Wednesday, September 27, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሦስት መንገዶችን ከ6.3 ቢሊዮን ብር በላይ ለመገንባት ስምምነት ተፈረመ

ተዛማጅ ፅሁፎች

– መከላከያ ረዥሙን የሲሚንቶ ኮንክሪት መንገድ ይገነባል

ሁለት የቻይናና አንድ አገር በቀል ኮንትራክተሮች 6.37 ቢሊዮን ብር ወጪ ይጠይቃሉ የተባሉ የሦስት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት የሚያስችላቸውን ስምምነት ፈረሙ፡፡ በ2007 በጀት ዓመት ለኮንትራክተሮች ይሰጣሉ ከተባሉ ፕሮጀክቶች ውስጥ የሦስቱን የመንገድ ሥራዎች የወሰዱት ቻይና ሬል ዌይ ሰባተኛ ግሩፕ ሊሚትድ፣ ቻይና ፈርስት ሃይ ዌይ ኢንጂነሪንግ ኮ ሊሚትድና አገር በቀሉ የመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ናቸው፡፡ ሚያዝያ 6 ቀን 2007 ዓ.ም. ሦስቱም ኮንትራክተሮች ሥራውን በይፋ በመረከብ የተፈራረሙ ሲሆን፣ ቻይና ሬል ዌይ ሰባተኛ ግሩፕ ሊሚትድ የተረከበው ፕሮጀክት በደቡብ ክልል የሚገኘውን የኦሞ ወንዝ-ተርጫ መንገድ ግንባታ ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት 83.4 ኪሎ ሜትር ርዝመት ሲኖረው፣ ጨረታውን አሸንፎ ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ጋር የተዋዋለበት ዋጋ 1.67 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ቻይና ፈርስት ሃይ ዌይ ኢንጂነሪንግ ኮ ሊሚትድ የተባለው የቻይና ኩባንያ ደግሞ በአማራ ክልል የቢልባላ-ሰቆጣ መንገድ ፕሮጀክትን በ2.04 ቢሊዮን ብር ለመገንባት ተዋውሏል፡፡ ይህ መንገድ 98.7 ኪሎ ሜትር ርዝመት አለው፡፡ መከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ደግሞ በአፋር ክልል የሚገኘውን ከዲቸቶ-ጋላፊ መገንጠያ ኤሊዳር-በልሆ ድረስ ያለውን 80.5 ኪሎ ሜትር መንገድ ለመገንባት ተዋውሏል፡፡ ኢንተርፕራይዙ ይህንን መንገድ ለመገንባት ጨረታውን ያሸነፈበት ዋጋ 2.66 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ከሦስቱም መንገዶች የግንባታ ኮንትራት ውል መረዳት እንደተቻለው፣ ለፕሮጀክቶቹ የሚወጣው ጠቅላላ ወጪ በኢትዮጵያ መንግሥት የሚሸፈን ነው፡፡ የኦሞ ወንዝ-ተርጫ መንገድ በ42 ወራት፣ የቢልባላ ሰቆጣ መንገድ በ39 ወራት፣ የዲቸቶ-ጋላፊ መገንጠያ ኤሊዳር-በልሆ መንገድ ደግሞ በ39 ወራት እንደሚጠናቀቅ የኮንትራት ስምምነት ውሉ ያሳያል፡፡ በመከላከያ ኮንስትራክሽን ከሚገነባው 80.5 ኪሎ ሜትር ውስጥ 63.5 ኪሎ ሜትሩ የሚገነባው በሲሚንቶ ኮንክሪት ነው፡፡ ከ40 ዓመታት በላይ እንዲያገለግል በሲሚንቶ ኮንክሪት ሪጂድ ፔቭመንት ደረጃ ይገነባል የተባለው ይህ መንገድ በኢትዮጵያ የመንገድ ግንባታ ታሪክ በዚህን ያህል ኪሎ ሜትር ርዝመት በሲሚንቶ ኮንክሪት የሚገነባ ረዥሙ መንገድ ይሆናል ተብሏል፡፡ እስካሁን በሲሚንቶ ኮንክሪት እየተገነባ ያለ ረዥሙ መንገድ ከጫንጮ-ደርባ-በቾ ባለው መንገድ ፕሮጀክት ውስጥ ያለው ከአሥር ኪሎ ሜትር ያነሰ መንገድ ነው፡፡ የመከላከያ ኮንስትራክሽን የአሁኑ የመንገድ ግንባታ በተለየ የሚታይ ነው ተብሏል፡፡ ሦስቱ ኮንትራክተሮች ከዚህ ቀደም ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን ተረክበው በማጠናቀቅ የሚታወቁ ሲሆኑ፣ በተጨማሪም በመጠናቀቅ ላይ ያለ ፕሮጀክት በእጃቸው ላይ ይገኛል፡፡ በተለይ ቻይና ፈርስት ሃይ ዌይ ኢንጂነሪንግ ኮ ሊሚትድ የተባለው የቻይና ኮንትራክተር፣ የአዲስ-አዳማን የፍጥነት መንገድ በመገንባት ይታወቃል፡፡ መከላከያ ኮንስትራክሽንም የበረሃሌ ዳሎል የመንገድ ግንባታን በማጠናቀቅ ላይ ያለ ሲሆን፣ ከመቐለ አደዋ ድረስ በሦስት ተከፋፍሎ እየገነባ ካለው የመንገድ ሥራ ውስጥ የአንደኛውን ግንባታ ያከናወነ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በበጀት ዓመቱ እስካሁን ለኮንትራክተሮች ካስተላለፋቸው ከአሥር በላይ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች መካከል አብዛኛዎቹን የቻይና ኮንትራክተሮች ወስደዋቸዋል፡፡ የሦስቱን የመንገድ ፕሮጀክቶች ስምምነቶች የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣንን በመወከል የፈረሙት ተጠባባቂ ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ሲሳይ በቀለ፣ የቻይና ሬል ዌይን በመወከል ሚስተር ሊ ቹዋን፣ በቻይና ፈርስት ሃይዌይ በኩል ደግሞ ሚስተር ዡ ዩንግ ሽንግ ስምምነቶቹን ፈርመዋል፡፡ በመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ በኩል ደግሞ የኢንተርፕራይዙ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ወልዳይ በርሔ ስምምነቱን ፈርመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች