የሚቻለው ደግሞ፣ በተለይ በፖለቲካው ዓውድ ውስጥ የሚታየው ጨለምተኝነትና ጽንፈኝነት ሲረግብ ነው፡፡ ለዚህም ከስሜታዊነት የፀዳ ድርድር የግድ ነው፡፡ በመርህ አልባ ጉዞ የትም አይደረስም፡፡

ሕዝባችን በመላው የአገራችን ክፍሎች በተለያዩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ማኅበረሰቦች ስያሜ እየተጠራ የተለያዩ ቋንቋዎች፣ ባህሎች፣ እምነቶችና ልማዳዊ ጉዳዮች ቢኖሩትም በሥነ ልቦና ግን የተገናኘ ነው፡፡ ይህ ለዘመናት የዘለቀ ሥነ ልቦናዊ አንድነት የተለያዩ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን አንድ ላይ ለመኖር፣ በአንድነት አገርን ለመጠበቅና ከዚያም አልፎ ተርፎ በጋብቻ ጭምር ለመተሳሰር አብቅቷቸዋል፡፡ ይህ ወደር የሌለው ተምሳሌታዊ መስተጋብር አሁንም በፅናት እንደቀጠለ ነው፡፡ ነገር ግን አሳሳቢ ጉዳዮች አሉ፡፡

ይህንን የሕዝብ ለሕዝብ ሰላማዊና ታሪካዊ ግንኙነት ችግር ውስጥ የሚከቱ በርካታ ህፀፆች በተለያዩ ጊዜያት ተፈጽመዋል፡፡ በሕዝባችን አርቆ አሳቢነትና መልካም ባህሪ ምክንያት እንጂ፣ በአገራችን ውስጥ የተፈጸሙ ጥፋቶች  በዚህ ዘመን ሌላ ገጽታ ይፈጥሩ እንደነበር መካድ አይቻልም፡፡ ይህም ሆኖ ግን ይህ ታላቅ ሕዝብ ሁሉንም መከራና ችግር እንደ አመጣጡ ተቋቁሞ በሰላም፣ በፍቅርና በመከባበር አገራችንን አሁን ያለችበት ደረጃ ላይ አድርሷታል፡፡ የዚህ ወደር የሌለው የሕዝብ አርቆ አሳቢነት በአብነት ሊዘከር ካልቻለ ችግር አለ፡፡ ምልክቶችም ይታያሉ፡፡

በዚህ ዘመን አገሪቱ ከአሀዳዊ ወደ ፌዴራል አስተዳደር ተለውጣ በሕዝቦች እኩልነት ላይ የተመሠረተ የፌዴራል ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ሥርዓት መመሥረቱ በሕገ መንግሥቱ ተደንግጓል፡፡ ምንም እንኳ የፌዴራል ሥርዓት ቅርፁ ላይ በፖለቲከኞች መካከል አለመግባባት ቢኖርም፣ ወደ አሀዳዊ ሥርዓት መመለስ የማይቻለበት ዘመን ላይ ነው ያለነው፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱ በጊዜ ሒደት እያደገና እየጎለበተ እንዲሄድ፣ የአገራችንም ሕዝብ የሥርዓቱ እኩል ተጠቃሚ የሚሆንበትን አሠራር ማስፈንና ተቋማትን ማጠናከር ግን ጊዜ የሚሰጠው ተግባር አይደለም፡፡ በፌዴራል አወቃቀሩ ለአገሪቱ የሚበጃትን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ደግሞ የሁሉም ወገኖች ተሳትፎና ርብርብ ግድ ይላል፡፡ በፖለቲካው ዓውድ ውስጥ ያሉ ሁሉም ወገኖች ከስሜታዊነት የፀዳ ድርድር በማድረግ ብሔራዊ መግባባት ላይ እንዲደርሱ ብርቱ ጥረት መደረግም አለበት፡፡ አገሪቱ በመርህ መመራት ይኖርባታል፡፡  

