– ብሔራዊ ሎጂስቲክስ ስትራቴጂ የመንግሥት የሞኖፖል ድርሻ እንዲነሳ ጠይቋል
በእንግሊዙ ናታን አማካሪ ኩባንያ ለሁለት ዓመት የተጠናውና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም የቴክኒክና የፋይናንስ ድጋፍ ያደረገለት ብሔራዊ ሎጂስቲክስ ስትራቴጂ፣ በጎረቤት አገሮች ውስጥ የሚገኙ ወደቦችን በጋራ የማልማት ሐሳብ አቀረበ፡፡ መንግሥት በስትራቴጂው መሠረት በሌሎች አገሮች ውስጥ ወደብ የማልማት እንቅስቃሴ እንደሚያደርግ ይፋ አደረገ፡፡
ብሔራዊ የማሪታይምና ሎጂስቲክስ ስትራቴጂው መጠናቀቁን በማስመልከት፣ ለመንግሥት ባለሥልጣናት የሰነድ ማስረከብ ሥነ ሥርዓት የተካሄደው ሚያዝያ 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ነበር፡፡ በሥነ ሥርዓቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ቋሚ ተወካይና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ዕርዳታ አስተባባሪ ኢዩጂን ኦውሱ፣ የስትራቴጂውን ሰነድ ለትራንስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ወርቅነህ ገበየሁ አስረክበዋል፡፡ ኦውሱ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ ለመጪዎቹ 45 ዓመታት የአገሪቱ የሎጂስቲክስ እንቅስቃሴ ምን መምሰል እንደሚገባው አጥንቷል ያሉት ይህ ስትራቴጂ፣ በአራት ምዕራፎች ተከፋፍሎ የሚተገበር ነው፡፡ የመጀመሪያው ምዕራፍ ከመጪው ዓመት ጀምሮ በአጣዳፊ መተግበር የሚገባቸው ጉዳዮች ላይ በማተኮር ይተገበራል ብለዋል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም አንድ ሚሊዮን ዶላር የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ ያደረገበት የሎጂስቲክስ ስትራቴጂ፣ የአገሪቱን የባቡር ትራንስፖርት የማስፋፋት ዓላማም አካቷል፡፡ ሚኒስትር ወርቅነህ ለጋዜጠኞች እንዳብራሩት፣ በመጪው ዓመት ሥራ ይጀምራል ተብሎ የሚጠበቀው የባቡር መስመር ብሔራዊ የሎጂስቲክስ ስትራቴጂ አካል ሲሆን፣ የአገሪቱን የከባድ ጭነቶች ምልልስ ያቃልላል፡፡ አንዱ ባቡር የ16 ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎችን ተክቶ እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡
አቶ ወርቅነህ በተለይ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ማብራሪያ በሰሜን፣ በደቡብ፣ በምሥራቅና በምዕራብ የአገሪቱ የገቢና ወጪ ንግድ በሮች በኩል የባህር በሮቻቸውን ለመጠቀም ቅርበት ያላቸው አገሮች ወደቦችን ከመጠቀም ባሻገር፣ ወደቦቻቸውን በጋራ ማልማት የመንግሥት ሐሳብ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ‹‹ለምሳሌ በበርበራ ወደብ ላይ ከሶማሌላንድ መንግሥት ጋር ድርድር ጀምረናል፡፡ ፖርት ሱዳንን በሚመለከት አብሮ ለማልማት ዝግጅት እየጀመርን ነው፡፡ ብቻችንን ሳይሆን ከጎረቤት አገሮች ጋር በመተባበር የምንሠራው ነው፤›› በማለት የመንግሥትን ፍላጎት ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ሁሉንም የጎረቤት አገሮች ወደቦችን በስትራቴጂው መሠረት የመጠቀም ፍላጎት እንዳላትም ይፋ አድርገዋል፡፡
ከዚህ ባሻገር ግን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም አማካይነት የተጠናው ስትራቴጂ ካቀረባቸው የመፍትሔ ሐሳቦች መካከል፣ የማሪታይምና የመርከብ አገልግሎቶች በመንግሥት በሞኖፖል ከመያዝ ተላቀው የግል ኩባንያዎች እንዲሳተፉባቸው የሚጠይቀው ይገኝበታል፡፡ ይህንን በሚመለከት ከጋዜጠኞች ተጠይቀው ሲያብራሩም፣ መንግሥት የቀረቡለትን ሐሳቦች ከአገሪቱ ሕጎች ጋር አጣጥሞ እንደሚተገብራቸው ገልጸው፣ በመንግሥት በሞኖፖል የመያዛቸው ነገር ግን ከሕዝብ ተጠቃሚነት አኳያ አከራካሪ እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡
የማሪታይም ጉዳዮች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን አበራ በበኩላቸው፣ የአገሪቱ የሎጂስቲክስ ዘርፍ በተለይም በመርከብ ትራንስፖርትና በማሪታይም አገልግሎት መስክ የግል ኩባንያዎችን ተሳትፎ የሚጠይቅ ከሆነ መንግሥት አማራጩን ይጠቀማል ብለዋል፡፡ በሎጂስቲክስ ዘርፍ ለአገሪቱ ከወጪ ቅነሳና ከጊዜ ቁጠባ የሚያስገኝ አማራጭ ሁሉ ታሳቢ ይደረጋል ያሉት አቶ መኮንን፣ ይህ የሚሆነው ለግለሰቦች ተብሎ ሳይሆን፣ ለአገሪቱ ሎጂስቲክስ ዘርፍ መሻሻል ሲባል ነው ብለዋል፡፡ የግል ኩባንያዎችን የማሳተፉ ተግባር ቀስ በቀስ ሊከናወን የሚችል መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በምክትል ጠቅላይ ሚኒትስትር ደረጃና በአቶ ወርቅነህ ገበየሁ ምክትል ሰብሳቢነት የሚመራ ብሔራዊ የሎጂስቲክስ ምክር ቤት መቋቋሙ የተገለጸ ሲሆን፣ የአገሪቱን ጠቅላላ የሎጂስቲክስ ሥርዓት የሚመራ ቦርድም መሰየሙ ታውቋል፡፡
በአገሪቱ ያለው የሎጂስቲክስ ሥርዓት ከአደረጃጀቱ ጀምሮ እስከ አፈጻጸሙ ድረስ ባለው እርከን ውስጥ በርካታ ችግሮች እንደሚስተዋሉ ባለሥልጣናቱ ያምናሉ፡፡ በዓለም ባንክ መመዘኛ መሥፈርቶችም ከሰሐራ በታች በሚገኙ አገሮች ከሚታየው ችግር የባሰውን ኢትዮጵያ እያሳየች እንደምትገኝም ኢዩጂን ኦውሱ አስታውሰዋል፡፡ ኢትዮጵያ የኤክስፖርት ዕቃዎችን ለውጭ ገበያ ለማቅረብና ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት እስከ ጂቡቲ ወደብ ባለው ሒደት ውስጥ 40 ቀናት እንደሚፈጅባት የዓለም ባንክ ሪፖርት ያመለክታል፡፡ ይህንን ጊዜ ወደ አሥር ቀናት ለማውረድ የሚቻልባቸውን የሎጂስቲክስ አሠራሮች ጨምሮ በርካታ የመፍትሔ ሐሳቦች በአዲሱ የሎጂስቲክስ ስትራቴጂ ቀርበዋል፡፡