በአንድ በኩል አሁን ባለው ሁኔታ በአገሪቱ ሕዝብ መፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ ፌዴራላዊ ሥርዓት መመሥረቱ በእርግጠኝነት ሲነገር፣ በሌላ በኩል ደግሞ የቀድሞ ቁስሎችን እየነካኩ የሕዝብን አብሮነትና የአገሪቱን ህልውና የሚፈታተኑ ተግባሮች በአደባባይ ይታያሉ፡፡ እነዚህ ጠቃሚ ያልሆኑ ድርጊቶች የሕዝባችንን ለዘመናት የዘለቀ አብሮ የመኖርና የመተሳሰብ ባህል ሲያደፈርሱ፣ የአገሪቱን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ሥጋት ውስጥ ይከታሉ፡፡ በገዥዎች በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የተፈጸሙ አሉታዊ ድርጊቶችን ከዛሬው ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣም ለመፍትሔ መትጋት ሲገባ፣ ትርምስ ሊፈጥሩ የሚችሉ ችግሮችን ማራገብ ከጉዳት ይልቅ ጥቅም የለውም፡፡ ይልቁንም የወደፊቷ ዴሞክራሲያዊትና የሁሉም ሕዝቧ መመኪያ የሆነች አገር ለመገንባት መነሳት ይበጃል፡፡ ችግሮችን ከመቆስቆስ ይልቅ ከስሜታዊነት የፀዳ ድርድርና ውይይት ውስጥ መግባት ይመረጣል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ የሚጓዙ ኃይሎችም ድርጊታቸውን በቅጡ ቢያጤኑት የግድ ይላል፡፡

በፖለቲካው ዓውድ ውስጥ ያሉ ሁሉም ወገኖች እከሌ ከእከሌ ሳይባሉ ‹‹የእኔ ብቻ ነው እውነት›› ከሚል ፌዝ ውስጥ ወጥተው፣ በሕዝባችን ውስጥ ለዘመናት የሰረፀውን የመግባባትና የመደራደር ባህል ይጎናፀፉ፡፡ በጽንፈኝነትና በጨለምተኝነት የተከበበው የአገሪቱ የፖለቲካ ሥነ ምኅዳር ሰጥቶ ለመቀበል መርህና ለድርድር እንዲመቻች በሁሉም ጎራ ያሉ ወገኖች ሊተጉ ይገባል፡፡ አገር የጋራ ነው ሲባል ያገባናል የሚሉ ዜጎች ሁሉ ይህንን አገራዊ ጥሪ ሊያስተጋቡ ይገባል፡፡ ይህ የሀቀኛ ዜጎች መርህ ሊሆን ይገባል፡፡ ተቃዋሚነትና ደጋፊነት በጥላቻና በጽንፈኝነት እየተዋጠ ብዙዎችን ተስፋ እያስቆረጠ ነው፡፡ ችግራችን ምንድነው ብሎ ተቀራርቦ ከመነጋገር ይልቅ፣ በዛቻና በድንፋታ የተሞላው የፖለቲካው ከባቢ ለውጥ አልባ ጉዞውን እስከ መቼ ሊቀጥል ይገባል? ይኼ በብርቱ ሊያሳስበን ይገባል፡፡ ከስሜታዊነትና ከደመነፍስ የፀዳ የውይይትና የድርድር መድረክ መፈጠር አለበት፡፡ መርህ አልባ ጉዞ ሊያበቃ የግድ ይላል፡፡

በተለይ ለፖለቲካ ሥልጣን በሚደረገው ፉክክር ለይቶላቸው ወደ ሌላ አቅጣጫ ከነጎዱት በተጨማሪ፣ በሰላማዊ ትግል ውስጥ ያሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች እርስ በርስ መነጋገር አቅቷቸዋል፡፡ ገዥው ፓርቲና ተቃዋሚዎቹ አያግባባንም በሚሉዋቸው መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር ሰጥቶ የመቀበል መርህን ማዕከላዊ ነጥብ ለምን ማድረግ እንዳዳገታቸው እንቆቅልሽ ነው፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ተቀራርቦ የመነጋገር ልምድ የላቸውም፡፡ ችግሩ እዚህ ደረጃ እየተንከባለለ በመጣባቸው በርካታ ዓመታት ውስጥ በፖለቲካ ትግሉ ውስጥ ያሉ፣ የነበሩና ከሒደቱ ራሳቸውን ያገለሉ ጭምር ለመፍትሔ ፍለጋ ሲተጉ ታይተው አይታወቅም፡፡ ገዥው ፓርቲ ‹‹ፅድቅም መንገድም እኔ ነኝ›› ብሎ በሩን ሲዘጋጋ፣ ተቃዋሚዎቹም ‹‹የራስህ ጉዳይ›› ያሉ ይመስላሉ፡፡ ይኼ የት ያደርሳል? በዚህም ምክንያት ተፅዕኖዎችና ጫናዎች እየበረቱ ናቸው፡፡ እስከ መቼ ነው በዚህ ዓይነቱ መንገድ መጓዝ የሚቻለው? በአንድ ፓርቲ አድራጊነትና ፈጣሪነት አገር የት ድረስ ትጓዛለች? መነጋገርና መደማመጥ በሌለበትስ ድርድር እንዴት ይታሰባል? ለአገር ህልውናና ብሔራዊ ደኅንነትስ ይበጃል ወይ? በጣም በጣም ያሳስባል፡፡

ይህ ታላቅና አኩሪ ሕዝብ ለዘመናት ላዩ ላይ የተጫነበትን መከራና ስቃይ ችሎ አገሩን ከወራሪዎችና ከቅኝ ገዥዎች ሲከላከል የኖረውና ለጥቁር ሕዝቦች መመኪያ የሆነውን ታላቁን ፀረ ኮሎኒያሊስት የዓደዋ ጦርነት በድል አድራጊነት የተወጣው፣ ለአገሩ በነበረው ከፍተኛ የሆነ የቀናዒነት ስሜት ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ላቅ ያለ የሞራል ልዕልና በተለይ በሁሉም የአገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች ዘንድ ዕውቅናና ክብር ሊሰጠው ይገባል፡፡ የአገር ህልውናና ክብር፣ እንዲሁም ለሕዝብ ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤትነትና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ቁርጠኛ አቋም አለን የሚሉ ወገኖች በሙሉ ራሳቸውን በአንክሮ ይገምግሙ፡፡ አሉታዊ በሆነ መንገድ ከመፈራረጅና ከመካሰስ ወጥተው ለዚህ የተከበረ ሕዝብ ክብር ሲሉ ወደ ድርድር ይግቡ፡፡ መርህ አልባ ከሆነ ጉዞ ይታቀቡ፡፡

በምርጫ ዋዜማ ላይ ተሁኖ የምን ድርድር ነው የሚሉ ካሉም፣ የመንግሥትን ሥልጣን ከመያዝ በላይ የአገር ህልውና ነው ድርድር የሚጋብዘው፡፡ ብሔራዊ መግባባት በሌለበትና ጭፍን ጥላቻና ጽንፈኝነት የአገሪቱን የፖለቲካ ዓውድ ባበላሸበት በዚህ ዘመን፣ ተቀራርቦ ከመነጋገርና ከመደራደር በላይ ተመራጭ ነገር የለም፡፡ በምርጫ ተወዳድሮ ማሸነፍና መሸነፍ ያለ፣ የነበረና ወደፊትም የሚቀጥል ቢሆንም፣ ብሔራዊ መግባባት በሌለበት ሁሌም የሚኖረው ጥላቻና መጠፋፋት ብቻ ነው፡፡ ከምርጫ ሒደት ጀምሮ እስከ ውጤት ድረስ ያለው ጉዞም ቢሆን የሚበላሸው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ መርህ አልባ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ አንድ ቦታ ላይ ተጎትቶ በመቀራረብ መነጋገር ይበጃል፡፡ ለዚህም ሲባል ነው የፖለቲካው ዓውድ ከስሜታዊነት ፀድቶ ድርድር ውስጥ መግባት ያለበት!    

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...

ሀብቱንና ትርፉን እያሳደገ የቀጠለው አዋሽ ባንክ

አዋሽ ባንክ በአዲስ አበባ ከተማ አዲስ ዋና መሥሪያ ቤት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ድጋፍና ተቃውሞ እኩል ይስተናገዱ!

ኢትዮጵያ ውስጥ ለረዥም ዓመታት ለመንግሥት ከሚቀርቡ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የመብት መከበር ጉዳይ ነው፡፡ ዜጎች ተፈጥሯዊም ሆኑ ሕጋዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው ለመንግሥት ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ ጥያቄው የቀረበለት...

ፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈለግላቸው!

መንግሥት ከኦነግ ሸኔ ጋር በታንዛኒያ ዳሬሰላም ከተማ ሲያካሂድ የነበረው ንግግር ያለ ውጤት መጠናቀቁን ካስታወቀ በኋላ፣ በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ሰላም ለማስፈን የነበረው ተስፋ...

ኢትዮጵያን ከግጭት ቀጣናነት ማላቀቅ የግድ ነው!

ፍሬ አልባ ፖለቲካዊ ልዩነቶች ወደ ግጭት እያመሩ ለአገርና ለሕዝብ የማያባራ መከራ ሲያቀባብሉ፣ ከትናንት ስህተቶች ለመማር ፈቃደኛ ያልሆኑ ፖለቲከኞችና ተከታዮቻቸው በእሳት ላይ ቤንዚን እያርከፈከፉ ጠማማ...